lørdag 8. juni 2013

ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ተቃውሞአቸውን አሰሙ



ግንቦት 30 በአዲስ አበባና በበርካታ የክልል ከተሞች “የሀይል እርምጃ ለህዝብ መልስ አይሆንም” በሚል ርዕስ የተጠራው የሙስሊሞች ተቃውሞ በደማቅና በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁ ታውቋል።


በአዲስ አበባና በበበርካታ የክልል ከተሞች ተቃውሞ ያሰሙት ሙስሊሞች ካስተጋቧቸው መፈክሮች መካከል፦” መብታችንን ለማስከበር የምናደርገው ትግል በሀይል እርምጃ አይጨናገፍም!፣ ለህዝብ የመብት ጥያቄ ሀይል መልስ አይሆንም! የታሰሩት መሪዎቻችን ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ ይፈቱ! መንግስት ከሀይማኖታችን ላይ እጁን ያንሳልን! እና ፍትህ እንሻለን!”የሚሉት ይገኙበታል።


እንዲሁም በፍትህ እጦት የተማረሩት እነዚሁ ሰልፈኞች፦<<መንግስት የለም ወይ? መንግስት የለም ወይ? >>እያሉ በዜማ ተማጽኖአቸውን ሲያሰሙ ተደምጠዋል።


ድ ም ጻችን ይሰማ ለሰልፉ ጥሪ በባደገበት መግለጫው፦<<የትግላችንን ሂደት ለመግታት መንግስት ከውስጥም ከውጪም የተለያዩ ጥቃቶችን ሲሰነዝር ቀይታል፤ በጥቃቱ ሙስሊሞችን ከትግሉ ሜዳ ለማስወገድ ታስቦ የነበረ ቢሆንም መንግስት የሚያስበውን ያህል ሲሳካለት ግን አልታየም፡፡>>ብሏል።


<<ይህ የመንግስት ጥቃት ሌት ተቀን አከብረዋለሁ ብሎ የሚለፍፍለትን፣ በተግባር ግን ሊገዛለት የማይፈቅደውን ሕገ መንግስት በመጣስ በተደጋጋሚ የተፈጸመ >>ሲልም አክሏል -ድምፃችን ይሰማ ኮሚቴ።


በሌላ በኩል የመንግስት ባለስልጣናት ባለፈው ሳምንት ተጠርቶ የነበረውን ሰላማዊ ሰልፍ – በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጲያዊያን ሙስሊሞች ከአንድ ዓመት በፊት ካነሱት ሃማኖታዊ ጥያቄ ጋር ለማያያዝ ሞክረዋል ያለው ኮሚቴው፤ይህም ለህዝብ ያላቸውን ንቀት የሚያሳይ ነው በሏል።


ዛሬ አዲስ አበባን ጨምሮ በ30 ከተሞች በተደረገው እጅግ ደማቅ ሰልፍ ሴት ሙስሊሞች ከወትሮው በተለየ መልኩ በዝተው መስተዋላቸው ተመልክቷል።


በተለይ በ አንዋር መስጊድ በተደረገው የተቃውሞ መርሀ-ግብር ሴት ሙስሊሞች በከፍተኛ እልህና ወኔ መሪዎቻቸው እንዲፈቱ በመጠየቅ ተቃውሟቸውን ሲገልጹ ተስተውለዋል።


የመብት ጥያቄ በማንሳታቸው ሳቢያ “ የ አሸባሪነት ክስ ተመስርቶባቸው የታሰሩት የሙስሊም አመራሮች ያለ አንዳች ፍትሕ ወህኒ ከተወረወሩ 18 ወራት እንዳለፋቸው ይታወቃል።


ሙስሊሞች ዛሬ ባደረጉት ሰልፍ መሪዎቻቸው እስኪፈቱ እና ሀይማኖታዊ ጥያቄዎቻቸው እስኪመለሱ ድረስ የተቃውሞ መርሀግብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በድጋሚ አረጋግጠዋል።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar