søndag 30. juni 2013
fredag 28. juni 2013
አንድነት ፓርቲ ሰኔ 30 በጎንደር ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ መጥራቱን አስታወቀ
አንድነት ፓርቲ የሶስት ወራት የህዝባዊ እንቅስቃሴ የትግል ስልቱን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ የህዝባዊ ንቅናቄው የመጀመሪያ የአደባባይ ላይ ሰላማዊ ሰልፍም በጎንደር ከተማ ሰኔ 30/10/2005 እንደሚያደርግ አስታውቋል -፡
በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ” በጎንደር እየተፈጸመ ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ሰዎችን በአደራ ማሰር፣ ለሱዳን ከህዝቡ እውቅና እና ፈቃድ ውጪ መሬት መሰጠቱን፣ በነጋዴዎች ላይ የሚፈጸመውን ኢ-ፍትሃዊ አሰራር፣ ለስራ የደረሱ ወጣቶች የፓርቲ አባል ካልሆኑ በስተቀር ስራ የማያገኙበትን ሁኔታ፣ በዘር ላይ የተመሰረተን ማፈናቀልና የኑሮ ውድነትን አስመልክቶ ህዝቡ የተቃውሞ ድምጹን በነቂስ ወጥቶ ” እንደሚያሰማ ለኢሳት በላከው መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡
ብዙ ሺ የከተማው ኗሪዎችም የተቃውሞ ፊርማቸውን ያኖራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ፓርቲው ገልጿል።
ሰላማዊ ሰልፉን በጎንደር ከሚገኙ የፓርቲው አባላትና አመራሮች ጋር የተሳካ ለማድረግ አዲስ አበባ ከሚገኘው ዋና ቢሮ አስተባባሪ አባላት የተላኩ ሲሆን የቅስቀሳ ስረቸውን መጀመራቸውን፣ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ፣ የብሄራዊ ምክር ቤትና በየመዋቅሩ ያሉ አባሎች በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ለመገኘት ወደ ጎንደር እንደሚያመሩ አክሎ ገልጿል።
ሰላማዊ ሰልፉ ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ ጎንደር ከሚገኘው የአንድነት ፓርቲ ቅርንጫፍ ቢሮ ተነስቶ ወደ መስቀል አደባባይ በማምራት በመስቀል አደባባይ በሚደረግ ልዩ ልዩ ፕሮግራም የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡
በጎንደር መስቀል አደባባይ ለሚገኘው ህዝብ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮችና ታዋቂ ግለሰቦች የሰላማዊ ሰልፉን ዓላማ የሚገልፅ ንግግር እንደሚያደርጉም ታውቋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን የአንድነት ፓርቲ ተወካይ የሆኑት ለኢሳት እንደተናገሩት ሰኔ 30 ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ማቀዳቸውን ለዞኑ ፖሊስ ጽህፈት ቤት፣ ለዞኑ አስተዳዳር እና ለዞኑ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ደብዳቤ ቢያስገቡም ሁለቱ ሲቀበሉ፣ የዞኑ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል ።
ያም ሆነ ግን ህጉ ማሳወቅ እንጅ ፈቃድ የማይጠይቅ በመሆኑ ሰላማዊ ሰልፉ ይካሄዳል ብለዋል
tirsdag 25. juni 2013
በ2005 ዓም ኢትዮጵያ ከወደቁ አገራት ምድብ ተመደበች
ፎሬን ፖሊሲ መጽሄት በእያመቱ በሚያወጣው የወደቁ አገራት ሪፖርት ወይም በእንግሊዝኛው አጠራር ፌልድ ስቴትስ ኢንዴክስ ኢትዮጵያ እንደ አለፉት አመታት ሁሉ ዘንድሮው የወደቁ ወይም በመውደቅ ላይ ካሉ 20 አገራት መካከል አንዷ ሆና ተመድባለች።
የህዝብ ቁጥር ፣ የስደተኛ ቁጥር፣ የህዝብ ብሶት፣ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት፣ ያልተመጣጠነ እድገት፣ የመንግስት ህጋዊነት፣ ማህበራዊ አገልግሎት፣ የደህንነት ጥበቃ፣ የሊህቃን መከፋፈልና የውጭ ጣልቃ ገብነት የሚሉት መስፈርቶች ተገምግዋል።
በዚህም መሰረት ከ1 እስከ 20 ያሉት አገራት ህልውናቸው አስተማማኝ ያልሆነ ከፍተኛ ችግር ያለባቸው ተብለው ተመድበዋል። ሶማሊያ ቀዳሚ የወደቀች አገር ስትባል፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ቻድ፣ የመን፣ አፍጋኒስታን፣ ሀይቲ ፣ ሴንትራል አፍሪካ ፣ ዝምባብዌ፣ ኢራቅ ፣ አይቮሪ ኮስት፣ ፓኪስታን፣ ጊኒ፣ ጊኒ ቢሳው፣ ኬንያ፣ ኒጀር፣ ኢትዮጵያና ቡሩንዲ ተከታታዮችን ደረጃዎች ይዘዋል።
ከሀያዎቹ አገራት የተሻሉ ተብለው በሁለተኛው ምድብ ውስጥ ከሚገኙት መካከል ደግሞ ሶሪያ፣ ዩጋንዳ፣ ላይቤሪያ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ኤርትራ፣ ማይናማር፣ ካሜሩን፣ ስሪ ላንካ፣ ባንግሊያዲሽ፣ ኔፓል፣ ሞሪታኒያ፣ ኢስት ቲሞር፣ ሴራ ሊዮን፣ ግብጽ ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ኮንጎ፣ ኢራን፣ ማሊ፣ ርዋንዳ እና ማላዊ ተመድበዋል።
የኢህአዴግ መንግስት ኢትዮጵያ በተሻለ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የደህንነት ጥንካሬ ላይ እንደምትገኝ በተደጋጋሚ ሲናገር ይሰማል። ይሁን እንጅ የፎሬን ፖሊስ መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ ባለፉት ተከታታይ አመታት ይህ ነው የሚባል የደረጃ መሻሻል አልታየባትም።
በዚህ አመትም ኤርትራ በአንጻራዊ መልኩ ከኢትዮጵያ በተሻለ ደህንነት ላይ እንደምትገኝ ሪፖርቱ ሲያሳይ፣ ኬንያ፣ ናይጀሪያና ሱዳን ደግሞ ከኢትዮጵያ አንሰው ተገኝተዋል።
søndag 23. juni 2013
የሱዳኑ ፕሬዚዳንት የአባይ ግድብ ግንባታን እንደሚደግፉ አስታወቁ
ሱዳን ትሪቢውን እንደዘገበው ፕሬዚዳንት በሽር የግድቡ ግንባታ ለኤሌክትሪክ ሀይል ፍጆታ የሚውል በመሆኑ በግብጽም ሆነ በሱዳን የውሀ ፍጆታ ላይ የሚኖረው ተጽኖ አይኖርም ብለዋል።
ግድቡን ለመሙላት በሚያስፈልግበት ወቅት እንኳ በግብጽም ሆነ በሱዳን የውሀ ድርሻ ላይ ተጽኖ አያመጣም ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ እንድትቀጥልም ጠይቀዋል።
ፕሬዚዳንት በሽር የሰጡት መልስ ግብጽና ሱዳን ቀድሞ የነበራቸው ጥብቅ ትስስር እየላላ መምጣቱን የሚያሳይ መሆኑን አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።
ሙስሊም ኢትዮጵያውያን በወልድያ ጠንካራ ተቃውሞ አሰሙ
ተቃውሞው ከአመት በላይ የዘለቀው የድምጻችን ይሰማ ተቃውሞ አንዱ አካል ቢሆንም ፣ የዛሬው የተቃውሞ መነሻ ግን የፌደራል ፖሊሶች ሐሙስ ጧት ከ35 አመታት በላይ ሲያገለግል የነበረውን የወልድያ እርዳታ ማህበር ቢሮ ማሸጋቸውን ተከትሎ የመጣ መሆኑን የአካባቢው ተወላጆች ለኢሳት ገልጸዋል።
ሰላም መስጊድ በሚባለው በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ድምጻችን ይሰማ ፣ መሐይም አይመራንም” የሚሉና ሌሎች መፈክሮችም ተደምጠዋል።
ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ አንዳንድ ከተሞችም ተመሳሳይ ተቃውሞዎች መካሄዳቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል
torsdag 20. juni 2013
የአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያውያን ለመብታቸው መከበር የሚያሰሙትን ድምጽ ይሰማል ሲሉ ወ/ሮ አና ጎሜዝ ተናገሩ
የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባል የሆኑት እና በምርጫ 97 ወቅት የህብረቱ የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ የነበሩት ወ/ሮ አና ማርያ ጎሜዝ ይህን የተናገሩት ኢትዮጵያውያን ዛሬ በአውሮፓ ህብረት መቀመጫ ፊትለፊት ባደረጉት የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ነው ።
ወ/ሮ አና ጎሜዝ የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያውንን ጩሀት ሰምቶ መልስ እንደሚሰጥ ተናግረው፣ በግላቸው ከኢትዮጵያውያን ጎን ቆመው ለውጥ እስከሚመጣ እንደሚታገሉ ተናግረዋል።
በተቃውሞው ላይ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ውስጥ እየደረሰ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ዘርዝረው ለአውሮፓ ህብረት ባለስልጣናት አቅርበዋል።
ከተቃውሞ ሰልፉ አዘጋጆች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ኤፍሬም ሻውል ሰልፉ የተሳካ እንደነበር ገልጸዋል።
mandag 17. juni 2013
ኢሳትን ሲመለከቱ የነበሩ 60 ሰዎች መታሰራቸው ተሰማ
በባሌ ሮቤ እና በጎባ ከተማ በቅርቡ ኢሳትን ሲመለከቱ የተገኙ ሰዎች ገናሌ እየተባለ በሚጠራው እስር ቤት ውስጥ መታሰራቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ግለሰቦቹ የተያዙት በተለያዩ ሰበቦች ቢሆንም ፍርድ ቤት ሲቀርቡ የሚቀርብባቸው ክስ ግን የተቃዋሚ ጣቢያ የሆነውን ኢሳትን ሲመለከቱ ተገኝተዋል የሚል ነው።
ከታሰሩት መካከል ወጣቶች እና አረጋውያን እንደሚገኙበት የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የፕሬስ ነጻነት ተከብሮአል በሚባልባት ኢትዮጵያ የባሌ ሮቤ እና ጎባ ከተማ ባለስልጣናት የወሰዱት እርምጃ ተገቢ አለመሆኑንና የተያዙት ግለሰቦች እንዲፈቱ የኢሳት ማኔጅመንት ጠይቋል።
ማንኛውም ዜጋ ከየትኛውም አቅጣጫ የሚመጣን መረጃ ያለምንም ተጽኖ ማግኘት እንደሚችል በህገመንግስቱ የተቀመጠ መብት መሆኑን የገለጸው ማኔጅመንቱ፣ ህበረተሰቡ አንዳንድ ባለስልጣናት አለቆቻቸውን ያስደሰቱ እየመሰላቸው በሚወስዱት እርምጃ ህብረተሰቡ ሳይደናገጥ ኢሳትን መመልከቱን እንዲቀጥል ፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትም የታሰሩ ሰዎች በአፋጣኝ እንዲፈቱ እንዲያደርግ ጠይቋል።
ኢሳት ካለፉት ስድስት ወራት ጀምሮ ስርጭቱን በቀጥታ በተሌቪዥን ለኢትዮጵያውያን እያስተላለፈ ይገኛል።
እነሱ ከ አባቶቻቸው አይበልጡም፤ እኛም ከ አባቶቻችን አናንስም>> በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ፤ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ ወረራና ደባ መፈፀም የጀመረችው ኢትዮጵያ ዛሬ በአባይ ላይ ግድብ ለመስራት ከመነሳቷ እጅግ በርካታ አመታት በፊት ጀምሮ መሆኑን በመጥቀስ ሀገራችን ከግብፅም ሆነ ከሌሎች የተቃጣባትን ተደጋጋሚ ወረራዎች በመመከትና ጠላቶቿንም ድባቅ በመምታት ነፃነቷን ጠብቃ መኖሯ ለጠላቶቿ መራር የሆነ እውነት ነው ብሏል።
ግብፅ በ ኢትዮጵያ ላይ ግልፅ እና ስውር ደባ የምትፈፅመው ኢትዮጵያ በወንዞቿ መጠቀም የማትችል ደካማ ሐገር እንድትሆን ለማድረግ ነው ያለው ሰማያዊ ፓርቲ፤ይህ ጥረቷ ግን ደካማ ኢትዮጵያን ለመፍጠር ከመሞከሯ ውጭ የምኞቷን ያህል አልተሳካላትም ብሏል።
<<ግብጽ እኛን ኢትዮጵውያንን እርስ በእርሳችን በማናከስ በጦርነትና በክፍፍል ተጠምደን ወንዞቻችንን የመጠቀም አቅም በማሳጣት ለዘለዓለም ብቸኛ ተጠቃሚ ሆና መኖር ትፈልጋለች>>ያለው ሰማያዊ ፓርቲ፤ << ይህ ካልተሳካላት ቀጥተኛ ወረራ በመፈፀም የወንዞቻችን ምንጮች ለመቆጣጠር እንደምትመኝ የየዘመናት ሙከራዎቿ ያመላክታሉ>>ብሏል።
ሰማያዊ ፓርቲ በማያያዝም -በአባይ ወንዝ ላይ የተጀመረው ግድብ ከሐገራዊ ጠቀሜታው ይልቅ የገዥውን ፓርቲ የስልጣን እድሜ ለማራዘም የታለመና ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የሚደለቅ ከበሮ መሆኑን ፓርቲያችን ይገነዘባል ብሏል።
<<የግድቡ ሥራ የገዥውን ፓርቲ የተለየ አሣቢነትና ተቆርቋሪነት የሚያሳይ አድርጎ ለማቅረብ የሚደረገው ልፈፋ ከተራ ጩኸት በዘለለ የዜጎችን ልብ የሚያማልል አይደለም፡፡>>ያለው ፓርቲው፤ << በአንፃሩ ከገዥው ፓርቲ አመለካከት ውጭ ያሉ ዜጎችን የግድቡ ሥራ የማይመለከታቸው አድርጎ ለማቅረብ የሚደረገው የወሬ ክምር ልብን የሚሰብር ርካሽ ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡>>ሲል ተችቷል።
በመሆኑም ለኢትዮጵያ ክብርና ኩራት መሠዋት ለዜጎችም ጥቅም መጠበቅ እነማን ምን እንደከፈሉና እንደሚያስቡ ለታሪክ በመተው ሃገርን መክዳትና መጥላትን በሌሎች ላይ ለመለጠፍ የሚደረገው ሩጫ ግን እንዲታሰብበት እንመክራለን ሲልም ፓርቲው ምክሩን አስተላልፏል።
ከዚህም ባሻገር <<የግድቡ ሥራ ከስም አወጣጥ ጀምሮ የፕሮጀክቱ አነዳደፍ፤ የፋይናንስ አሰባሰብ፣ ግንባታውን የሚያካሂዱ ድርጅቶች አመራረጥና ሌሎችም ጉዳዮች እጅግ ግልፅነት የጎደላቸውና ባለቤትነታቸውም ከኢትዮጵያ ህዝብ ተነጥቆ ለተወሰኑ ቡድኖች በተለይም ለገዥው ፓርቲ ፍላጎት ማሳኪያ እየዋለ መሆኑ ቀርቶ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በሚያስማማ ሁኔታ እንዲካሄድ ፓርቲያችን አጥብቆ ይጠይቃል፡፡>>ሰማያዊ ፓርቲ ጥያቄ አቅርቧል።
ፓርቲው መግለጫውን ሲያጠቃልልም፦<<አሁን የተፈጠረው ውጥረት በውይይት እንዲፈታ የኢትዮጵያ መንግስት ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲያደርግ እያሳሰብን ነገር ግን ግብፅ ይህን አልቀበልም በማለት ፍላጎቷን በሃይል ለማስፈፀም የምትፈልግ ከሆነ የአባቶቻችንን ታሪካዊ አሸናፊነት የምንደግመው መሆኑን ከታሪክ እንድትማር ለማስታወስ እንገደዳለን፡፡>>ብላል።
በሌላ ዜና ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ ባን ኪሙን ለግብጹ ፕሬዚዳንት ሙሀመድ ሙርሲና ለኢትዮጵያውያው ጠቅላይ ሚኒሰትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ስልክ በመደወል ፣ አገራቱ ችግሩን በውይይት እንዲፈቱ አሳስበዋል
fredag 14. juni 2013
አንድነት ፓርቲ ግብጽና ኢትዮጵያ ከጸብ አጫሪነት ድርጊት እንዲቆጠቡ ጠየቀ
ፓርቲው ” ሁሉንም ነገር ለፖለቲካ ፍጆታ ለማዋል የቆረጠ ፓርቲ የሀገርን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ መጣሉ የማይቀር ነው” በሚል ርእስ ባወጣው መግለጫ ” የግብጽና የኢትዮጵያ መንግሥት ከፀብ አጫሪ ድርጊት እንዲቆጠቡ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ከሚያበላሹ ፕሮፓጋንዳዎችን ከመንዛት እንዲታቀቡና ለዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጠረጴዛ ዙሪያ ንግግሮች ላይ እንዲያተኩሩ አሳስቦአል።”
አባይን መጠቀም የኢትዮጵያ ተፈጥሮዊ መብት መሆኑ እንዲታወቅ፣ሁለቱ ሀገሮች የአባይን ጉዳይ የውስጥ ፖለቲካቸው ማብረጃ ከማድረግ እንዲቆጠቡ፣ ሀገራዊ መግባባት አሁኑኑ እንዲፈጠር መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ፣ የአባይ ጉዳይ የፖለቲካ መጠቀሚያ መሆኑ እንዲያበቃም ፓርቲው ጥሪ አስተላልፎአል።
ገዥው ፓርቲ የአባይን ጉዳይ የኢህአዴግ ከዛም አልፎ የአንድ ግለሰብ ራዕይ ማድረጉ ከእለት ጉርሱ ቀንሶ ቦንድ እየገዛ ያለውን ህዝብ የግድቡ ባለቤት እንዳይሆን አድርጎታል የሚለው አንድነት፣ ወንዙ በጊዜያዊነት አቅጣጫውን በግንቦት ሃያ በዓል ቀን እንዲቀይር መደረጉ ግድቡ ለፖለቲካ ፍጆታ መዋሉን ያሳያል ብሎአል።
ገዢው ፓርቲ ሁሉን ነገር ለፖለቲካ ፍጆታ በማዋል ሥልጣንን ማስረዘም በሚል መርህ ተቀይዶ የዘነጋቸው ብዙ ሀገራዊ ተግባራት እንደነበሩና እንዳሉ ለመገመት ይቻላል የሚለው ፓርቲው፣ የተዘነጉ ነጥቦች ከሚላቸው መካከልም” በቂ የዲፕሎማሲ ስራ አለመስራት፤ ከዓባይ ተጋሪ ሀገሮች ጋር በቂና አስተማማኝ ውይይት አድርጎ ስምምነት አለመድረስ፤ ሀገሪቱ የጦርነት ስጋር ቢገጥማት ለመቋቋም በቂ ዝግጅት አለማድረግ፤ የገንዘብ ቁጥጥርና ሙስና ” የሚሉትን ጠቅሷል።
የኢህአዴግ ስርአት ፖለቲካኞችንና ጋዜጠኞችንና ‹‹ሽብርተኛ›› በማለት የሚፈርጅ፣ በልማት ስም ጭቆና የሚያካሂድ፣ ይቀናቀነኛል የሚላቸውን ኃይሎች ሁሉ ከምድረ ገጽ መጥፋት አለባቸው ብሎ የሚያስብ ፣ በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ብሔራዊ መግባባትን የሚፈታተን ነው የሚለው አንድነት፣ ስርአቱ አጣብቂኝ ውስጥ በወደቀበት ጊዜ እንኳን ሀገራዊ አጀንዳ ካላቸው ተቃዋሚዎች ጋር የመመካከር ሃሳብ የለውም ሲል ወቅሷል፡፡
የታቀደው ትልቅ ፕሮጀክት ያለ ሀገራዊ መግባባት እንዴት ሊሳካ ይችላል ሲል ጥያቄ የሚያቀርበው ፓርቲው፣ የግብፁ ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ ከተቃዋሚዎች ጋር ሲነጋገሩ፤ የሱዳን መንግሥትም የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት የተሻለ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ሲሞክር፣ሩ የኢትዮጵያ መንግሥት በአንጻሩ በግትርነት ማሰርና መፈረጁን በመቀጠል የሀገራዊ መግባባትን አደጋ ላይ ጥሎታል ሲል ጠንካራ ትችት አቅርቧል።
በሌላ በኩል ደግሞ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ የአባይን ጉዳይ የግሉ አድርጎታል በሚል ከተለያዩ ወገኖች እየቀረበበት ያለውን ትችት አቶ
በረከት ስምኦን የመንግስት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር አስተባብለዋል፡፡
አቶ በረከት ትላንት
ማምሻውን በግዮን ሆቴል ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ላይ ነው ይህን የጠቀሱት፡፡
የግንቦት20 ቀን ከፍሰት አቅጣጫ ማስቀየሩ ጋር የተገጣጠመው
በአጋጣሚ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ “አቅጣጫውን ለማስቀየር የታቀደው የግድቡ ስራ የተጀመረበት
ሁለተኛ ዓመት በማስመልከት መጋቢት 24 ቀን 2005 ዓ.ም ነበር፤ ነገር ግን በዚያ ቀን ስራው ሊደርስ
ባለመቻሉ በግንቦት ሃያ ዕለት እንዲሆን ተደርጓል” ብለዋል።
ኢህአዴግ ግድቡን የጀመረው ሕዝቡ አመጽ እንዳያስነሳ ለማስቀየስ ነው በሚል አንዳንድ ወገኖች ይናገሩ ነበር ያሉት
አቶ በረከት ፣ አሁን ደግሞ ኢህአዴግ ግድቡን የግሉ አደረገው በማለት እየተናገሩ ነው ብለዋል።
አቶ በረከት ስራውን ‹ፖለቲካዊ ለማድረግ ካልሆነ በስተቀር ኢህአዴግ ፕሮጀክቱ የእኔ ብቻ ነው ሊል የሚችልበት አንዳችም ምክንያት
የለውም በማለት የሚቀርብባቸውን ክስ አስተባብለዋል፡፡
አቶ በረከት ከአባይ ግድብ ጋር ተያይዞ ግብጽ ጦርነት ታነሳለች የሚል ስጋት መንግስታቸው እንደሌለው ገልጸው ነገር ግን ተቃዋሚዎችን በማስታጠቅ፣ ሰላይ በማሰማራት፣ ሰላምን በማደፍረስና አለመረጋጋትን በመፍጠር ረገድ ሙከራ ልታደርግ ትችላለች የሚል ግምገማ እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡
“አገሪቱ ተገድዳ ወደጦርነት ብትገባ የመከላከል አቅማችን የቱን ያህል ነው፣ምንስ ዝግጅት ተደርጓል?” በሚል
ለተነሱ ጥያቄዎች አቶ በረከት “ምንም የተደረገ ዝግጅት የለም” የሚል ምላሽም ሰጥተዋል፡፡
የአባይ ውሃ አቅጣጫ መቀየርን ተከትሎ በግብጽ በኩል የተነሳው ጩህት ለአትዮጽያ መልካም አጋጣሚ ነውም ብለዋል፡፡
“ከዚህ ቀደም የአባይን ውሃ ጉዳይ በተመለከተ በእኛና በግብጽ፣ በሱዳን መካከል ውስጥ ውስጡን መቆራቆስ ነበር፡፡
አሁን ግን የተፈጠረው አጋጣሚ ጉዳዩን አደባባይ አውጥቶታል፡፡ አሁን ብንናገር የምንሰማበት ሁኔታ ተፈርጥሮልናል”
ሲሉ አክለዋል።
በአባይ ጉዳይ የግብጻዊያን ሚዲያዎችና ፖለቲከኞች የከረረ አቋም በሚያንጸባርቁበት በዚህ ወቅት
የኢትዮጽያ ፓርላማ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍን ትላንት ማጽደቁ ይታወቃል፡፡
የናይል ተፋሰስን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለመጠቀም እ.ኤ.አ ከ1997 እስከ 2010 ድርድር ሲደረግ ቆይቶ ሰነዱ እ.ኤ.አ ከ2010 ጀምሮ
ለፊርማ ክፍት ሆኗል፡፡ ከዘጠኙ የተፋሰስ አገራት መካከል ግብጽ፣ ሱዳን እና ዴሞክራቲክ ኮንጎ ባይፈርሙም ኢትዮጽያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ዩጋንዳ እና ታንዛኒያ ፊርማቸውን በማኖራቸው ስምምነቱን በየአገራቸው ፓርላማ በማጸደቅ መተግበር ጀምረዋል።
የኢትዮጽያ ፓርላማ ይህን ሰነድ ማጽደቁ በግብጽና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረውን አዲስ ውጥረት ይበልጥ እንዳያባብሰው ተሰግቷል፡፡
mandag 10. juni 2013
የምርጫ 97 የሰኔ 1 ሰማዕታት ታስበው ዋሉ
በምርጫ 97 ወቅት “የተጭበረበረው የወላጆቻችች ድምጽ ይመለስ” በማለት ወደ አደባባይ ወጥተው በግፍ የተጨፈጨፉት የምርጫ 97 ሰምአታት 8ኛ አመት በተለያዩ ዝግጅቶች ታስቦ ውሎአል።
በሟቹ ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ ትእዛዝ ከ100 በላይ ኢትዮጵያውያን ሰኔ አንድ ቀን 1997 ዓም በአጋዚ ወታደሮች መጨፍጨፋቸው ይታወሳል። በተፈጥሮ ሞት ከተለዩት ከአቶ መለስ ዜናዊ በስተቀር ጭፍጨፋውን በመምራት የተባበሩት ሌሎች ባለስልጣኖች ዛሬም ድረስ ለፍርድ አልቀረቡም።
አንድነት ፓርቲ፣ መኢአድ እንዲሁም የሰማእታት ቤተሰቦች አመቱን በልዩ ክብር የሚዘክሩት ሲሆን፣ በዛሬው እለትም ቀኑ ተከብሮ ውሎአል።
በምርጫ 97 ወቅት የተሰውት ወጣቶች ለዲሞክራሲያዊ ስርአት በሚታገሉ ሀይሎች ዘንድ ” የዲሞክራሲ አርበኞች” እየተባሉ ይጠራሉ።
lørdag 8. juni 2013
ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ተቃውሞአቸውን አሰሙ
ግንቦት 30 በአዲስ አበባና በበርካታ የክልል ከተሞች “የሀይል እርምጃ ለህዝብ መልስ አይሆንም” በሚል ርዕስ የተጠራው የሙስሊሞች ተቃውሞ በደማቅና በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁ ታውቋል።
በአዲስ አበባና በበበርካታ የክልል ከተሞች ተቃውሞ ያሰሙት ሙስሊሞች ካስተጋቧቸው መፈክሮች መካከል፦” መብታችንን ለማስከበር የምናደርገው ትግል በሀይል እርምጃ አይጨናገፍም!፣ ለህዝብ የመብት ጥያቄ ሀይል መልስ አይሆንም! የታሰሩት መሪዎቻችን ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ ይፈቱ! መንግስት ከሀይማኖታችን ላይ እጁን ያንሳልን! እና ፍትህ እንሻለን!”የሚሉት ይገኙበታል።
እንዲሁም በፍትህ እጦት የተማረሩት እነዚሁ ሰልፈኞች፦<<መንግስት የለም ወይ? መንግስት የለም ወይ? >>እያሉ በዜማ ተማጽኖአቸውን ሲያሰሙ ተደምጠዋል።
ድ ም ጻችን ይሰማ ለሰልፉ ጥሪ በባደገበት መግለጫው፦<<የትግላችንን ሂደት ለመግታት መንግስት ከውስጥም ከውጪም የተለያዩ ጥቃቶችን ሲሰነዝር ቀይታል፤ በጥቃቱ ሙስሊሞችን ከትግሉ ሜዳ ለማስወገድ ታስቦ የነበረ ቢሆንም መንግስት የሚያስበውን ያህል ሲሳካለት ግን አልታየም፡፡>>ብሏል።
<<ይህ የመንግስት ጥቃት ሌት ተቀን አከብረዋለሁ ብሎ የሚለፍፍለትን፣ በተግባር ግን ሊገዛለት የማይፈቅደውን ሕገ መንግስት በመጣስ በተደጋጋሚ የተፈጸመ >>ሲልም አክሏል -ድምፃችን ይሰማ ኮሚቴ።
በሌላ በኩል የመንግስት ባለስልጣናት ባለፈው ሳምንት ተጠርቶ የነበረውን ሰላማዊ ሰልፍ – በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጲያዊያን ሙስሊሞች ከአንድ ዓመት በፊት ካነሱት ሃማኖታዊ ጥያቄ ጋር ለማያያዝ ሞክረዋል ያለው ኮሚቴው፤ይህም ለህዝብ ያላቸውን ንቀት የሚያሳይ ነው በሏል።
ዛሬ አዲስ አበባን ጨምሮ በ30 ከተሞች በተደረገው እጅግ ደማቅ ሰልፍ ሴት ሙስሊሞች ከወትሮው በተለየ መልኩ በዝተው መስተዋላቸው ተመልክቷል።
በተለይ በ አንዋር መስጊድ በተደረገው የተቃውሞ መርሀ-ግብር ሴት ሙስሊሞች በከፍተኛ እልህና ወኔ መሪዎቻቸው እንዲፈቱ በመጠየቅ ተቃውሟቸውን ሲገልጹ ተስተውለዋል።
የመብት ጥያቄ በማንሳታቸው ሳቢያ “ የ አሸባሪነት ክስ ተመስርቶባቸው የታሰሩት የሙስሊም አመራሮች ያለ አንዳች ፍትሕ ወህኒ ከተወረወሩ 18 ወራት እንዳለፋቸው ይታወቃል።
ሙስሊሞች ዛሬ ባደረጉት ሰልፍ መሪዎቻቸው እስኪፈቱ እና ሀይማኖታዊ ጥያቄዎቻቸው እስኪመለሱ ድረስ የተቃውሞ መርሀግብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በድጋሚ አረጋግጠዋል።
mandag 3. juni 2013
ኢህአዴግ ልሳኖቼን የሚያነብ በመጥፋቱ ለኪሳራ ተዳርጌአለሁ አለ
የኢህአዴግ አባላትን ፖለቲካዊና ርእዮተ-ዓለማዊ ብቃት ለማሳደግ ለአርሶ አደሩና ዝቅተኛ የትምህርት ዝግጅት ላላቸው አባላት አብዮታዊ ዲሞክራሲ ጋዜጣንና ከፍ ያለ የትምህርት ዝግጅት ላላቸው ደግሞ አዲስ ራእይ መጽሄትን እና አብዮታዊ ዲሞክራሲ መጽሄትን የይዘት እና የስርጭት ለውጥ በማድረግ ” ለማሰራጨት ቢሞከርም ፣ አመራሩም አባላቱም ለማንበብ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ለኪሳራ ተዳርገናል በማለት ድርጅቱ አስታውቋል።
ይህ የተገለጸው ብአዴን “የ10ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ግምገማዎች ፣ የተላለፉ ውሳኔዎችና የቀጣይ አቅጣጫዎች ” በሚል ርእስ ለከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሩ ባዘጋጀው ሰነድ ላይ ነው። ይህ 43 ገጽ ያለው ወረቀት ብአዴንም ሆነ ኢህአዴግ ያገጠመውን ችግር
በዝርዝር ያቀርባል።
የአመራር አመላመልን እና ድርጅቱን እየለቀቁ የሚሄዱ አባላት መብዛትን በተመለከተ የገጠመውን ፈተና ሲዘረዝር ” ድርጅታችን ገዢ ፓርቲ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሥራ ታታሪ ያልሆኑና በድርጅቱ ሥራ ለመቀጠር አልያም ስልጣናቸውን ተጠቅመው በአቋራጭ ለመክበር የሚፈልጉ ኃይሎች እየተቀላቀሉ ህልማቸው አልሳካ ሲላቸው ለቀው የሚሄዱ አባላት ቁጥር ትንሽ አይደለም” ብሎአል።
“በገጠር ታታሪ አባላት ቢመለመሉም ራሳቸውን ማውጣት እንጂ ሌላውንም መርቶና ደግፎ ለማሳደግ በቂ ትኩረት የማይሰጡ አባላት ቁጥራቸው ቀላል አይደለም” የሚለው ድርጅቱ፣ በከተሞች በጥቃቅንና አነስተኛ፣ በሲቪል ሰርቪሱና በትምህርት ተቋማት ምሁራን ላይ የትኩረት መስኮች ብለን በለየናቸው በቂ አባላት ካለመመልመላቸውም የተነሳ፣ የተመለመሉትም ከሥራ ትጋት ማነስ፣ ከህዝባዊ ወገንተኝነትና ከዓላማ ጽናት ጋር የተያያዙ ችግሮች የሚስተዋሉባቸው ሆነዋል ብሎአል።
የድርጅቱን ልሳናት በተመለከተ የገጠመውን ፈተና ሲያትት ” በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጋዜጣ የይዘትና የሥርጭት ለውጥ ለማምጣት የዝግጅት ለማሻሻል ጥረት የተደረገ ቢሆንም ልሳኑ ከአባላት አጥር ወጥቶ ሁሉም አርሶ አደር ዘንድ እንዲደርስ አልሞ አልተንቀሳቀሰም ” ብሎአል።
አዲስ ራዕይ መጽሔትን በተመለከተ ደግሞ ” በወቅታዊ፣ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ተመስርቶ በቂ ትንተና የሚቀርብበት መጽሔት ቢሆንም ለመጽሔቱ ትኩረት የማይሰጡ አባላት ቁጥር ትንሽ አይደለም። መጽሔቱን ከወሰዱም በኋላ ከማንበብና ከመወያየት ይልቅ፣ ሳያነቡና ሳይወያዩ የሚቀሩ አደረጃጀቶች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። መጽሔቱን አንብበው ከሚያገኙት እውቀት በላይ ለመጽሔቱ የሚያወጡት ገንዘብ በልጦ የሚታያቸው አባላት ቁጥር ትንሽ አይደለም። በአመራሩም በኩል ቢሆን መጽሔቱ አንድ ዋና የአባላት አቅም መገንቢያ መሳሪያ ነው ብሎ በእምነት መያዝ ላይ ጉድለቶች አሉ።
” ብሎአል።
አብዮታዊ ዴሞክራሲ መጽሔትን በተመለከተ ሲገልጽ ” መጽሔቱ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚታተም ቢሆንም ከአመራር ጀምሮ አባላቱም ጭምር ለዚህ መጽሔት የሰጡት ትኩረት ዝቅተኛ ነው። ዋናው ችግር የአመራሩ ነው።
መጽሔቱ ወቅታዊና አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ጥራት ያለው ጽሑፍ ይዞ እንዲቀርብ አልተደረገም። አመራሩም በቂ ተሳትፎ የለውም። በሥርጭት ረገድም ቢሆን ስለመጽሔቱ ፋይዳ በቂ ቅስቀሳ ተደርጎ አባላትና ሌሎች ፍላጎት ያላቸው እንዲገዙት አልተደረገም። በመሆኑም የአመራሩንና የአባሉን አቅም የሚገነባ መጽሔት መሆኑ ቀርቶ ታትሞ በአግባቡ ስለማይሠራጭ ኪሣራው ድርጅታችንን ተጨማሪ ወጭ የሚጠይቅ ሆኖ ይገኛል። ” ብሎአል።
” አመራሩና አባላት አደገኛ የሆነ የንድፈ-ሃሳብ ድህነት የሚታይባቸው በመሆኑ ይህን ከንባብ ባህል ዝቅተኝነት ጋር የተያያዘ የፖለቲካዊና ርዕዮተ-ዓለማዊ ግንዛቤ ዝቅተኛነት በአሳሳቢነቱ ተመልክቶ ለማስተካከል ሁሉም በያለበት ርብርብ ሊያደርግ ይገባል” ብሎአል ።
ከድርጅቱ ሰነድ ለመረዳት እንደሚቻለው በክልሉ ውስጥ የሚታየው ድህነት፣ የመልካም አስተዳደር እና ማህረበራዊ ችግሮች መሰረታዊ ምክንያት የአመራር ድህነት ነው።
ሰማያዊ ፓርቲ የጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ ለማደናቀፍ መንግስት ሰበቦችን እየፈለገ ነው
የአዲስ አበባ መስተዳድር ሰማያዊ ፓርቲ የጠራውን ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ ለማደናቀፍ በተለያዩ ክፍለከተሞች ስብሰባ መጥራቱ ታውቋል።
የተለያዩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለኢሳት እንደገለጹት መስተዳድሩ በሰልፉ ላይ ብዙ ህዝብ እንዳይገኝ ለማድረግ ከቤት ጋር የተያያዙ አጀንዳዎችን በማንሳት ህዝቡ ወደ ተቃውሞ ሰልፉ እንዳይሄድ ለማድረግ እየጣረ ነው።
“ኢህአዴግ ድህነትን ለፖለቲካ ድጋፍ ማስገኛ እየተጠቀመበት መሆኑን፣ በከተማው ያሉ የቤት እና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት የማየፈልገውም ህዝቡ መሰረታዊ ነገሮች ከተማሉለት ድጋፍ አይሰጠኝም ብሎ በማሰብ የህዝቡን ድህነት የፖለቲካ ድጋፍ መግዢያ ማድረጉን የሚያሳይ ነው” በማለት ዘገባውን የላከልን ሪፖርተራችን ከአዲስ አበባ ገልጿል።
ግንቦት25 እሁድ ሰልፉ በታቀደለት መሰረት ከተካሄደ ከምርጫ 97 በሁዋላ የመጀመሪያው የተቃውሞ ሰልፍ ይሆናል።
Abonner på:
Innlegg (Atom)