fredag 6. juli 2018

ሰበር ዜና….ብጹዕ አቡነ ማቲያስ ስልጣናቸውን በሚቀጥሉት ሳምንታት በፈቃዳቸው ሊለቁ ነው

ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ እና ዶ/ር ደብረጽዮን
ባለፈው ሳምንት ሲካሄድ የነበረውና ለአራት ቀናት ያክል የተካሄደው  36ኛውየሰበካ  መንፈሳዊ  ጉባዔ   ላይ ከሌሎች ጳጳሳትና ከቤተክህነት አስተዳደር ጋር በአደባባይ እስጥ አገባ ውስጥ ያሳለፉት አቡነ ማትያስ በጉባዔው ጣልቃ ስልጣናቸውን ለመልቀቅ እንደሚፈልጉ ለቅርብ ሰዎቻቸው ተናግረዋል። በቤተክህነቱ አካባቢ ስልጣናቸውን የሚገዳደሩና የማይታዘዟቸው እየበዙ በመምጣታቸው ክፉኛ የተበሳጩት አቡነ ማቲያስ በመጪው ጊዜ በሚጀምረው የሲኖዶሱ ጉባዔ ላይ መልቀቂያ ማቅረብ እፈልጋለሁ ብለዋል። የፓትርያርኩ እርምጃ ያሳሰበው መንግሥት ፓትርያርኩ ሀገሪቱ ያለችበትን አስቸጋሪ ሁኔታ አጢነው ስልጣን ከመልቀቅ ይልቅ በውይይት ችግሮችን እንዲፈቱ ከማክሰኞ  ምሽት  ጀምሮ አንድ ቡድን በመላክ እያግባባቸው ነው።
አቡነ ማትያስ የቤተክርስቲያኒቱ የወንጌል ማስፋፋትና ትምህርት አንድ አሀድ ከሆነው ማኀበረ ቅዱሳን ጋር የተካረረ ውዝግብ ውስጥ  የቆዩ ሲሆን መንግሥት ማኅበሩን እንዲዘጋው  እስከመጠየቅ ደርሰዋል። ማኀበሩ በቅርቡ የጀመረውን የቴሌቭዥን ስርጭትም   ህገወጥ  በመሆኑ ሊታገድ ይገባል ባይ ናቸው አቡነ ማትያስ።  ፓትርያርኩ  ለአራት ቀናት  በተካሄደው    የመንፈሳዊ ሰበካ ጉባዔ ላይ የማኅበረ ቅዱሳን ተወካዮች እንዳይካፈሉ ትዕዛዝ ሰጥተው ማኅበሩን እንዳይሳተፍ ማድረግ ቢችሉም የቤተክህነት አስተዳደርና ሌሎች ገዳማት የማኅበረ   ቅዱሳንን   ሚና የሚያጎላና የሚያወድስ ሪፖርት ማቅረባቸው አቡነ ማትያስን አስከፍቷቸዋል።
ጉባዔው ማኅበረ ቅዱሳንን ከማውገዝ ይልቅ ለቤተክርስቲያኒቷ አለኝታ የሆነና ድጋፍ  ሊደረግለት  የሚገባ መሆኑንም የተናገሩ አባቶች ነበሩ። በአራቱ ቀን ጉባዔ ከአቡነ ፋኑኤል ጋር የከፋ የቃላት  ልውውጥ ያደረጉት ፓትርያርኩ ብዙውን ጊዜ በዝምታና በማኩረፍ እንዳሳለፉ ከጉባዔው ተሳታፊዎች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የውዝግቡን  መካረር  ተከትሎ መንግሥት የጉባዔውን ሂደት በቅርብ ሲከታተል የቆየ ሲሆን በማጠቃለያ የአቋም መግለጫ ላይ የማኅበረ ቅዱሳን የቴሌቭዥን ስርጭት “ህገ- ወጥ” መሆኑን የሚገልፅ አንቀፅ ከጉባዔተኛው ስምምነት ውጪ እንዲጨመር መደረጉ ብዙዎችን አሳዝኗል። አንቀፁ የተጨመረው አቡነ ማትያስን “ተሰሚ” አድርጎ ለመሳል “በትዕዛዝ” የተካተተ እንደሆነ ከቃለጉባዔ መዝጋቢዎች ተሰምቷል።
አቡነ ማትያስ
ምንጭ አንድነት ጋዜጣ

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar