fredag 14. juni 2013
አንድነት ፓርቲ ግብጽና ኢትዮጵያ ከጸብ አጫሪነት ድርጊት እንዲቆጠቡ ጠየቀ
ፓርቲው ” ሁሉንም ነገር ለፖለቲካ ፍጆታ ለማዋል የቆረጠ ፓርቲ የሀገርን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ መጣሉ የማይቀር ነው” በሚል ርእስ ባወጣው መግለጫ ” የግብጽና የኢትዮጵያ መንግሥት ከፀብ አጫሪ ድርጊት እንዲቆጠቡ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ከሚያበላሹ ፕሮፓጋንዳዎችን ከመንዛት እንዲታቀቡና ለዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጠረጴዛ ዙሪያ ንግግሮች ላይ እንዲያተኩሩ አሳስቦአል።”
አባይን መጠቀም የኢትዮጵያ ተፈጥሮዊ መብት መሆኑ እንዲታወቅ፣ሁለቱ ሀገሮች የአባይን ጉዳይ የውስጥ ፖለቲካቸው ማብረጃ ከማድረግ እንዲቆጠቡ፣ ሀገራዊ መግባባት አሁኑኑ እንዲፈጠር መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ፣ የአባይ ጉዳይ የፖለቲካ መጠቀሚያ መሆኑ እንዲያበቃም ፓርቲው ጥሪ አስተላልፎአል።
ገዥው ፓርቲ የአባይን ጉዳይ የኢህአዴግ ከዛም አልፎ የአንድ ግለሰብ ራዕይ ማድረጉ ከእለት ጉርሱ ቀንሶ ቦንድ እየገዛ ያለውን ህዝብ የግድቡ ባለቤት እንዳይሆን አድርጎታል የሚለው አንድነት፣ ወንዙ በጊዜያዊነት አቅጣጫውን በግንቦት ሃያ በዓል ቀን እንዲቀይር መደረጉ ግድቡ ለፖለቲካ ፍጆታ መዋሉን ያሳያል ብሎአል።
ገዢው ፓርቲ ሁሉን ነገር ለፖለቲካ ፍጆታ በማዋል ሥልጣንን ማስረዘም በሚል መርህ ተቀይዶ የዘነጋቸው ብዙ ሀገራዊ ተግባራት እንደነበሩና እንዳሉ ለመገመት ይቻላል የሚለው ፓርቲው፣ የተዘነጉ ነጥቦች ከሚላቸው መካከልም” በቂ የዲፕሎማሲ ስራ አለመስራት፤ ከዓባይ ተጋሪ ሀገሮች ጋር በቂና አስተማማኝ ውይይት አድርጎ ስምምነት አለመድረስ፤ ሀገሪቱ የጦርነት ስጋር ቢገጥማት ለመቋቋም በቂ ዝግጅት አለማድረግ፤ የገንዘብ ቁጥጥርና ሙስና ” የሚሉትን ጠቅሷል።
የኢህአዴግ ስርአት ፖለቲካኞችንና ጋዜጠኞችንና ‹‹ሽብርተኛ›› በማለት የሚፈርጅ፣ በልማት ስም ጭቆና የሚያካሂድ፣ ይቀናቀነኛል የሚላቸውን ኃይሎች ሁሉ ከምድረ ገጽ መጥፋት አለባቸው ብሎ የሚያስብ ፣ በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ብሔራዊ መግባባትን የሚፈታተን ነው የሚለው አንድነት፣ ስርአቱ አጣብቂኝ ውስጥ በወደቀበት ጊዜ እንኳን ሀገራዊ አጀንዳ ካላቸው ተቃዋሚዎች ጋር የመመካከር ሃሳብ የለውም ሲል ወቅሷል፡፡
የታቀደው ትልቅ ፕሮጀክት ያለ ሀገራዊ መግባባት እንዴት ሊሳካ ይችላል ሲል ጥያቄ የሚያቀርበው ፓርቲው፣ የግብፁ ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ ከተቃዋሚዎች ጋር ሲነጋገሩ፤ የሱዳን መንግሥትም የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት የተሻለ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ሲሞክር፣ሩ የኢትዮጵያ መንግሥት በአንጻሩ በግትርነት ማሰርና መፈረጁን በመቀጠል የሀገራዊ መግባባትን አደጋ ላይ ጥሎታል ሲል ጠንካራ ትችት አቅርቧል።
በሌላ በኩል ደግሞ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ የአባይን ጉዳይ የግሉ አድርጎታል በሚል ከተለያዩ ወገኖች እየቀረበበት ያለውን ትችት አቶ
በረከት ስምኦን የመንግስት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር አስተባብለዋል፡፡
አቶ በረከት ትላንት
ማምሻውን በግዮን ሆቴል ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ላይ ነው ይህን የጠቀሱት፡፡
የግንቦት20 ቀን ከፍሰት አቅጣጫ ማስቀየሩ ጋር የተገጣጠመው
በአጋጣሚ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ “አቅጣጫውን ለማስቀየር የታቀደው የግድቡ ስራ የተጀመረበት
ሁለተኛ ዓመት በማስመልከት መጋቢት 24 ቀን 2005 ዓ.ም ነበር፤ ነገር ግን በዚያ ቀን ስራው ሊደርስ
ባለመቻሉ በግንቦት ሃያ ዕለት እንዲሆን ተደርጓል” ብለዋል።
ኢህአዴግ ግድቡን የጀመረው ሕዝቡ አመጽ እንዳያስነሳ ለማስቀየስ ነው በሚል አንዳንድ ወገኖች ይናገሩ ነበር ያሉት
አቶ በረከት ፣ አሁን ደግሞ ኢህአዴግ ግድቡን የግሉ አደረገው በማለት እየተናገሩ ነው ብለዋል።
አቶ በረከት ስራውን ‹ፖለቲካዊ ለማድረግ ካልሆነ በስተቀር ኢህአዴግ ፕሮጀክቱ የእኔ ብቻ ነው ሊል የሚችልበት አንዳችም ምክንያት
የለውም በማለት የሚቀርብባቸውን ክስ አስተባብለዋል፡፡
አቶ በረከት ከአባይ ግድብ ጋር ተያይዞ ግብጽ ጦርነት ታነሳለች የሚል ስጋት መንግስታቸው እንደሌለው ገልጸው ነገር ግን ተቃዋሚዎችን በማስታጠቅ፣ ሰላይ በማሰማራት፣ ሰላምን በማደፍረስና አለመረጋጋትን በመፍጠር ረገድ ሙከራ ልታደርግ ትችላለች የሚል ግምገማ እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡
“አገሪቱ ተገድዳ ወደጦርነት ብትገባ የመከላከል አቅማችን የቱን ያህል ነው፣ምንስ ዝግጅት ተደርጓል?” በሚል
ለተነሱ ጥያቄዎች አቶ በረከት “ምንም የተደረገ ዝግጅት የለም” የሚል ምላሽም ሰጥተዋል፡፡
የአባይ ውሃ አቅጣጫ መቀየርን ተከትሎ በግብጽ በኩል የተነሳው ጩህት ለአትዮጽያ መልካም አጋጣሚ ነውም ብለዋል፡፡
“ከዚህ ቀደም የአባይን ውሃ ጉዳይ በተመለከተ በእኛና በግብጽ፣ በሱዳን መካከል ውስጥ ውስጡን መቆራቆስ ነበር፡፡
አሁን ግን የተፈጠረው አጋጣሚ ጉዳዩን አደባባይ አውጥቶታል፡፡ አሁን ብንናገር የምንሰማበት ሁኔታ ተፈርጥሮልናል”
ሲሉ አክለዋል።
በአባይ ጉዳይ የግብጻዊያን ሚዲያዎችና ፖለቲከኞች የከረረ አቋም በሚያንጸባርቁበት በዚህ ወቅት
የኢትዮጽያ ፓርላማ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍን ትላንት ማጽደቁ ይታወቃል፡፡
የናይል ተፋሰስን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለመጠቀም እ.ኤ.አ ከ1997 እስከ 2010 ድርድር ሲደረግ ቆይቶ ሰነዱ እ.ኤ.አ ከ2010 ጀምሮ
ለፊርማ ክፍት ሆኗል፡፡ ከዘጠኙ የተፋሰስ አገራት መካከል ግብጽ፣ ሱዳን እና ዴሞክራቲክ ኮንጎ ባይፈርሙም ኢትዮጽያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ዩጋንዳ እና ታንዛኒያ ፊርማቸውን በማኖራቸው ስምምነቱን በየአገራቸው ፓርላማ በማጸደቅ መተግበር ጀምረዋል።
የኢትዮጽያ ፓርላማ ይህን ሰነድ ማጽደቁ በግብጽና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረውን አዲስ ውጥረት ይበልጥ እንዳያባብሰው ተሰግቷል፡፡
Abonner på:
Legg inn kommentarer (Atom)
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar