torsdag 15. januar 2015

ሰማያዊ ቲሸርት የለበሱ ወጣቶች ከስላሴ በዓል ላይ ተባረሩ

በነገረ ኢትዮጵያ

• ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ‹የፈራ ይመለስ› የሚል ቲሸርት አስለብሶ ሲበጠብጠኝ ሰንብቷል፡፡›› የየካ ክፍለ ከተማ ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ

• ‹‹ገዥው ፓርቲ ጥላውን የማያምንበት ደረጃ ላይ ደርሷል!›› አቶ ዮናታን ተስፋዬ
semayawiዛሬ ጥር 7/2007 ዓ.ም የዓመቱን የስላሴ በዓል ለማክበር አራት ኪሎ የሚገኘው ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን የተገኙ ወጣቶች ሰማያዊ ቲሸርት በመልበሳቸው በፖሊስ እንደተባረሩ የአይን እማኞች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ፖሊስ ‹‹ያመነ፣ የተጠመቀ ይድናል!›› የሚል ሰማያዊ ቲሸርት የለበሱትን ወጣቶች ቲሸርቱን እንዲያወልቁ ሲጠይቅ ወጣቶቹ አናወልቅም በማለታቸው ከበዓሉ ማባረሩን እማኞቹ ገልጸዋል፡፡ ከተባረሩት ወጣቶች መካከል አብዛኛዎቹ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚገቡትንና የሚወጡትን አማኞች በማስተባበር ላይ እንደነበሩ የተገለጸ ሲሆን የተባረሩት ወጣቶች ይታሰሩ አይታሰሩ የታወቀ ነገር የለም፡፡

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የመጡ ከፍተኛ ኃላፊዎች ለጥምቀት በዓል ሰማያዊ ቲሸርት ያዘጋጁትን የጃንሜዳ አካባቢው የጥምቀት በዓል አስተባባሪዎች፣ ያዘጋጁት ሰማያዊ ቲሸርት በዓሉ ላይ እንዳይለበስ በተደጋጋሚ እያስጠነቀቁ እንደሚገኙ ምንጮች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ በፖሊሶችና በደህንነቶች ተደጋጋሚ ጫናም ለጃንሜዳ አካባቢ ወጣቶች የተዘጋጀው ሰማያዊ ቲሸርትና ‹‹ያመነ፤ የተጠመቀ ይድናል›› የሚለውን ጥቅስ በነጭ ቲሸርት እና በሌላ ጥቅስ እንድንቀይር ተገደናል ብለዋል፡፡ በአንጻሩ የፈረንሳይና ቤላ አካባቢ ወጣቶች ሰማያዊ ቲሸርቱን እንዲቀይሩ ጫና ቢደርስባቸው አንቀይርም በሚል አቋማቸው መጽናታቸው ታውቋል፡፡

በተመሳሳይ ጥር 6 የአዲስ አበባ መስሪያ ቤቶችና ወረዳዎች ኮሚኒኬሽን ኃላፊዎች አዲስ አበባ መዘጋጃ ቤት ባደረጉት ስብሰባ የየካ ክፍለ ከተማ ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ፈረንሳይ ሌጋሲዮን አካባቢ ‹የፈራ ይመለስ› የሚል ሰማያዊ ቲሸርት አስለብሶ ሲበጠብጠኝ ሰንብቷል፡፡›› ሲል ሪፖርት ማቅረቡን የስብሰባው ተሳታፊዎች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

ስለ ጉዳዩ ያነጋገርናቸው የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ‹‹ደህንነት፣ ፖሊሶችና ካድሬዎች እያንዳንዱን የህዝብ እንቅስቃሴ ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር በማገናኘት ወቀሳ የሚያቀርቡት ህዝብ ውስጥ ብሶት እንዳለ፣ ሰማያዊም የህዝብን ብሶት እንደሚያሳማ ስለሚያውቁ፣ ከምንም በላይ ገዥው ፓርቲ የራሱን ጥላ የማያምንበት ደረጃ ላይ ስለደረሰ ነው›› ሲሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመብት ጥያቄ ባነሱባቸው ጊዜያት ሁሉ ገዥው ፓርቲ ሰማያዊ ፓርቲን ‹‹የሙስሊም ፓርቲ ነው›› በሚል ሀሰተኛ ወሬ ሲያሰራጭ እንደነበርና ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በሰጠው የ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› ስልጠና ሰማያዊ ፓርቲን ሲወቅስ እንደከረመ ያስታወሱት ኃላፊው አሁንም ፓርቲውን ከእያንዳንዱ የህዝብ እንቅስቃሴ ጋር እያገናኘ ቢበረግግ አያስገርምም ብለዋል፡፡

ጃዝ አምባ የጀመረው፣ የጣይቱ ሆቴል ቃጠሎ እያነጋገረ ነው (ግን ለምን?)

(ኢ.ኤም.ኤፍ) ባለፈው እሁድ ማለዳ ላይ በእቴጌ ጣይቱ ሆቴል ላይ የደረሰው የእሳት አደጋ ብዙዎችን ማነጋገር ጀምሯል። የሆቴሉ ስራ አስኪያጅም ሆኑ የእሳት አደጋ ሃላፊዎች አንድ የተስማሙበት ነገር ቢኖር፤ እሳቱ ከማብሰያው ኩሽና እንዳልተነሳ ነው።

 አሁን ብዙዎች የተስማሙት “የእሳቱ መነሻ ጃዝ አምባ ላውንጅ ነው” በሚለው ሃሳብ ላይ ሲሆን፤ እዚያ ውስጥ ደግሞ እሳት ሊያስነሳ የሚችል ነገር አለመኖሩን ይስማሙበታል። ይህ ከሆነ ደግሞ “አደጋው ድንገተኛ ሳይሆን፤ ምናልባት ሆን ተብሎ በሰው የተፈጸመ ሊሆን ይችላል” የሚለው መላምት እየተጠናከረ ይገኛል።

“ለምን ማቃጠል አስፈለገ?” የሚለውን ከመረመርን ደግሞ ‘ምናልባት በጃዝ አምባ ኪነጥበባዊ ስራዎች የተናደዱ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ’ ወደሚል ሌላ መላምት ይወስደናል። በተለይም ከቅርብ ግዜ ወዲህ በጃዝ አምባ የሚቀርቡ የኪነ ጥበብ ስራዎች ለየት ብለው፤ አሁን ያለውን አስተዳደር የሚያወግዙ ሆነው በመገኘታቸው ሊሆን ይችላል፤ የሚል ሌላ ሃሳብ ብቅ እያለ ነው።

በቅርቡ የተለቀቀው የሜሮን ጌትነት አወዛጋቢ ግጥም እና ሌሎች ስራዎች የኢህአዴግ ካድሬዎችን ማስቆጣቱ የሚታወስ ነው። የቁጣቸውም መነሻ… በተለይ ሜሮን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ውስጥ ስትሰራ ለተመለከተ “የአስተዳደሩ ደጋፊ ናት” የሚል ግምት ሊወስድ ይችላል። ሆኖም በቅርቡ በጣይቱ ሆቴል ውስጥ በሚገኘው ጃዝ አምባ ላውንጅ የተቀረጸው የሜሮን ጌትነት ቪዲዮ ግን በተቃራኒው፤ አሁን ያለው አስተዳደር የሚፈጽመውን በደል ያጋለጠ በመሆኑ፤ ኢህአድጋውያን በተደጋጋሚ ቁጣቸውን ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።

 ይህን አወዛጋቢ የሜሮን ጌትነት ግጥም ላላዩት እንዲያዩ በድጋሚ በመጋበዝ፤ ሪፖርተር ጋዜጣ በእሳት አደጋው ጉዳይ ግራና ቀኙን አነጋግሮ ለንባብ ያበቃውን ጽሁፍ ከዚህ ቀጥሎ እናቀርባለን።



‹‹የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች እንደደረሱ ቢያጠፉ ሆቴሉን ማትረፍ ይቻል ነበር›› የእቴጌ ጣይቱ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ
‹‹በተደወለልን በሁለት ደቂቃ ውስጥ ደርሰናል›› የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል ባለሥልጣን
አዲስ አበባ ከተማ በተቆረቆረች በ19ኛ ዓመቷ በአሁኑ አጠራር በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ፒያሳ በ1898 ዓ.ም. በተገነባውና 109ኛ ዓመቱን ባስቆጠረው እቴጌ ጣይቱ ሆቴል ላይ፣ ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ከማለዳው 2፡15 ሰዓት አካባቢ የደረሰው የእሳት ቃጠሎ እያወዛገበ ነው፡፡

ለእሳቱ መነሻ ቦታና ምክንያቱ እስካሁን ያልተደረሰበትና በቃጠሎው ምን ያህል ንብረት እንደወደመ የሆቴሉን ባለቤቶች ጨምሮ መግለጽ የሚችል አካል ባይገኝም፣ ከሆቴሉ ሕንፃ ጋር ተያይዞ በተሠራው ‹‹ጃዝ አምባ ላውንጅ›› መዝናኛ የመጀመሪያው እሳት የታየ ከመሆኑ አንፃር፣ የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን ፈጥኖ ደርሶ ቢሆን፣ እሳቱን እዚያው የታየበት ቦታ ማስቀረት (ማጥፋት) ይቻል እንደነበር በአካባቢው የተገኙ ሰዎች እየገለጹ ነው፡፡

በዕለተ ሰንበት (እሑድ) ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ከማለዳው 2፡15 ሰዓት አካባቢ የእሳት አደጋው እንደተነሳ እንደሰሙና መኖሪያቸው ከሆቴሉ ብዙም ያልራቀ በመሆኑ፣ በአሥር ደቂቃ ውስጥ መድረሳቸውን የሚናገሩት የእቴጌ ጣይቱ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ አቶ አያሌው ታደሰም፣ የአካባቢው ነዋሪዎችና በቃጠሎው ወቅት በሥፍራው የነበሩ ሰዎች በሚሉት ይስማማሉ፡፡
የስልክ ጥሪ በደረሰው በሁለት ደቂቃ ውስጥ በአደጋው ቦታ መድረሱንና ያለውን ኃይል ሁሉ በመጠቀም፣ አደጋው ወደ ሌላ አካባቢ ሳይዛመት ሊቆጣጠር እንደቻለ እየገለጸ የሚገኘውን የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣንን የሚቃወሙት ሥራ አስኪያጁ፣ የባለሥልጣኑ ሠራተኞች ‹‹በሁለት ደቂቃ ደርሻለሁ›› ማለታቸውን ‹‹በፍፁም አልደረሱም›› በማለት ተቃውመዋል፡፡

እንደ አቶ አያሌው ገለጻ፣ በሁለት ደቂቃ ወይም በሌላ ማለቱን ትተው በደረሱበት ወቅት ማጥፋት ቢጀምሩ ኖሮ፣ እሳቱ ወደ ሆቴሉ ሕንፃ ሳይዛመት ጃዝ አምባ ላውንጅ ላይ እያለ ማጥፋት ይችሉ ነበር፡፡ ስልካቸው አልሠራ በማለቱ በመኪና እዚያው ድረስ ተሄዶ እንደተነገራቸውና ነጋሪው መጥቶ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደደረሱም ይዘውት የመጡት የእሳት ማጥፊያ ተሽከርካሪ ማጥፋት የሚችል ባለመሆኑ እሳቱ ወደ ሆቴሉ ሊዛመት መቻሉን አስረድተው፣ ‹‹ስለ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ፍጥነትና መዘግየት በወቅቱ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ይናገሩ፤›› ብለዋል፡፡

እሳቱ ከማብሰያ ክፍል ስለመነሳቱ የተጠየቁት ሥራ አስኪያጁ፣ ‹‹እሳቱ መቶ በመቶ ከማብሰያ ክፍል (ኪችን) አልተነሳም፡፡ መነሻው የሚሆነው ጃዝ አምባ እንደሚሆንና ምክንያቱ ደግሞ ቀድሞ የተቀጣጠለውና ሙሉ በሙሉ የወደመውም እሱ ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ ጃዝ አምባ እየነደደ የሆቴሉ ማብሰያ ክፍል በሥራ ላይ እንደነበረና በማብሰያ ክፍል ውስጥ የነበሩትን እሳት አባባሽ ነገሮችን ቀድመው ማስወገድ መቻላቸውንም ገልጸዋል፡፡

በጃዝ አምባ ላውንጅ ውስጥ እሳት ሊያስነሳ የሚችል ነገር ስለመኖሩ ተጠይቀው፣ በጃዝ አምባ ውስጥ ሊቀጣጠል ወይም እሳት ሊያስነሳ የሚችል ነገር እሳቸው እንደማያውቁ ገልጸው፣ በወቅቱ ምን እንደነበርም ማወቅ እንዳልቻሉ አስረድተዋል፡፡ ጃዝ አምባ ላውንጅ አብዛኛውን ጊዜ የሚሠራው በምሽት ከመሆኑ አንፃር እሳቱ በተነሳበት ወቅት ሥራ ስለመኖሩ የተጠየቁት ሥራ አስኪያጁ፣ እሳቸው ጠዋት ባይኖሩም የላውንጁ ሠራተኛ የሆነ አንድ ሰው ከጠዋቱ አንድ ሰዓት አካባቢ ገብቶ መውጣቱን እንደሰሙ ጠቁመዋል፡፡ ጃዝ አምባ ላውንጅ መሥራት ከጀመረ ከሦስት ዓመታት በላይ እንደሆነውም ተናግረዋል፡፡

እቴጌ ጣይቱ ሆቴል ባለአንድ ፎቅ ሲሆን፣ አሥር የመኝታ ክፍሎች እንዳሉትና በእያንዳንዱ ክፍል ሁለት ሁለት አልጋዎች በመኖራቸው፣ በጠቅላላው 20 አልጋዎች እንዳነበሩ ሆነው ሙሉ በሙሉ መቃጠላቸውንም ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ደንበኞቻቸው የውጭ አገር ዜጐች መሆናቸውንም አክለዋል፡፡ በሆቴሉ ውስጥ የነበሩ ቁም ሳጥኖች ከእነዕቃዎቻቸው፣ የተለያዩ ታሪካዊ ምሥሎች፣ ቅርፃ ቅርፆችና ሌሎች ብዙ ዕቃዎች መውደማቸውንም ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን ግን፣ በአካባቢው ነበርን የሚሉትንም ሰዎች ሆነ ሌላ አካል የሚለውን አይቀበልም፡፡ የባለሥልጣኑ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ደጋፊ የሥራ ሒደት መሪ አቶ ሰለሞን መኰንን ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ እቴጌ ጣይቱ ሆቴል ላይ ቃጠሎ እንደተነሳ መረጃ የደረሳቸው ከማለዳው 3፡08 ሰዓት ነው፡፡ የእሳት አደጋ መከላከል ቡድኑ ወዲያው ተሰማርቶ በሁለት ደቂቃ ውስጥ በቦታው ደርሷል፡፡


 ‹‹አደጋው ከባድ ነበር፡፡ የባለሥልጣኑ ሰባት ቅርንጫፍ ጣቢያዎች ከባለሙያዎችና ከማሽኖች ጋር ተሰማርተው በመረባረባቸው እሳቱን መቆጣጠር ተችሏል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡
የባለሥልጣኑ ሠራተኞች ከነማሽኖቻቸው ደርሰው በተለያዩ አቅጣጫዎች እሳቱን እየቆረጡ ማጥፋት ባይችሉ ኖሮ፣ በአካባቢው የሚገኙ መሥሪያ ቤቶችንና መኖሪያ ቤቶችን ሊያዳርስና ሊያጠፋ ይችል እንደነበር የተናገሩት የሥራ ሒደት መሪው፣ ‹‹በስንት ሰዓት እሳቱ ተነሳ? በስንት ሰዓት እናንተ ደረሳችሁ? የሚለው ጥያቄ ለእኛ አይጠቅምም፡፡

 እኛ የምንሠራው የእሳት ቃጠሎ ተነሳ ተብሎ የተደወለበትን አስበን ነው፡፡ ወዲያው ስላልተደወለ እሳቱ ሊስፋፋ ችሏል፤›› ብለዋል፡፡

በሆቴሉና በባለሥልጣኑ መካከል ያለው ርቀት አጭር ከመሆኑ አንፃር የደረሱበት ሰዓት መዘግየቱን በተመለከተ ተጠይቀው፣ ጥሪው በደረሳቸው በሁለት ደቂቃ መድረሳቸውን የተናገሩት አቶ ሰለሞን፣ እንደተባለው እቴጌ ጣይቱ ሆቴል ለባለሥልጣኑ ቅርብ ከመሆኑ አንፃር የዘገዩት እነሱ ሳይሆኑ፣ ጥሪው የደረሰበት ጊዜ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ባይዘገይ ኖሮ ብዙ ንብረት ማትረፍ ይቻል እንደነበርም አስረድተዋል፡፡
አቶ አያሌው ማብሰያ ክፍሉ ቆይቶ እንደተቃጠለ የተናገሩ ቢሆንም፣ አቶ ሰለሞን ግን ለእሳቱ መባባስ ምክንያቱ በማብሰያ ቦታ አካባቢ የነበሩ ቁሳቁሶች መሆናቸውንና ቃጠሎውንም ከባድ እንዳደረጉት ገልጸዋል፡፡ 113 የባለሥልጣኑ ሠራተኞች በ12 ተሽከርካሪዎችና በአምስት አምቡላንሶች ታግዘው፣ 236,300 ሊትር ውኃና 500 ሊትር ፎም በመርጨት ቃጠሎውን መቆጣጠር መቻላቸውን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል፡፡ አደጋውን ለመቆጣጠርም ከሁለት ሰዓት በላይ መፍጀቱን ጠቁመው፣ ምክንያቱ ደግሞ ሆቴሉ ከጥድ እንጨት የተሠራ በመሆኑ በቀላሉ ማጥፋት ስለማይቻል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የጃዝ አምባ ላውንጅ ባለቤቶች ወይም ኃላፊዎችን ለማግኘት ባለመቻሉ በእነሱ በኩል ያለውን መረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡
በእቴጌ ጣይቱ ሆቴል ግቢ ውስጥ ሕብረት ባንክ፣ የትኬት መሸጫ ቢሮና ሌሎች ድርጅቶች ተከራይተው ይሠራሉ፡፡ የትኬት መሸጫ ቢሮ ኃላፊዎችና የሌሎቹ ድርጅቶች ባለቤቶች ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል ባለሥልጣን በወቅቱ ደርሶ ቢሆን ኖሮ እሳቱን መቆጣጠር ይቻል ነበር፡፡

በተመሳሳይ የሕብረት ባንክ አክሲዮን ማኅበር ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. በፕሬዚዳንቱ አማካይነት መግለጫ የሰጠ ሲሆን መገናኛ ብዙኃንን፣ ኅብረተሰቡንና ሌሎች የሚመለከታቸው አካሎች እሳቱን ለማጥፋትና የደረሰውን አደጋ ለሕዝብ ለማሳወቅ ያደረጉትን አስተዋጽኦ አድንቋል፡፡ በሆቴሉ ግቢ ውስጥ በነበረው ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ላይ ምንም ዓይነት የገንዘብም ሆነ የመረጃ ሰነዶች መቃጠል እንዳልደረሰበት አስታውቋል፡፡

ደንበኞቹ በሞባይል፣ በኢንተርኔት፣ በኤቲኤምና በሌሎቹም አገልግሎቱን እያገኙና የሚያገኙ በመሆናቸው ምንም ዓይነት ሥጋት እንደሌለ ገልጿል፡፡ እሳት ያልበገረው ካዝናውን በግራይንደር በመቁረጥ ገንዘቡ ተቆጥሮ ከመዝገቡ ጋር ተመሳክሮ ትክክለኛነቱ መረጋገጡን አስታውቋል፡፡

እቴጌ ጣይቱ ሆቴል በቀድሞ የኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ለአቶ ፍፁም ዘአብ አስገዶም መሸጡ ይታወሳል፡፡ አሁንም የሆቴሉ ባለቤት አቶ ፍፁም ናቸው፡፡ በአፄ በዳግማዊ ምኒልክ ባለቤት እቴጌ ጣይቱ ብጡል በ1898 ዓ.ም. ነው የተገነባው፡፡ የመንበረ ፀሐይ እንጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያንን ሊመርቅ የመጣው ሕዝብ ምግብና ማረፊያ አጥቶ ስለነበር፣ አፄ ምኒልክ የሌሎች አገሮች የሆቴል ልምድን ከቀሰሙ በኋላ፣ በ1898 ዓ.ም. ‹‹ሆቴል›› የሚል ስያሜ ሰጥተውት ሥራ መጀመሩን የንጉሠ ነገሥቱ ዜና መዋዕል ፀሐፊ የነበሩት ፀሐፌ ገብረሥላሴ ካሰፈሩት መረጃ መገንዘብ ይቻላል፡፡

ሆቴሉ ከተሠራ በኋላ ሕዝብ ሊጠቀምበት ባለመቻሉ አፄ ምኒልክ መኳንንቱን እየሰበሰቡ በተደጋጋሚ በመጋበዛቸው፣ የእሳቸውን ብድር ለመመለስ መኳንንቱ ‹‹እቴጌ ውቴል ሄደን እንብላ›› ማለት ስላበዙ ‹‹እቴጌ ሆቴል›› የሚለውን መጠሪያ እንዳገኘም ይታወቃል፡፡

መጠሪያው እስከ 1967 ዓ.ም. የቆየ ቢሆንም፣ ደርግ የንጉሠ ነገሥት ሥርዓቱን ካስወገደ በኋላ ስያሜውን ‹‹አውራሪስ›› ብሎ ነበር፡፡ እስከ ውድቀቱ ድረስ (1983 ዓ.ም.) ሲጠራበት መቆየቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ እቴጌ ሆቴል በይፋ የተመረቀው ከ107 ዓመት በፊት ጥቅምት 25 ቀን 1900 ዓ.ም.ነበር፡፡
ምንጭ፡ ሪፖርተር ጋዜጣ።

 

onsdag 14. januar 2015

በዞን 9 ጦማርያንና ጋዜጠኞች ላይ የቀረበው ክስ በድጋሜ ‹‹ተሻሻለ››

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
ጦማርያኑና ጋዜጠኞቹ ጥር 6 ቀን 2007 ዓ.ም ለ15ኛ ጊዜ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የተሰየመው ቀደም ብሎ በጦማርያኑ እና ጋዜጠኞች ላይ የተመሰረተው ክስ እንዲሻሻል ባዘዘው መሰረት የፌደራል አቃቤ ህግ ክሱን ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ያላሻሻላቸው ነጥቦች ስለነበሩ እነዚህኑ ነጥቦች በድጋሜ አሻሽሎ እንዲቀርብ ባዘዘው መሰረት የተሻሻለውን ክስ ለመስማት ነበር፡፡
36884-zone9-bloggers4
በመሆኑም የፌደራል አቃቤ ህግ አሻሽየዋለሁ ያለውን ክስ ይዞ ቀርቧል፡፡ ክሱ ‹‹ሌሎች ብዙ ‹ኬዞች› ስላሉ›› በሚል ምክንያት በችሎቱ ላይ በንባብ እንዲሰማ አልተደረገም፡፡ ተሻሻለ የተባለው ክስ ለተከሳሾችና ለጠበቆች እንዲደርስ የተደረገውም እዚያው ችሎት ውስጥ ነው፡፡
ክሱ በንባብ ባለመሰማቱና ጠበቆቹና ዳኞቹም ስላላነበቡት በሚል ተሻሻለ በተባለው ክስ ላይ ምንም አስተያየት አልቀረበም፡፡ በመሆኑም ክሱ መሻሻል አለመሻሻሉን ለመመርመርና ብይን ለመስጠት ለጥር 20 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
የጦማርያኑ እና ጋዜጠኞች ጠበቃ የሆኑት አቶ አምሃ መኮንን እንዳሉት በቀጣዩ ቀጠሮ ላይ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ተሻሽሎ ካልሆነ ነጥቦቹን ፍርድ ቤቱ ውድቅ ያደርጋል ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በእኛ በኩል ከዚህ በኋላ የማሻሻያ ሀሳብ አቅርበን ጊዜ አንፈጅም፤ ከሚቀጥለው የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ መደበኛ ክርክራችንን መቀጠል ነው የምንፈልገው›› ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በዛሬው የችሎት ውሎ ላይ በጣም ብዙ እስረኛ (ተከሳሽ) ችሎቱ ውስጥ በመገኘቱ ምክንያት ከፍተኛ የቦታ ጥበት ማጋጠሙ ተስተውሏል፡፡ በአጠቃላይ እስከ 70 የሚደርሱ እስረኞች በችሎቱ ተገኝተዋል፡፡ ስለሆነም ችሎቱን መታደም የቻሉት ጥቂት ጋዜጠኞችና ዲፕሎማቶች ብቻ ሆነዋል፡፡ የተከሳሽ ቤተሰብና ወዳጅ ዘመዶች ችሎቱን መታደም አልቻሉም፡፡

mandag 12. januar 2015

Hiber Radio: የሕወሓት አስተዳደር ተለጣፊ አንድነት ፓርቲ መመስረቱ… የግንቦትና አርበኞች ግንባር ውህደት መነቃነቅ መፍጠሩ… ባለስልጣናቱ ለውጭ ሚዲያዎች የዋጋ ግሽበት መኖሩን ማመናቸውና ሌሎችም

 


  • ጋዜጠኛ ሃብታሙ አሰፋ
    ጋዜጠኛ ሃብታሙ አሰፋ
    የህብር ሬዲዮ ጥር 3 ቀን 2007 ፕሮግራም
    የኢሳት ኤርትራ መግባትና የአርበኞች ግንባርና የግንቦት ሰባትን ውህደት በተመለከተ ከጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ጋር ቆይታ አድርገናል (ሙሉውን ያዳምጡ)
    <…ምርጫ ቦርድ በአራት ቀን ውስጥ ጊባዔ አድርጉ አለ ባልጠበቀው ሁኔታ ከመላው አገሪቱ ጉባዔተኛው መጥቶ ጉባዔው ሲደረግ በስፍራው ሳይገኝ ተለጣፊ አንድነት አቋቁሜያለሁ አለ ። ኢ/ር ግዛቸውን የመረጠው የጠቅላላ ጉባዔ አባላት መካከል ከ209 በላይ ተገኝቶ አቶ በላይ ፈቃዱን መርጧል ሕግ የለም እንጂ ሕግ ቢኖር ያ በቂ ነው ከዚህ በሁዋላ አንድነት ከሚበረከክ ቢፈርስ ይሻላል ….>
    አቶ አስራት አብርሃም የአንድነት ተጠባባቂ የሕዝብ ግንኙነት የነበሩ የዛሬውን የአንድነት ጉባዔና የምርጫ ቦርድን ሕገ ወጥ አካሄድ በተመለከተ ከሰጡን ማብራሪያ(ሙሉውን ያዳምጡት)
    በፓሪስ የተደረገው የሽብር ጥቃት፣ የመናገር ነጻነትና ተከትሎት የመጡት ጥአቄዎች(ልዩ ዘገባ)
    <<የሞት ጉዞ>> መጽሐፍ ደራሲ ከሆነው ጋዜጠኛና ደራሲ ግሩም ተክለሀይማኖትን ካለበት የመን እንዲሁም የ <<ምስጦቹ>> መጽሐፍ ደራሲ ተዘራ ታምራትን ከግብጽ ካይሮ ስለ መጽሐፋቸው አወያይተናል (ሙሉውን ያዳምጡት)
    ሌሎችም
    ዜናዎቻችን
    በኢትዮጵያ ያለው የዋጋ ግሽበት እየጨመረ መሔዱን የአገዛዙ ባለስልጣናት ለውጭ ሚዲያ አመኑ
    በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው ጥንታዊው ጣይቱ ሆቴል ዛሬ በተነሳው የእሳት ቃጠሎ ከፍተኛ ውድመት ደረሰበት
    የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ጋና ላይ ተከስክሶ ወደቀ
    አንድነት ፓርቲ በአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤው ፕሬዝዳንቱን ደግሞ መረጠ
    ምርጫ ቦርድና ሕውሓት በጋራ አንድነት የሚል ተለጣፊ ድርጅት ፈጥረው ፕሬዝዳንት ያሉት ተመረጠ
    በተለጣፊው አንድነት ምርጫ ላይ አባላት ያልሆኑና የደህንነቱ መ/ቤት ሰዎች በአካባቢው እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል
    ትንሳኤ ኢህአፓ በድርጅቱ ስም የሚንቀሳቀሱት ቡድኖች ከእርስ በእርስ ጥሎ ማለፍ ለፀረ ወያኔ ትግሉ ቅድሚያ በመስጠት ዛሬም አንድ ላይ እንዲመጡ ጠየቀ
    የግንቦት ሰባትና የአርበኞች ግንባር ውህደት በአገር ውስጥና በውጭ መነቃቃት እየፈጠረ ነው https://soundcloud.com/hiber-radio-las-vegas-1

    torsdag 8. januar 2015

    ሁለት የኢሳት ጋዜጠኞች በድንበር አካባቢ ያሉ እንቅስቃሴዎችን ለመዘገብ ወደ ኤርትራ መሄዳቸው የበርካታ ኢትዮጵያንን እያነጋገረ ነው።

    ኢሳት በትናንት በዘገባው እንዳስታወቀው ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን እና ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም  ወደ ኤርትራ ያቀኑት  በኤርትራ ድንበር አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የ ኢት ጰያ ተቃዋሚዎች እያደረጉት ያለውን እንቅስቃሴ በዓይን
    አይቶ ለመዘገብ፤እንዲሁም  ከተሳካላቸው በወደፊቱ የኢትዮጰያና የኤርትራ ግንኙነት ዙሪያ  የኤርትራ ባለስልጣናትን ቃለ ምልልስ ለማድረግ ነው። ይህን ተከትሎ  እጅግ በርካታ ኢትዮጰያውያን ለጋዜጠኞቹ ያላቸውን አክብሮትና አድንቆት  በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።
    እነኚህ ወገኖች ፤ጋዜጠኞቹ-  እንደ ጋዜጠኛ በተግባር መሬት ላይ ያለውን ነገር አይተው ለህዝብ ለማሳወቅ  ወደ ድንበር ማምራታቸው ፤ ለሙያቸው የተሰጡ መሆናቸውን የሚያመላክት ከመሆኑም ባሻገር – ውሳኔያቸው በሁለቱ ሀገራት ህዝቦች መካከል መልካም መቀራረብና ወንድማችነት እንዲኖር  የሚያበረክተው አስተዋጻኦ ከፍተኛ  ነው ብለዋል።
    አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በየመን መንግስት ለኢህአዴግ ተላልፎ መሰጠቱ  ያስቆጣቸው  ኢትዮጰያውያን ደግሞ፤ በማህበራዊ ሚዲያዎችም ሆነ ወደ ኢሳት ስልክ በመደወል  በሰጡዋቸው አስተያየቶች  ፤ጋዜጠኞቹ የወሰዱትን ድፍረት በማድነቅ በሰላም እንዲመለሱ ምኞታቸውን ገልጸዋል። እነኚህኞቹ  ጋዜጠኞቹ በሰላም  እንዲመለሱ ምኞታቸውን እየገለጹ ያሉት ፤ በሀገር ቤት ያሉ ጋዜጠኞችን  ለእስርና ስደት የዳረገውና በኢሳት ክፉኛ የሚበሳጨው የኢህአዴግ መንግስት እንደ አቶ አንዳርጋችው ጽጌ ጋዜጠኞቹን በመንገዳቸው ላይ  በገንዘብ እንዳያስጠልፋቸው በመስጋት ነው።
    በሌላ በኩል የገዥው ፓርቲ አባላት የሆኑ ካድሬዎች ደግሞ፤ የጋዜጠኞቹ ለዘገባ ወደ ኤርትራ ማቅናት  ከተሰማ በሁዋላ ቁጣና ንዴታቸውን ያለመቋረጥ በመግለጽ ላይ ናቸው። በአሁኑ ወቅት ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን እና ፋሲል የኔዓለም  በሰላም ኤርትራ ከመግባታቸውም በላይ በነጻነት በመንቀሳቀስ የሄዱበትን ስራ እየከወኑ ይገኛሉ።
    ጋዜጠኛ መሳይ በፌስ ቡክ ገጹ አስመራ ከተማን ከሁዋላው አድርጎ በተነሳው ፎቶ ስር ባሰፈረው ጽሁፍ፦<<አስመራ፡ ተራራ ላይ የከተመች፡ ጥንታዊ ገጽታዋን ያለቀቀች ውብ ከተማ። ኢሳት አስመራ ገብቷል፡፡ ሰላማዊውን ትግል በሰፊው እየዘገብን ነው። ዱር ቤታቸው አድርገው በሃይል ህወሀትን ለማስወገድ የተዘጋጁትን ሃይሎች ደግሞ በአካል ተገኝተን ልናያቸው ነው፡፡ባልደረባዬ ፋሲል የኔዓልምም ከአምስተርዳም አስመራ ከቷል። ታሪካዊ ጉዞ ነው፡፡>>ብሏል።
    በሚቀጥሉት ቀናት ወይም ሳምንታት ፋሲልና መሳይ በኤርትራ ቆይታቸው ከስፍራው  የሚያጠናቅሯቸውን ዘገባዎች  በቀጥታ የምናቀርብ መሆኑን ከወዲሁ እናሳውቃለን።

    ሁላችንም አንዳርጋቸው ጽጌን እንሁን!!!


    በህወሓት ሙሉ ቁጥጥር ስር የሚገኘው የፌደራል ፓሊስ በእሁድ ታህሣሥ 28 ቀን 2007 ዓ.ም. የቴሌቪዥን ፕሮግራሙ በግፍ እስር ላይ የሚገኘውን የግንቦት 7 ዋና ፀሐፊን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን አቅርቦት ነበር። ይህ የ10 ደቂቃዎች ምስል ለቁጥር በሚያታክት ብዛት ተቆራርጦ የተቀጣጠለ በመሆኑ አቶ አንዳርጋቸው ምን ተጠይቆ ምን እንደመለሰ ማወቅ አይቻልም። ስለሆነም በንግግሩ ይዘት ላይ አስተያየት መስጠት ይናገረው አይናገረው በአልታወቀ ጉዳይ ማብራሪያ መስጠት ይሆናል።  ስለዚህም፣ በንግግሩ ይዘት ላይ ጊዜ ከማጥፋት ህወሓት አንዳርጋቸው ጽጌን አሁን ማቅረብ ለምን እንደፈለገ መተንተን ይበልጥ ጠቀሜታ  አለው ብሎ ግንቦት 7 ያምናል።
    አሁን ህወሓት በውስጥም በውጭም ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የገባበት ጊዜ ነው፤ በራሱ በድርጅቱ ውስጥም ሰላም የለም። ህወሓት የትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሩ ስር እንደሆነ አድርጎ በመቁጠር መላዋን ኢትዮጵያን ለመዝረፍና ለማጥቃት እንደ መንደርደሪያ፤ በሌላኛው የኢትዮጵያ ክፍል ተቃውሞ ሲበዛበት ደግሞ እንደ መደበቂያ ዋሻ ሲጠቀምበት የነበረው ጊዜ አብቅቶ የትግራይ ሕዝብ በህወሓት ላይ ማመጹ በግልጽ በተግባር እየታየ ነው። በርካታ የትግራይ ልጆች በህወሓት ላይ ነፍጥ አንስተዋል፤ ከፊሎቹ ደግሞ በሰላማዊ ትግል ህወሓትን ማስወገድ ይቻላል ብለው በክልላቸውም ከክልላቸውም ውጭ ከህወሓት ጋር ፍልሚያ ገጥመዋል። ህወሓት መሠረቴ ነው ከሚለው የትግራይ ክልል ፈጽሞ ሊነቀል የሚችል መሆኑ ግልጽ ምልክቶች እየታዩ ነው። የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) ከትግራይና ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያገናኘው የአማርኛና የትግርኛ የቴሌቪዥን ፕሮግራም መጀመሩ የህወሓት ሹማምንትን ናላ ያዞረ እርምጃ ሆኗል።
    የህወሓት ሌላው መተማመኛው የጦር ሠራዊቱ ነበር። ህወሓት፣ የኢትዮጵያን መከላከያ ጦር ሠራዊት ዘረኛ በሆነ መንገድ አደራጅቶ፤ ከፍተኛ አመራሩን በታማኝ አባላቱ ሞልቶ ተደላድሎ  የተቀመጠ መስሎ  ታይቶ ነበር። አሁን ግን ይህም ምስል አሳሳች እንደሆነ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት የኢትዮጵያ ጠላት የሆነውን ህወሓትን የማገልገል ፍላጎት የሌላቸው መሆኑን፤ እንዲያውም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን በመቆም የህወሓትን ውድቀት ለማፋጠን ያላቸውን ጉጉት በግልጽ እያሳዩ ነው። አየር ኃይል ውስጥ ያለው ተቃውሞ ገሀድ የወጣ  ዜና ሆኗል። እንደ አየር ኃይል ገሀድ የወጣ ዜና አይሁን እንጂ በሌሎችም የሠራዊቱ ክንፎች ያለው አመጽ ተመሳሳይ የጡዘት ደረጃ ላይ ደርሷል።
    ብአዴን እና ኦህዴድ ውስጥ ለአገራቸው ለኢትዮጵያ፣ እንወክለዋለን ለሚሉት ሕዝብ እና ለራሳቸው ክብር ያላቸው አባላት ብቅ ብቅ እያሉ ነው። ብአዴንንና ኦህዴድ እንደ ድሮ ፍጽም ታማኝ አገልጋዮች የመሆናቸው ጊዜ እያበቃ ነው። ደኢህዴንም ቢሆን ሙሉ በሙሉ የሚታመን አይደለም። ጊዜው ለህወሓት እጅግ የመክፋቱ ምልክት ደግሞ እራሱ ህወሓት ውስጥም ስምምነት የሌለ መሆኑ ነው። ህወሓት ይይዘው ይጨብጠው ጠፍቶታል።
    ለዓመታት የዘለቀው የሙስሊም ወገኖቻችን ተቃውሞ እረፍት ነስቶት እያለ በባህርዳር የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ወገኖቻችን ተቃውሞ ተጨመረበት። የአምቦውን ተቃውሞ አዳፈንኩ ሲል የጎንደር ተቀሰቀሰበት። ለጉራና ለሀብት ዘረፋ ሲል ያስጀመረው  የአባይ ግድብ፣ ጥበቃው ብቻ እንኳን ፋታ የሚነሳ ሥራ ሆነበት። ጋምቤላ፣ አፋርና፣ ሶማሊ የግጭት ቀጠናዎች ከሆኑ ዓመታት አስቆጠሩ።
    ከላይ የተዘረዘሩት ጉምጉምታዎች፣ ተቃውሞዎችና አመጾች ተቀናጅተው የመጡ ዕለት መድረሻ እንደሚያጣ የተገነዘበው ህወሓት ትኩረት ማስቀየሻ መፈለጉ ግድ ነበር። በግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ እምነት በአሁኑ ሰዓት የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ወደ ሚዲያ መቅረብ ምክንያቱ ይህ ነው። አንዳርጋቸውን ወደሚዲያ በማቅረብ ትኩረትን የማስቀየስ ስትራቴጂ!
    የፊልሙ ማጀቢያዎች የነበሩት የሂውማን ራይትስ ዎች ሪፓርት፣ ስለእንግሊዝ ጋዜጣ የተነገረው፣ አሜሪካ ስለምትፈጽመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተዘከረው፣ ወዘተ … ወዘተ የሚያመላክቱት አንድ አቢይ ሀቅ አለ። ይህም ኢትዮጵያዊያን ፀሐይና ብርድ ሳይበግራቸው “እኔ አንዳርጋቸው ጽጌ ነኝ” እያሉ በእንግሊዝ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፣ በእንግሊዝ ኤምባሲዎች እና በአውሮፓ ኅብረት ሲያደርጓቸው የቆዩ ተቃውሞዎች ውጤታማ መሆናቸው ነው። በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የፈጠሩት ጫና ወያኔን ወደ ተከላካይነት አውርዶት “እኔ ንፁህ፣ አሜሪካ ርኩስ” እንዲል አድርጎታል።  ወያኔ፣ ስለንፅህና ምስክርነትት ይሰጥልኛል ብሎ ተስፋ ያደረገው ደግሞ ራሱ ነፃነቱን ገፎ እስረኛው ያደረገው ሰው መሆኑ ጥረቱ እንደምን ውል አልባ እንደሆነበት ያሳያል። ንፅህናን ነፃ ባልሆነ ሰው ማስመስከር ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው? ይህ ክስተት፣ የኢትዮጵያዊያን ዘርፈ ብዙ ተቃውሞ የወያኔን የመከላከል አቅም ማዳከሙን በግልጽ ያሳያል። ይህ ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ ብሥራት ነው።
    ከላይ የተዘረዘሩት ምክንያቶች ህወሓት አንዳርጋቸውን ወደሚዲያ ለማቅረብ ምክንያት ይሁኑ እንጂ የአንዳርጋቸው ለሶስተኛ ጊዜ በወያኔ ቴሌቬዥን መታየት በኢትዮጵያዊያን ላይ የፈጠረው ስሜት ህወሓት ከጠበቀው ፈጽሞ የተለየ ነው።
    ኢትዮጵያዊያን አንዳርጋቸውን ሲያዩ የሚታያቸው ጽናት፣ አርበኝነትና አልበገር ባይነት ነው። የአንዳርጋቸው ምስል በታየ ቁጥር ኢትዮጵያዊያን ፀጉራቸው ይቆማል፤ ደማቸው ይፈላል። ወያኔዎች አንዳርጋቸውን የፈለጉትን ቢያናግሩት ችግር የለም። ለጊዜው በእጃቸው ውስጥ ስለሆነ ያላለውን ያለ ሊያስመስሉ እንደሚችሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቃል። ወደፊት ደግሞ ሊናገር ያልፈለገውን ያናግሩት ይሆናል። ይህ ሁሉ የሚያመጣው ለውጥ የለም። አንዳርጋቸው ስለወያኔ ምንነትና ማንነት ማንም ሳያስገድደዉ በነፃነት አገር ዉስጥ በግልጽ ተናግሯል፣ አሁንም ወያኔዎች እራሳቸዉ በሰሩት ፊልም ዉስጥ እነሱ በማይገባቸው መንገድ ለኢትዮጵያን ሕዝብ ተናግሯል። እንኳንስ እነሱ እሱም ራሱ በማይገባው መንገድ አንዳርጋቸው ኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ ገብቷል። አንዳርጋቸውን ስናይ በህወሓት ፋሽስታዊ መዳፍ ውስጥ የወደቁብንን ጀግኖቻችንን ሁሉ ያስታውሰናል። በአስር ሺዎች ይቆጠራሉ። የአንዳርጋቸው ምስል ለግላጋ ወጣቶች፣ በሳል አዛውንት፣ ምርጥ ወንድሞችና እህቶች በወያኔ እስር ቤቶች ፍዳቸውን እያዩ መሆኑን ያስታውሰናል። ምስሉ ብቻውን ያናግረናል፣ ያነቃናል፣ ያነሳሳናል!!!
    ግንቦት 7:  የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አንዳርጋቸው ጽጌን፣ በርካታ ጀግኖቻችንን፣እራሳችንንና አገራችንን ከወያኔ እስር ነፃ ለማውጣት ክንዳችንን እናበርታ፤ ሁላችንም “እኔም አንዳርጋቸው ጽጌ ነን” እንበል፤ ሁላችንም አንዳርጋቸው ጽጌን እንሁን ይላል።
    ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!

    fredag 2. januar 2015

    በድሬዳዋ አየር ሃይል ውጥረት የበዛበት ግምገማ ተካሄደ

    አራት ከፍተኛ ማእረግ ያላቸው የአየር ሃይል አብራሪዎች መጥፋታቸውን ተከትሎ በድሬዳዋ የአየር ሃይል ምድብ ሲካሄድ የነበረው የ3 ቀናት ግምገማ ሃሙስ እለት ተጠናቋል።
    በግምገማው ላይ አብራሪዎች፣ አሰልጣኞች፣ ቴክኒሻኖችና ሰራተኞች የተገኙ ሲሆን፣ ሰራተኞቹ ስለጠፉት አብሪዎች የተሰማቸውን ስሜት እንዲናገሩ፣ የሚያውቁትን ሚስጢር እንዲያወጡ ሲገደዱ ሰንብተዋል። ብዙዎች ” ስለጠፉት አብራሪዎች ምን ትላላለችሁ?’ እየተባሉ ሃሳባቸውን እንዲናገሩ የተጠየቁ ሲሆን፣ በሚሰጡት ሃሳብ ተንተርሶ የደህንነት ሃይሎች ተጨማሪ ምርምራ እንደሚያካሂዱ በግምገማው ላይ የተሳተፉ ወገኖች ገልጸዋል።
    በግመገማው ላይ የተገኙት አዛዦች በሙሉ እጅግ ተናደው መሰንበታቸውን የሚናገሩት ምንጮች፣ በግቢው ውስጥ ያለው ድባብ ውጥረት የበዛበት በመሆኑ ሰራተኞች ተረጋግተው ስራቸውን ለመስራት አልቻሉም። የእርስ በርስ ጥርጣሬውና አለመተማመኑ የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱንም ሰራተኞች ገልጸዋል።
    በዚህ ሳምንት ስርአቱን አናገለግልም ብለው ወደ ኬንያ የተሰደዱትን አብራሪዎች በተመለከተ ኢሳት ለወደፊቱ ዝርዝር መረጃዎችን እንደሚያቀርብ ለመግለጽ ይወዳል።