****ሰኞን በቃሊቲ ****
‹‹መጽሐፉ በመውጣቱ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡
‹‹መጽሐፌን በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊ ወገኖቼም ቢያነቡት ደስ ይለኛል››
ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ
————–
ዛሬ ረፋድ ላይ ከወዳጄ አቤል አለማየሁ ጋር ቃሊቲ ሄደን የቀድሞ የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ባልደረባችን የነበረውን ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬን ለመጠየቅ ተቀጣጥረን ነበር፡፡ አቤል፣ ከቀጠሯችን 20 ደቂቃ ያህል ዘግይቶ መስቀል አደባባይ ደረሰና ደወሎ ተገናኘኝ፡፡ ሁለታችንም በ2007 ዓ.ም በአካል የተገናኘነው ዛሬ ነበር፡፡ ‹‹በ2007 ም ቀጠሮ አታከብርም?›› ብዬ ቀለድኩበት፡፡ ….
ሚኒባስ ታክሲ ተሳፍረን ቃሊቲ ደረስን፡፡ የተለመደ ፍተሻውም ታለፈ፡፡ ነገር ግን፣ እስከዛሬ አጋጥሞኝ የማያውቀው አዲስ ፍተሻ መኖሩን አቤል ነገረኝ፡፡ በዘመናዊ ኤሌክትሮኒክስ ማሽን ጫማ እና ቀበቶን አውልቆ በድጋሚ መፈተሽ ግድ ነበር፡፡ ይህም ታለፈና ‹‹ሸራተን›› ተብሎ ወደሚጠራው የቃሊቲ እስር ቤት አመራን፡፡ ይህንንም የእስረኛ መጠየቂያ ቦታ ስመለከተው ለመጀመሪያ ጊዜ በመሆኑ በማያቸውን ነገሮች ላይ ትኩረት መስጠቴ አልቀረም፡፡
አንድ ጥግ ላይ፣ በአጭር ርዝመት በእንጨት የተሰራች መጠየቂያ ጋር ደርሰን ቆምን፡፡ ለአንዱ ጥበቃ ፖሊስ ውብሸትን እንዲያሥጠራልን ነገርነው፡፡ ውብሸትም ከደቂቃዎች በኋላ ወደእኛ መጣ፡፡ ፊቱ በፈገግታ ተሞልቶ ነበር፡፡ ብርቱካናማ ቲ-ሸርት አድርጓል፡፡ በቅድሚያ ያገኘሁት እኔ ነበርኩ፡፡ ተቃቅፈን ሰላምታ እየተለዋዋጥን እያለ ከለበሰው ልብስ አኳያ ‹‹የቀለም አብዮት ልትጀምር ነው እንዴ?›› አልኩትና ትንሽ ተሳሳቅን፡፡
ከአቤልም ጋር ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ የጋራ ወጋችንን ቀጠልን፡፡ ብዙ ሃሳቦች የተወያየነው በቅርቡ ለንባብ ስላበቃው ‹‹የነጻነት ድምጾች›› የሚል ርዕሥ ስላለው የመጽሐፍ ሁኔታ ነበር፡፡ በመጽሐፉ መውጣት በጣም ደስ ብሎታል፤ ይህም ፊቱ ላይ በግልጽ ይነበባል፡፡ ብዙ መከራን አሳልፎ ይህንን ማየት መቻሉ በጨለማ ውስጥ እንዳለች ሻማ ይቆጠራል፡፡ ለረዥም ወራት በኩላሊት ህመም እየተሰቃየ ከዝዋይ ወደቃሊቲ ለሕክምና መጥቶ እንኳን የረባ ሕክምና ሳይደረግለት ውሃ ጠጣ ነበር የተባለው፡፡ ልብ አድርጉ፣ የዝዋይ ውሃ ጠጠር ያለበት መሆኑ እየታወቀ ወደ ዝዋይ እንዲመለስ ተደርጓል፡፡ የወላጅ አባቱን የሞት መርዶ የሰማው በዘዋይ እስር ቤት ነው፡፡ ሌሎች አስቸጋሪ ነገሮች በውብሸት ሕይወት ውስጥ አልፈዋል፡፡ የሚቀየር ነገር ከሌለ ደግሞ 11 የእስር ዓመታቶች ከፊቱ ይጠብቁታል፡፡ ይህ ሁሉ ታልፎ ይህቺን የተስፋ ብርሃን እንኳ በእስር ቤት ማየቱ ከምር ደስ ይላል – ለሞራሉ!
…ይህህ መጽሐፉን ሙሉ በሙሉ አንብቦ የጨረሰው ዓቤል፣ አንዳንድ ጥያቄዎችን ከመጽሐፉ በመነሳት ሲያቀርብለት እሱም ሲያስረዳ እና ሲመልስለት እያለ ወዳጃችን ሰለሞን ሞገስ አጠገባችን ደረሠ፡፡ የውብሸት ጠያቂዎችም ሶስት ሆንን፡፡ …
‹‹አሁን ከማን ጋር ነው የታሰርከው?›› ስል ጥያቄዬን አቀረብኩለት፡፡ ከገብረዋድ (የቀድሞ የገቢዎች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን መ/ቤት ምክትል ዳይሬክተር እና በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ጉዳቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኝ) እና ከአንድ ሌላ ልጅ ጋር አንድ ክፍል ውስጥ ነኝ›› አለን፡፡ ገረመኝ፤ አብረው ይሆናሉ ብዬ አልገመትኩም ነበር፡፡
‹‹ለአቶ ገብረዋድ አንድ ጥያቄ ጠይቅልኝ?›› አልኩት ለውብሸት፡፡
‹‹ምን?››
‹‹ከሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ለፍርድ ቤቱ አንድ አቤቱታ አቅርበው ነበር፡፡ በወቅቱ እኔም በችሎት ነበርኩ፡፡ ‹በማዕከላዊ ሰብዓዊ መብታቸው መጣሱን ሲናገሩ ገርሞኝ ነበር ያዳመጥኩት፡፡ በእርግጥ ማንም ሰው በእስር ላይ እያለ ሰብዓዊ መብቱ መጣስ የለበትም፡፡ ነገር ግን፣ አቶ ገብረዋድ የመንግሥት ከፍተኛ ሹመኛ በነበሩበት ጊዜ የተቃውሞ ፓርቲ አመራሮች፣አባላት፣ ጋዜጠኞችና በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ የሚገኙ ዜጎች በተለያየ ምክንያት ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ሲቀርቡ፣ በማዕከላዊ የምርመራ እስር ቤት ሰብዓዊ መብታቸው መጣሱን ለፍርድ ቤት አቤቱታ በተደጋጋሚ ሲያቀርቡ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መስማታቸው አይርቀም፡፡ ያኔ ዝም ብለው አሁን በራሳቸው ላይ ሲደርስ ስለመብት ጥሰት መናገራቸው ተገቢ ነበር ወይ? የመብት ጥሰት በራስ ላይ ሲደርስ ብቻ ነው ወይ ድምጽን ማሰማት የሚገባው?!›› አልኩት፡፡
ጥያቄዬን አድምጦ እጠይቅልሃለሁ አለኝ፡፡
የተለያዩ ነገሮችን እየተወያየን እያለ አንዲት ወጣት ልጅ ምግብ እና አነስተኛ ጥራቱን የጠበቀ ፍራሽ ይዛ በአቅራቢያችን መጣች፡፡ አቤል ‹‹ገብረዋድ ጋር ነች›› አለ፡፡ ወዲያው አቶ ገብረዋድ መጣ፡፡ ምቾት እና ነጻነት ባልተሰማው መንገድ ‹‹ሰላም ናችሁ›› የሚል ቃል ከአንደበቱ ወጣና ከውብሸት ጀርባ አልፎ ከምትጠይቀው ልጅ ጋር በትግርኛ ቋንቋ መነጋገራቸውን ቀጠሉ፡፡ ጠይቀን እንደተረዳነው ከሆነ ልጁ ነች፡፡ እኔም ጥያቄዬን ለአቶ ገብረዋድ ላቀርብለት አስቤ ከውስጤ ጋር አውርቼ ነበር፡፡ ነገር ግን፣ ከነበርንበት ቦታ አኳያ አመቺ ስላልነበረ ተውኩት፡፡ አቶ ገብረዋድም፣ ቀድሞን ወጣና ፍራሽ እና ምግቡን ይዞ ቻው ብሎን ሄደ፡፡ …
ውብሸትም መጽሐፉን አስመልክቶ እንዲህ አለን፡- ‹‹መጽሐፉ በመውጣቱ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ መጽሐፉን ሁሉም ሰው ቢያነበውም ደስ ይለኛል፡፡ ስለሀገራችን የእስር ቤት አስቸጋሪ ሁኔታ እና ስለሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች መጠነኛ መረጃ ያገኛል፡፡ መጽሐፌን በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊ ወገኖቼም ቢያነቡት ደስ ይለኛል፡፡›› ካለ በኋላ የዳያስፖራ ማኅበረሰብን በተመለከተ ይህቺን ሃሳብ አከለ፡፡
‹‹ዳያስፖራዎች ስለሀገራችን ሁኔታ ያገባናል ስለሚሉ ነው በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ድምጻቸውን በማሰማት ሰልፍ የሚወጡት፡፡ ይህን ባያስቡ ኖሮ በየካፌው ቡና እየተጠጣ ዝም ማለት ይቻላል፡፡ ከታሰርኩ በኋላ ‹‹ፍኖተ ነጻነት›› ጋዜጣን የማንበብ ዕድሉን አግኝቼ ነበር፡፡ አንዲት ሴት የእኔን ፎቶግራፍ ደረቷ ላይ አድርጋ [የታሰሩ ጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞች ይፈቱ! የሚል] የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ድምጻን ያሰማችበትን ምስል ተመለከትኩና፡፡ ሴትየዋ እኔን አታውቀኝም፡፡ ግን የእኔን የእስር ጉዳት ለመቃወም አደባባይ ወጥታለች፡፡ ይህ ለሀገር ከመቆርቆር የሚመነጭ ነው››
…ባለኝ መረጃ መሰረት የውብሸት መጽሐፍ ጥሩ እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ሁለተኛ ዕትምም በቅርቡ ይገባል፡፡
…ከእኛ ራቅ ብሎ የሚገኘው ፖሊስ ከሌሎች ፖሊሶች ጋር ተነጋገረና ‹‹ሰዓት ሞልቷን፤ በቃችሁ›› አለን፡፡
እኛም ውቤን ‹‹አይዞን!›› በማለት አቀፈን የስንበት ሰላምታ ሰጥተነው ተለየነው፡፡ ‹‹አቶ ገብረዋድን ጠይቅልኝ ያልኩህን እንዳትረሳ›› በማለትም በድጋሚ አስታወስኩት፡፡
***FJ 2007****
tirsdag 23. september 2014
mandag 22. september 2014
የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ ለብድር ዕዳ አደጋዎች የመጋለጥ ዕድሏ እየሰፋ ነው አለ
ሰሞኑን ለሦስት ቀናት ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት የዓለም ባንክ ማኔጂንግ ዳይሬክተርና የኦፕሬሽን ዋና ኃላፊ ስሪ ሙሊያኒ ኢንድራዋቲ፣ እያደገ የመጣው የብድር ዕዳ መጠን በኢትዮጵያ ላይ አደጋዎችን ሊያስከትል እንደሚችል ገለጹ፡፡
ኢንድራዋቲ ባለፈው ረቡዕ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ምንም እንኳን የአገሪቱ የብድር ዕዳ መጠን ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ ያለው ድርሻ አነስተኛ ቢሆንም፣ የዕዳውን መጠን በግልጽነት ለማስተዳደር የሚችልና ግልጽነት የሰፈነበት አስተዳደር ማስፈን የመንግሥት ግዴታ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ አገሪቱ ያለባት ጠቅላላ የብድር መጠን 20 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 12 ቢሊዮን ዶላር ከውጭ ምንጮች የተገኙ ብድሮችን የሚሸፍን የዕዳ መጠን ነው፡፡ በዚህ መሠረት ከጠቅላላ አገር ውስጥ ምርት አኳያ የዕዳው ድርሻ 44 ከመቶ መድረሱን ይጠቁማል፡፡
ኢንድራዋቲ እንደሚገልጹት፣ ይህ አኃዝ ዝቅተኛ በሚባለው የዕዳ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ነገር ግን የመንግሥት የኢንቨስትመንት ወጪዎች እየተበራከቱ በመምጣታቸው ምክንያት የዕዳ መጠኑን በዚያው ልክ እያደገ በመሆኑ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በሚመለከት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ከሚመለከታቸው ሚኒስትሮች ጋር መነጋገራቸውን አስረድተዋል፡፡ ከውይይቶቹ መካከልም በመንግሥት አስተዳደር ማሻሻያ ሪፎርሞች ላይ ያተኮረው አንዱ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በዚህም መንግሥት በአስተዳደራዊ መዋቅሮቹ ላይ ማሻሻያ በማድረግ፣ ግልጽነትና ኢኮኖሚውን በብቃት የማስተዳደር ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የኢንቨስትመንት ወጪን መነሻ በማድረግ፣ በኢትዮጵያ እየጨመረ የሚገኘውን የብድር ዕዳ መጠንና ሊከሰት የሚችለውን አደጋ ለመቋቋም የሚያስችል አሠራር ማምጣት እንደሚገባቸው መክረዋል፡፡
‹‹ይህንን ለማከናወን አስተማማኝ የፋናይናንስ ሪፖርት ያስፈልጋል፡፡ ግልጽነትና ወጥነት በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ተዓማኒነት ያለው መረጃ መኖሩ ግድ ይላል፡፡ አሁን እየታየ ያለው የብድር ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይ ተጨማሪ የተጋላጭነት አደጋ ማስከተሉ በእርግጠኝነት የማይቀር ነው፤›› ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ የብድር ዕዳዋን ለማቃለል የወጪ ንግድ ሚዛኗ ወሳኝ መሆኑን ኢንድራዋቲ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ባለፉት ሦስት ዓመታት በወጪ ንግድ መስክ አገሪቱ ዝቅተኛ ውጤት ስታዝመገዘብ መቆየቷ ለብድር ዕዳ ያላትን ተጋላጭነት አስፍቶታል ይባላል፡፡
አገሪቱ ስታዝመግብ የቆየችው የኢኮኖሚ ዕድገት መልካም የሚባል መሆኑን የጠቀሱት ኢንድራዋቲ፣ ይህም ሆኖ ኢኮኖሚው መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ብዙ እንደሚቀረው ገልጸዋል፡፡ የኢኮኖሚው ዕድገት በርካታ የሥራ መስኮችን ሊፈጥሩ የሚችሉ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለማምጣት ብዙ መንገድ ይቀረዋል ያሉት ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ፣ ባንኩ የኢንዲስትሪ ዞኖች ግንባታን ፋይናንስ እያደረገ እንደሚገኝም አስታውሰዋል፡፡ በአዲስ አበባ ቦሌ ለሚ ሁለተኛ ምዕራፍና በአቃቂ ቃሊቲ ቂልንጦ አካባቢ ለሚገነቡ ሁለት የኢንዱስትሪ ዞኖች የሚውል የ250 ሚሊዮን ዶላር ብድር መፍቀዱን፣ በኢትዮጵያ የባንኩ ዳይሬክተር ጉዋንግ ዚ ቼን ገልጸዋል፡፡
ባንኩ ለመሠረተ ልማት ከሚሰጠው ድጋፍ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ለመሠረታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራምም ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ተዘዋውረው በጎበኟቸው የሴፍቲኔት ጣቢያዎች ጥሩ ውጤት እንዳዩ ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ ተናግረው፣ እየጨመረ በመጣው የከተሞች የምግብ እጥረት ተጋላጭነት ሳቢያ በድምሩ አሥር ሚሊዮን ሰዎች በሴፍቲኔት ፕሮግራም ይታቀፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ይፋ አድርገዋል፡፡
ስሪ ሙልያኒ ኢንድራዋቲ የዓለም ባንክን ከመቀላቀላቸው አስቀድሞ የኢንዶኔዥያ የፋይናንስ ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የኢኮኖሚ ጉዳዮች አስተባባሪ ሚኒስትር በመሆንም ሠርተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2010 የዓለም ባንክን የተቀላቀሉት ኢንድራዋቲ፣ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ደረጃ የሚመሯቸው በርካታ መስኮች አሉ፡፡ በማኔጂንግ ዳይሬክተርነት ሥልጣናቸው የባንኩን የአካባቢያዊ ሥራዎች በጠቅላላ የመምራት ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡
søndag 21. september 2014
የኢህአዴግ አምባሳደር በስዊዲን ወየንሽት ታደሰ የእንቁላል ድብደባ በከፍተኛ ሁኔታ ደረሰባት።
በስዊዲን የሚገኙ ኢትዮጵያኖች ከዚህ በሆላ እንደድሮው በውጪ እየወጡ መዝናናት የለም በማለት አምባሳደሯን እንቁላል በመወርወር ከፍተኛ የሆነ ውርደት እንድተከናነብ አድርገዋል። አብረዋት የነበሩ የወያኔ ጠባቂዎችም ራሳቸውን ከድብድባው ለማምለጥ ሲሉ ጥለዋት ሄደዋል። የስዊድን ፖሊሶች በርካታ የፖሊስ መኪናዎችን በማምጣት ጸጥታውን ለመቆጣጠር የቻሉ ሲሆን ከረጅም እግታ በሆላ በፖሊሶች እርዳታ ከመኪናዋ ወጥታ ለመሄደ ችላለች።
እንቁላል አትጨርሱ ዛሬ የባንዳዎች እና የነነዋይ ውርደት በእንቁላል ቢጫ እናድረጋቸዋለን እና እሶ ላይ ብቻ አትጨርሱ፣ መኪናው የእንቁላል ጌጥ በዛበት የሚል አስቂኝ ክስተቶችም ነበሩበት።
በውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያኖች በተጠናከረ መልኩ የወያኔን ባለስልጣናት በሄዱበት የማዋረድና እጃቸው ደም የተበከለ መሆኑን በተደጋጋሚ እየተነገራቸው ሲሆን በቅርቡ በተመሳሳይ ሬድዋን ሁሴን በዋሽንግተን ዲዲ የደረሰበት ውርደት ይታወሳል።
በአሁኑ ሰአት በርካታ የወያኔ ባለስልጣኖች ወደ ውጪ መጓዝን እንደማይመርጡ የደረሰን ሪፖርት ያመላክታል።
በስዊዲን የኢትዮጵያ አባሳደር ላይ የገማ አሳና እንቁላል እንዳይወረወርባቸው ሲከላከሉ የሚያሳይ ፎቶ
ሕዝቡና ተማሪው በአገር ጉዳይ ከኢህአዴግ ጋር መግባባት አልቻልንም በማለት ስልጠናው እንዲቋረጥ ጠየቀ።
የጎንደር ዩንቨርስቲ ተማሪዎች ብሶታቸውን በከፍተኛ ቁጣ ገልጸዋል።
- ለወያኔ ባለስልጣናት የቀረበው ሪፖርት እንደሚያሳየው ስልጠናው ምንም የስኬት ፍንጭ አላሳየም።
- የሃምሳ አመት እቅድ ለምን አስፈለገ የስልጣን ጥመኝነትን ያሳያል።
- ለሶስተኛ ዙር ስልጠና ምዝገባ እየተካሄደ ነው።
- በኢሕአዴግ ውስጥ ያሉ አመራሮችም ይሁኑ አባላቶቹ የአስተዳደር ብቃት የላቸውም።
- ኢትዮጵያውያን በህግ ፊት እኩል የሚሆኑት እና ፍትህ የሚነግሰው ቀን እንናፍቃለን።
- በቫት ስም መንግስት ዘረፋ ይዟል በህጉ ቫት አይከፈልበትም የተባለው የጤና ዘርፍ ሳይቀር ቫት እየቆረጠ ነው።
በየአከባቢው እየተካሂደ ያለው ልማታዊነትን ሽፋን አድርጎ የስልጣን ማስረዘሚያ ሰበካ (ስልጠና) እንደቀጠለ ቢሆንም በህዝቡ እና በአሰልጣኞች መካክል ከፍተኛ የሆነ አለመግባባት ከመከሰቱም በላይ ህዝቡና ተማሪው በአገራችን ጉዳይ ከኢህአዴግ ጋር ልንግባባ አልቻልንም ስለዚህ አበል ይቅርብን እና ስልጠናውን አቋርጡልን በማለት እየጠይቀ መሆኑን ዘገባዎች አመልክተዋል። ሰልጣኞች እንደሚሉት እየተካሄደ ያለው ስልጠና ሳይሆን የፖለቲካ ሰበካ ነው ይህ ደሞ የተለያየ አስተሳሰብ ያላቸውን ህዝቦች ለማደናቆር ካልሆነ በስተቀር ተቀባይነት የለውም። ስለዚህ የያዛችሁን ስልት ቀይራችሁ ህዝብ መሃል ግቡና አናግሩን እንጂ በ አበል እና በቀበሌ ጥቅማጥቅም አታስገድዱን፡ አያዋጣችሁም ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለአዲስ አበባ የኢሕአዲግ ጽ/ቤት ቅርብ የሆኑ ምንጮች እንደጠቆሙት እስከዛሬ በተሰጡ ስልጠናዎች የተሰብሰቡ ሪፖርቶች እንደሚይመለክቱት ሕዝቡም ይሁን ተማሪው በተጻራሪነት እንደቆሙ እና በድርጅቱ ላይ ከፍተኛ ጥላቻ እና ማንጓጠጥ ያሳዩ መሆኑን የጠቆመ ሲሆን ስልጠናው ምንም የስኬት ፍንጭ አላሳየም ብሏል።
በጎንደር ዩንቨርስቲ ለየት የሚያደርግው ተማሪው ብሶቱን በከፍተኛ ቁጣ መግለጹ ነው።
በጎንደር ዩንቨርስቲ ተማሪው በዩንቨርስቲው ትምህርት ላይየና በመምህራን ጉዳይ ከፍተና ቁጣ በማሰማት ላይ ሲሆን ዩንቨርስቲው በመልካም አስተዳደር እጦት እና በሙስና እየታመሰ መሆኑን ተነግሯል በአንድ ምት ጊዜ ውጽት ብቻ 3 ፕሮፌሰሮች 3 ዶክተሮች 14 ሁለተኛ ዲግሬ ያላቸው ምሁራን ልምድ ያላቸው መምህርን ጎንደር ዩንቨርስቲን ለቀዋል።ለዚህ ምክንያቱ ደሞ የዩንቨርስቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር መንገሻ አምባገነንነት እና ፈላጭ ቆራጭነት መሆኑን ተማሪዎቹ አስምረውበታል።
የዩንቨርስቲው አመራር እና ቦርዱ አምባገነን ናቸው ያሉት ተማሪዎች በሙስና እና በወገንተኝነት የተዘፈቁ ስለሆኑ በዩንቨርስቲው ከ20 አመት በላይ ያገለገሉ ምሁራን እንዲለቁ ምክንያት ህነዋል።በ2007 ይነሳሉ ተብለው የነበሩት እና በጣም አስቸጋሪ ባህሪ እንዳላቸው የሚነግርላቸው የዩንቨርስቲው ፕረዚደንት ፕሮ.መንገሻ በኢሕ አዴግ ብባለስታን ድ/ር ስንታየው ትእዛዝ እንዲቀጥሉ መደረጉን ተማሪውን አስቆጥቷል።
በጎንደር ዩንቨርስቲ ተማሪው በዩንቨርስቲው ትምህርት ላይየና በመምህራን ጉዳይ ከፍተና ቁጣ በማሰማት ላይ ሲሆን ዩንቨርስቲው በመልካም አስተዳደር እጦት እና በሙስና እየታመሰ መሆኑን ተነግሯል በአንድ ምት ጊዜ ውጽት ብቻ 3 ፕሮፌሰሮች 3 ዶክተሮች 14 ሁለተኛ ዲግሬ ያላቸው ምሁራን ልምድ ያላቸው መምህርን ጎንደር ዩንቨርስቲን ለቀዋል።ለዚህ ምክንያቱ ደሞ የዩንቨርስቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር መንገሻ አምባገነንነት እና ፈላጭ ቆራጭነት መሆኑን ተማሪዎቹ አስምረውበታል።
የዩንቨርስቲው አመራር እና ቦርዱ አምባገነን ናቸው ያሉት ተማሪዎች በሙስና እና በወገንተኝነት የተዘፈቁ ስለሆኑ በዩንቨርስቲው ከ20 አመት በላይ ያገለገሉ ምሁራን እንዲለቁ ምክንያት ህነዋል።በ2007 ይነሳሉ ተብለው የነበሩት እና በጣም አስቸጋሪ ባህሪ እንዳላቸው የሚነግርላቸው የዩንቨርስቲው ፕረዚደንት ፕሮ.መንገሻ በኢሕ አዴግ ብባለስታን ድ/ር ስንታየው ትእዛዝ እንዲቀጥሉ መደረጉን ተማሪውን አስቆጥቷል።
ህዝቡና ተማሪው ዛሬ በጠዋቱ እነዚህን ሲናገሩ አርፍደዋል።
1 ኢሕአዲግ የሃምሳ አመት እቅድ አውጥቷል መጀመሪያ ደረጃ የ50 አመት እቅድ በማን ማንዴት ነው የሚያውጣው ሃምሳ አመት ከህዝብ ፍቃድ ውጪ የመግዛት እቅድ ኢሕአዴግ አለው ማለት ነው ይህንን አንቀበልም ሃገሪቷን ሌላ አደጋ ውስጥ ለመክተት ካልሆነ በቀር ማንም መንግስት እንዲህ አያቅድም።
2 ኒኦሌቤራሊዝምን እና ሶሻሊዝምን እየጠላችሁ ልማታዊ ዲሞክራሲ ትሉናላችሁ ከየትኛው የትናው እንደሚሻል እንኳን ግንዛቤ የላችሁም በውቀት ያልጠገባ አመራር እና አባል ታቅፋችሁ ሃገር እንዲት እንደምትመሩ በፍጹም አቅቷቹሃል እና አስቡበት
3 የትምህርት ጥራት አውርዶ የዩንቨርስቲዎችን ቁጥር ማብዛቱ፡ተቀሜታው ምንድነው ? በጎንደር ዩንቨርስቲ ዋና ነጥብ የሆነው በዩንቨርስቲው ውስጥ ያለው ትምህርትን የመግደል አምባገነናዊ አስተዳደር በስፋት ተነስቶ እንደነበር ሰልጣኖች ጠቁመዋል።
4. የከተሞችን እድገት በተመለከተ አንጻራዊነት አይታይም የይስሙላ ልማት ፕሮፓጋንዳ እንጂ እድገት የለም መንግስት ባወጣው ህግ በጤናው መስክ ፋርማሲዎች ቫት አያስከፍሉም ይባላል በተዘዋዋሪ ግን የቫት ማሽን አስገብተው እያስከፈሉ ነው ይህ የመንግስትን በዝባዥነት ያሳያል ።ብነጻ ገበያ ሰበብ መንግስት እጁን በገብያ ውስጥ እየከተተ የህዝቡን ንሮ እያደፈረሰ ነው ።ጎን ለጎን የጉምሩክ ቀረጥ የሚጠየቀው ከ እቃው በላይ ነው ይህ ደሞ የከብያውን ትራንዛክሽን እየጎዳው ነው የሚሰራው ለህገር ነው ወይንስ ለዘረፋ ህዝቡ ተማሯል መፍትሄ እንጅ ስልጠና አንፈልግም።
5 መንግስት ሙስኛ ባለስልጣናት ተንሰራፍተዋል እያለ ነው ራሳችሁ ያመናችሁበትን እርምጃ ክመውሰድ ይልቅ እናንተ እርምጃ የምትወስዱባችው ከኢህአዲግ ፖለቲካ ጋር ሲኳረፉ ነው ይህ አግባብ አይደለም ሁሉም ስው በህግ ፊት እኩል መሆኑ ማረጋገጥ የተሳነው መንግስት እንዴት ስልጠና ይሰጣል።
onsdag 17. september 2014
በሶማሊ ክልል የተፈጸመው ኢሰብአዊ ድርጊት ” ገዢው ፓርቲ ለህዝብ ያለውን ንቀት ያሳያል” ተባለ
የቀድሞው የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት የህዝብ ግንኙነት ስራ አማካሪ እና የክልሉ የወጣቶች ሊቀመንበር በመሆን ካገለገለ በሁዋላ የተለያዩ
የቪዲዮ ማስረጃዎችን በመያዝ ከአገር የወጣው ወጣት አብዱላሂ ሁሴን ፣ “ኦ ኦጋዴን” በሚል ያስተላለፈው አጭር የዶክመንታሪ ፊልም፣ በስልጣን ላይ ያሉት ገዢዎች ለሶማሊ፣
ለኢትዮጵያና በአጠቃላይ ለሰው ልጆች ያላቸውን ንቀት ያሳያል ብሎአል።
ዘገባውን ከተመለከተ በሁዋላ ህመም እንደተሰማው የገለጸው አብዱላሂ፣ አስከሬን እንዲለቅሙ ሲገደዱ የነበሩት ሲቪሎች ሁኔታ በእጅጉ እንደረበሸው ገልጿል አንዳንድ የመንግስት ደጋፊዎች
ኦብነግ አካባቢውን ለመገንጠል የሚንቀሳቀስ በመሆኑ፣ በአባለቱና በደጋፊዎቹ ላይ የተወሰደው እርምጃ ትክክል ነው በማለት በማህበራዊ ድረገጾች ላይ ሲጽፉ ተመልክተናል፣ ለዚህ ምን አስተያየት
አለህ የተባለው አብዱላሂ፣ ” ይህን የሚሉ ሰዎች ማፈር አለባቸው በማለት መልሷል ወጣት አብደዱላሂ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ልዩነታቸውን አስወግደው በአንድነት በመነሳት
በስልጣን ላይ ያለውን ሃይል ማስወገድ እንደሚገባቸውም አብዱላሂ መልእክት አስተላልፏል።
የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጭ ግንባር /ኦብነግ የአማርኛ ክፍል ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ሃሰን አብዱላሂ በበኩላቸው፣ በክልሉ የሚፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰት የቆየ መሆኑን ገልጸው፣ ድርጅታቸው
በደቡብ አፍሪካ፣ በሄግ፣ በስዊድንና በጄኔቫ ጉዳዩ ተጣርቶ ተጠያቂ የሚሆኑት ባለስልጣኖች በህግ እንዲጠየቁ አቤቱታ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
መንግስት የተገደሉት የኦብነግ አባላት እንጅ ሲቪሎች አይደሉም በሚል ለማስተባበል ቢሞክር የእናንተ ምላሽ ምን ይሆናል ተብለው የተጠየቁት አቶ ሃሰን፣ መንግስት በራሱ የሚተማመን ከሆነ
አካባቢውን የጦር ቀጠና ማድረጉን ትቶ ለውጭ ጋዜጠኞችና የሰአብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ክፍት በማድረግ አለበት በማለት፣ በክልሉ የሚፈጸመው ጥቃት በህዝቡ ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
tirsdag 16. september 2014
አቶ የሽዋስ አሰፋ የርሃብ አድማ አደረገ
በማዕከላዊ ምርመራ ታስሮ የሚገኘው የሰማያዊ ፓርቲ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ የሽዋስ አሰፋ የአራት ቀን የርሃብ አድማ
ማድረጉን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል። አቶ የሸዋስ ከጳጉሜ 4 ጀምሮ አዲሱን አመት በርሃብ አድማ ያሳለፈ ሲሆን ቅዳሜ መስከረም 3/2007 ዓ.ም ምግብ እንደቀመሰ ባለቤቱ ወይዘሮ
ሙሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጻለች፡፡
አቶ የሽዋስ የርሃብ አድማ ያደረገው ከታሰረበት ሐምሌ 1/2006 ዓ.ም ጀምሮ ከጠበቃው ጋር ከአንድ ጊዜ በላይ መገናኘት ባለመቻሉና ዘመድ እንዲሁም የኃይማኖት አባት
እንዳይጎበኘው በመከልከሉ ነው፡፡
የሽዋስ አሰፋ በባለቤቱ ብቻ በሳምንት አንድ ቀን እንዲጎበኝ የተፈቀደለት ሲሆን የርሃብ አድማ ባደረገባቸው ቀናት ባለቤቱ ምግብ ስታስገባ ለየሸዋስ ምግቡ እንደደረሰው ተደርጎ ባዶ
ሳህን ሲደርሳት መቆየቱን፣ ባለቤቱ የበዓል ቀን ልትጎበኘው በሄደችበት ወቅት ‹‹ወጥቷል›› ተብላ መመለሷን፣ በማግስቱ ልጆቹን ይዛ ልትጠይቅ ስትሄድም ‹‹ስብሰባ ላይ ናቸው!››
በሚል እንዳታገኘው በመደረጓ ለ15 ቀናት ሳትጠይቀው መቆየቷን ጋዜጣው ዘግቧል።
በሌላ በኩል ጠበቃው ተማም አባ ቡልጉ አቶ የሽዋስን ለማግኘት በተደጋጋሚ ወደ ማዕከላዊ ቢያቀኑም ሳያገኙት እንደቀሩ ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል።
fredag 12. september 2014
የዩክሬይን ክራሚያና የሩስያ ጉዳይ ስለኢትዮጵያና ኤርትራ ያልተዘጋ አጀንዳ ምን ያሰተምረናል?
(አክሊሉ ወንድአፈረው – የግል አስተያየት)
መስከረም 2, 2007 (ስፕተምበር 12 2014 )
ለመንደርደሪያ ያህል፦ ለመሆኑ በታሪክ ክራሚያ ዩክሬን ወይስ ሩሲያ ነበረች?
ጠቅለል ባለ ሁኔታ የክራሚያን ያለፉት 200 ዓመታት ታሪክ ስንመለከት በዋናነት የሩሲያ አካል ሆና መቆየቷን እናያለን። በሌኒን የሚመራው የሶሻሊስት አብዮት ከተቀጣጠለ ከ 1917 በሁዋላም ቢሆን ክራሚያ በሶቭየት ህብረት ዕቅፍ ውስጥ አንድ ራስ-ገዝ አስተዳደር ሆና ቆይታለች።
ክሬሚያ የዩክሬን አካል የሆነችው ባውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1954 በወቅቱ የራሽያ ኮሚኒስት ፓርቲና ያገሪቱ መሪ በነበሩት በኒኪታ ክሩስቼቭ ሲሆን፤ እኘህም ሰው የትውልድ ቦታቸውና የፖለቲካ አጋራቸው ለሆነችው ዩክሬን በስጦታ መልክ ከሰጡ በሁዋላ ነበር፡፡ በወቅቱ ይህ ጉዳይ ለሶቭየት ፖለቲካ መሪዎችም ሆነ ለክራሚያ ነዋሪዎች አስጨናቂ ጉዳይ አልነበረም፡ ለምን ቢሉ ዩክሬን የሶቭየት ህብረት አንድ ክፍለ ሀገር (ሪፐብሊክ) የነበረች ሲሆን የክራሚያ ዩክሬን ውስጥ መግባት ለአስተዳደር አመቺነት ካልሆነ በስተቀር በጊዜው ሌላ ሰፊ የፖለቲካ እንደምታ አልነበረውምና ነው። ከዚያም አልፎ በተለይ በምስራቅ አውሮፓ ይገኙ የነበሩት ሁሉም ሶሻሊሰት ሀገሮች በሶቭዬት ሶሻሊስት ሪፐብሊክ የበላይነት ጥላ ስር እንዳንድ ሀገር ሆነው (በሶሻሊስት ዓለማቀፋዊነት መርህ) ይመሩ ስለነበርም እንኳንስ በአንድ ሀገር ስር ያሉ ያስተዳደር ክልሎች በተለያዩ ሶሻሊስት ሀገሮችም መካከል ቢሆን ድንበርና ድንበርተኘነት ታላቅ ቁምነገር ያለው ተደርጎም ይወሰድ እንዳልነበር ማሰታወስ ያስፈልጋል።
የክራሚያ ነዋሪዎች በማንነት አንጻር ራሳቸውን እንዴት ይመለከታሉ?
ይህ ጉዳይ አጅግ አወዛጋቢና በዪከሬን ግጭት ውስጥ ተፋላሚ የሆኑ ክፍሎችም የግል አቌማቸውን የብዙሃኑን ፍላጎት እንደሚንጸባርቅ አድርገው የሚሟገቱበት ዕውነታ ነው::
በዩክሬይን ስልጣኑን የጨበጡት ክፍሎች እና ደጋፊዎቻቸው “የክራሚያ ነዋሪዎች ራሳቸውን የሚያዩት ከሁሉም በላይ ከራሽያ የተለዩና ዩከሬንያዊ አድርገው ነው የሚቆጥሩት” የሚለውን አመለካከት ሁሉም ስው እንዲቀበለው ይፈልጋሉ:: ክራሚያ የዩክሬን አካል ሆና የቆየችበትን ጊዜ በማጣቀሰም በተለይም አዲሱ ትውልድ የተማረውም፤ ያደገውም ስለዩክሬን እየተነገረው ስለሆነ ስለ ራሽያዊነት የሚሰማውም የሚያውቀውም ቅንጣት ያህል ነገር እንደሌለና ይህም በመሆኑ ከራሽያ ጋር የሚያገናኝው ስንሰለት እንደተበጣጠስ ደጋግመው ሲናገሩ ይደመጣሉ::
በክራሚያ ውስጥ የሚታየውና የሚጨበጠው እውነታ ግን ሌላ ነው:: ከ 60 ዓመታት የዩክሬን አካልነት እና ከ23 አመታት ሙሉ ለሙሉ መለያየት በሁዏላም የከሬሜያም ሆነ ሌላው የምሥራቅና ደቡብ ምሥራቅ ዩክሬን ነዋሪዎች የሚሰማችው ስሜት ግን ከሩሲያ ጋር ያላችው የቀደመ ትስስር አንጅ የዩክሬን አካልነት ሆኖ አልተገኘም:::
ከዚህ በታቸ የሚታየውና በቅርቡ የተካሄደ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ከ 70% (ሰባ ከመቶ) የማያንሱ ክራሚያዎች ራሳቸውን የሚቆጥሩት ብቻ ሳይሆን ትስስርንም ቢሆን የሚሹት ከሩሲያ ጋር እንደሆነ ያመለክታል::
Data: Razumkov Center; Figure: Grigore Pop-Eleches and Graeme Robertson/The Monkey Cage
ይሀ ሁኔታ የሚያሳየው ከአቅመቢሷ ዩክሬን ጋር ከመዳበል ይልቅ ሰፋና ጠንከር ካለችው ሩሲያ ጋር መሆኑ ምን ያህል ጠቀሜታ እንዳለው መገንዘብን ብቻ ሳይሆን የረጅሙ ጊዜ ትስስር የፈጠረውን ማንነትንም በቀላሉ መበጣጠስም እንደማይቻል ነው::
በዚህም ምክንያት ይመስላል ክራሚያዎች በተለያየ ሁኔታ በዩክሬን ውስጥ ማንነታቸውን ሊያሰከብሩ ሲጥሩ ቆይተውና ሳይሳካላቸው ባሉበት ሁኔታ ዩክሬን ጓዟን ጠቅልላ በአውሮፓ ማህበረሰብ ዕቅፍ ስር ለመግባት ርምጃ መውሰድ ስትጀምር ሁኔታው ስላልጣማቸው ከገቡበት ፈተናና አጣብቂኝ እንድትታደጋቸው ሩሲያን የተማጸኑት።
ቀደም ሲል በምዕራቡ ዓለም ፖለቲካ ተንታኞች ክራሚያወች ወደ ራሽያ መዋሀድን አይፈልጉም፤ ፍላጎታቸው ከሌላው አውሮፓ ጋር ይበልጥ መተሳሰር ነው በማለት ደግመው ደጋግመው ይናገሩ ወይም ያስተጋቡ እንጂ በማርች 2014 ሬፈረንደም ሲካሄድ ግን 97% የሆነው ህዝብ ነበር ዩክሬንን ትቶ ወደ ራሽያ መቀላቀልን የመረጠው። ይህ ሁኔታ የክራሚያ ተወላጆች ከሩሲያ ጋር ለረጅም ዘመናት ከነበራቸው የታሪክ፣ የፖለቲካ፤ የቤተሰብ፣ የባህል፣ የስነ ልቦናና፣የማሕበራዊ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ መለያየት ችለናል፤ በራሸያና በክራሚያወች መካከል የነበረውን የአንድነትና የትስስር ስሜት አጥፍተነዋል፤ ብለው ሲያስቡ ለነበሩ ሁሉ መርዶና የራስ ምታት ነው የሆነባቸው::
ክራሚያውያን ከሩስያ ጋር መልሶ ለመቀላቀል ከ 90 በመቶ በላያ በሆነ ድምጽ ፍላጎታቸውን ገልጸው ደስታቸውን ሲገልጹ ) Mike Collett-White and Ronald Popeski SIMFEROPOL/KIEV Sun Mar 16, 2014 SIMFEROPOL/KIEV (Reuters) – Russian)
ባሁኑ ሰአት በክሬሚያ የሚታየው ሁኔታ በሻቢያ ስር የወደቀውን ህዝብ የማንነት ጥያቄ በተመለከተ ብዙ ጉዳዮችን እንድናገናዝብ ያስገድዳል። ላለፉት 23 አመታት “የኛ ሀገር ነች; የማንነታችን መግለጫ ነች”; ብለው ከሚመለከቷት እና ከሚወዷት ኢትዮጰያ ተነጥለውና በኤርትራ ውስጥ ከነመሬታቸው ተገደው ከሚገዙት የአፋር፤ ኩናማ፤ ኢሮብ፤ የሀማሴን፣አካለጉዛይ እና ሌሎችም ወገኖቻችን ሁኔታ ጋር እጅግ ይመሳሰላል። ታላቁ የአፋር ተወላጅ የተከበሩት ቢትወደድ ዓሊ ሚራህ፣ “እንኳንስ ህዝቡ ግመሎቻችንም ቢሆኑ የኢትዮጵያን ባንዲራ ያውቃሉ” ሲሉ የተናገሩት ታላቅ መሪ ቃል ስለአፋር ህዝብ የማይናጋ ጥልቅ ኢትዮጽያዊነት በቂ ማስረጃ ነው። ከዚህም ሌላ ቅድመ ሻቢያ/ወያኔ ከኢትዮጵያዊነት ውጭ ምንም አናውቅም ብለው ስለቆሙ በሻቢያ ሰራዊት በተደጋጋሚ የተደበደቡት የኩናማ፤ የሳሆ ወዘተ ወገኖች ታሪክ ኢትዮጰያዊነትንና የትዮጵያዊነትን ስሜት ከነዚህ ህዝቦች መለየት እንደማይቻል ወይም እጅግ ረጅም ጊዜ እንደሚወስድ ያመላክታል።
በመሀል ብዙ ቅሬታ እንደተከሰተ አጠያያቂ ባይሆንም ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር ለማሰተሳሰር ስለታገሉትና ስለወደቁት አርበኞች፣በልጆቻችውና በልጅ ልጆቻቸው አዕምሮ ውስጥ በአሁኑ ሰአት ምን አይነት ስሜት እንደሚመላለስ የክራሚያ ተመክሮ ፍንጭ ሊሰጥ ይችላል:: በተለይም ደግሞ የክሬሚያ አዲስ ትውልድ አሁንም ከአማሪጮች ሁሉ ወደ ራሸያ ማዘንበሉን እንደመረጠ ስንመለከት አበረታች ሁኔታ ቢፈጠር በሻቢያ ስር በምትገኘው ኤርትራ ውስጥ ሊከሰት የሚችለውን ዕውነታ መገመት አይከብድም::
የክራሚያን ሁኔታና ዕውነታ ስንመለከት፤ የህወሀት መሪወች ሲሰብኩት የቆየውና አሁን ደግሞ ባንዳንድ ተቃዋሚወች ውስጥም እየሰረጸ ያለው “የኤርትራ ጉዳይ ያለቀለት ጉዳይ ነው” የሚለው አመለካከት የህዝብን ሰነልቦናዊ ጥንካሬ ወደሚቦረቡር እና ብሄራዊ ጥቅምንም ወደሚጎዳ ተግባር እንዳያነጉደን ያሰጋል። የሀገር ጥቅም የሚጠበቀው ጽናት እና ጥራት ባለው ራዕይ ላይ በተመሰረተ ትግል እንጂ ጊዚያዊ ጥቅምን ለማሳደድ ሳያላምጡ በመዋጥ ወይም ደግሞ መሰረታዊ የሀገር ጥቅምን “እሱን አሁን እርሱት” በሚል ራእይ የለሽ አካሄድ ከቶውንም ሊሆን አይችልም::
ሩሲያ ስለ ክራሚያ ምን ያስጨንቃታል?
ሩሲያ በኢኮኖሚም ሆን በወታደራዊ ሃይል በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊነትና ተደማጭነት ያላት ታላቅ ሀገር እንደመሆኑዋ በቆዳ ስፋቱዋም ቢሆን አሁንም ባንደኘነት ደረጃ ላይ ትገኛለችል። ባንጻሩ ደግሞ ክራምያ በህዝብ ቁጥርም ሆነ በኢኮኖሚ ለሩስያ እዚህ ግባ የማይባል አስተዋጽኦ ነው የሚኖራት። በኢኮኖሚ አንጻር ብቻ ካየነው በዋናነት ተጠቃሚዋ ከራሚያ እንጂ ሩሲያ አትሆንም፡፡ ሆኖም ግን የዘር ሓረግና ታሪክን የሚገዛው ገንዘብ ብቻ አደለምና ክራሚያ በሩስያ (ሩስያም በክሬምያ) በታሪክም ሆነ በህዝቡ ሥነ-ልቦና ላይ እጅግ ቁልፍ ቦታ አላቸው፡፡ይህ ሁኔታ ምን ያህል መሰረት ያለው እንደሆነ ለመገንዘብ የሚቀጥሉትን ታሪካዊ ሁኔታዎች እንመልከት፡
- በጊዜው በመዳከም ላይ የነበረው የኦቶማን ኢምፓየር እና ራሸያ በኦክቶበር 1853 ውጊያ ውስጥ የገቡት በክሬምያ ጉዳይ ነበር፡፡ ውጊያው የተቀሰቀሰው ሩሲያ በክራሚያ የነበሩ የኦርቶዶክስ ክርስትና ተከታዮችን ከጥቃት ለማዳን በወሰደችው እርምጃ ነው ።
- ይህን ተከትሎ ከ 1853–1856 ባንድ በኩል በራሸያ በሌላ በኩል ደግሞ በፈረንሳይና እንግሊዝ ጥምር ጦር መሀል የተካሄደው ጦርነት በክሬምያ ውስጥ ነበር፡፡
- የቦልሽቪኮችን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ ነጩ ሰራዊት ( the white army) እየተባለ የሚጠራውና ሶሻሊዝምን በሚቃወሙ የምዕራብ ሃይሎች ይደገፍ የነበረው የተቃዋሚዎች ሀይል በ1920 የመጨረሻውንና ወሳኙን ውጊያ ያካሄዱትም በዚሁ በክሬሚያ ነበር።
- በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከፍተኛ ደም የፈሰሰበት ጦርነት ከተካሄደባቸው ቦታዎች ውስጥ ክራሚያ አንዷና በዋናነት የምትጠቀስ ነች።
- የጀርመን ናዚዎች ክራሚያን ለመያዝ ባደረጉት ወረራ ከ 170 ሽህ በላይ የሶቭየት ጦር የተሰዋ ሲሆን በወቅቱ ፋሽስቶችን እስከመጨረሻ የመከተችው ኣና የጀግኖች ከተማ በመባል ልዩ ሽልማት የተሰጣት የክራሚያ ዋና መናገሻ የሆነችው ሴቫስቶፖል ነበረች። በወቅቱ ምዕራብ ዩክሬን የፋሽስቱ ሂትለር ተባባሪ በመሆን በሽዎች የሚቆጠሩትን ጸረ-ፋሽስት ሃይሎች እንደገደሉና እንዲሰደዱ እንዳደረጉ ታሪክ መዝግቦታል።
- በሁለተኛው ያለም ጦርነት ማጠቃለያ በሦስቱ ተባባሪ ሐያላን ሀገሮች (Allied Forces) መሪዎች ያሜሪካው ፍራንክሊን ሩዝቬልት፣ የሩሲያው ጆሴፍ ስታሊን እና የኢንግሊዙ ዊንስተን ቸርችል መካከል የተደረገው ስብሰባ የተካሄደው በያልታ ፣ ክራሚያ ውስጥ ነበር።
ይህ ሁሉ በራሽያውያንና ክራሚያ መካከል ያለውን ከፍተኛ የታሪክና የሰነልቦና ትሰሰር አንዱ ሌላውን ለምን እንደሚፈልግ ያሳያል::
ይህ ብቻ ሳይሆን ክራሚያ ለሩሲያ የምታስገኘው ጂኦ-ፖለቲካዊና ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታም እጅግ ትልቅ ነው። ክራሚያ ቀደም ሲል የሶቭየት ህብረት በሁዋላም የሩሲያ ፌዴሬሽን ባህር ሀይል የሆነው ብላክ ሲ ፍሊት የጦር ሠፈር ነች። በዩክሬን ውስጥ የራሽያ ፍቅር የሌለው መንግስት ሥልጣን ቢይዝ የሩሲያን ደህንነት ዛሬም ባይሆን ነገና ከነገ ወዲያ አደጋ ላይ ሊጥለው እንደሚችል ራሸያ ጠንቅቃ ታውቃለች። ይህ አደጋም አፍንጫዋ ስር ሲከሰት እጅ አጣጥፎና ምንም እንዳልተፈጠረ በማስመሰል ማለፍን የራሸያ መሪወችም አልፈለጉም። ስለዚህም ቀልጠፍና ፈርጠም ያለ እርምጃ መውስድን አስፈላጊ ሆኖ አግኝተውታል። የራሽያው ፕሬዚደንት ፑትን በቅርቡ ለሀገሪቱ ፓርላማ ባደረጉት ንግግር ክራሚያ ለሩሲያ ምን ያህል ስትራተጂያዊ አስፈላጊነት እንዳላት ሲገልጹ “ ወደ ሜዴትራንያንና ወደ ጥቁር ባህር መሽጋገሪያችን የሆነችው ሶቫስቶፖል በባዕዳን ቁጥጥር ስር ሆና ማየት ከቶውንመ ተቀባይነት የለውም “ ነበር ያሉት።
ከላይ ስንደረደርበት የቆየሁት አመለካከት ወዳገራችን ሁኔታ ሲመለስ፤ ኢትዮጵያሰ ስለ ኤርትራ ምን ያስጨንቃታል የሚለውን ጥያቄ ማጫሩ አይቀሬ ነው። ከዚህ አኳያ እያንዳንዱ ሰው የየራሱን ምርምር አድርጎ መደምደሚያ ላይ እንዲደርስ ያስፈልጋል ብዬ አስባለሁ። ሆኖም ግን ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በኢኮኖሚ፣ በሀገር ደህንነት ወዘተ አንጻር እጅግ ብዙ ጉዳት እንደደረሰባት እና ወደፊትም መገመት የሚከብድ አደጋ እንደተጋረጠባት ብዙወች በመረጃ አስደግፈው ጽፈውበታል። በኢኮኖሚ አንፃር ብቻ ሲታይ እንኴ የራሷን ወደብ እንድታጣ የሆነችው ኢትዮጵያ ለጂቡቲ መንግስት ለወደብ ኪራይ የምትክፍለው ገንዘብ በየቀኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠር እንደሆነ ይታወቃል:: ይሀ ገንዘብ ለሀገር ልማት ቢውል ኖሮ የምን ያክል ህጻናትን ህይወት ማዳን እንደሚቻል ምን ያህል ተጨማሪ ትምርት ቤት ጤና ጣቢያ ማቌቌም እና ህይወት ማዳን እንደሚቻል ስናስብ የሁኔታውን አንገብጋቢነት ለመገንዘብ ይረዳል::
አሁን ካለው አሀዝ ስንነሳ ኢትዮጵያ የራሷን ወደብ አጥታ ለጅቢቲ የምትከፍለው ወጪ በያመቱ ለአንዳንዱ ወረዳ በሚሊዮኞች የሚቆጠር ተጨማሪ በጀት ለመመደብ የሚያሰችል ነው። ይህ ታዲያ ድህነትን ለመቀነስ፣ ለልማት ወዘተ ምን ያህል አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ማንናውም ጤነኛ አእምሮ የሚገነዘበው ነው።
በዚህ አንጻር ሰፋ ያለ ግንዛቤ ለማግኘት ለሚፈልግ ሁሉ የዶ/ር ያዕቆብ ሐይለማርያም “አሰብ የማን ናት”፤ የአምባሳደር ዘውዴ ረታን “የኤርትራ ጉዳይ”፤ ባዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የታተመውን “የአክሊሉ ማስታወሻ” ጥሩ ግንዛቤና መረጃ ሊሰጡ የሚችሉ መጻህፍት መሆናቸውን መጥቀስ እወዳለሁ።
የሶቭየት ህብረት መፈራረስ ክራሚያና ኤርትራ
የሲቭየት ህብረት መፈራረስን ተከትሎ በነበረው ያልተረጋጋ ወቅት ክራሚያም በግርግር ከዩክሬን ጋር ተደባልቃ ከራሸያ ተገንጥላ እንድትሄድ አድርገዋል የሚባሉት እንኳንስ ለሀገር ለራሳቸውም ማሰብ ይሳናቸው ነበር እየተባለ የሚነገርላቸው ፕሬዚደንት ቦሪስ ዬልሰን ናቸው:: ግለሰቡ የዚሀ አይነት ውሳኔ ሲወስኑ የክሬሚያን ታሪክ፣ ስትራተጂክ ጠቀሜታ ወዘተ ከቁብ አላስገቡትም፣ የህዝቡንም ስሜት ቦታ አልሰጡትም ነበር። የሳቸው ሩጫ ከምን እንደመነጨ በግልጽ በማይታወቅ መልኩ ጎርባቾቭ የቀደዱትን የለውጥ መንገድ በመለጠጥ ሶቭየት ህብረትን በማፈራረስ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ክራሚያን በተመለከተም የሶቭየት ህብረት ታላቅ የባህር ሀይል የሆነው ብላክ ሲ ፍሊት ንብረት ሽያጭና ገንዘብ መሰብሰብ ላይ ነበር ትኩረታቸው። ያም ሆኖ በንግድ አንጻር እንኳ እዚህ ግባ የሚባል ገንዘብ አላገኙበትም።
የክራምያን ጉዳይ መደምደሚያ ለመስጠት የተሞከረው በሶቭይት ሕብረት ባጠቃላይ እንዲሁም በራሽያና በተቀሩት ሶሻሊስት ሀገሮች ታይቶ የማይታወቅ ቀውስ እና አለመረጋጋት በሰፈነበት ወቅት ነበር። በዚያ የቀውስ ወቅት በቂ የሆነ አማራጭና ረጋ ብሎ ለማሰብ ጊዜ ሳይኖር ሬፈረንደም ተካሄደና 58% የሚሆን ህዝብ ደገፈው በማለት ክራሚያ ከሩሲያ ተለይታ የዩክሬን ግዛት ሆና እንድትሄድ ተወሰነ።
ይህ ጉዳይ ግን በብዙ ዜጎች ልብ ውስጥ ቁርሾ አስከተለ፤ ጠባሳም ጣለ። የጊዜው ሁኔታ ባይመችና በወቅቱ ማድረግ ስለሚገባቸው ነገር ግራ ቢጋቡም፤ እጅግ ብዙ የክራሚያ ኑዋሪዎች ልባቸው መሸፈቱ አልቀረም፡፡ በዘሩም በታሪኩም ራሽያዊ ነኝ ብሎ የሚያምነው የክሬምያ ሀዝብ የለም ዩክሬናዊ ነህ ሲባል ጥርሱን ነከሰ። ሆኖም ግን በወቅቱ የሚያዳምጠው አላገኝም። ያ ታምቆ የቆየ ቅሬታ አሁን በቅርቡ አመጽ ወልዶ እነሆ እየሆነ ያለውንና የሆነውን ዓለም እየመሠከረ ነው።
የኤርትራ ከኢትዮጵያ የመገንጠል ዕውነታ ከሶቭየት ህብረት መፈራረስ እና ከቀዝቃዛው ጦርነት “መገባደድ” ጋር በቅርብ የተቆራኘ ነበር፡ “ህዝበ ውሳኔ” (ሬፈራንደም ) የተባለው ሂደትም በሀሪቱ በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ በነበረችበት፣ ገና ቋሚ መንግስት እንኳን ሳይኖራት ነበር። በ“ህዝበ ውሳኔ” ሂደት ውስጥም የኢዮጵያዊነት አማራጭ በታፈነበት ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ የሚያምነውና የሆነውን የአፋርና ኩናማ፣ የሳሆ፤ ወ.ዘ.ተ ህዝብንም ፍላጎት ለማክበር ምንም ጥረት ሳይደረግና ውጤቱም ሳይታይ በግድ ያልሆነውንና ያላመነበትን ማንነት ተቀበል ተብሎ የተጠናቀቀ የግርግር ሁኔታ ነው። ይህ ስለሆነም እነሆ እስካሁን የቀጠለው ቅሬታ የመሳሪያ ግጭትን ወልዶ ካንድ ቀውስ ወደሌላ በመሽጋገር ላይ ይገኛል።
የሚገርመው ከስልሳ አመት በሓላ ሩሲያ በክሩስቼቭ ጊዜ የተጀመረውን ያስተዳደር ክልል ማሸጋሸግ እና በቦረስ ዬልሲን ዘመን የተወሰደውን የረጅም ጊዜ ዕይታ የጎደለውን የፖለቲካ ርምጃ ለማረም የተዘጋጀ ድርጅትና መሪ አግኝታለች። ኢትዮጵያችን ግን በሁሉም መልኩ ሀላፊነት የጎደለውን የመለስ ዜናዊ ለሀገር ደንታ ቢስ የሆነ ውሳኔ ለማረም እና ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ጥቅም በድፍረት የቆመ የመንግስት መሪ ገና አልታደለችም። ያም በመሆኑ መከራውም ቀጥሏል መፍትሄውም እየተወሳሰበ መሄዱ አይቀሬ ሆኗል።
የተባበሩት መንግሥታት “የዩክሬንን ሀገራዊ አንድነት ስለማሰከበር” ያካሄደው የድምጽ አሰጣጥ
የክሬሚያ ነዋሪወች በዩክሬን ስር መተዳደርን አንፈልግም ብለው ማጉረምረም ሲጀምሩ ነው ታላላቆቹ የምእራብ መንግስታት ሁኔታውን ለማዳፈን መሯሯጥ የጀመሩት። የክሬምያን ህዝብ ታሪክ፣ ፍላጎትና ማንነት ጠንቅቀው የሚያውቁት ምዕራባውያን ጭንቀታቸው ያነጣጠረው በክሬምያ ላይ ሳይሆን ሩሲያ እንደገና ተጠናክራ በመውጣት ጉዳይ ላይ ስለሆነ ይህንን ለማከሽፍ፣ ባለፈው የካቲት መጨረሻ ገደማ ዩክሬን ውስጥ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠው መንግስት ባመጽ ሲፈነቀል ቃል ያልተነፈሱት ምዕራባውያን፤ በክራሚያ የተደረገውን ሬፈረንደም ተከትሎ ዩክሬን ተወረረ፣ ወዘተ፤ የሚለውን ከበሮ መደለቅ ጀመሩ። ከሁካታው በስተጀርባ ግን አሁን ባለው ሁኔታ ምዕራባውያኑም ሆኑ ራሱ የዩክሬይን መንግስት የክራሚያ ጉዳይ ያለቀለት እንደሆነ የተቀበሉት ይመስላል። ሩጫው ሊፈጠር የሚችለውን ሌላም ምስቅልቅል ሁኔታ ለመቀነስ ምናልባትም ራሱ የዩክሬን እንደሀገር የመቀጠል ጉዳይ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ የመጨነቅ፣ ሰፋ ያለ የርስ በርስ ጦርነት ባውሮፓ ውስጥ እንዳይቀሰቀስ የመፍራት ጉዳይ እንጂ ክራሚያን የማስመለስ ፍላጎት አይመስልም።
የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ጥበቃው ምከር ቤት (ድምጽን በድምጽ ሽሮ ጥርስ-አልባ የሆነው) እና ጠቅላላ ጉባኤውም በዚህ ጉዳይ ያስተላለፈውና ከፍተኛ ክፍፍል የነበረበት ውሳኔ “ይህን ብለን ነበር “ ከማለት የማያልፍ ነው። ጠንከር ያለ የማዕቀብ እርምጃ ወሰዱ የተባሉት አሜሪካና የአውሮፓ ማህበረሰብም ቢሆኑ ርምጃቸው ጥቂት ባለስልጣኖችን የሚነካ ከመሆን አላለፈም።
ቀረብ ብሎ ሲታይ ደግሞ ያፍሪካ መንግስታት በተለይም የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግስታት የወሰዱት አቋም ትኩረትን የሚስብ ነው፡፡ የሁለቱም ወኪሎች በተባበሩት መንግስታት ውሳኔ አሰጣጥ ላይ የክሬምያን ከዩክሬን መገንጠል ሳያወግዙም ሳይደግፉም ድምጽ ተአቅቦ (አብስቴን) በማድረግ ማለፉቸውን እንገነዘባላን።
ይህ የድምጽ አሰጣጥ ከብዙሀኑ ያፍሪካ ሀገሮች የተለየ አይደለም፤ በተባበሩት መንግሰታት ምክር ቤት ”የዩክሬንን ሀገራዊ አንድነት ማሰከበር “ በሚል ርእስ የክራሚያን መገንጠል ለመቃወም የቀረበውን ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብ የደገፉ ያፍሪካ ሀገሮች 19 ብቻ ሲሆኑ የተቃውሞ ድምጽ ያሰሙ ሁለት (ሱዳንና ዚምባብዌ ) ድምጸ ተአቅቦ ያደረጉ ደግሞ ወደ 22 ያፍሪካ ሀገሮች ነበሩ። ከነዚህም ውስጥ ኢትዮጰያና ኤርትራ ይገኙበታል። ይህ በሶሰት ቦታ የተከፈለ የድምጵ አሰጣጥ የሚያሳየው የተባበሩት መንግሥታትም ሆነ ያፍሪካ አንድነት ማህበር በተመሳሳይ ሁኔታዎች ላይ የሚወስዷቸው አቋሞች ከሀገራቸው ፖለቲካ፣ እና ከሚያስገኝላቸው ጥቅም አንጻር እንጂ ከቋሚ መተክልና ዕምነት በመነሳት እንዳልሆነ ነው፡፡
ከዚህ ሁኔታ መገንዘብ እንደሚቻለው ለተመሳሳይ ሁኔታወች እያንዳንዱ ሀገር ስለሚወስደው እርምጃ ወሳኙ ጉዳይ “የተባበሩት መንግስታት ወይም ያፍሪካ አንድነት ህግ” ሳይሆን እያንዳንዱ ሀገር የሚያገኘው ጥቅማ ጥቅም እንደሆነ ነው። ባጭሩ የሀይል አሰላለፉን የሚገዛው መተክል (ፐሪንስፕል) ሳይሆን በጊዜው ሀገራት የሚያገኙት ጥቅም እና የሀይል ሚዛን ይመስላል።
Abonner på:
Innlegg (Atom)
