31 March 2019
የአዲስ አበባ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ጥያቄ የማንሳትም ሆነ የመፍትሔ ሐሳብ የማቅረብ መብት አለው፡፡ በአዲስ አበባ ጉዳይ የሚደረግ ንግግርም ሆነ ውይይት፣ ክርክርም ሆነ ድርድር ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መሆን ይኖርበታል፡፡ ስለመላዋ ኢትዮጵያም ሆነ ስለአዲስ አበባ የሚነሱ ጥያቄዎችም ሕጋዊ፣ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ይዘት እንዲኖራቸው ሲደረግ የጽንፍ ግብግቦች ይወገዳሉ፡፡ ከዴሞክራሲ የጨዋታ ሕግ ያፈነገጡና የአንድ ወገን የበላይነትን ለመጫን የሚደረጉ መውረግረጎች የማያስፈልጉትን ያህል፣ በስሜታዊነት እየተነዱ ለፍጥጫ የሚዳርጉ ደመነፍሳዊ እንቅስቃሴዎችም ለማንም አይጠቅሙም፡፡ የአዲስ አበባም ሆነ የመላ አገሪቱ ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው በጉልበት ሳይሆን፣ በጨዋነትና በሠለጠነ መንገድ ብቻ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ‹አዲስ አበባ የማን ናት?› የሚለው አሰልቺ ጥያቄ ከኢትዮጵያውያን አዕምሮ ውስጥ መውጣት አለበት፡፡ ይህ የስግብግብነት መገለጫ የሆነ ጥያቄ ለአርቆ አሳቢዎቹና አስተዋዮቹ ኢትዮጵያውያን አይመጥናቸውም፡፡ አዲስ አበባ ከመላ ኢትዮጵያውያን አልፋ ልክ እንደ ኒውዮርክ፣ ጄኔቫና ብራሰልስ የዓለም ከተማ መሆኗ መታወቅ አለበት፡፡ የኋላቀሩ የጽንፈኝነት ሒሳብ ማወራረጃ መሆን የለባትም፡፡
ኢትዮጵያውያን በአዲስ አበባም ሆነ በመላ አገሪቱ የሚያሳስቧቸው በርካታ ችግሮች አሉባቸው፡፡ ከሰብዓዊና ከዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች ጀምሮ፣ እስከ መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ድረስ ከመጠን ያለፉ ችግሮች አሉ፡፡ ከድህነት ወለል በታች በሆነ ኑሮ በርካታ ሚሊዮኖች ይማቅቃሉ፡፡ የባሰባቸው ደግሞ በአደገኛ የጉዞ መስመሮች አገር ለቀው ይሰደዳሉ፡፡ እንደ ሰደድ እሳት በሚፋጅ የኑሮ ውድነት የሚጠበሱ ዜጎች ቁጥር አታካች ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ በተቃርኖ የተሞላው ፖለቲካ የአቅጣጫ መጠቆሚያ እንደሌላት መርከብ በከንቱ ይባዝናል፡፡ ኃላፊነት የጎደላቸው ግለሰቦችና ስብስቦች በእያንዳንዱ ጉዳይ ቅራኔ ሲፈበርኩ ውለው ያድራሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ቅደም ተከተልና ዋና ሥራችንን መለየት ካልቻልን፣ በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች የምንፈጥራቸው ችግሮች ተያይዘን እንድንጠፋ ያደርጉናል፡፡ በኢትዮጵያ የዛሬ ዓመት የተጀመረውን ለውጥ እያደናቀፉ ያሉት ፋይዳ ቢስ ተቃውሞዎችና ጥርጣሬዎች ናቸው፡፡ አንድ ላይ መቆም ሲቻል በተቃርኖ መለያየት መዘዙ የከፋ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ጉዳይ ሲነሳ ‹‹ልዩ ጥቅም›› የሚባለውን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ በመጥቀስ፣ ሁሉንም ነገር ለማጋበስ ማሰብ ዕብደት ነው፡፡ አዲስ አበባ በውስጧ አቅፋ የያዘቻቸው ነዋሪዎቿ (ከመላ አገሪቱ የተሰባሰቡ መሆናቸው ታሳቢ ሆኖ)፣ በዙሪያዋ ያሉ አርሶ አደሮች፣ ብዙ ነገሮችን የሚመጋገቡ ዙሪያዋን ያሉ ከተሞች፣ ወደፊት አዲስ አበባ መጥተው ለመኖር የሚያስቡ ዜጎች፣ ወዘተ. እንዳሉ መረሳት የለበትም፡፡ ስለዚህ የሁሉንም ወገኖች ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረገ ሕጋዊ፣ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ አሠራር እንዲሰፍን የሁሉም ድርሻ መሆን አለበት፡፡ ከዚህ ውጪ መተሳሰብን፣ ሰጥቶ መቀበልንና ሰብዓዊነትን እየገፉ በጉልበት እንሞካከር ማለትም ሆነ ቅራኔ መዝራት ለማንም የማይጠቅም ኋላቀርነት ነው፡፡ በየትም ዓለም እንደሚታወቀው ከተማ ይሰፋል፣ ያድጋል፣ ይዘምናል፡፡ ከገጠርና ገጠር ቀመስ ከሆኑ ከተሞች የሚመጡ ሰዎችን ይቀበላል፡፡ የግብርና ምርቶችን ከአካባቢው አርሶ አደሮች ሲወስድ፣ ለአርሶ አደሮች የኢንዱስትሪ ምርቶችን ያቀርባል፡፡ ሁለቱ በበርካታ ጉዳዮች እየተገናኙ ጥቅሞቻቸውን በፍትሐዊነት ያስከብራሉ፡፡ በዚህ ሒደት ደግሞ አንዱ ሌላውን እንዳይበድል ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡ በዚህ መንፈስ ተከባብሮና ተባብሮ መሥራት ሲቻል መቃረን ፋይዳ ቢስ ይሆናል፡፡
በአሁኑ ጊዜ እጅግ በጣም አሳሳቢ የሆነው ጉዳይ ለውጡን የሚመራው ቡድን ላይ ጥርጣሬና ተቃውሞ ማየሉ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ለውጡ ተደናቅፎ ወደ ኋላ መመለስ ከተጀመረ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማሰብ ይገባል፡፡ አሁን ዋነኛው ጉዳይ ዴሞክራሲ የሚፈልጋቸውን መሠረታዊ ነገሮች ማመቻቸትና ማበልፀግ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ንጣፍ የሆኑት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማክበር፣ የዴሞክራሲ መደላድሎችን ማመቻቸት፣ በሚለያዩ ጉዳዮች ላይ በጨዋነትና በሥርዓት መነጋገር፣ በሐሰተኛ መረጃዎች ላይ በመንጠልጠል ለፀብ አለመፍጠንና ንቃተ ህሊናን ማጎልበት ልዩ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህንን የዴሞክራሲ ጅምር በጥያቄዎችና በጫጫታዎች ጋጋታ እንዲቀጭ ዕድል ከመስጠት ይልቅ፣ ችግሮች ሲያጋጥሙ መፍትሔ ለመስጠት መትጋት ይሻላል፡፡ ከዚህ በፊት ያጋጠሙ መልካም ዕድሎች በተደጋጋሚ እንዴት እንዳመለጡ ይታወቃል፡፡ አሁንም ሌላ ዕድል ይኖራል በማለት ይኼንን ዕድል ማበላሸት የማይወጡት ችግር ውስጥ ይከታል፡፡ አዲስ አበባን የሁላችንም ናት ብሎ የበለጠ ማሳደግና ማስዋብ በታሪክ ያስከብራል፡፡
የአዲስ አበባ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ መገንዘብ ያለባቸው፣ ከጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍና ኪሳራ በመለስ ያለው የጋራ ጥቅም እንደሚበልጥ ነው፡፡ በተለይ የፌዴራል መንግሥት፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከወገንተኝነት የነፃ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ይህ ኃላፊነት ከወገንተኝነት ነፃ እንዲሆን የሚጠየቀው እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል የመሰለውን ካርድ እየመዘዘ ሲመጣ፣ የማይወጡበት ቅርቃር ውስጥ ስለሚከት ነው፡፡ በግል፣ በመንግሥት ወይም በፓርቲ የተለያዩ አቋሞችን እያንፀባረቁ ማደናገር አይገባም፡፡ ሕዝብም ይህንን ግልጽነት ይጠይቃል፡፡ በሌላ በኩል የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ የፖለቲካ አቀንቃኞች ኃላፊነት ሊሰማቸው ይገባል፡፡ ሕዝብን ለጋራ ዕድገት ከማሠለፍ ይልቅ ለማቃረን ነገር መቆስቆስ ውጤቱ ተያይዞ መጥፋት ነው፡፡ አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆኗን በመገንዘብ ለጋራ ጥቅም በአንድነት መሥራት እየተቻለ፣ መሰሪ ድርጊት ውስጥ መገኘት የታሪክና የትውልድ ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ ለነፃነት፣ ለፍትሕና ለእኩልነት ታግለናል እየተባለ አምባገነንነትን መልሶ የሚያቋቁም ድርጊት ውስጥ መገኘት ያሳፍራል፡፡ ከዚህ ዓይነቱ አሳፋሪና ከንቱ ድርጊት ውስጥ በፍጥነት መውጣት የግድ ይላል፡፡ አዲስ አበባን የጽንፈኝነት ሒሳብ ማወራረጃ ማድረግ ተገቢ አይደለምና!