የኢትዮጵያ ህዝብ እያካሄደ ያለውን የፍትህና የእኩልነት ጥያቄ ለማፈን ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠረው የራሱ ፓርላማ ሳይቀር እየተቃወመው በጉልበት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በህዝባችን ላይ የጫነው እብሪተኛው
የህወሃት አመራር በሞያሌ ከተማ ያሰማራው ነፍሰ ገዳይ የአጋዚ ጦር ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ መጋቢት 1 ቀን 2010 ዓም በሞያሌ ከተማ ሠላማዊ ዜጎች ላይ የሚዘገንን ጭፍጨፋ በመፈጸም በርካታ ሠለማዊ ዜጎችን ገድሏል።
ይህንን ጭፍጨፋ አስመልክቶ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም የተቋቋመው የኮማንድ ፖስት በትናንትናው ዕለት መጋቢት 2 ቀን 2010 አ.ም ባወጣው መግለጫ ጭፍጨፋውን ያካሄደው የሠራዊት ክፍል “የኦነግ ሠራዊት በከተማው ገብቷል” የሚል የተሳሳተ መረጃ ተቀብሎ እንደሆነና 9 ሠላማዊ ዜጎች ውድ ህይወታቸውን እንዳጡ፤ 12 የሚሆኑት ደግሞ ቆስለው ሆስፒታል እንደገቡ አረጋግጧል። ጥቃቱ ሲፈጸም የተመለከቱ የከተማው ነዋሪዎች በበኩላቸው የሟቾች ቁጥር 17 መድረሱንና ከፍተኛ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል የተወሰዱና ነፍሳቸው በሞትና በህይወት መካከል እያጣጣረች በመሰቃየት ላይ የሚገኙ ከሟቾች ቁጥር በእጥፍ እንደሚበልጡ እየተናገሩ ነው።
ህወሃት በአገዛዝ ዘመኑ እንዲህ አይነት የጅምላ ጭፍጨፋ በሠላማዊ ዜጎች ላይ ሲፈጽም የመጀመሪያው ጊዜ እንዳልሆነ ህዝባችን በሚገባ ያውቃል። መሪዎቹ ገና የበረሃ ትግል ላይ በነበሩበት ወቅት የፖለቲካ አላማቸውን የተቃወሙ ቁጥራቸው ከሠላሳ ሺህ በላይ የሆኑ የትግራይ ተወላጆችን አንድ በአንድ እየረሸኑ የመጡ መሆናቸውን ታሪክ በማይደበዝዘው ብዕሩ መዝግቦታል። በለስ ቀንቷቸው ሥልጣን ላይ ከወጡም ቦኋላ በመጀመሪያዎቹ የሥልጣን ዘመናቸው አማራውንና ኦሮሞውን ለማጨራረስ በበደኖ፤ በአርባ ጉጉ ፤ በወተር፤ በአረካ ፤ በአሰላ ሠራዊታቸውን በማዝመት በርካታ ሠላማዊ ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ አስገድለዋል። ከዚያም በኋላ በሃዋሳ፤ በጋምቤላ ፤ በኦጋዴን ፤ በአዲስ አበባ፤ በባህርዳር ፤ በጎንደር ፤እና በተለያዩ የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች ተመሳሳይ ጭፍጨፋ ሲፈጽሙ ኖረዋል። በነዚህ ሁሉ ጭፍጨፋዎች፤ የሃብት ዘረፋና አድሎአዊ አሠራር የተማረረው ህዝባችን በሠላማዊ መንገድ ተቃውሞውን በብዛት መግለጽ ከጀመረበት ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህም በተለያዩ የኦሮሚያና አማራ ከተሞች ከሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች በየአደባባዩ ተጨፍጭፈዋል። መንፈሳዊና ባህላዊ በዓላትን ለማክበር የወጡ ዜጎች ሳይቀሩ ከዓመት በፊት በቢሾፍቱ የኢሬቻ በዓል ላይ፤ ከሁለት ወራት በፊት ደግሞ የጥምቀት በዓል ለማክበር በወጣው የወልዲያና አካባቢው ነዋሪዎች ላይ ዘግናኝ የሆነ ተመሳሳይ ጭፍጨፋ ተፈጽሟል። አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ ካለፈው ሶስት ሳምንታት ወዲህም በአምቦ፤ በጉደር ፤ በወሊሶ ፤ በሱሉልታ፤ በለገጣፎ ፤ በጂማ ፤ በወልቂጤ ፤ በመቱ ፤ በነቀምቴ ፤ በጊምቢ ፤ በመንዲ ፤ በደምቢዶሎ፤ በምሥራቅ ሃረርጌ ወዘተ ቁጥራቸው በግልጽ ያልታወቀ በርካታ ንጹሃን ዜጎች በተመሳሳይ ጭካኔ ተገድለዋል። በብዙ ሺ የሚቆጠሩት ደግሞ ወደ እሥር ቤት ተግዘዋል።
ከትናንት በስቲያ በሞያሌ ከተማ ነዋሪዎች ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ በቅርብ ጊዜያት ከተፈጸሙት ተመሳሳይ ጭፍጨፋዎች ልዩ የሚያደርገው አገዛዙ የተለመደውን የጭካኔ እርምጃውን ለመውሰድ ምንም አይነት ምክንያት ሳይኖረውና በከተማው ውስጥም ሆነ በአካባቢው ምንም አይነት እንቅስቃሴ በለሌበት ሰዓትና ቀን ሰዎች በብዛት በሚኖርበት የከተማው ጎዳና ላይ በሚንቀሳቀሱትና በተኩሱ ተደናግጠው የንግድ መደብሮቻቸውን በዘጉት ዜጎች ላይ ቤቶቻቸውን በርግዶ በመግባት የተፈጸመ የሽብር እርማጃ መሆኑ ነው ። ለዚህም የተሰጠው ምክንያት “የኦነግ ታጣቂዎች ከተማ ውስጥ ገብተዋል” የሚል የተሳሳተ መረጃ ነው ተብሏል። የኦነግ ሠራዊት ከተማ ውስጥ ገብቶ እንኳ ቢሆን ምንም አይነት መሣሪያ ያልታጠቁ ዜጎች በጥርጣሬ በተገኙበት እንዲገደሉ የሚፈቅድ ህግም ሆነ አሠራር የለም። በዚህም የተነሳ ይመስላል ጭፍጨፋው እንዲካሄድ ሠራዊት አስታጥቀው በመላው አገሪቱ ያዘመቱት የህወሃት መሪዎችና የኮማንድ ፖስቱ ከህዝብ የሚቀሰቀስባቸውን ቁጣ ለማለዘብና ከአለም አቀፍ ማህበረሰብ በተለይም ከምዕራባዊያን ወዳጆቻቸው ሊሰነዘርባቸው የሚችለውን ውግዘት ለማስቆም ፈጥነው የሽብር ጥቃቱን ታዘው በፈጸሙት 5 የሠራዊቱ አባላት ላይ በማላከክ “ተጠያቂዎቹን ለህግ ለማቅረብ ምርመራ ጀምረናል” የሚል መግለጫ ያወጡት። ከእስከ ዛሬው ልምድ ህወሃት አልሞ ተኳሾቹን በአብዛኛው የአገራችን ማህበረሰብ ላይ በማዝመት ሲፈጽማቸው ለኖረው ጭፍጨፋ አንዳችም ጊዜ ተጠያቂ የሆነ ሰው ህግ ፊት አቅርቦ እንደማያውቅ ጠንቅቆ የሚያውቀው የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ምዕራባዊያን ወዳጆቹ በዚህ የኮማንድ ፖስት መግለጫ ሊደለሉ ይችላሉ ብሎ አይታሰብም።
ይልቁንም ከዚህ መግለጫ መማር የተቻለው ከበላይ አለቆቹ ትዕዛዝ በመቀበል በገዛ ወገኑ ላይ ጭፍጨፋና ሰቆቃ እያደረሰ ያለው ተራው የመከላኪያ ሠራዊት አባላትና የበታች መኮንኖች ለሚፈጽሙት ለያንዳንዱ ጭፍጨፋ ተጠያቂነት ሲመጣ ሃላፊነት ሊወስድላቸው የሚችል አንዳችም የህወሃት ወይም የኮማንድ ፖስት አመራር እንደሌለ ግልጽ መሆኑ ነው።
አርበኞች ግንቦት 7 በሞያሌ ንጹሃን ዜጎች ላይ የተወሰደውን ይህንን ጭፍጨፋ በጥብቅ እያወገዘ ለዚህ ተጠያቂዎቹ የሽብር ጥቃቱን ከፈጸሙ የሠራዊቱ አባላት በተጨማሪ ይህንን የሽብር እርምጃ በወገን ላይ እንዲወሰድ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ ሠራዊቱን በከተማው ያሰፈረው የኮማንድ ፖስትና ከኮማንድ ፖስቱ በስተጀርባ ያለው የህወሃት አመራር መሆናቸውን ያስታውቃል።
ለሃብት ዘረፋ ምንጭ ያደረጉትን የመንግሥት ሥልጣን ዕድሜ ለማራዘም ሲሉ በሠላማዊ ዜጎቻችን ላይ እንዲህ አይነት የጭፍጨፋ እርምጃ እያስወሰዱ ያሉት የኮማንድ ፖስቱና የህወሃት አመራሮችን ለህግ ለማቅረብም ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 ከሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሆኖ አስፈላጊውን ሁሉ ትግል ማካሄዱን በጽናት ይቀጥላል።
ህወሃት በሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ እንዲህ አይነት ጭፍጨፋ፤ እስርና እንግልት መቆሚያ እንደማይኖረው ያለፈው 27 ዓመታት ተሞክሯችን በቂ ትምህርት ሰጥቶናል። በመሆኑም ይህንን ጭፍጨፋ ለማስቆም የሚቻለው በሁሉም የአገራችን ክፍል የሚኖረው ህዝባችን በኦሮሚያና በአማራ አካባቢ እየተካሄደ ያለውን ህዝባዊ ተቃውሞ በመቀላቀል የህወሃትን አገዛዝ ፍጻሜ ለማምጣት በጋራ ስንንቀሳቀስ እና የህግ የበላይነት የሰፈነበት ሥርዓት በአገራችን ሲመሰረት ብቻ መሆኑን አርበኞች ግንቦት 7 መላውን ህዝባችንን ማስታወስ ይወዳል።
በመከላኪያ ሠራዊት፤ በፖሊስና የጸጥታ ጥበቃ ተቋማት ውስጥ ያላችሁ ወገኖች !
በአለቆቻችሁ ትዕዛዝ በማንኛውም ዜጋ ላይ ለምትፈጽሙት ግድያ ፤ እስርና ሰቆቃ በህግ የተጠያቂነት ጊዜ ሲመጣ “አለቆቼ አዘውኝ ነው” በማለት ከተጠያቂነት ነጻ መውጣት እንደማይቻል በዓለም አቀፍ ህግ ካለው ድንጋጌ በተጨማሪ በሞያሌ ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ ወንጀል በናንተ ላይ ለማላከክ አገዛዙ ከሰጠው መግለጫ ትምህርት ልትቀስሙ ይገባል። ስለዚህ ህዝብ አንቅሮ የተፋው ይህ የህወሃት አገዛዝ እናንተን እንደመሣሪያ ተጠቅሞ የሥልጣን ዕድሜውን ለማራዘም የሚያደርገውን ማንኛውንም ሙከራ ለማስፈጸም የሚሠጣችሁን ትዕዛዝ እንቀበልም በማለት ህዝባዊ ወገናዊነታችሁን እንድታሳዩና ከለውጥ ፈላጊው ማህበረሰባችሁ ጎን እንድትሰለፉ አርበኞች ግንቦት 7 ወገናዊ ጥሪውን ያቀርብላችኋል።
በህወሃት ነፍሰ ገዳዮች ጥይት ህይወታቸውን ላጡ ሰማዕታት ቤተሰቦች ፤ ወዳጅ ዘመዶች ሁሉ አርበኞች ግንቦት7 መጽናናቱን ይመኛል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !
አርበኞች ግንቦት 7
አርበኞች ግንቦት 7
መጋቢት 3/ 2010 ዓም
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar