ሰላም ለሁሉም ፍላጎታችን መሳካት መሠረት ነው፡፡ ያለ ሰላም ዕቅዶቻችንንም አገራዊ ራዕያችንንም ከግብ ለማድረስ አንችልም፡፡ ሰላም ማጣት የሚያስከፍለው ዋጋ እንደዘበት አይታይም፡፡ ሕይወትና ንብረትን በማሳጣት ብቻ አይወሰንም፡፡ ሰላም ያጣ ሕዝብና አገር ማንነቱንና ክብሩን ያጣል፡፡ የውርደት ማቅ የለበሰ፣ ለተመጽዋችነትና ለእንግልት የተዳረገ እንደሚሆን የእኛው የኋላ ታሪክ ምስክር ነው፡፡
ለሰላም ሳንካ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በመነጋገርና በመደማመጥ መፍትሔ ማግኘት ሲቻል በበሬ ወለደ ወፈ ሰማይ ወሬዎች ሳቢያ ኢትዮጵያ እየተፈተነች ነው፡፡ እንኳንና ለግጭት ለጭቅጭቅ በማያበቁ አጀንዳዎች አንዱ ሌላው ላይ ጦር እንዲያነሳ የሚደረግበት ነውረኛ ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደምናየው የግጭቶች ምንጭ ተብለው የሚጠቀሱ ጉዳዮች አንገታችንን ያስደፋሉ፡፡ እንደ ሕዝብ፣ እንደ አገር እንዲህ ያለውን ክፋትና ነውር ከየት ተማርነው የሚያሰኙ ጸያፍ ድርጊቶች በጓዳችን እያየን ነው፡፡ ነገን የማያስመኙ፣ ተስፋን የሚያሳጡ ክፋቶች የዕለት ዜና እወጃ ሆነዋል፡፡
ነገሩን ጠለቅ ብለን ስናየው አንዱ በሌላው ወገኑ ላይ እንዲነሳበት ጥቂት ክፉ ጠንሳሾች የሚያራግቡት ወሬ ለዚህች አገር አደጋ እየሆነ ነው፡፡ ‹‹ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው›› የሚለው የአበው አባባል እኛው ላይ የተተረተ እስኪመስል ድረስ በወሬ የሚነዳው፣ ማን አለ፣ ለምን አለ፣ እንዴት ተባለ፣ በምን ተፈልጎ ተባለ ወዘተ. የሚሉ መሠረታዊ ጥያቄዎችን በማነሳትና በመመርመር ምላሽ ከማግኘት ይልቅ ነሲበኞች ዋጋ ከፍለው ሌላውንም እያስከፈሉ ነው፡፡
መልካም አጋጣሚዎችን በአግባቡ ከመጠቀም ይልቅ እኔ ብቻ ከሚል እሳቤ ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› እንዳለችው እንስሳ በየቦታው በተቧድኖ የሚደረጉ ግርግሮች ሰላምን በማወክ ለውድቅት እያንደረዱን ነው፡፡ ጨዋነትን በመቃረን የራስ ፍላጎትን ለመጫንና ለማስተግበር ማሴር እየተበራከተ ነው፡፡ አንዱ ሌላውን ችሎና ተጋግዞ፣ ያለችውን ተቃምሶ ይኖር የነበረውን የኅብረተሰብ ክፍል፣ ያለፍላጎቱ በመጎትጎትና በማስገደድ ጭምር የሚፈጸም ጥቃት እየባሰበት ሲመጣ እያየንም እየሰማንም ነው፡፡ አንዳንዴም በጋራ መኖር ጥቅማችንን ይነካናል የሚሉና አሻግሮ ነገን የመመልከት አቅም ያነሳቸው ጥቂት ግለሰቦች በማንነት ስም የሚለኩሱት የጥፋት ክብሪት መልሶ ራሳቸውን እንደሚፈጃቸው አያውቁም፡፡ ወይም ደግሞ አውቀውም አጥፍቼ ልጥፋ ያሉ ይመስላሉ፡፡
በታሪኳ የተፈናቀሉትን የምታስጠልለው፣ የተሰደዱትን የምታስጠጋው ኢትዮጵያ የዓለም ቁንጮ ተፈናቃዎች ምንጭ ሆና መገኘቷ እንደ ሕዝብ ለእኛ ከውርደት በላይ የሕልውናችን ማክተም ምልክት እየቀረበ የመምጣቱ ፍንጭ እንዳይሆን ማሰብ ይኖርብናል፡፡
በግጭት ያተረፉ ይኖራሉ፡፡ የግጭት ነጋዴዎች ግን ለልጆቻችን ነገን ለሚያስናፍቁን እንቦቅቅላዎቻችን፣ ለወጣቶችና ጎምሶቻችን፣ ለቅርሶቻችንና ለመከበሪያ ማንነታችን ቦታ የሌላቸው በሰው ቁስል እንጨት የሚሰዱ፣ በሰው ሲቃ የሚንደላቀቁ የደም ከበርቴዎች እንደሆኑ ብንገነዘብ የሚያጣላን ችግር ምንኛ ኢምንት እንደሆነ በተረዳን ነበር፡፡
ተወደደም ተጠላ በለውጥ መንገድ ላይ በኩራት ለማራመድ የኢትዮጵያችን ሰላሟ መጠበቁ ግድ ነው፡፡ ጥያቄ አለኝ፣ ችግር ደርሶብኛል ተጎድቻለሁ የሚለው አካል ሁሉ ለሚያነሳው ጉዳይ ምላሽ መስጠት የሚጠበቅበት አካል ኃላፊነቱን በሐቅና በአግባቡ በመመለስ ከግርግርና ካለመተማመን የፀዳ ማኅበረሰብ በመፍጠር ችግሮችን የመፍታት አቅም ማዳበር አለበት፡፡ ለዚህ መተባበርና መነሳት የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንዳየነው የአገር ሽማግሌዎች የሃይማኖት አባቶች አባገዳዎች ያበረከቱዋቸው አስተዋጽኦ እንደ ምሳሌ የሚወሰድና ሽማግሌ አያሳጣን ብለን እስከማወደስ የደረስንባቸውን የመረጋጋት ሥራ ተሠርተዋል፡፡
ነገር ግን ካለው ችግር አንፃር አሁንም በየባህሉና በየሃይማኖቱ አንቱ የተባሉ ሽማግሌዎች ተግባር የተገኘው መረጋጋት በአግባቡ መጠቀም ካልቻልንና በሰበብ አስባቡ ለግጭትና ለልዩነት በር የሚከፍቱ አጀንዳዎችን ይዞ በመምጣት አንፃራዊን ሰላም መልሶ የሚበርዝ ከሆነ የሽምግልና ትርጉሙ አልገባንም ማለት ነው፡፡ ደግሞም እዚህም እዚያ ለሚከሰቱ ግጭቶች ሁሉ ሽማግሌዎችን እያፈላለጉ መዝለቅ አይቻልም፡፡ ዜጎች ራሳቸውን መግራት፣ እንዴት ተባብሮ መኖር እንደሚገባን በማሰብ ካልተራመድን አገርን በጋራ ለማራመድ ይቸግራል፡፡
ስለሰላም የሚያስተምር አባት እንዴት እናጣለን፡፡ የሰላምን አስፈላጊነት ለመረዳት ከእልቂታችን መማር አይጠበቅብንም፡፡ እንደሞኝ ከራሳችን ሳይሆን ከሌሎች ለመማር የሚያበቁ በርካታ እልቂቶችን በዚያችን አይተናል፡፡ እያየንም ነው፡፡ ስለዚም የሰላም አስተማሪዎች ሊበራከቱልን ይገባል፡፡ በልጆቻችን ዘንድ ስለፍቅርና አንድነት፣ መልካምነትና መተሳሰብን በማስረጽ የነገ ሕይወታቸው እንዲያበራ በማድረግ በኩል ወላጆች፣ ጎረቤትና ሰፈር አድባሩ አለሁ ይመለከተኛል ሊል ይገባዋል፡፡
ሰላም የሁሉ ነገር መሠረት ነው የሚባለው አውቀንም ሆነ ሳናውቅ በፈጠርነው ግጭት በሚፈሰው ደም በመውደድ የግልና የአገር ሀብት እንዳይባክን ማድረጉ ብቻ አይደለም፡፡ ሰላም ከሌለ ነግዶ ማትረፍ የለም፡፡ እያንዳንዷ ግጭት ኢኮኖሚው ላይ የሚማረረው ተፅዕኖ ሁሉንም ይጎዳል፡፡ ጉዳቱን ለማካካስ ደግሞ የበለጠ ያደክማል፡፡ ጠባሳውንም መሻር ለየቅል ይችላል፡፡
ስለዚህ በሰበብ በአስባቡ እየተነሱ ሰላምን የሚያናጉ ተግባሮችን መፈጸም የማይሽር ጠባሳ ከህሊና የማይወጣ ፀፀትም ያስከትላል፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ላይ ነች ሲባል ሁሉም ጥያቄ በአንድ ይመለሳል ማለት አለመሆኑን ለመገንዘብ የሚያቅተን ከሆነ ነገር የተሻለ ነገር ማግኘት አንችልም፡፡ ሁሉም ተነስቶ አዋቂና ፈራጅ ላለመሆን የሚሻ ከሆነም ለውጥ መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡
በለውጡ የተገኘውን መልካም ጅምር ለማስቀጠል ከተፈለገ ሰላም ወሳኝ እንደመሆኑ ሁሉ ዕድሉን በአግባቡ መጠቀም እንዳይችል እንቅፋት መሆን ነገን ማበላሸት ነው፡፡
ነገሮችን ረጋ ብሎ ማመዛዘን የሚኖርብን ጊዜ ላይ ነን፡፡ በየፌስቡኩ የሚዥጎደጎደውን ክፉ ክፉ ነገር እየለቀሙ እሱንም እያራገቡ ነገር ማቀጣጠሉ የሚመረጥ ከሆነ ይህችን አገር እያበጀናት አይደለም፡፡ ዛሬ ለውጡን የሚመሩ አካላት የእስካሁን ጉዞ ብዙ ተስፋ እየሰጠ የመሆኑን ያህል ይኼንን ተስፋ ለማጉበጥ የሚደረጉ ጥረቶች የተሻለ ነገር እንደሚያመጡ እየታወቀ ጥቂቶች የሚያራምዱት አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ቆም ተብሎ ሊታሰብባቸው ይገባል፡፡ ሰላም እያሳጡ ሰላም ማምጣት እንዳልተቻለ አድርጎ ማንፀባረቅም በጎ አይደለም፡፡
በተለይ አግባብም ይሁን አግባብ ስለመሆኑ የማይታመንባቸው ጥያቄዎችን የሚያቀርቡ አካላት ፈራጅም ሆነው መታየታቸው ነገር ብዙ የሚያነጋግር ቢሆንም ሁሉም እንደ ዜጋ ባለበት ኃላፊነት አቋሙን ያንፀባርቅ እንጂ እኔ ብቻ አይሆንም፡፡
በአጠቃላይ የዚህች አገር የሰላም መጓደል ዕድሜ በተራዘመ ቁጥር ለሥርዓት አልበኝነትም በር እየከፈተ ስለሚሄድ ብዙ ነገር ሊያሳየን ይችላል፡፡ ስለዚህ አሁንም የሕግ ማስከበር ሥራ በብርቱ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ዛሬ ዝም ብለን የለቀቅነው ነገር ለሕግ ተገዥ የሆነ ኅብረተሰብ በእኩልነት የሚያምን ትውልድ ሊኖረን ይገባል፡፡
10 March 2019
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar