ሀገሪቱን እየመራሁ እገኛለሁ በሚለው ቡድን ውስጥ ውጥረት መንገሱ ተሰማ፡፡ ምንጮች እንደጠቆሙት ከሆነ፣ በቀጣይ ጊዜም ‹‹የስልጣን መልቀቂያ›› የሚያስገባ ባለስልጣን ይኖራል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ የስርዓት ለውጥ እየጠየቀ በሚገኝበት በዚህ ሰዓት፣ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ‹‹ስልጣን በቃኝ›› የሚል አጀንዳ ይዘው መምጣታቸው ይታወቃል፡፡ የኦህዴዱ አቶ አባዱለ ገመዳ የጀመሩትን ‹‹የስልጣን መልቀቂያ ጥያቄ›› የብአዴኑ አቶ በረከት ስምዖንም መከተላቸው ይታወቃል፡፡
ቀደም ባለው ጊዜም ቢሆን ውጥረት ውስጥ የነበረው ገዥው ፓርቲ፣ አሁን ደግሞ የለየለት አለመረጋጋት ውስጥ እንደሚገኝ ምንጮች ለቢቢኤን ያደረሱት ዘገባ ያስረዳል፡፡ ገዥው ፓርቲ አሁን ላይ የህዝብን ተቃውሞ የሚቀለብስበት አጀንዳ ላይ እየመከረ እንደሚገኝ የገለጹት ምንጮቹ፣ በቀጣይ ደግሞ አንድ አመራር የስልጣን መልቀቂያ እንዲያስገባ በማድረግ ትኩረት ለመሳብ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ምንጮቹ ያክላሉ፡፡ ሰሞነኛው የህዝብ ተቃውሞ ፓርቲውን ይበልጥ እንቅልፍ እንደነሳውም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ካለፈው ዓመት ጀምሮ በነበረው የህዝብ ተቃውሞ ቅርቃር ውስጥ የገባው የህወሓት መንግስት፣ የተለያየ የመደለያ ፖለቲካ ቢጠቀምም ሳይሳካለት መቅሬ ይታወሳል፡፡ አንደኛው የስርዓቱ የፕሮፓጋንዳ አጀንዳ የነበረው፣ ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› የነበረ ሲሆን፣ ይህ አካሄድ ስላላዋጣው አሁን ደግሞ፣ የስልጣን መልቀቂ የሚል አጀንዳ ይዞ ብቅ ማለቱን ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡ በባለስልጣናት የተጀመረው የስልጣን መልቀቂያ ጥያቄ፣ በቀጣይ ደግሞ ህዝብ ተቃውሞ በሚያሰማባቸው የኃይማኖት ተቋማት ላይም እንደሚቀጥል ከምንጮች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከአራት አቅጣጫዎች ስልጣኑ የተናጋበት ገዥው ቡድን፣ የመጨረሻ የፖለቲካ መፍትኤ ብሎ የወሰደው ነባር ባለስልጣናትን ከህዝብ ፊት ዞር ማድረግ ሲሆን፣ ይህ አካሔዱ ግን ብዙም ትኩረት እንዳልሳበ ተረድቷል ይላሉ- ታዛቢዎች፡፡ አቶ በረከት ስልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ አቀረቡ የሚለው ዜና፣ ቢያንስ የአቶ አባ ዱላ ገመዳን ያህል እንኳን ትኩረት አለመሳቡ፣ ህዝብ ያፓርቲውን ጨዋታ እንደነቃበት አመላካች መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ይገልጻሉ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ለተቃውሞ አደባባይ መውጣቱን ሊያቆም የሚችለው የስርዓት ለውጥ ከተደረገ ብቻ ነው ሲሉም አስተያየት ሰጪዎቹ ያክላሉ፡፡ (BBN NEWS)
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar