አለም አቀፍ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ግብረ-ሃይል
አለም አቀፍ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ግብረ-ሃይል ዲያስፖራ ኢትዮጵያዊያን ዘመዶቻቸዉን ለመርዳት፣ ለንግደና ለግንባታ ወደ አገር ቤት የሚልኩት የዉጭ ምንዛሬ (ዶላር፣ ዩሮና፣ ፓዉንድ) የህወሓት አገዛዝ እጅ እንዳይገባ በማድረግ ላይ ያነጣጠረ ዘመቻ መጀመሩ ይታወቃል።
ግብረ-ሃይሉ የህወሓት አገዛዝ በእጁ የሚገባዉን የዉጭ ምንዛሬ ባንድ በኩል ኢትዮጵያዊያንን ለማፈንና ለመግደል የሚጠቀምባቸዉን መሳሪያዎች ከዉጭ ለመግዣና በሌላ በኩል ከአገሪቱ የሚዘርፈዉን ሃብት ወደዉጭ ለማሸሺያ እንደሚጠቀምበት ጠቅሶ፣ የዚህን አገዛዝ እድሜ ለማሳጠር በርካታ ኢትዮጵያዊያን የህይወት ዋጋ እስከመክፈል በደረሰ ቆራጥነት በሚታገሉበት ባሁኑ ወቅት፣ ካገራቸዉ ወጥተዉ በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የህዝባቸዉን የነጻነት ትግል ለማገዝ የአገዛዙን የዉጭ ምንዛሬ አቅም ማመናመን ቀላሉ፣ ቀጥተኛዉና ባጭር ጊዜ ዉስጥ ዉጤት ሊያስገኝ የሚያስችል ተግባር እንደሆነ ማስገንዘቡ የሚታወስ ነዉ።
ግብረ-ሃይሉ፣ ስለዚህ ዘመቻ ለአሜሪካ ድምጽ የአማርኛ ፕሮግራም የሰጠዉን ቃለ-መጠይቅ ተከትሎ የህወሓት አገዛዝ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሰሞኑን በዉሸት የተሞላ፣ ተራና አጭበርባሪ ምላሽ ሰጥቷል።
በተለይ ቃል አቀባዩ የሬምታንስ ዘመቻዉ የሚጎዳዉ ከዉጭ በሚመጣ ሬሚታንስ ላይ የሚደገፉ ወገኖቻችንንና እርሳስና እስክርቢቶ መግዣ የሚሆን ገንዘብ የሌላቸዉን ተማሪዎች ነዉ ሲል ከተለመደዉ የህወሓት-ወያኔ የቅጥፈት መጽሃፍ የተወሰደ፣ ጊዜዉ ያለፈበት ማደናገገሪያ አስተላልፏል። በተለይ ግን ዘመቻዉ ኢትዮጵያዊነት የሚጎድለዉ ድርጊት ማለቱ ለአገዛዙ ያለዉን ህሊና ቢስ ታማኝነትና ለኢትዮጵያዊያን የማመዛዘን ችሎታ ያለዉን ንቀት የሚያሳይ ስላቅ ነዉ። ከደቂቅ ህጻናት እስከ አረጋዉያን ድረስ አዉሬአዊ በሆነ ጭካኔ የሚገድል ዘረኛና ወንጀለኛ አገዛዝ እያገለገሉ የአገራቸዉና የወገናቸዉ ሰቆቃ ጧት ማታ የሚያብሰለስላቸዉን ኢትዮጵያዊያን በጸረ-አገራዊነት እና በጸረ-ኢትዮጵያዊነት ለመዉቀስ የሚያስችል ሞራላዊ መሰረት ሊኖር አይችልም። ኤፈርትን የመሳሰሉ የዝርፊያ እና የጎሰኝነት ተቋማት አደራጅቶ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የኢትዮጵያን ህዝብ ከሚመዘብር ስርአት ጋር በሎሌነት አብሮ እየሰሩ ለኢትዮጵያዊያን እና ኢትዮጵያዊነት ወገንተኛ መሆን ፍጹም አይቻልም።
የሬምታንስ እቀባ ዘመቻዉ ኢላማ አንድና አንድ ብቻ ነዉ፤ የኢትዮጵያን ህዝብ ለሃያ ሰባት አመታት በጫማዉ ስር ረግጦ የያዘዉ የህወሓት-ወያኔ አገዛዝ ነዉ።
የኢኮኖሚ ጫናዎች በደቡብ አፍሪካ (አፓርታይድ ላይ በተደረገ ትግል)፣ በአሜሪካ (የጥቁሮች የእኩልነት ትግል)፣ በህንድ (የነጻነት ትግል) አፋኛና ግፈኛ ስርአቶችን ለማንበርክ ከፍተኛ ሚና ተጫዉተዋል። ስለዚህም፣ በአገራችሁ ፍትህ፣ እኩልነትና ሰብአዊ መብቶች ተከብረዉ ለማዬት የምትሹ ዲያስፖራ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ለዘመድ፣ ወዳጅ፣ ንግድና ግንባታ ብላችሁ ወደ አገር ቤት የምትልኩት የዉጭ ምንዛሬ በዚህ አፋኝና ገዳይ አገዛዝ እጅ እንዳይገባ በማድረግ የበኩላችሁን ወገናዊና አገራዊ ግዴታ እንድትወጡ ግብረ-ሃይሉ በድጋሚ ጥሪውን ያቀርባል። ይህም ማለት፦
ሀ)አገር ቤት ለሚኖሩ ዘመዶቻችሁ ገንዘብ በምትልኩበት ወቅት፣ እንደ ዌስተርን ዩንየንና መኒ ግራም የመሳሰሉትን መደበኛ የባንክ መስመሮችን እንዳትጠቀሙና በምትኩ በየአካባቢያችሁ የሚገኙ፣ ከህወሓት አገዛዝ ጋር ንኪኪ የሌላቸዉና ከባንክ ዉጭ ገንዘብ የማስተላለፍ አገልግሎት የሚሰጡ ነጋዴዎችንና ግለሰቦችን እንድትጠቀሙ፤ በባንክ መላክ ብቸኛዉ አማራጭ ለሚሆንባችሁ ደግሞ የምትልኩትን የገንዘብ መጠን ወይም የጊዜ ፍጥነት እንደሁኔታዉ እንድትቀንሱ፤
ለ)የአገሪቱ ሰላም በታወከበትና ያገዘዙ ባለሟሎች ሳይቀሩ ገንዘባቸዉን ወደዉጭ በሚያሸሹበት በአሁኑ ወቅት፣ የትዉልድ አገራችሁ ቤት ለመስራትም ሆነ በንግድ ወይም ሌላ ቢዝነስ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ የምታስቡ ዲያስፖራ ኢትዮጵያዊያን፣ እቅዳችሁን ለጊዜዉ እንድታዘገዩት ወገናዊ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን።
በመጨረሻም፣ ለወትሮዉ በዉጭ የምንኖር ኢትዮጵያዊያን ለምናሰማዉ ስሞታ መልስ ለመስጠት ደንታ ያልነበረዉ የህወሓት-ወያኔ አገዛዝ፣ ባሁኑ ጊዜ ፈጥኖ ምላሽ መስጠቱ ከሚገኝበት ከፍተኛ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አጣብቂኝ ጎን፣ የዉጭ ምንዛሬ እቀባዉ ሊፈጥር የሚችለዉ ፈጣንና ወሳኝ ጫና እንዳስደነገጠዉ የሚያሳይ ስለሆነ ላልሰሙት እያሰማችሁ ትግሉን እንድትቀጥሉበት አደራ እንላለን።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
አለም አቀፍ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ግብረ-ሃይል
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar