መንግስት በርሃብ ለተጠቁት ዜጎች እርዳታ እየሰጠ እንዳልሆነ ታወቀ
• ‹‹ሰው በርሃብ እያለቀ ነው››
• ‹‹የሚላስ የሚቀመስ የለም፡፡ ቤተሰባችን ፈርሷል››
• ‹‹እርዳታ ቢሰጥማ ከዚህ ድረስ አንመጣም ነበር፡፡››
መንግስት በርሃብ ለተጎዱት ዜጎች እርዳታ እየሰጠ እንዳልሆነ ቀያቸውን ለቀው አዲስ አበባ የገቡት የርሃቡ ሰለባዎች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ ከወሎ የተለያዩ አካባቢዎች በርሃብ የተጠቁ ዜጎች ህይወታቸውን ለማትረፍ ወሎ ውስጥ ከሚገኙት ከተሞች አልፈው ወደ ጎጃም፣ ጎንደርን እንዲሁም አዲስ አበባ እየተሰደዱ ሲሆን አዲስ አበባ በርካታ ተጎጅዎች ህፃናትን አዝለው እየለመኑ ይገኛሉ፡፡ የነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር ካነጋገራቸው መካከል ሁሉም መንግስት ለርሃቡ ተጎጅዎች እርዳታ እየሰጠ እንዳልሆነ ገልፀዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸውና ጎረቤቶቻቸውም እንደነሱ ቀያቸውን ጥለው ወደ መተማ፣ ሁመራ፣ ባህርዳር፣ ደሴ፣ እንዲሁም ወደ አዲስ አበባ መሰደዳቸውን በሀዘን ገልፀዋል፡፡
rehab3
ወሎ ውስጥ ጮሬ ሶዶማ ከተባለ ቦታ ተነስታ እንደመጣች፣ አዲስ አበባ ከገባች ሶስት ሳምንት እንደሆናት የገለፀችውና ሁለት ህፃናትን ይዛ ስትለምን ያገኘናት፤ በግምት በ30ዎቹ መጨረሻ ዕድሜ የምትገኝ እናት ‹‹የመጣነው የሚላስ የሚቀመስ ስለሌለ ነው፡፡ ከብቶቻችን አልቀዋል፡፡ አዝመራ የሚባል የለም፡፡ ሰው በርሃብ እያለቀ ነው፡፡ እኛ ሴቶቹ ወደ ከተማው ስንመጣ ወንዶቹ ደግሞ ወደ ሁመራና መተማ ሄደዋል፡፡ እኛም ከዚህ የመጣነው ጉልበት ስላለን ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ደካሞች በዛው አካባቢ ቀርተዋል፡፡›› ስትል በሀዘን ገልፃልናለች፡፡ መንግስት እርዳታ አይሰጥም ወይ ብለን ላነሳንላት ጥያቄም ‹‹ምንም እርዳታ አልተሰጠንም፡፡ እርዳታ ቢሰጥ ኖሮ ቤታችን ጥለን አንመጣም ነበር፡፡ ባያበቅልም መሬት አለን፡፡ የከተማው ሰው ይሻላል ብለን ነው ወደዚህ የመጣነው›› ስትል ስለ ርሃቡ አስከፊነትና መንግስትም እርዳታ እየተሰጠ እንዳልሆነ ገልፃልናለች፡፡
rehab 4
ባለቤቷ ወደ መታማ ሲሄድ እሷም ቤቷን ጥላ ወደማታውቀው አዲስ አበባ እየጠየቀች እንደመጣች የገለፀችልን ወጣት በበኩሏ ‹‹ቤቴ ተፈትቷል፡፡ ባለፈው አመት ከብቶችም እህልም ነበረን፡፡ ዘንድሮ ግን ምንም ነገር የለም፡፡ ጊዜው ከፍቷል፡፡ ባሌ ወደ መተማ ሄዷል፡፡ እኔም ልጄን አዝዬ እስከ ደሴ በእግሬ መጣሁ፡፡ ከዛ በኋላ እየለምንኩ ከዚህ ደርሻለሁ፡፡ ማንም እርዳታ አልሰጠንም፡፡›› ስትል ስለሁኔታው ገለፃልናለች፡፡
ከመርሳ ወረዳ እንደመጡ የገለፁልንና ከልጃቸው ልጅ ጋር እየለመኑ ያገኘናቸው የ65 አመት አዛውንት በበኩላቸው ‹‹ዝናቡ ሲቀር ከብቶቻችንም ሞቱ፡፡ አዝመራ የሚባልም ነገር የለም፡፡ ከመርሳ ደሴ እየለመንኩ መጣሁ፡፡ ደሴም እንደኛ ብዙ ሰው አለ፡፡ አገኝ ብሎ በየከተማው ተሰራጭቷል፡፡ ወደዚህ ይሻላል ብዬ በለመንኳት ተሳፍሬ መጣሁ፡፡ ርሃቡ ሲብስብን ወደማናውቀው አገር መጣን፡፡›› ሲሉ የርሃቡን አስከፉነት ገልፀውልናል፡፡
‹‹እርዱኝ!›› እያሉ እየለመኑ ያገኘናቸው ከኬሚሴ አካባቢ እንደመጡና ከ8 ቀን በፊት አዲስ አበባ እንደደረሱ የገለፁልን ሌላኛዋ እናትም ቤታቸውን ጥለው እንደመጡና፣ ሌሎች ቤተሰቦቻቸው ወደ የት እንደሄዱ እንኳን እንደማያውቁ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ መንግስት እርዳታ እየሰጠሁ ነው እንደሚል ስንገልፅላቸው ‹‹ለእኔ አልደረሰኝም፡፡ እርዳታ ተሰጠኝ ያለም አልሰማሁም፡፡ እርዳታ ቢሰጥማ ከዚህ ድረስ አልመጣም ነበር፡፡ አሁን ነው ከከተማው ሰው ትንሽ ትንሽ እያገኘን ያለነው፡፡ በየ ከተማው ስንደርስ ሰው አይነፍገንም›› ሲሉ ከህዝብ እንጅ ከመንግስት እርዳታ እንዳላገኙ ገልፀዋል፡፡
rehab 5
ካሳንቺስ አካባቢ ልጅ አዝለው ታክሲ ተሳፋሪዎችን ምንም አይነት ቃል ሳያሰሙ ልጃቸውን በመዘርጋት ብቻ እንዲረዷቸው እየጠየቁ ያገኘናቸው እናትም የራሳቸውንና የታዘለውን ልጅ ነፍስ ለማዳን ቀያቸውን ጥለው ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡
የርሃቡ ተጎጅዎች አዲስ አበባ ውስጥም ነፍሳቸውን ለማቆየት በጠራራ ፀሀይ ሲለምኑ እንደሚውሉና ምቹ ያልሆነ ቦታ አንድ ላይ የሚያድሩ በመሆኑ ልጆቻቸው ለበሽታ እየተጋለጡ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ተማሪ የነበሩና በርሃቡ ምክንያት ለማቋረጥ የተገደዱት ልጆቻቸው ከእነሱ ጋር ወይንም ወደ ሌላ አካባቢ ነፍሳቸውን ለመዳን መሰደዳቸውን፣ በያለፉበት ከተማም በርካታ ስደተኛ እንዳለም ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡