mandag 11. desember 2017

አቶ ጌታቸው አሰፋ እና ዶ/ር ደብረጺዮን የሚመሩት የደህንነት ባለስልጣናት የተገኙበት ሚስጥራዊ ስብሰባ መካሄዱ ታወቀ

የጸጥታ ኃይሎች ዜና (ህዳር 30, 2010 ዓ.ም)
የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት መስሪያ ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋ እና አዲሱ የህወሓት ሊቀ መንበር በሆነው ዶ/ር ደብረፅዮን ሰብሳቢነት ከፍተኛ የደህንነት ባለስልጣናት የተገኙበት ስብሰባ ተደርጓል። በዚህ ስብሰባ ላይ በመከላከያ የወታደራዊ መረጃ ሰራተኞች በሚስጥር የተገኙበት እንደሆነ ታውቋል። ስብሰባው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስተር መስሪያ ቤት ጎን በሚገኘው የደህንነቱ መስሪያ ቤት እንደተደረገ ለማወቅ ተችሏል። በስብሰባው ላይ ከተለያዩ ክፍሎች የመጡ የደህንነት ባለስልጣናት በወቅታዊ የሃገሪቱ ሁኔታ ላይ የሚያተኩሩ ዘገባዎችን አቅርበዋል። እንዲሁም በደህንነቱ የተሰበሰቡ የህዝቡን ምልከታ ያሳያሉ የሚባሉ የህዝብ አስተያየቶች ቀርበዋል። በስብሰባው ላይ ህዝቡ ለስርአቱ ያለው ጥላቻ ከመቸውም ጊዜ በላይ እየጨመረ ይገኛል፤ በኦህዴድና ብአዴንም ህወሃትን የሚቃወሙ ድምጾች እየበረከቱ መምጣቻቸውን ተገልጿል። በመከላከያ ሰራዊቱ በከፍተኛ ቁጥር እየከዳ መምጣቱ እና በሰራዊቱ ውስጥ እየታየ የመጣውን ለአዛዦች አልታዘዝም ባይነት የሚያትት ሪፖርት በስብሰባው ላይ የተገኙ የወታደራዊ መረጃ ሰራተኞች አቅርበዋል። ተሰብሳቢዎቹ በሰራዊቱና በአዛዦቹ መካከል ከፍተኛ የሆነ ልዩነት እየተፈጠረ መምጣቱ ከፊለፊታችን ትልቅ አደጋ የደቀነ ጉዳይ ነው ሲሉ መግለጻቸው ተስተውሏል። በተለይ ሃገሪቱ ውስጥ ለሚፈጠሩ ችግሮች ህውሃትን ብቻ ተጠያቂ ከማድረግ ባሻገር የትግራይ ህዝብንም በጅምላ ተጠያቂ የማድረግ ሁኔታዎችም እየተስተዋሉ መምጣታቸውን በስብሰባው ላይ ተነስቷል። በጠላትነት ተፈርጀው ክትትል የሚደረግባቸው ይቅርና ተራው የህብረተሰብ ክፍል፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ በመከላከያ ውስጥ ያሉ ወታደሮች፣ በአመራርነት ከሚገኙ የብአዴን እና የኦህዴድ ሰዎች ሳይቀር ህወሓትን በጠላትነት ከመመልከታቸውም በላይ የትግራይ ብሄርን በሙሉ በጠላትነት እንደሚመለከቱ የሚያሳዩ መረጃዎች አሉን በማለት የደህንነቱ ባላስልጣናት አስረድተዋል። ባጠቃላይ አፋጣኝ እርምጃዎች ተወስደው ነገሮች ካልተስተካከሉ በስተቀር በአሁን ሰአት ህዝቡ በመንግስት ላይ ተስፋ እየቆረጠ መጥቷል በማለት አጽንኦት የሰጡ የደህንነት ባለስልጣናት እንደነበሩ መረጃዎችን ያስተላለፉልን ወኪሎቻችን ይገልጻሉ። በስብሰባው ላይ የተጨመቁ የህዝብ አስተያየቶች ናቸው ተብለው የተገለጹት በደህንነቱ የሰብአዊ መረጃ ኦፊሰሮች የተሰበሰበ ስለሆነ ታማኝነቱ ከፍ ያለ ነው በማለት አያይዘው የደህንነቱ ባለስልጣናት ገልጸዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተወሰኑ የደህንነት ባለስልጣናት ህዝቡ እንደዚህ እያማረረ ያለው በመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት ነው በማለት ለማስረዳት ሞክረዋል። ከትግራይ ክልል የመጡ የደህንነት ባለስልጣናት ከትግራይ ክልል ውጭ የሚኖሩት የትግራይ ህዝብ በስጋት እንደሚኖሩ እና በተለይ በአማራና በኦሮሚያ የሚኖሩ ከጠላት ብቻ ሳይሆን ከወዳጅ አባላት ሳይቀር ጥቃት እየተሰነዘረባቸው እንደሆነ አሁንም ምንም አይነት ዋስትና የለንም የሚል አቤቱታ እያቀረቡ እንደሆኑ ገልጸዋል። ይህ ደግሞ በህወሓት ላይ ከውጭም ከውስጥም ከፍተኛ ጫናዎች ውስጥ እንዲገባ አድርገውታል በማለት ተናግረዋል። በስብሰባው ላይ የተገኙ የደህንነት ባለስልጣናት ሰፊ ውይይቶችን ካደረጉ በኋላ ቀጣይ መወሰድ ስለሚገባቸው እርምጃዎች ተነጋግረዋል። በዚህም መሰረት በብአዴን እና ኦህዴድ ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ በመውሰድ ድርጅቶቹን ሙሉ በሙሉ የማጽዳት ስራዎች እንዲሰሩ በማለት ለዝርዝር አፈጻጸም የደህንነቱ መስሪያ ቤት አፋጣኝ እርምጃዎችን መውሰድ የሚችልበትን ሁኔታ አጥንቶ ተፈጻሚ እንዲያደርግ ወስነዋል። የጸረሰላም ሃይሎች ላይ በተጠናከረ መንገድ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በማድረግ በሃገር ውስጥ እየፈጠሩ ያሉትን ተጽኖ መቋቋምና ጨርሶውኑ ለማጥፋት የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አጽኖት ሰጥተዋል። የክልሎች የጸጥታ ተቋማት ሙሉ በሙሉ ለደህንነቱ መስሪያ ቤት ተጠሪ እንዲሆኑ በማድረግ የቁጥጥር ተግባራትን በመፈጸም የደህንነቱን ስራ የተቀላጠፈ መደረግ እንዳለበት ወስነዋል። ባጠቃላይ ደህንነቱ መወጣት የሚገባውን ሚና በመጫወት በአሁኑ ሰአት እየተፈጠሩ ያሉ የጸጥታ ችግሮችን ለመቋቋም የሚያስችለውን እርምጃዎች በመውሰድ ሀገሪቷን የማረጋጋት ስራዎችን ማከናወን እንዳለበት በስብሰባው ላይ የተገኘው የህወሃቱ ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጺዮን አሳስቧል። አያይዞም በመስዋእትነት ያገኘነውን ድል ለማንም አሳልፈን የምንሰጥበት እድል እንደሌለ ከመግለጹም በላይ ህወሃት ከምንጊዜውም በላይ ተጠናክሮ እንዲወጣ ሁሉም የበኩሉን እንዲያበረክት በሥብሰባው ላይ ለተገኙት የደህንነት ባለስልጣናትና የወታደራዊ መረጃ ሰራተኞች አስረድቷል። አቶ ጌታቸው አሰፋ በበኩሉ ከመከላከያ የመጡት የወታደራዊ መረጃ ሰራተኞች ላይ ትልቅ ሃላፊነት መውደቁን በመጠቆም ከደህንነቱ መስሪያ ቤት ጋር እየተናበቡ በሚወርድላቸው መመሪያ መሰረት ስራዎችን እንዲያከናውኑ አሳስቧል። አቶ ጌታቸው አሰፋ በስብሰባው ላይ ብአዴን እና ኦህዴድ የጸረ ሰላም ሃይሎች መጠቀሚያ እየሆኑ ስለሆነ በድርጅቶቹ ውስጥ የማጽዳት ስራዎችን በአስቸኳይ በማከናወን ከምንጊዜውም በላይ ጠንካራ ሆነን እንወጣለን በማለት ገልጿል። በስብሰባው ላይ የተገኙ ወኪሎቻችን እንደሚያስረዱት የወታደራዊ መረጃ ሰራተኞች በከፍተኛ ሚስጥር ስብሰባው ላይ እንዲካፈሉ መደረጉ በመከላከያ እና በደህንነቱ ዋና መስሪያ ቤት መካከል ያለመተማመን እንዳለ ይገልጻሉ። አቶ ጌታቸው አሰፋ ከመከላከያ ጋር ባለው ቅራኔ ምክንያት መከላከያ ውስጥ የራሱን መረብ ለመዘርጋት ሙከራዎችን እያደረገ እንደሆነ ወኪሎቻችን አያይዘው ይገልጻሉ

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar