fredag 6. juli 2018

ነፃነት ተጎናፅፈናል የብልፅግና ጉዞም ተጀምሯል ለወጡን እንጠብቅ! (ታዬ ደንዳዓ

ለኢትዮጵያ ህዝብ
ለወጡን እንጠብቅ! (ታዬ ደንዳዓ)
እንደ ህዝብ እና እንደ ሀገር ፍላጎታችን ነፃነት እና ብልፅግና ነዉ። ይህ ያልተሳካልን በእርግማን ሳይሆን ከጅቦች አገዛዝ ራሳችንን ማላቀቅ ባለመቻላችን ነዉ። አሁን ነፃነት ተጎናፅፈናል። የብልፅግና ጉዞም ተጀምሯል። ክብር እና ዕድሜ ለዶር አብይ እና ለጓዶቻቸዉ! በሦስት ወር ጊዜ ዉስጥ በጣም ብዙ ለዉጥ አይተናል። በዝህ ፍጥነት በሁለት እና ሦስት ዓመታት በሀገራችን መሠረት ያለዉ ሠላም፣ ዴሞክረሲ እና ልማት ይገነባል። ለዝህ ላበቁን ቄሮዎች፣ ፋኖዎች እና ዘርማዎች ክብር ይገባል።
ጅቦች ግን እያዛጉ ነዉ። ነፃነታችንን አይፈልጉም። የነሱ ብልፅግና በችጋራችን ላይ የተመሠረተ ነዉ። ስለዝህ ለዉጡን ቀልብሰዉ ወደነበርንበት ሊመልሱን እየተሯሯጡ ነዉ። ሩጫቸዉ በሁለት አቅጣጫ ነዉ። አንደኛዉ ሠላም ማደፍረስ ነዉ። በዝህ ረገድ ሰዉን ለመግደል እና ንብረት ለማዉደም ቅጥረኛን አሰልጥነዉ ከብዙ ገንዘብ ጋር አሰማርቷል። በተለያዩ ቦታዎች በየቀኑ ቦምብ እየተያዘ ነዉ። በየቦታዉ ሰዉ ሲሞት እና ንብረት ሲወድም ስጋት ይሰፍናል። የኢትዮጵያ ህዝብ ሠላም ካጣ የዶር አብይን አስተዳደር ጠልቶ የጅቦችን አገዛዝ ይመኛል። ያኔ ጅብ የሚፈልገዉን ያገኛል።
ሁለተኛዉ ደግሞ የኢኮኖሚ አሻጥር ነዉ። ጅቦች በተደራጀ ሌብነት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በበላይነት ተቆጣጥሯል። ብዙ ሸቀጦች በእነሱ እጅ ነዉ። ይህን አቅም በመጠቀም የገበያን ነፃ ዉድድር ለማወክ አቅዷል። ገባያ ሲዛባ አርተፍሻል እጥረት ይፈጠራል። ይህ ህዝብን ለረሀብ ይዳርጋል። ህዝብ ደግሞ ሲራብ በዶር አብይ አስተዳደር ላይ ይነሳል። በዝህ መሀል ጅብ ወደ ስልጣኑ ይመለሳል። ስሌቱ ይህን ይመስላል።
ስለዝህ ምን እናድርግ? ዋናዉ ጉዳይ ይህ ነዉ። ተጨማሪ ነፃነትን እንጅ ባርነትን አንሻም! ያገኘነዉን ዉጤት ለማስጠበቅ እና ተጨማሪ ስኬት ለማስመዝገብ ደግሞ ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋፅኦ ማድረግ አለብን።
1. እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በያለበት የሀገሩ ደህንነት ሆኖ የጅቦችን እንቅስቃሴ በአንክሮ መከታተል አለበት። አዲስ ነገር ባዬ ጊዜ በመረጃ አስደግፎ ለፀጥታ አካላት ያሳዉቅ። ሰላማችን በእጃችን ላይ ነዉ።
2. የኢኮኖሚ ችግርን በተመለከተ
ሀ. አያንዳንዳችን አሻጥረኞችን እንከታተል። ችግር ከተከሰተ ተጠያቂዉ መንግስት ሳይሆን የቀን ጅብ መሆኑ ከወዲሁ ይታወቅ።
ለ. ሀገር ወዳድ በለሀብቶች የሚፈጠሩ ክፍተቶችን ለመሙላት ከወዲሁ ዝግጅት ያድርጉ።
ሐ. መንግስት ችግሮችን ወደ ዕድል ይቀይር። የኢኮኖሚ አሻጥረኞችን በጥብቅ ተከታትሎ ንብረታቸዉን በመዉረስ ለህዝብ ጥቅም ያዉል። በቦታቸዉ ደግሞ ስራ አጥ ወጣቶችን አሰልጥኖ እና አደራጅቶ ያስገባ። ጫዉ ለራሱ ሲል ይጣፍጣል።
3. የኢትዮጵያ የፀጥታ ሀይል አባላት ከህዝብ ጋር እጅና ጓንት በመሆን ለሀገራቸዉ አንድነት እና ሠላም ዘብ መቆም አለባቸዉ።
ህብረታችን የማይንደዉ ተራራ የለም! የተባበረ ህዝብ ሁሌም አሸናፊ ነዉ!
ሠላም ዋሉ!

► መረጃ ፎረም - JOIN US

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar