ላለፉት ሶስት ወራት ስኬታማ ህዝባዊ ንቅናቄ ሲያደርግ የቆየው አንድነት ፓርቲ የመጀመሪያውን ዙር ለሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት ህዝባዊ ንቅናቄ መስከረም 19 ቀን 2006 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ከሰላሳ ሶስቱ ፓርቲዎች ጋር በሚያደርገው ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ያጠናቅቃል፡፡ የህዝባዊ ንቅናቄው አካል የሆነው የበይነ መረብ ዘመቻ(online social media campaign) ከመስከረም 14-18 ቀን 2006 ዓ.ም ይደረጋል፡፡ ዘመቻው ትኩረት የሚያደርገው የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት ህዝባዊ ንቅናቄ ቀዳሚ አጀንዳ በሆነውና የፀረ ሽብር ህጉ እንዲሰረዝ በሚጠይቀው የትኩረት ነጥብ ላይ ነው፡፡
ለአምስት ቀናት የሚቆየው የበይነ መረብ ዘመቻ አንድነት ፓርቲ የጸረ ሽብር ህጉ እንዲሰረዝ የጠየቀባቸውን ጉልህ ህገ መንግስታዊ መሰረታዊያን በማብራራት ህዝባዊ ንቅናቄውን በበይነ መረብ (online social media campaign) የሚያቀጣጥል ነው፡፡ የበይነ መረብ ዘመቻው የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው መሰረታዊ ህገ መንግስታዊ መብቶችን የሚደፈጥጠው የፀረ ሽብር ህግ እንዲሰረዝና መንግስት ህገ መንግስቱን እንዲያከብር የሚጠይቅ ነው፡፡
በዚህ ዘመቻ የተለያየ ርዕዮተ አለም የሚከተሉ ሆኖም ህገ መንግስቱ እንዲከበር የሚጠይቁ የዴሞክራሲያዊ ኃይሎች አባላት፣ ነፃ የሲቪክ ማህበረሰብ አባላት፣ የሀገሬ ጉዳይ ይመለከተኛል ለሚሉ ዜጎች፣ የመብት አራማጆች(አክቲቪስቶች) እና ህገ መንግስቱ እንዳይሸራረፍ የሚፈልጉ የኢህአዴግ አባላት እንደሚሳተፉበት ይጠበቃል፡፡
ለበይነ መረብ ዘመቻው የተዘጋጁ የፕሮፋይል ምስሎችና የከቨር ምስሎችን በመቀየር እንዲሁም #millionsofvoices የሚለውን ሀሽ ታግ በመጠቀም የሚተላለፉ መልዕክቶቻችንን በማሰራጨት ለህገ መንግስት የበላይነት እንዲቆሙ በአክብሮት ይጠየቃሉ፡፡
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ
ለሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት
ግብረ ኃይል
ለሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት
ግብረ ኃይል
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar