– የማኅበራዊ ሚዲያ ሠራዊት ሊገነባ ነው
ኢሕአዴግ ውስጣዊ የድርጅቱ ዴሞክራሲ ተጨናግፎ እንደቆየ አመነ፡፡ በኢትዮጵያ ሶሻል ሚዲያ በአክራሪውና ፅንፈኛው የተቃውሞ ኃይል ቁጥጥር ሥር መዋሉ፣ ጥላቻንና የእርስ በርስ ግጭትን ለመቀስቀስ ዋና መሣሪያ ሆኖ ማገልገሉን የገለጸው ኢሕአዴግ፣ በተደራጀ አኳኋን የራሱ የማኅበራዊ ሚዲያ ‹‹ሠራዊት›› በመገንባት ይህን እንቅስቃሴ ለመግታት መወሰኑን ገልጿል፡፡
ሰሞኑን ይፋ የሆነው የመስከረም-ጥቅምት 2009 የድርጅቱ የፖለቲካ ንድፈ ሐሳብ መጽሔት አዲስ ራዕይ ሦስት ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች ይዞ የወጣ ሲሆን፣ አንደኛው ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን የሚመለከት ነው፡፡
ጥልቅ ህዳሴ የማድረግ ተነሳሽነት ባለፉት 25 ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስቀጠል፣ ዕድገቱን የፈጠረው የሕዝቡ ፍላጎት ከፍ ማለትና ከድርጅቱ የውስጥ የመታደስ ጥያቄዎችን መሠረት ያደረገ እንደሆነ ጽሑፉ ያስረዳል፡፡
በገጽ 23፣ ‹‹በውስጣችን በተለይ ደግሞ በአመራር ደረጃ በመንግሥታዊ ሥልጣን የነበረው አተያይና አጠቃቀም ፈር እየለቀቀ መሄዱን ተከትሎ፣ ለሕዝብና ለአባላት ጥያቄ ትክክለኛ ምላሽ መስጠት ሳይችል ቀርቷል፤›› በማለትም ያብራራል፡፡ ‹‹የኪራይ ሰብሳቢነት የበላይነት ባለበት ሁኔታ ፀረ ዴሞክራሲያዊነት በእኛ ውስጥ ብቻ ሳይታጠር እስከ ኅብረተሰቡ ድረስ ዘልቆ ይስፋፋል፡፡ በዚህም የተነሳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየገነነ የመጣው ኪራይ ሰብሳቢነት ውስጣዊ ዴሞክራሲያችንን በመጫን መላወሻ ምህዳሩን ሲያጠበው ቆይቷል፤›› በማለትም ያክላል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት እንዳይገደብ ጥንቃቄ ለማድረግ አዲስ አቅጣጫ እንደያዘም አስታውቋል፡፡ በኢሕአዴግ ውስጥ ፀረ ዴሞክራሲያነትንና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመታገል የሚንቀሳቀሱ አባላትና አመራሮች ለተለያዩ ዓይነት ጥቃት ሲጋለጡ፣ አድርባይነትና ቸልተኝነትን ሲበረታታ መቆየቱ ለዚህ መነሻ እንደሆነ ጽሑፉ ያስረዳል፡፡
የዴሞክራሲ ተቋማትን ለመገንባትና ለማጠናከር ተቋማዊ አሠራርን ለማስፈንና አስፈላጊ የቁጥጥርና የኢንስፔክሽን ተቋማትን ለመገንባት፣ በተለይ አባላትና የድርጅቱ አመራር አካላት ከምንም ዓይነት የጥገኝነት መረብና ቡድን ነፃ ለማድረግ ማቀዱንም ኢሕአዴግ ገልጿል፡፡ የምርምርና የጥናት ተቋማትም ለማጠናከር አስቧል፡፡
‹‹የማኅበራዊ ሚዲያ ሠራዊት››
በተለይ ደግሞ የሲኤንኤንን ዘገባን ዋቢ በማድረግ 83 ሚሊዮን የሐሰት አካውንቶች በማኅበራዊ ሚዲያ መከፈታቸውን በመጥቀስ፣ ‹‹የመረጃ ምንጮችን ማንነት በእርግጠኝነት ለማወቅ የማይቻልበትና የተጠያቂነት አሠራር የሌለበት በመሆኑ የሐሰት መረጃዎች በሰፊው ይሠራጩበታል፤›› ይላል፡፡ የኢትዮጵያ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም የዚሁ የዓለም አቀፉ ገጽታ ነፀብራቅ መሆኑን የሚገልጸው ይኸው ጽሑፍ፣ በተለይ በኢትዮጵያ ፅንፈኛ የፖለቲካ አመለካከት ምንጭና መገለጫ መሆኑን የተለየ ባህሪ አላብሶታል ይላል፡፡
‹‹ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ተጠብቆ በሰላምና በዕድገት ጎዳና ልንዘልቅ የምንችለው እርስ በርስ ተከባብረንና ተቻችለን መኖር ስንችል ብቻ ነው፤›› የሚለው ጽሑፉ፣ ማኅበራዊ ሚዲያው ይህንን እሴት በማጎልበት ፈንታ የአክራሪና የፅንፈኛ ኃይሎች የጥላቻ ፖለቲካ መራመጃ መሣሪያ ሆኖ ይታያል፤›› በማለት ይደመድማል፡፡ በሕዝቦች መካከል ጥላቻንና ዘረኝነትን እንዲሁም የእርስ በርስ መተላለቅን ቅስቀሳ የሚደረግበትና በአገር ውስጥ ያለውም ሆነ ዳያስፖራው ፅንፈኛው ተቃዋሚ ኃይል፣ ሶሻል ሚዲያውን እንደ ዋነኛ የእኩይ ዓላማው ማስፈጸሚያ መሣሪያ አድርጎ መጠቀሙን ያብራራል፡፡
የአክራሪውንና የፀረ ሰላም ኃይሉ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ዒላማ ያደረጉት መንግሥትንና የኢሕአዴግ ገጽታ ለማጉደፍ፣ ሕዝባዊ ተቀባይነትና ዓመኔታን ለማሳጣት ወጣቱንና የተማረውን የኅብረተሰብ ክፍል በተራ አሉባልታና የውሸት ፕሮፖጋንዳ እንዲጠመድ ማድረጋቸውን ይተነትናል፡፡ በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፅንፈኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለይ ፌስቡክን ለአፍራሽ ተግባራቸው የሚያግዙ ኃይሎችን ለማሰባሰብ፣ መንግሥት ያስመዘገባቸው ስኬቶች ጥላሸት ለመቀባት ይጠቀሙበታል ይላል፡፡ የፓርቲና የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ስም በሐሰት ለመወንጀል፣ በግንባሩ አባል ፓርቲዎች መካከል ግጭት እንዳለ አስመስሎ ለመሳልና የአንድ ብሔር የበላይነትን እንደነገሠ አስመስለው ለማሳየት ማኅበራዊ ሚዲያውን በመጠቀም ላይ መሆናቸውን ይገልጻል፡፡ ሥርዓቱን የሚደግፉትን ለማስገለልና ተስፋ ለማስቆረጥ የግለሰቦችን ሰብዕና የሚነኩ መግለጫዎች በመለጠፍ ጭምር፣ የቻሉትን ርቀት መጓዛቸውንም ጽሑፉ ያትትል፡፡ በእምነት ሽፋን የሚካሄዱ የሃይማኖት አክራሪነትም ለፖለቲካ ትርፍ ማግኛ ለመጠቀም ከተገበሯቸው ሥልቶች ቀዳሚው ማኅበራዊ ሚዲያ መሆኑን ያስረዳል፡፡
ጽሑፉ እንደሚለው የእነዚህ ኃይሎች የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ድምር ውጤት ልማታዊው የሰው ኃይል በተራ አሉባልታና የጥላቻ ፖለቲካ ተጠምዶ፣ ዕውቀቱንና ጉልበቱን ለልማትና ለአገር ግንባታ እንዳይውል ማሰናከል ነው፡፡ ኢሕአዴግ እንደ ድርጅት የተሳሳቱ አስተሳሰቦችም ቢሆን ሐሳብን በነፃነት በመግለጽ የሚያምን እንደሆነ ኢሕአዴግ አስፍሯል፡፡ ‹‹ድርጅታችን ኢሕአዴግ የሚኖረው አማራጭ ሚዲያው የሚሰጠውን ዕድል አሟጦ መጠቀምና የሚፈጥራቸውን ሥጋቶች ደግሞ መቀነስ ብቻ ነው፤›› ይላል፡፡ ይህ የሚሆንበት ምክንያት ዴሞክራሲን ከማስፋት እንጂ፣ ከቴክኖሎጂ አንፃር የሶሻል ሚዲያውን አገልግሎት ማቋረጥ ወይም መግታት የማይቻል እንደሆነ ያስረዳል፡፡
‹‹ኢሕአዴግ አዲሱን ሚዲያ ከመጠቀም አንፃር የሚገባውን ሠርቷል ለማለት አያስደፍርም፤›› በማለትም በቅርብ ዓመታት ስትራቴጂ ተቀርፆለት እንቅስቃሴ መጀመሩን ያስረዳል፡፡ ከሰባት ሚሊዮን በላይ አባላት እንዳሉት የሚገልጸው ኢሕአዴግ እስካሁን በተደራጀና በጥራት ማኅበራዊ ሚዲያ አለመጠቀሙን መገምገሙን ገልጾ፣ በተለያዩ መስኮች የሚያደርገው የልማት ሠራዊት የመገንባት ልምድ በማኅበራዊ ሚዲያ እንደሚጠቀምበት ይገልጻል፡፡ አጠቃቀሙም ተጠያቂነት ባለበት፣ እውነተኛ መረጃና ሐቅ ላይ የተመሠረተና በተደራጀ አኳኋን እንደሚሆንም ያብራራል፡፡ በአመለካከትም በክህሎትም በድርጅቱ አባላት ላይ ነበሩ ያላቸው ችግሮች በመቅረፍ፣ ‹‹ሶሻል ሚዲያውን የሕዝብ ግንኙነት ሥራችን መሣሪያ አድርጎ መጠቀም ግድ ከሚለው ምዕራፍ ላይ ይገኛል፤›› ይላል፡፡
‹‹የአመለካከትና የክህሎት ችግር ቀርፈን ወደ ሥራው ካልገባን፣ ብዙውን ወጣት ኃይል ለፀረ ሰላም ኃይሎች ፍላጎት ማስፈጸሚያ አሳልፈን ልንሰጠው እንችላለን፤›› ሲልም ይገልጻል፡፡ በዚህም መሠረት በሐሳብ ትግሉ የኢሕአዴግ አስተሳሰብን የበላይነት ማረጋገጥ የሚችል የሶሻል ማዲያ ሠራዊት የመገንባትና በርካታ ተጠቃሚዎችን ማሰባሰብ መቻል አማራጭ እንደሌለው በመግለጽ፣ በዚህ ሒደት የፅንፈኛውን ተቃዋሚ አፍራሽ እንቅስቃሴ ማጋለጥና መመከትም ትኩረት እንደሚሰጠው ያብራራል፡፡ ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ዩቲዩብና ብሎጎች ትኩረት እንደሚሰጣቸውም ይጠቅሳል፡፡
መጽሔቱ በአሁኑ ወቅት የኢትዮ ቴሌኮም የቅርብ ጊዜ መረጃ ዋቢ በማድረግ በኢትዮጵያ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር በተጠናቀቀው 2008 ዓ.ም. ቁጥሩ ወደ 13.6 ሚሊዮን መድረሱን ይገልጻል፡፡ እንዲሁም ደግሞ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ፌስቡክ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በኅዳር 2003 ዓ.ም. ከነበረበት 250 ሺሕ የተጠቃሚ ቁጥር በአራት እጥፍ ዕድገት አሳይቶ በ2005 ዓ.ም. አንድ ሚሊዮን መድረሱን፣ እንዲሁም ደግሞ በወቅቱ በተደረገ ትንበያ መሠረት የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ቁጥር እስከ 2010 ዓ.ም. አራት ሚሊዮን ይደርሳል የሚል እንደነበር ያትታል፡፡ ሆኖም በሰኔ 2008 ዓ.ም. ድረስ ብቻ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ቁጥር 4.3 ሚሊዮን መድረሱንና በውጭ የሚኖሩ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውን ተጠቃሚዎች ጨምሮ፣ በአጠቃላይ ከአምስት ሚሊዮን በላይ እንደሚሆን ያብራራል፡፡
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar