lørdag 26. mai 2018

የኢትዮጵያ ትግልና የአንዳርጋቸው ጽጌ ግንኙነት ለምን የቁርባን ግንኙነት ሆነ?! (መስቀሉ አየለ)


መስቀሉ አየለ
Andargachew Tsige is British national
Andargachew Tsige's father Tsige Habtemariam.
አቶ ጽጌ ሃብተማርያም
የአንዳርጋቸው አባት አቶ ጽጌ ስድስት እህትና ወንድሞቻቸውን አይናቸው እያየ ለጣሊያን ባደሩ ባንዳዎች እንደ አይሲስ በገጀራ ሲታረዱ እሳቸውና አንዲት እህታቸው ብቻ ነበሩ የተረፉት። እህቲቱ ባዩት ሁኔታ ልባቸው ከተሰበረበት አልጠገን ብሎ ከሰው ሳይነጋገሩ፣ በህጻንነታቸው መንኩሰው በዘጠና አመታቸው ሞቱ። አቶ ጽጌ ግን አርበኞቹን የሚመሩ አንድ የታወቁ ደጃዝማች አግኝተዋቸው ለአንድ ጉራጌ ገበሬ ደብዳቤ ጽፈውና ማህተም አትመው ጦርነቱ እስኪያልቅ ድረስ አደራ ሰጥተዋቸው ወደ ግንባር ሄደዋል።ያን ግዜ ብላቴናው ጽጌ እድሜያቸው ስድስት ወይንም ሰባት ቢሆን ነው፤እርግጡን አላውቀውም; እንደ እከሌ ልጅ ባክል ነው ይላሉ።
ጦርነቱ ሲያልቅ አርበኛው ደጃዝማች አልተመለሱም።ስለሆነም ባንዲራ ስትነሳና ንጉሱ ወደ አገር ውስጥ ሲመለሱ የጉራጌው ባላባት አራት አመት ሙሉ የያዙዋቸውን አቶ ጽጌን አዲስ አበባ ወስደው ንጉሱ ከቤተክርስቲያን ሲመለሱ እግራቸው ስር ተደፍተው አቤት አሉ፤ “ምን ሆነሃል?” ሲባሉ ደብዳቤውን እና “ብላቴናውን ጼጌ ሃብተማርያምን ተረከቡኝ፤ ስመ እግዚአብሔር ጠርቸ የተቀበልኩት አደራ ነው” አሉ። ታሪካቸው ቢነበብ ልብ የሚነካ ሆኖ ተገኘ። ደጃዝማቹም በህይወት አልተመለሱምና ንጉሱ ብላቴናውን በጉዲፈቻ ተቀብለው አዳሪ ትምህርት ቤት አስገቡዋቸው። የመጀመሪያውም የፊደል ሰራዊት አባል ሆነው ትምህርታቸውን አጠናቀቁ።
አቶ ጽጌ ሃብተማርያም በቀይ ሽብር ዘመን እንደገና የአንድ ልጃቸውን አስከሬን በመቶ ብር ገዝተዋል፤ ራሳቸውም ተሸክመው ከእስር ቤት እንዲያወጡ ተገደዋል። በዚህም የተነሳ በዚህች አገር ላይ ያለው ውስብስብ ፖለቲካ አንዳርጋቸውን በአባቱ በኩል ዘር አልባ አድርጎ አስቀርቶታትል። እርሱ ዘር ማንዘሮቹ ዋጋ በከፈሉበት አገር የባንዳዎቹ የልጅ ልጆች ደግሞ እርሱን አስረው በክፋታቸው ልክ እልሃቸውን ተወጥተውበታል። የአንዳርጋችውም ጽናቱ ፣ስለ አገርና ነጻነት ያለው ጥልቅ ፍልስፍና እንዲሁም አርባ አመት ሙሉ ያደረገው ያልተቋረጠ ተጋድሎ ይህን እየሰማና እያየ ማደጉ ነው። አረጋዊው ጽጌ ሃብተ ማርያምም ሶስት እሩቡን ወጥተው በአራተኛው እሩብ የእድሜ መገዳደጃ ላይ ማረሚያ ቤት ደጃፍ ቆመዋል ስንል ግብግቡ የተጀመረው ከሶስት ትውልድ በፊት ነው ለማለት ነው።መለስ ዜናዊ ይኼንን ስለሚያውቅ ቤተሰቡን በሙሉ “The Militant Family” ብሎ ይጠራው ነበር ።