lørdag 17. januar 2015

“ሉዓላዊነትና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ” ዓብይ ጉዳይ! – ኣረጋዊ በርሄ


gebru-asrat-bookኣቶ ገብሩ ኣስራት ´ሉዓላዊነትና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ´ በሚል ርእስ ትልቅ መፅሓፍ ፅፈዋል፤ ትልቅነቱ ሃገርን ያክል ዓብይ ስብስብ የሚንዱ ወይም የሚገነቡ ርእሰ ጉዳዮች – ማለት ሉዓላዊነትና ዲሞክራሲ- በኢትዮጵያችን የደረሱበትን ኣሳሳቢ ደረጃ ኣስመልክቶ እንድንመክርበት በጥልቀት መርምሮ ስላስቀመጠልን ነው። ከዚህም ኣልፎ ላሳሳቢው ችግር መፍትሄ ይሆናሉ ያላቸውን ኣንኳር ፍሬነገሮች ግልፅ ኣድርገዋል። ከዚህ በመነሳት ይህ ትላልቅ ርእሶችን ያነገበ መፅሓፍ እንዴት መታየት እንዳለበት፤ ግድፈቶቹን ሳልተው የበኩሌን ኣስተያየት ኣጠር ባለ መልኩ ለማከል እወዳለሁ።
መፅሓፉ በ6 ምዕራፎች የተከፈለ ሲሆን የመጀመርያ 2ቱ ምዕራፎች ሉዓላዊነትና ዲሞክራሲ ኣሁን ለደረሱበት ኣሳፋሪ ደረጃ ማገናዘብያና ታሪካዊ መንደርደርያ ሲሆኑ፣ የተቀሩት 4ቱ ደግሞ የሉዓላዊነትና ዲሞክራሲ መሸርሸር እንዴት እንደተከናወነና በኢትዮጵያ ማሕበረ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ይዘት ላይ ያስከተለው ኣሉታዊ ተፅእኖ ይተነትናሉ። በመጨረሻም የመፍትሄ ሓሳቦችን በመሰንዘር ያጠቃልላል።
ብዙዎቹ ጠበብት እንደሚስማሙት ሉዓላዊነት የኣንድን ሃገር መብትና ጥቅም ለማስከብር የሚያገለግል ከፍተኛው ሕጋዊ ስልጣን መጨበጥ ማለት ነው። ይህ ከፍተኛው ሕጋዊ ስልጣን ከሃገራችን እውነታ ኣኳያ ሲታይ በኣሁኑ ወቅት ምን ያህል እንደተሸረሸረና ያስከተለው ጉዳት በጥቅሉ ቢታወቅም በዝርዝር ማወቁና የደረሰው ጥፋት ይሽር ዘንድ፣ ብሎም እንዳይደገም የያንዳንዱ ዜጋ ተቀዳሚ ሓላፊነት በመሆኑ ይህ መፅሓፍ ለዚህ ሓላፊነት ንቁና ብቁ የማድረግ ተልእኮ ኣለው እላለሁ።
ይህንን ሃገራዊ መብትና ጥቅም ማስከብር የመንግስት ተቀዳሚ ሓላፊነት ቢሆንም፤ ከ24 ዓመታት በፊት ስልጣን የጨበጠው ህወሓት/ኢህኣዴግ መንግስታዊ ስልጣኑ የተገለገለበት ሂደት ሲመረመር፣ ጭራሽ በሚገርም ሁኔታ የህዝቡን መሰረታዊ መብቶች በመጨፍለቅና የሃገሪቱን ኣንጡራ ጥቅሞች ለዘራፊዎች ኣሳልፎ በመስጠት እንደነበረና እንደሆነ እነሆ ኣቶ ገብሩ ከርቀት ሳይሆን በሓላፊነት ተቀምጦ ከውስጥ እንደተገነዘበው ያረጋግጥልናል። ገብሩ ይህን የኣፈናና የክህደት ቅንብር ሲታገለው እንደቆየና ዋጋ እንደከፈለበትም ከመፅሓፉ ጋር ስንከንፍ እንገነዘባለን።  የሃገር ሉዓላዊነት ሲደፈር የሃገሬው ህዝብ መጎዳቱና መቃወሙ ነባራዊ ስለሆነ፣ ይህን ፍትሃዊ ተቃውሞ ለማዳፈን ሲባል ደግሞ ዲሞክራሲያዊ መብቶች መጨፍለቅ ኣብሮ የሚሄድ የስርዓቱ ዋነኛ ፖሊሲም ተግባርም እንደሆነ በራሱ ጭምር ከደረሱ በደሎች በመነሳት ያብራራልናል። ይኸው በግልፅ የተቀመጠውን ሃቅ ደግሞ በበቂ መረጃዎች ስለታጀበልን ለመገንዘብ ኣይከብድም፤ ለግላዊ ምክንያት ዓይንን ካልጨፈኑ ወይም ህሊናን ካልሸጡ በስተቀር።
በመጀመርያው ምዕራፍ እንደተቀመጠው በኣንድ በኩል የኢትዮጵያ ህዝብ ክብሩንና ዳር ድንበሩን ለማስከበር ከመሪዎቹ ጋር በመተባበር ባካሄደው መራራ ትግልና በከፈለው እጅግ ከባድ መስዋዕትነት የባዕዳን ወረራና ሴራ እንዳከሸፈና ሉዓላዊነቱን ኣስከብሮ እንደኖረ ሲታወቅ፤ በሌላው በኩል የመለስ ዜናዊና ግብረ ኣበሮቹ ሚና ደግሞ ያንን በኣያሌ መስዋዕትነት የተገነባው ሉዓላዊነትን ለመሸርሸር ብቻ ሳይሆን ኣሳልፎ ለመስጠትም እንደነበረና፣ ምን ያህልም አክርረው እንደተረባረቡበት በንፅፅር ያስረዳል። በዓለም ዙርያ ይሁን በሃገራችን ታሪክም እንደሚታወቀው ሁሉ፣ መሪዎች የሚታወቁበት ትልቁ ሚናቸው የሃገር ሉዓላዊነትን በመጠበቅና ዳር ድንበርን በማስከበርና ሲሆን የመለስ ሚና ደግሞ የተገላቢጦሽ፤ ሉዓላዊነትን ኣሳልፎ በመስጠት በመሆኑ ልዩ ከሃዲ መሪ ያደርገዋል።
በ2ኛው ምዕራፍ በዋናነት የምንረዳው መለስ ዜናዊና ግብረ ኣበሮቹ በትግሉ ወቅት ስውር ዓላማቸውን ለማሳካት የታጋይነት ካባ ለብሰው በማድፈጥ፣ ለህዝቦች መብትና ለሉዓላዊነት መከበር የቆሙትን ሃይሎች በተቀነባበረ ሴራ ከውስጥ እንዴት መምታት እንደቻሉ ይተነትናል። እራሱ ገብሩንና መሰሎቹን እንዴት ጠልፈው እንደጣልዋቸው ወደሁዋላ ቢያብራራልንም፣ በተመሳሳይ መልክ ቀደም ብለው ከተጠለፉት ታጋዮች ትምህርት ሳይወስድ ቀርቶ መዘናጋቱ ግን ሳይገርመኝ ኣልቀረም። ኣስመሳዮችና ከሃዲዎች ወደፊትም ሊኖሩ ስለሚችሉና እንደኣሁኑ ኣዘቅት ውስጥ ላለመዘፈቅ የዚሁን ሴራ ኣደገኛነት ተተንትኖ መቅረብ ትልቅ ትምህርት የሚገበይበት ነው። ይህ ኣውዳሚ ሴራ በሚገባ የተተነተነ ቢሆንም መለስ ዜናዊና ግብረ ኣበሮቹ ራሱ ገብሩን እንዴት እንዳጠመዱትና ምን ድረስ እንደወሰዱት ቢያክልበት ኖሮ ትንተናውን በይበልጥ ያጠናክረው እንደነበር ጥርጥር የለኝም።
እነዚህ ሁለት ምዕራፎች እንደ መንደርደርያ ኣድርገን ብንወስዳቸው፤ የሚቀጥሉት 4 ምዕራፎች ሉዓላዊነት የተሸረሸረበትና ዲሞክራሲ የተረገጠበት ተግባራዊ ሂደት በማያሻማ ጭብጣዊ ኣገላለፅ በዝርዝር ያትታል። እዚህ ላይ ሉዓላዊነትን ማስደፈርና ዲሞክራሲን መጨፍለቅ ለምን ኣስፈለገ ? የሚል መሰረታዊ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፤ ይገባልም። ዝርዝር ሂደቱን ስንመለከት የመለስ ዜናዊና ግብረ ኣበሮቹ የግል ስልጣን ጥም ማርካት ያስከተለው ረቂቅ በሽታ እንደሆነ ሊደረስበት ይቻላል። የግል ስልጣን በሽታ የተጠናወታቸው መሪዎች፥ በሌሎች መሪዎችም እንዳየነው፥ ለግል ስልጣናቸው መንከባከብ እስካገለገለ ድረስ ሉዓላዊነት ቢደፈር ፡ ዴሞክራሲ ቢጨፈለቅ ጉዳያቸው ኣይደለም። ለባዕዳን ሃይሎችም ተገዝተው የሚያገለግሉ “መሪዎችም” እንዳሉ ይታወቃል። ከነዚህኞቹ ኣንዱ መለስ ዜናዊ ሳይሆን ኣይቀርም። ይህ በተለያየ መልክ የሚንፀባረቀው ረቂቅ በሽታ ኣሁንም ወደፊትም ሊኖር ስለሚችል መድሓኒቱ የሚገኘው ከነቃና ከተደራጀ ህዝብ ብቻ ነው። ስልጣን በግለሰዎች እጅ እንዳይወድቅ፣ ህዝብ በየመልኩ ተደራጅቶ የስልጣን ባለቤትነቱን የሚያረጋግጥበት ስርዓት ፈጥሮ መኖር ይኖርበታል።
ወደ ዝርዝር ጉዳዮች ስንገባ፤ ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በይፋ መረገጥ የጀመረበት መቼና እንዴት እንደሆነ ገብሩ በማያሻማ ሁኔታ ያስረዳል። በ1983 ዓ/ም ሰንዓፈ – ኤርትራ ውስጥ በነመለስ ተረቆ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ነጻ ሆኖ ሳይመክርበት በላዩላይ የተጫነው ቻርተር ተግባር ላይ ሲውል ነው። ይህ ቻርተር ለህዝቡ ሳይሆን ለግላቸው የሚያገለገሉበት መንግስት እንዲፈጥሩ ኣስችሏቸዋል። “ኦነግ ፣ ሻዕብያና ህወሓት/ኢህኣዴግ የተስማሙበት ይህ ሰነድ በኢትዮጵያ የሚመሰረተው የሽግግር መንግስት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ኣሳድረዋል።” (ገብሩ፤ ገጽ 181) ካለ በኃላ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የዴሞክራሲ ጥሰቱን ኣያይዞ ሲያብራራው፤ ለሉዓላዊነት መከበር ሊቆሙ የሚችሉትን ህብረ-ብሄር ድርጅቶች “ኣስተሳሰባቸው በህዝቡ ውሳኔ መሸነፍ እስካልተረጋገጠ ድረስም ትምክህተኞችና ጸረ-ሰላም ሓይሎች ናቸው በሚል ከሚቋቋመው የሽግግር መንግስት እንዲገለሉ ማድረጉ ተገቢ ኣልነበረም” በማለት የህዝቡ ይሁን የድርጅቶቹ ዴሞክራሲዊና ፖለቲካዊ መብቶች በመርገጥ  ሃገሪቱን ለማያባራ ቀውስ እንደዳረጉዋት በተጨባጭ ያስገነዝበናል። ሰፊው ህዝብን የሚያገል ተግባራት ሁሉ ዞሮዞሮ ወደ ቀውስ ማምራቱ ኣይቀርም። ሃገር የጋራ እንደሆነ ሁሉ እነዚህ መብቶችም የሁሉም ናቸውና ይህን ሃቅ ማወላገዱ ሰላምን ማደፍረስ ብሎም ኣመፅን መጋበዝ መሆኑ በሁሉም ዘንድ እንደታወቅ የግድ ይላል።
ብዙም ሳይቆይ ቻርተሩ “ሕገ-መንግስት” ወደ ተባለው ሰነድ ተቀይሮ፤ በዚህ ሰነድ ከለላ ህዝቡን ያገለለ ግን ደግሞ በህዝቡ ስም በኣውዳሚነቱ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ሴራ ተፈፅመዋል። ከባሕር- በር ማጣት ጀምሮ የሃገሪቱን ኣንጡራ ሃብቶች እስከ ማስዘረፍ የደረሰ ክሕደት መፈፀሙ ገብሩ በዝርዝር ያስረዳል። በዚህ ወቅት 144000 (ኣንድ መቶ ኣርባ ኣራት ሺ) ኢትዮጵያዊያን ከኤርትራ በግፍ ሲባረሩ ጥብቅና የቆሙት ለወገናቸው፣ ግፍ ለደረሰበት ኢትዮጵያዊ ሳይሆን ለግፈኛው ሻዕብያ መሆኑ ሲታይ (በሰነድም, EPRDF News Bulletin,…August 30, 1991. ላይ ሲያረጋግጡ) የብዙ ሰው ልብ ማድማታቸው ጠቅሸ ማለፍ እፈልጋለሁ።
ሓምሌ 1983 ሻዕብያ ኣስመራ ላይ በጠራው የኢኮኖሚ ኮንፈረንስ ኢትዮጵያን የመዝረፍ ዕቅዱ ግልፅ እንዳደረገው፣ ገብሩና ባልደረቦቹ (ስብሓት ነጋን ጨምሮ) በታዛቢነት ተገኝተው ተገንዝበዋል። በኢትዮጵያ ኣየር መንገድ፤ ባንኮች፤ ኣውራ ጎዳና ስራ፣  ወ.ዘ.ተ. ገብተው በራሳቸው ዕቅድ እንደሚሰሩ ተዝናንተው ግልፅ ኣድርገዋል። “የኤርትራን የእድገት ኣቅጣጫ ኣስመልክቶ የፖሊሲ መነሻ ሓሳብ የሚያቀርበው ምሁር፣ ኢትዮጵያ ገብተን ራሳችን መንገድ ቀይሰን መገንባት ኣለብን ሲል እብድ ይሁን ደንቆሮ ባይገባኝም ከሻዕብያ ኣመራር ያገኘውን መመሪያ መሰረት ኣድርጎ እንደተናገረ ግን ግልፅ ነበር” (ገብሩ፤ገፅ 193) ይለናል።
ይህ የዝርፍያ ዕቅድ እንዲሁ እቅድ ብቻ ሆኖ ኣልቀረም፣ በየዘርፉ ተግባራዊ ሆኖዋል። የኢትዮጵያ ከተማዎችን እየዳሰሰ ከኤርትራ ኬንያ የሚመላለሰው የኮንትሮባንድ ስምሪት፤ የውጭ ምንዛሪ ቅርምት፤ የቡና – ሰሊጥ- እንጨት ወዘተ ዝርፊያ፤ የጦር መሳርያና የኣልኮል መጠጥ ሸቀጡ ደርቶ እንደነበረ ያደባባይ ሚስጥር ነው። ሰውም ተዘርፈዋል / ታፍኖ ተወስደዋል። ለዚህ ማፍያዊ ስምሪት መሳካት መለስ ዜናዊ ተባባሪ ብቻ ሳይሆን ኣስፈፃሚም ነበረ። በህጉ መሰረት የሃገሪቱ መንግስት ምክር ቤት፤ ፓርላማ ወይም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሳያውቁት በድብብቆሽ 1.2 ቢልዮን ብር ከኢትዮጵያ ግምጃ ቤት ወጥቶ ለሻዕብያ እንዲሰጥ ማድረጉ (ገፅ 211) ኣንድ ኣብነት ነው።
ሻዕብያ የመለስና ስብሓት ተባባሪነት ብቻውን ኣላጠገበውም። ልቅ ምኞቱን ለማሳካት ወታደራዊ ሓይልን መጠቀም ፈልጎ የሰራዊት ምልመላና ስልጠና በገፍ ተያያዘው። የጦር ዝግጅቱ ያሳሰባቸው “ተወልደ፤ ኣውዓሎምና ገብሩ፣ ሻዕብያ ወደ ጦርነት እያመራ እንደነበር ቅንጣት ታኽል ጥርጣሪ ኣልነበረንም” ሲል ገብሩ፤ በኣንፃሩ ስብሓት ነጋ ግን መረጃው ሻዕብያ ወደ ጦርነት ማምራቱ ኣያመለክትም እያለ ሲቃወም እንደነበረ ያስረዳል። ቀጥሎም በባድመ ጦርነት ዋዜማ የህወሓት ማ/ኮሚቴና የኢህኣዴግ ስራ ኣ/ኮሚቴ በጋራ የኢትዮጵያ ጦር ኣስመራ ድረስ ዘልቆ የጠላትን ሓይል ማሽመድመድ ኣለበት ብሎ ሲወስን፣ (ገፅ 286) መለስ መቃወሙ ብቻ ሳይሆን በጠነጠነው ሴራ የብዙሃኑ ውሳኔ ግቡ ሳይመታ ከከባድ ኪሳራ ጋር ተኮላሽቶ እንዲቀር ኣድርገዋል። በፆሮና ግንባር ብቻው የነበረው ከባድ ኪሳራ ሲታይ መለስና ግብረ-ኣበሮቹ ለታጋዩ ወገን የነበራቸውን ደንታ ቢስነት በግልፅ ያረጋግጣል።
ገብሩ እንዳስጨበጠን፤ ኢሳያስ ኣፈወርቂ ጦሩን ሲደልብ፤ መለስ ዜናዊ ጦሩን ሲበትንና የተረፈውን ሲያኮላሽ፤ ስብሓት ነጋ ደግሞ የሁለቱን ሴራ ሲሸፋፍን በማህሉ ሃገርና ህዝብ ሲታመሱና ሲማቅቁ ማየቱ እጅግ ኣሳዛኝ ነበር። ዋናው ቁምነገሩ ግን ማሳዘኑ ኣይደለም። ከዚሁ ኣልፎ ለምን እንዲህ ሊሆን እንደቻለ መጠየቁ ኣግባብነት ያለው ዜግነታዊ ግዴታ መሆኑ ነው። ለዚህም ነው በግለ ሰዎች እጅ ላይ የወደቀች ሃገር እጣ ፈንታዋ ይኸው ኣሳዛኝ ተርእዮ የሚሆነው የምንለው። ባጠቃላይ እንደዚህ ዓይነቱ ግለ ሰዎች የሚቆጣጠሩት ስርዓት – የፈለገው ያህል ይመፃደቁ- በኣብዝሃው ስርዓት እስካልተተካ ድረስ ኣፈናው፣ ሰቆቃውና ውርደቱ ማቆምያ ኣይኖረውም።
መለስ በሓሳብ የተቃወሙትን የድርጅቱ ኣባላት ለመምታት ሲል 160 ዓመታት ወደ ኃላ ተጉዞ “ቦናፓርቲዝም” የሚባለው ፅንሰ ሓሳብ የመዘዘበትን መሰሪ ቅጥፈት ስንመለከት ደግሞ፣ ሃገሪቱና ህዝቡ ምን ያህል የኣንድ ግለ ሰብ መጫወቻ እንደነበሩ ያስረዳናል። ቦናፓርቲዝም ምን ማለት እንደሆነ ገብሩ (ገፅ 354-5) በግልፅ ኣስፍሮታል። እንዲያው በጥቅሉ ቦናፓርቲዝም የኣምባገነንነት ኣንዱ ገፅታ ሆኖ በተለይ የኣንድ ኣወናባጅ ሰው ፈላጭ ቆራጭነትን ያመለክታል። ሆኖም መለስ ይህ የራሱን ባህርያት ውስጥውስጡን ለተቃዋሚዎቹ በመለጠፍ ቀድሞ በህቡእ ከመታቸው በኃላ እራሱ  ምንደኛ ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ ኣረፈው። ይህን ተከትሎ የመጣው ኣሳዛኝና ኣሳፋሪ ድርጊቶቹም ገብሩ በማስረጃ ደግፎ ኣቅርቦልናል። ከብዙ በጥቂቱ፣
  • ለሃገር ሉዓላዊነት የቆሙትን “ኣፈንጋጮች” ብሎ በመሰየም በግሉ ውሳኔ ከስራቸው ማባረሩ (ገፅ 399)
  • በህዝብ ድምፅ ለብሄራዊ ምክር ቤት የተመረጡትን በግላዊ ጥላቻና ማን ኣህሎብኝነት የህዝቡን ውሳኔ ረግጦ ማገዱ (ገፅ 400)
  • “ኢንተርሃምዌ” በሚል የታወቀው የዘር ግጭት ቅስቀሳ ኢህኣዴግ እንዲጠቀምበት ውሳኔ ማስተላለፉ (ገፅ 434-5)
  • የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን “ሕገ-መንግስት መናድ” በሚል ክስ እስር ቤት እንዲወረወሩ ማድረጉ (ገፅ 442-3)
  • የሲቪል ማሕበረ ሰብ እንቅስቃሴ እንዳይኖር ኣፋኝ ሕግ ኣስወጥቶ በስራ ላይ ማዋሉ (ገፅ 444)
  • ሓሳብን በነፃነት መግለፅ እንዳይዳብር ነፃ ፕሬሱን ጨምድዶ እጁ ውስጥ ማስገባቱና ጋዜጠኞችን ኣስሮ ማሰቃየቱ (ገፅ 445)
  • በፀረ-ሽብር ሽፋን ኣፋኝ ኣዋጅ ዘርግቶ ተቃዋሚዎችን በሰበብ ኣስባቡ መፍጀት (ገፅ 447-8) ሊጠቀሱ የሚችሉ የፀረ-ዴሞክራሲ ዘመቻው ኣብነቶች ናቸው።
እነዚህና ሌሎች ያልተጠቀሱ ፀረ-ዴሞክራሲና ፀረ-ሉዓላዊነት ድርጊቶቹ መለስን ተራ ኣምባገነን ሳይሆን ኣወናባጅ ኣምባገነን ያደርጉታል። የማወናበድ መሰሪነቱ ኣልታይ ያላቸው የዋሆች፣ የጥቅም ጉዳይም ተጨምሮበት፣ መታለላቸው ኣልቀረም። ለዚህም ነው ተከታዮቹ መለስን እንደ ብልጣብልጥ ሳይሆን እንደ ኣዋቂ የሚዘምሩለት። የገብሩ መፅሓፍ የመለስን ኣስመሳይ ገፅታ ፈጦ በግልፅ እንዲታይ ስለ ኣደረገ ተከታዮቹ ባሁኑ ጊዜ በመዝሙራቸው እያፈሩ ይገኛሉ። በኣድርባይነቱ የሚቀጥሉ ካሉም የባሰውኑ መዋረድ ኣይቀርላቸውም። ያም ሆኖ የመለስን ኣወናባጅ ባህርያት ሲያጋልጡና ሲቃወሙ የነበሩት የፖለቲካና የፕሬሱ ኣባላት እንደዚሁም የድርጅቱ ኣባላት (እነ ሓየሎምን ጨምሮ) የጥቃቱ ዒላማዎች ሆኖው እንዳለፉ መዘንጋት የሌለበት ሃቅ መሆኑ ላስታውስ እወዳለሁ። ለዚህም ነው በኢትዮጵያችን ዴሞክራሲ የተዳፈነው፤ ኣሁንም ተዳፍኖ የሚገኘው።
ኣቶ ገብሩ በመፅሓፉ በጥልቀት የመረመረው የሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ መረገጥ ኢትዮጵያን ምንኛ ኣዘቅት ውስጥ እንደከተታት ለመገንዘብ – የየዋሆቹና የኣድርባዮቹ መወድስ ወደ ጎን ትተን – ተገቢው (ለጂቲመት) የባሕር በር ማጣትና ያስከተለው ከባድ እዳ እና በተጨባጭ በየዓረብ ሃገር ኤምባሲ በራፍ የሚኮለኮለው ህዝብ ቁጥር ወይም በየባሕሩ የሚሰምጠውና በየምድረበዳው ቀልጦ የሚቀረው የወጣቱ ብዛት ማስተዋል ብቻውን በቂ በሆነ ነበር። ጥናታዊ መረጃ ካስፈለገም የተባበሩት መንግስታት ዕድገት ፕሮግራም (ዩ.ኤን.ዲ.ፒ. 2013) ብንመለከት ኢትዮጵያ በሰብኣዊ ዕድገት ኣመልካች ከ 187 ሃገሮች በ 173 ኛው ደረጃ ኣዘቅዝቃ ትገኛለች። ይህ ደግሞ የመናጢ ሃገሮች ተርታ ነው። 41% ህዝቧ ከድህነት ወለል በታች የሚኖርባት ሃገር ዕድገት ኣለ ብሎ ማውራት የዕድገት ትርጉም መሳት ብቻ ሳይሆን የህዝቡን ኣሰቃቂ ሁኔታ ረስቶ በግለሰብ ኣምልኮ መጠመድ ነው። ኣድርባይነት ! ያውም ክላሲካል ኣድርባይነት ይሉታል።
ለዚህ ሁሉ ፍዳ ምክንያቱ ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲን ጨፍልቆ ኣምባገነንነትን ያነገሰው የመለስና ግብረ-ኣበሮቹ ሰንካላ ፖሊሲ መሆኑ መፅሓፉ በመረጃ ኣጅቦ ያስረዳል። የመፅሓፉ ዋናው ይዘት ይህ ሲመስል በመጨረሻም ከምንገኝበት ኣስከፊ ሁኔታ መውጣት የምንችልበትን ገንቢ ሓሳቦች ገብሩ በሚገባ ሰንዝረዋል።
የብዙ ሰው ዓይን ከፋች የሆነው፣ ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲን የሚያህሉ ትላልቅ ሃገራዊ ርእሰ ጉዳዮች በጥልቀት ተተንትነው መቅረባቸው ስለ ሃገሩ ሉዓላዊነትና ስለ ዴሞክራሲ ለሚጨነቅ ሁሉ ገብሩ ትልቅ ስጦታ ኣበርክተዋል። መፅሓፉ በዋናነት ለትውልድ የሚተርፍ ነው። ሆኖም፣ ማንም መፅሓፍ ፍፁም ኣይሆንምና ኣልፎ ኣልፎ ግድፈቶች መስለው የታዩኝን ኣንድ-ሁለት ነጥቦች ማንሳት እወዳለሁ።
1ኛ/ ቃለ-ምልልስ ኣለመጠቀም፣
ውስብስብ ታሪክ ያዘለና ፖለቲካዊ ይዘት ያለው መፅሓፍ በበርካታ ዋቢ መፃሕፍትና ጥቂት ሰነዶች ቢሸኝም ቅሉ፣ በዛ ረጅም ውጣ ውረድ ውስጥ በቀጥታ ተሳታፊ የነበሩትን (ሃገር ቤትም ባእድ ሃገርም የሚገኙትን) ነባር ኣባላት በማነጋገር ለቀረበው ይዘትና ትንታኔ ቃላቸውን ቢያክሉበት፣ ሚዛናዊነቱን በይበልጥ ከማጉላቱ በላይ ግድፈቶችንም ይሞላ ነበር እላለሁ። ይህ ግድፈት የፈጠረው ክፍተት የራሴ ገጠመኝን በማውሳት በሁለት/ሶስት ኣብነቶች ላስረዳ፣
ለምሳሌ፣ በገፅ 71 “ ከኢዴሕ ጋር የተካረሩ ውግያዎችን በምናካሂድበት በ1969 ዓ/ም በጋ ላይ ኣረጋዊ በርሄ ሽሬ እንዳስላሴ ገብቶ ከደርግ ባለስልጣናት ጋር እንደተነጋገረ … ተኩሉ ሃዋዝ (ኣሁን በህይወት የሌለ) ነገረኝ …እስካሁን ከኣረጋዊ የቀረበ ይፋዊ መግለጫ የለም” ይላል። ገብሩ ከኣረጋዊ ጋር በዚህና በሌላ ትላልቅ ጉዳዮች ላይ ቃለ-ምልልስ ቢያድርግ ኖሮ እውነታውን በቀላሉ ሊያገኘው ይችል ነበር። ይሁንና ላነሳው ጥያቄ መልሱ ‘ኣዎን ተነጋግሬ ነበር’ ነው።
ሁኔታውን ማወቅ ለፈለገ ባጭሩ እንዲህ ነበር፣ በኢድሕ ግስጋሴ ስጋት ያደረበት፣  ሽሬ የመሸገው የደርግ ጦር ኣዛዥ እንገናኝ በሚል ያገሩ ሽማግሌ ላከብን። ምዕራብ ግንባር የነበርነው ኣመራር (ስብሓት ነጋን ጨምሮ) በጉዳዩ መከርን። ግንኙነቱ ትጥቅ ያስገኝልናል ከሚል መላምት እኔ እንዳገኘው ተወሰነ፤ ከተማው ጥግ ተገናኘን። ባጭሩ እሱ በተሎ ትጥቅ ሊያቀርብልን እንደማይቻለው፣ እኔም የሁለታችን ስምሪት ማቀናጀት እንደማይቻል ሓሳብ ተለዋውጠን በዚሁ ተለያየን፣ ግንኙነቱም እዛው ኣበቃ። ለገብሩ “በወቅቱ የማይታሰበው ውይይት” ለኛ ግን ታሳቢ ነበር።
በጭንቀት መኖር የተገደደው ደርግ ከዛ በኃላም ሊገናኘን ሞክሮ ኣልተሳካለትም። ዝርዝሩ የፈለገ ጠይቆ መረዳት መብቱ ነው።
2ኛ/ ቁምነገሩን የሚያስት የቃላት ኣጠቃቀም፡
እዚህ ላይ ተራ ቃላት የሚመስሉ 2 ኣምሮች (ኮንሰፕትስ)፣  ግርግር እና ማፈግፈግ (በሞራላዊ ወይም በዲፕሎማሲያዊ እሳቤ ተጠቅሞ ሊሆን ይችላል) ፣ ኣለቦታቸው ገብተው  እውነታውን እንዴት እንደቀየሩት ኣሳያለሁ።
ሀ/ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ኣባል የነበረው ታጋይ ተኽሉ ሃዋዝ “… በቁጥጥር ስር ከዋለ በኃላ በእስር ቤት በተፈጠረ ግርግር ሕይወቱ ኣልፏል” ይላል (ገጽ 151)። በግርግር ሕይወቱ ኣልፏል ሲል እንደ ኣጋጣሚ፣ በትርምስ፣ ሳይታሰብ ሞተ ለማለት ይመስላል። ሃቁ ግን ሆን ተብሎ ነው የተገደለው። የተለየ ኣቛም ስለ ያዘ ተገደለ ማለቱ ይበቃ ነበር፣ ያልታሰበበት ከማስመሰል።
እንደገና የማእከላይ ኮሚቴ ተወካይ የነበረው ሸዊት ዳኘውም በዚሁ መልክ “… እስር ተበይኖበት እዛው በተነሳ ግርግር የድርጅቱ ሰለባ ሆነዋል” ይላል (ገጽ 90)። ሸዊት የግርግር ሰለባ ኣልነበረም፣ ሃቁ የመለስ ጥቃት ሰለባ እንጂ።
ለ/ በሶስት ቦታ (ገጽ 108፣ 113 እና 114) መለስ ዜናዊ ከጦርነት ማፈግፈጉና ሂስ እንደደረሰበት ይተርካል። ማፈግፈግ በወታደራዊ ስምሪት፣ ተመክሮበት የሚፈፀም ስልታዊ ንቅናቄ ነው፣ ሂስም ቅጣትም ኣያስከትልም። ከጦርነት ቀጠና መሸሽ ግን ሂስም ቅጣትም ያስከትላል። ተቀጥቷልም። በመለስ ላይ ኣመራሩ የበየነው ቅጣት ኣነሰ ተብሎ ያኔ ለተከሰተው ቀውስ (ሕንፍሽፍሽ) ኣንዱ ምክንያት እንደነበረም ማከሉ ሃቁን ያጎላዋል። ስለዚህታሪኩ እንዳይዛባ ኣለቦታው የገባው ኣፈገፈገ ፣ የሚለው ኣምር ሸሸ ወይም ሸሽቶ በሚለው ቃል መተካት ይኖርበታል።
3ኛ / በድርቅ ዙርያ ትልቅ ግድፈት
የ1977 ዓ/ም ድርቅ በህዝቦቻችን ላይ ያደረሰው ኣሰቃቂ እልቂት ፣ የሻዕብያ ኢ-ሰብኣዊነት ተጨምሮበት ምን ያህል ፈታኝ እንደነበረና የተደረጉ “ጥረቶች” በሰፊው ተብራርተዋል። ሆኖም እዚህ ላይ ሁለት የሚከነክኑ ዓበይት ጉዳዮች ተዘለዋል።
ኣንደኛው/ በዛ ቀውጢ ወቅት ማሌሊት ለተባለው ጤዛ ድርጅት ምስረታ ተብሎ ሁሉም የህወሓት ካድሬዎች ከነኣመራሩ ኣንድ ወር ሙሉ በድግስ ሲንንበሸበሽና ስንዘፍን መክረማችን፣ ኣፄ ሃ/ስላሴንና ደርግን በተመሳሳይ ኣስነዋሪ ድርጊት እንዳላወገዝን ሁሉ !!!
ሁለተኛ\ እና ዋናው ያኔ በድርቁ ምክንያት ከተሰበሰበው 100 (ኣንድ መቶ) ሚልዮን ብር 50% ማሌሊትን ማጠናከርያ፣ 45% ህወሓትን መደጎምያ፣ 5% ብቻ በድርቅ ለሚጠቃው ህዝብ በማእከላይ ኮሚቴው ስብሰባ መመደቡና ድርጊቱ የግፍ ግፍ መሆኑ ኣልተጠቀሱም። ይህ የበጀት ምደባ በኣብዝሃው ማ\ኮሚቴው ስብሰባ ጸድቆ፣  ቃለ ጉባኤውም በጽሑፍ ሰፍሮ፣ በቴፕ ተቀድቶ በህወሓት ሰነዶች ማእከል ይገኛል። ከህወሓት ፋይሎች ኣልፎም የዓለምኣቀፍ የረድኤት ማሕበራት፣ እንደነ ቢቢሲ የሚድያ ተቋማትን ኣሁንም እያተራመሰ ይገኛል። በግለሰብ ደረጃም ታዋቂው የቢቢሲ ጋዜጠኛ ማርቲን ፕላውት፣  ዘፋኙ ቦብ ጌልዶፍ፣ ኢኮኖሚስቱ ፕሮፌሰር ደስታ ኣሳየኸኝ፣ ወዘተ ኣሁንም ይተቹበታል። “ኣህያውን ፈርተው ዳውላውን” እንዲሉ ገብሩ በጋራ ህዝባችን ላይ የደረሰው ጭካኔን ኣጉልቶ የሚያሳየው ትልቁ ነጥብ (ባእዳን ኣሁንም የሚነታረኩበት) ትቶ ስለተከናወኑ “መልካም” ነገሮች ብቻ መተረኩ ጭራሽ ኣልገባኝም።
ይህ ነውረኛ የበጀት ምደባ ኣስመልክቶ ኣምባሳደር-ነበር ኣውዓሎም ወልዱ ለኣዲስ ኣድማስ ጋዜጣ 27 ጥቅምት 2003 ዓ\ም ገጽ 21 ላይ ባሰፈረው መረጃ፣ “ 35% ለህዝቡ፣ 65% ለድርጅቱ ተከፋፍለዋል” ያለውን የተሻለ ጥቆማ ቢሆንም በቃለ ጉባኤው ከሰፈረው ሃቅ ጋር ግን ኣይጣጣምም። ስለዚህ ይህ ጉዳይ በድርቅ የተጠበሱት ሚልዮኖችን የሚመለከት፣ ላንዳንዱም መራር ትዝታ ስለሆነ ተስተካክሎ ይፋዊ መግለጫ እንዲሰጥበት ከወዲሁ ኣቶ ገብሩን ኣሳስባለሁ። ዋናው ቁምነገሩ ያለፈውን ጥፋት በግልፅ በማየት ይህ ዓይነት በደል ለወደፊቱ እንዳይደገም ለማድረግ ነው።
4ኛ/ ወደ ዝርዝር ሳልገባ፣ ከወደ ኃላ የተወራለት ወታደራዊ መመርያ (“ዶክትሪን”) በምንም መልኩ እንዳልታየ፣ በከተማ የተነደፈው የመጀመርያው የድርጅቱ ፕሮግራም እንደነበረና ቅጂው ኣሁንም እንደሚገኝ፣ ስለ የኢህኣፓ ምርኮኞች ኣያያዝ የቆየው የህወሓት ምርኮኛ ኣያያዝ ደንብ እንዳልተከተለ፣ ከግድፈቶች ተርታ ሊጨመሩ የሚችሉ ኣብነቶች ናቸው።
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ ግድፈቶች ስጠቁም ዋናውን ርእሰ ጉዳይ፣  ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲን ኣስመልክቶ ለቀረበው ሰፊና ጥልቅ ጥናታዊ ዘገባ፣ ላይ ምንም ዓይነት ኣሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራሉ ከሚል እንዳልሆነ ላረጋግጥ እወዳለሁ። እንዳውም ለዚህ ትልቅ ሃገራዊ ጉዳይ፣ ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ፣ ተብሎ ለተደረሰው መጽሃፍ ከሚቀርቡ ኣሉታዊ ትችቶች በተመለከተ ኣንድ ሁለት ነጥቦች ላክል።
የመጽሓፉ ርእስ ብሎም ይዘት ከጅምሩ እስከ ማብቂያው በሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ ያጠነጠነ ሆኖ እያለ ኣንዳንድ ”ተቺዎች”፣ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ እንዲሉ፣ በሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ ላይ ኣንድም ቃል ሳይተነፍሱ በደራሲው ስብእና ላይ የባጡን የቆጡን ሲደረድሩ ይታያሉ።  ሃተታቸው ተጠቃሎ ሲታይ፣ ለምን ተሳስቸ ነበር ትላለህ ? ለምን ድርጅታችን ሲሳሳት ነበር፣ ኣሁንም እየሳሳተ ነው ትላለህ ? መሪዎቻችንን ለምን ታጋልጣለህ ? የሚሉ ናቸው። 1ኛ ነገር የማይሳሳት ድንጋይ ብቻ ነው፣ 2ኛ/ ስሕተትን ማየትና ሌላው እንዲማርበት ማድረግ ብልህነት ነው፣ 3ኛ/ ስሕተቱንና ችግሩን ተገንዝቦ እርማት የሚሰነዝር ሰው ኣርቆ ኣሳቢ ነውና ለነዛ ዓይነቱ “ተቺዎች” ዝርዝር መልስ ሳልሰጥ ባጭሩ ግን ለድርጅትና ለመሪዎቹ ጥብቅና ከመቆም ይልቅ ለሃገርና ለህዝብ ማስቀደም ይሻላል እላለሁ።
ጭራሽ የሚገርመው ደግሞ ሳያነቡ የሚተቹ “መሪዎች” መከሰታቸው ነው። ከነዚህ ኣንዱ –  ጠንቋይ ኣይሉት ነብይ  – ስብሃት ነጋ ነው። ለዚህ ሰውም የምለው ነገር ካለ “የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ኣላስደፈርኩም፣ ዴሞክራሲን ኣልረገጥኩም” ብለህ የኣንዲት ገፅ ፅሑፍ ኣቅርብ ብቻ ነው።
በቁምነገር መታየት ያለበት ሌላው ነገር፣ ገብሩ በመፍትሄነት ከሰነዘራቸው ዓበይት ነጥቦች ኣንዱ “ኢትዮጵያዊነትና የብሄረሰብ መብቶች ኣይነጣጠሉም” በማለቱ የሚወርዱትን የተቃውሞ ትችቶችን ይመለከታል። እነዚሀ ተቺዎች ጭራሽ የብሄረሰብ መብት ብሎ መነሳት የለበትም፣ የግለ ሰብ መብት መከበር ብቻ በቂ ነው። የብሄረሰብ መብት  ማስተናገድ ኢትዮጵያዊነትን ያዳክማል ወይም ይበታትናል ባዮች ናቸው። ይህ ዓይነቱ ሙግት በሌላ ጊዜም ተደጋግሞ ይሰማል። ፖለቲከኞችም ለተለያየ ዓላማ ይጠቀሙበታል። ሆኖም ይህ ኣመለካከት ማህበረሰባዊ ዕድገትን፣ ታሪክንና በመሬት ላይ ያለው ሃቅን ካለማንፀባረቁ ባሻገር የባሰ ብተና ወይም ቀጣይ ቀውስ እንጂ መፍትሄ ኣያመጣም። ለምን?
የግለሰብ መብት የግድ መረጋገጥ ያለበት ተፈጥሮኣዊም ፖለቲካዊም መብት መሆኑ ኣያጠያይቅም። ያለ የግለሰብ መብት መከበር፣ ዕድገት (ስልጣኔም ይሁን ፈጠራ) ኣይኖርምና። ይህ የግለሰብ መብት በኢትዮጵያችን ከተረገጠ ቆይተዋል። ዛሬ ግለሰቡ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሳይሆን የኢህኣዴግ ጢሰኛ (ሳብጀከት) ወደ መሆን ወርዷል። ለዚህም ነው ሁዋላ ቀርነት መለያችን ሆኖ ያለው።
የግለሰብ መብት ሲባል ግን ይዘትና መልክ የሰጠው ማን ነው ብሎ መጠየቅ የግድ ይላል። የግለሰብ መብት ይሁን እንደ ግለሰብ መኖር ራሱ ትርጉም የሚያገኘው በማሕበረሰቡ ከለላ ውስጥ ሆኖ ነው። ከማሕበረሰቡ ውጭ ግለሰቡ እንደ ሰው መኖርም ማደግም ኣይችልም። በእንሰሳት ማህል ያደገ ህፃን ከሰው የተወለደ ቢሆንም የእንሰሳቱ ጠባይ እንደሚይዝ ማስረጃዎች ኣልጠፉም። ስለዚህ ግለሰብና ማሕበረሰቡ ካስተሳሰብም ይሁን ከመብት ኣኳያ ነጣጥሎ ማየቱ ትክክል ኣይሆንም። የኢትዮጵያ ህዝብ ሲባል የተነጣጠለ ግለሰብ ድምር ማለት ሳይሆን ግለሰቡን ኢትዮጵያዊ ሰው ያደረገው ውስብስቡ ማሕበራዊው ስብስብ ጭምር ነው። የማሕበራዊው ስብስብ ኣንዱ ኣካል ብሄረሰብ (ወይም “ጎሳ”) ነው። ወረድ ካለም ቤተሰብ ይገኛል።
እንግዲህ ኣንድ ግለሰብ በሃገሩ መብቱን ሲነጠቅና መብቱን ለማስጠበቅ ዓቅም ሲያጣ፣ ተወደደም ተጠላ የሱን ዓይነት ችግር ከደረሰባቸውና ከሚመሳሰሉት ጋር ተሰባስቦ፣ ሓይል ፈጥሮ መብቱን ለማስከበር መፍጨርጨሩ ተፈጥሮኣዊም ዝንተሞገታዊም ሂደት ነው። ይህ ክስተት ድሮም ኣሁንም ኣለ። ኣድልዎ እስካለ ድረስ ወደ ፊትም ይኖራል። በዚህ ታሪካዊ ማዕቀብ (ኮንቴክስት) ስር ስንገነዘበው፣ የግለሰብና የማሕበረሰብ ትስስር እንደማይነጣጠሉ ሁሉ፣ ኢትዮጵያዊነትና የብሄረሰቦችዋ ህልውናም ይሁን መብት ተነጣጥሎ መታየት ኣይኖርበትም። ምናልባት የብሄረሰብ ወይም “ጎሳ” ህልውና ከነጭራሹ ካልካዱ ወይም ካልናቁት በስተቀር።
በማጠቃለል፣ ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ ዋናዎቹ የህዝብ እሴቶች እንደመሆናቸው መጠን እነዚህን እሴቶች ማእከል በማድረግ ባለፈው ሩብ ክፍለ-ዘመን ኢትዮጵያ ፊት የተደቀኑ ችግሮችና ህዝቡ ያጋጠሙት ፈተናዎች ኣቶ ገብሩ በጥልቀት ኣቅርበዋል። የሃገር ሉዓላዊነትና የህዝብ ዴሞክራሲ መብቶች የጋራ እሴቶች ሆኖው በጋራ ሓላፊነት ሊጠበቁ ሲገባ ነገር ግን ኣንድ ግለሰብና ግብረ-ኣበሮቹ እጅ ላይ ወድቀው የደረሰው ፍዳ ኣሁንም እንዳላበራ በስፋት ዘርዝረዋል። ከዚህም ባሻገር ከገባንበት የቀውስ ኣዙሪት መውጫውና ዘላቂ መፍትሄ የምንቀዳጅበት ብልሃቱ ኣመላክተዋል። ይኸውም ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲን የሚከበርበት ህዝቡ የሚቆጣጠረው የጋራ ስርዓት በቅድሚያ መመስረት ነው።
ኣቶ ገብሩ ለራሱ ሳይሳሳ፣ ሃገርንና ህዝብ በማስቀደም ለፍቶ ላቀረበልን ትልቅ መፅሓፍ ያን ያክል ምስጋና ይገባዋል።
ኣረጋዊ በርሄ     14.01.2015

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar