tirsdag 21. mai 2019

በሃገር ቤት የምትኖሩ አካል ጉዳተኛ ወገኖች ከውጭ ወደ ሃገር ቤት ከቀረጥ ነፃ የቤት አውቶሞቢል እንደሚያስገቡ ያውቃሉ?


በኢትዮጵያውስጥ ለምትኖሩ አካል ጉዳተኞች የሚያስደስት ዜና መንግስት ከቀረጥ ነፃ አውቶሞቢሎች እንድታስገበ በፈቀደው መሰረት የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ስናበስረዎ በደስታ ነው። የእዚ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማጋራት ይተባበሩ


mandag 1. april 2019

የአዲስ አበባ ዱካ


‹‹እንጦጦ ላይ ሆኜ አዲስን ሳያት
ባለፈርጥ ኮከብ መስላ አገኘኋት፡፡››
የዚህ መንቶ ግጥም ደራሲ በእምነት ገብረ አምላክ ናቸው፡፡ ሐያሲው እንዳለው ደራሲው የአዲስ አበባ፣ የሚያውቃት አዲስ አበባ ውበት በድንገት ያነቃው ያነሆለለው ባለቅኔ ነው፡፡
የሥነ ግጥም መምህሩ፣ የሥነ ግጥም ፈካሪው ነፍስ ኄር ብርሃኑ ገበየሁ እንደተረጎመውም ‹‹የገጣሚው አድናቆት የመነጨው ከምሽት ትዕይንት ነው ማለት ይቻላል፤ ለምን ቢሉ አንድም ለአድናቆቱ ማንጸሪያ፣ ለአድናቆቱ መያዣ የመረጠው ምስል ባለፈርጥ ኮከብ ነውና፤ አንድም ኮከብ በምናባችን የሚከሰተው የብርሃን ምስል ነውና፡፡ አገላለጹ ውብ ነው፤ ምስሉም የተባና ሳይሆን ለተደራሲውም አዲስ ውበት ትሆናለች፡፡››
ገጣሚው በአጭሩ ‹‹አዲስ›› ያላት፣ ሌሎችም ድምፃቸውን ረገጥ አድርገው ‹‹አዲሳባ›› የሚሏት አዲስ አበባ ከተመሠረተች 132 ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡
በ19ኛው ምዕት ዓመት መገባደጃ ላይ የተቆረቆረችው አዲስ አበባ የፖለቲካ፣ የሕግና የንግድ ማዕከል ሆና የዘለቀችው፣ ለአፍሪካ መዲናነት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ ልዩ ተቋማት መናኸሪያነት በመብቃት ነው፡፡ ይልቁንም አዲስ አበባ በውስጧ ያላቀፈቻቸው የኢትዮጵያ የተለያዩ ቋንቋዎች ተናጋሪ ብሔረሰቦች የሉም ማለት ይቻላል፡፡ የየብሔረሰቡ ባህላዊ መገለጫ እስከሆኑት ምግባ ምግብ ድረስ፡፡
አንድ የመዲዪቱ የሚሌኒየሙ ድርሳን እንደሚያመለክተው፣ የመዲናዪቱን ሁል አቀፍ ገጽታ/ሞዛይክነት ያስተዋሉ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ማዕከል ብቻ ሳትሆን የባህልና የቋንቋ ሙዚየም ነች፡፡
በኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ምሥረታ እውን ከሆነበት በተለይ ከሁለት ሺሕ ዓመት ወዲህ ጎልተው ከሚታወቁት መዲናዎች አክሱም ከላሊበላና ጎንደር ከተሞች በመቀጠል የምትወሳው አዲስ አበባ ናት፡፡
ከተማዋ በተመሠረተች በሃምሳኛ ዓመቷ በፋሺስት ጣሊያን አገዛዝ ለአምስት ዓመታት ከመተዳደሯ በስተቀር ለ127 ዓመታት በአገሬው አስተዳደር ሥር የተለያዩ አደረጃጀቶችን አሳልፋለች፡፡
የአዲስ አበባ ዱካ

ዘመናዊ የከተማ አስተዳደር ‹‹የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት›› የተመሠረተው በ1909 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ሲሆን አስቀድሞ መጠሪያው የነበረው የከተማው ማኅበር ቤት (Municipality) ነው፡፡ ማዘጋጃ ቤት የሚለውን ስያሜ ያገኘችው በ1920 ዓ.ም. መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በ1928 ዓ.ም. ሚያዝያ 27 በኢትዮጵያና ጣሊያን ሁለተኛ ጦርነት ፋሺስቶች አዲስ አበባ ከተማን ሲቆጣጠሩና ለአምስት ዓመታት ሲቆዩ የራሳቸውን አስተዳደር መሥርተው ነበር፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ ጣሊያን ግዛትን መሥርተው ኤርትራና ሶማሊያን (የሞቃዲሾ) ያካተተ ስድስት ግዛቶች ሲመሠርቱ፣ አንደኛውና ማዕከላዊው ግዛት በአዲስ አበባ ስም የተቋቋመ ነበር፡፡ 
ፋሺስት ጣሊያን ከተወገደ በኋላ በግማሽ ምዕት ዓመት ውስጥ በተለያዩ አስተዳደራዊ መዋቅሮችና አስተዳደሮች ከተማዋ አልፋለች፡፡ ከዘውዳዊው ሥርዓት የጠቅላይ ግዛት አከፋፈል በኋላ በዘመነ ደርግ ስያሜው በክፍለ ሀገር ሲተካ ከ14ቱ ክፍላተ ሀገር አዲስ አበባን እንደ 15ኛ ትታሰብ እንደነበር ይወሳል፡፡
በ1980 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) ሲመሠረት አከላለሉ በ25 አስተዳደር አካባቢና በ5 ራስ ገዞች የነበረ ሲሆን፣ አዲስ አበባ ራሷን የቻለች የአስተዳደር አካባቢ ሆናለች፡፡ መልክዓ ምድራዊ ገጽታዋም ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙ እንደ ጫንጮ፣ አቃቂ፣ ሆለታና ሌሎች የአዲስ አበባ አካባቢ ገጠር አውራጃዎች ተብለው እንደነበረ ይታወቃል፡፡
ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ሲመጣና የሽግግር መንግሥት በ1984 ዓ.ም. ሲመሠረት አዲስ አበባ ‹‹ክልል 14›› በሚል የራሷ አስተዳደር የነበራት መዲና ስትሆን፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) በ1988 ዓ.ም. ዕውን ሲሆን ክልልነቷ ቀርቶ የፌዴራል መዲና ሆናለች፡፡
ቅድመ አዲስ አበባ
አዲስ አበባ ከተማ በ132 ዓመታት ውስጥ ካስተዳደሯት ሠላሳ ከንቲባዎች ሃያ ሁለተኛው ከንቲባ ዘውዴ ተክሉ (ኢንጂነር) ከዓመታት በፊት ከሪፖርተር መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ስለ ከተማዪቱ ጥንተ ታሪክ ከተለያ መነሻዎች በመነሳት እንዲህ ተርከውታል፡፡
‹‹አዲስ አበባ እንዴት ነው የነበረችው? ማን ነው የቆረቆራት? የሚለው ነገር ሁለት መነሻዎች አሉት፡፡ በታሪክ ውስጥ የመጀመርያው መነሻ 14ኛው ክፍለ ዘመን ነው፡፡ በዚህ ክፍለ ዘመን የአፄ ዳዊት ሦስተኛ ከተማ ነበረች ነው የሚባለው፡፡ ነገር ግን እንደገና በታሪክ ወደኋላ ሲኬድ ማለትም በአራተኛው ክፍለ ዘመን የአክሱም ነገሥታት መጥተው ነበር፡፡ በአራተኛውና በአምስተኛው ክፍለ ዘመን የነበሩት አብርሃና አጽብሃ መቀመጫቸውን እዚህ አድርገው ነበር የሚል ታሪክ አለ፡፡ በዚያን ጊዜ የቀረው ማስታወሻ ለአዲስ አበባ ከተማ የየካው ዋሻ ሚካኤል ነው፡፡ አብርሃና አጽብሃ የመሠረቱት ዋሻ ነው፡፡ ዋሻው በመቆየቱ የተነሳ ስላረጀ ነው በአሁኑ ጊዜ ያለው የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን መሠረቱ የተሠራው፡፡ ከዚህ አኳያ የአዲስ አበባ ዙሪያ ሲታይ ለረጅም ጊዜ በኤረር ተራራ አካባቢ በርካታ ነገሥታት ነግሠዋል፡፡ ከተማቸውም አድርገዋታል፡፡ ስለሆነም ኤረርና በዚሁ አካባቢ በርካታ የአክሱም ነገሥታትን ጨምሮ 30 የሚሆኑ የሰሎሞናዊ ነገሥታት ነግሠዋል፡፡ 
‹‹እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ታሪክ ከነገሥታት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በመሆኑም የ237 ነገሥታት ሒደት አንድ ጊዜ ከአክሱም ወደ ላሊበላ ሸዋ፣ ከሸዋ ደግሞ ወደ ጎንደር እንደገና ደግሞ ከጎንደር ወደ ሸዋ ነው የመጣው፡፡ በ16ኛው ክፍለ ዘመን እንደገና ኤረር የአፄ ልብነ ድንግል ከተማ ነበር፡፡ ከኢማም አሕመድ (ግራኝ) በኋላ ደግሞ ወደ ሰሜን ሲያፈገፍጉ በመሀሉ ረጅም ጊዜ ያልፋል፡፡ ከዚህ በኋላ ማዕከላዊ መንግሥት ሲረጋጋ አዲስ አበባ እንደገና በአፄ ምኒልክ ዘመን ዋና ከተማ ሆነች፡፡ 
‹‹አፄ ምኒልክ ከተማቸውን ሌላ ዘንድ ለመቆርቆር ሲያፈላልጉና ጥረት ሲያደርጉ በሰሜን ሸዋ የምትገኘውን ‹‹ሊቼን› ከተማ አድርገዋት ነበር፡፡ በኋላ ግን የአያቶቼን ከተሞች ባገኝ በሚል ፍለጋ ላይ ስለነበሩ ፋሪ ላይ ከተማ ለማድረግ ሞክረው ነበር፡፡ መጨረሻ ግን ሱሉልታ አካባቢ እንዳሉ ‹እንጦጦ ላይ የአፄ ዳዊት የጥንቱ ከተማ መሠረቱ ተገኘ› የሚል መልዕክት ተላከባቸው፡፡ ከዚያ በኋላ አስቆፍረው ሲያዩት እውነትም የከተማ ቅሪት ነበር፡፡ 
‹‹አዲስ አበባ የእንጦጦ ተከታይ ነች፡፡ ይህም የሆነው በመሬቱ ምቹነት ምክንያት ነው፡፡ አዲስ አበባ ልዩ ልዩ ስሞች ያላቸው በርካታ አካባቢዎችም ነበሯት፡፡ እነሱም ኮልፌ፣ ጉለሌ፣ ፊንፊኔ፣ ወዘተ. የሚባሉ ናቸው፡፡ ፊንፊኔ የሚባለውም ፍል ውኃ አካባቢ ነው፡፡ የሚመነጨው ፍል ውኃው ወደ ላይ ‹‹ፊን›› የሚል ስለሆነ ይህንኑ ተመሥርቶ የተሰጠው ስም ነው፡፡ አዲስ አበባ አጠቃላይ ስሟ ግን ‹‹ሸገር›› በሚል ነበር የሚጠራው፡፡ ይህንንም በልጅነቴ በወሬ ሲነገርና በኦሮሚኛ ሲዘፈን እሰማ ነበር፡፡ ሁለት መሠረቶች አሉ፡፡ በ1876 አዲስ አበባ ተመሠረተች የሚል መጽሐፍ አለ፡፡ ነገር ግን ትክክሉ በ1879 ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ‹የመጀመርያው ቤት በእቴጌ ጣይቱ ተሠራ፡፡ ከተማዋንም አዲስ አበባ አሏት› የሚል መጽሐፍ አለ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው እንግዲህ የአሁኑ ከተማነቷ ዋና ታሪክ ያለው፡፡ 
አቶ አማረ ሽፈራው ለአዲስ አበባ ዘመናዊት በር ከፋቾች በሚል ርዕስ ባዘጋጁት መጣጥፍ ‹‹አዲስ አበባ መቼ? የት? እንዴት? ለምን ተቆረቆረች?›› የሚለውን ጥያቄ ‹‹የአፄ ምኒልክ ግቢ ጥናታዊ ዘገባ›› በሚል ርዕስ በባህል ሚኒስቴር የቅርስ ጥናትና ጥበቃ መምሪያ በነሐሴ 1976 ዓ.ም. የተዘጋጀውን ጥናታዊ ሰነድ በመጥቀስ የሚመልስ ዳሰሳ አድርገዋል፡፡ 
ሰነዱ እንደሚያስረዳው፤ በአሥራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን አፄ ምኒልክ የሸዋ ንጉሥ በነበሩበት ወቅት ቀደም ሲል በኦሮሞ ብሔረሰብ ንቅናቄና ቀጥሎም በኢማም አህመድ ኢብን ኢብራሂም (ግራኝ) ሳቢያ የአገሪቱ መዲና ከሸዋ ወደ ጎንደር በተሻገረበት ዘመናት ከማዕከላዊ መንግሥት ቁጥጥር ውጪ ሆኖ የቆየውን የደቡብ ኢትዮጵያ ክፍልና አስተዳደር ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ ወታደራዊ ኃይላቸውን ለማጠናከር የሚችሉበት አመች ዋና ከተማ በመሀል ሸዋ ለመመሥረት ያስባሉ፡፡ 
‹‹በ1877 ምኒልክ ከፍል ውኃ በስተሰሜን ከሚገኘው የእንጦጦ ተራራ ላይ ከነሠራዊታቸው ሠፈሩ›› ይልና ሰነዱ ይህም ሥፍራ ቀደም ሲል የአፄ ልብነ ድንግል መቀመጫ እንደነበር ዝዋይ ሐይቅ በሚገኘው ደሴት ብራና ላይ የተጻፈ ‹‹ትንቢት›› መገኘቱንና ምኒልክም ይህንን መሠረት በማድረግ መዲናቸውን ከወጨጫ ወደ እንጦጦ ማዛወር መሻታቸውን ያስረዳል፡፡ ከዚህ በኋላ በንጉሥ ዳዊት 1381-1410 ዘመነ መንግሥት የተሠራ ነው ተብሎ የሚታመን የጥንት ከተማ ፍርስራሽ ከእንጦጦ 15 ኪሎ ሜትር በስተሰሜን ምሥራቅ ሱሉልታ ከተባለው ሥፍራ መገኘቱንም ሰነዱ ጠቅሶ ምኒልክም ቦታውን ከጎበኙ በኋላ ‹‹እኛም ይህንን መስለን መገንባት አለብን›› በማለት በተናገሩት መሠረት እንጦጦ በዋና ከተማነት መቆርቆሯን ያስረዳል፡፡ 
‹‹በሌላ በኩል ደግሞ በጊዜው በነበረው የመከላከል ስልት እንጦጦ የአካባቢው ገዥ መሬት በመሆኑ ሌላውን ግዛት ለመቆጣጠር በጣም አመች እንደነበር ሰነዱ አልሰወረም፡፡ ዳሩ ግን እንጦጦ በተቆረቆረች በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ በአካባቢው የማገዶና የውኃ ችግር ከመፈጠሩም በላይ የአየር ጠባዩም ነፋሻማና በጣም ቀዝቃዛ፣ እያደገ ለሚሄድ ከተማ ደግሞ አመችነት የሌለው በመሆኑ፣ ከዚህ የተሻለ ሌላ ቦታ ላይ አዲስ ከተማ መመሥረት ማስፈለጉን ሰነዱ ይገልጻል፡፡ 
‹‹የእንጦጦ ለከተማ አመች አለመሆን ከግርጌዋ ወደሚገኘው ለምለም ረባዳማ ሥፍራ ለተደረገው መንቀሳቀስ ምክንያት ሆነ›› የሚለው ጥናታዊው ሰነድ፣ ምኒልክና ጣይቱም በፍልውኃ ጠበል በመማረክ በ1876 ዓ.ም. ከክረምት ወራት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ከነአጃቢዎቻቸው ከእንጦጦ ወደ ፍልውኃ በመውረድ በድንኳን መቀመጣቸውን ጠቅሷል፡፡ 
ከዚህ በኋላ ጣይቱ በአካባቢው የተፈጥሮ ውበት በመማረክ ምኒልክን ቤት የሚሠሩበት መሬት እንዲሰጧቸው ጠየቁ፡፡ ምኒልክም ፈቀዱላቸው፡፡ ፍል ውኃንም እንደጠበልና እንደመዝናኛ በመጠቀም ብዙውን ጊዜ የአካባቢው ሰዎች እየመጡ እንደሚያርፉበት አስረድቷል፡፡ 
በተለይም ምኒልክ በተለያየ ወቅት ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ በሚሄዱበት ጊዜ በፍል ውኃ (ፊንፊኔ) አካባቢ ለማረፋቸው የተለያዩ ማስረጃዎች መኖራቸውን አመልክቷል፡፡ 
በሌላ በኩል ደግሞ አፄ ምኒልክ ጥቅምት 4 ቀን 1879 ዓ.ም. ሠራዊታቸውን በፍል ውኃ ሜዳ ላይ አሰባስበው ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ሲሄዱ፣ እቴጌይቱ በበኩላቸው ከአንዳንድ የምኒልክ መኳንንት ተፅዕኖ ነፃ ለመሆን ‹‹ጠበል እጠመቃለሁ›› በሚል ሰበብ ከቤተ መንግሥቱ ውጭ በፍል ውኃ አካባቢ መቆየቱን በመምረጣቸው መኳንንቱ ለእቴጌይቱ በሥፍራው አንድ እልፍኝና ማዕድ ቤት እንዳሠሩላቸው ይኸው የባህል ሚኒስቴር ጥናታዊ ሰነድ ይተርካል፡፡ 
እቴጌ ጣይቱ በ2ኛ ደረጃ ከእንጦጦ አካባቢ ነዋሪዎችና ከደጃዝማች ወልደ ገብርኤል አባ ሰይጣን አፈንግጦ የተመለሰው የቁጥር ደሞዝተኛ ጦር አደጋ እንዳያስከትል በመሥጋት ምኒልክ ከሐረር እስከተመለሱ ድረስ በጊዜያዊነት በፊንፊኔ በተሠራላቸው እልፍኝና ማዕድ ቤት መቆየታቸውንም ሰነዱ ያወሳል፡፡ 
‹‹በመጨረሻ በንጉሡ ፈቃድና ትዕዛዝ ፊንፊኔ በዋና ከተማነት እንድትቆረቆር ተወሰነ፡፡ የንጉሡም ግቢ በአካባቢው ካለው ከ‹‹ቱሉ ፊንፊኔ›› ኮረብታ በአንድ ጋሻ (400 ሺሕ ካሬ ሜትር) መሬት ላይ ተሠራ፡፡ ዙሪያውንም ብዙ ቤቶች የምኒልክን ቤተ መንግሥት እየከበቡ መሥራት ተጀመረ፡፡ ፊንፊኔም ‹‹አዲስ አበባ›› በሚል ስያሜ የኢትዮጵያ መዲና ለመሆን በቃች፡፡
ከ1983 ዓ.ም. በኋላ በሽግግር መንግሥት ዘመን ክልልነትን፣ በኢፌዴሪ ውስጥፌዴራላዊ ግዛት የሆነችው አዲስ አበባ፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ራሷን በራሷየማስተዳደር ሥልጣኗ የሚተገብረበት ሕግ የወጣላት 1989 .ሲሆን፣በሕገ መንግሥቱም በአዲስ አበባ ቻርተርም መሠረት የከተማዋ ስምና ስያሜአዲስ አበባ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የአማርኛ ሥነ ግጥም መምህር አልፎም በመሔስ ይታወቅ የነበረው አቶ ብርሃኑ ገበየሁ እንደጻፈው፣ በአማርኛ ሥነ ግጥም የአዲስ አበባ ምስል ተደጋግሞና ተዘውትሮ የሚገኘው በትዝታና ናፍቆት ግጥሞች ውስጥ ነው፡፡ የሰው ልጅ ገነትም ሆኖ የትውልድ ቀየውን፣ በተራዛሚውም አገሩንና ወንዙን አይረሳም፤ የአማርኛ ገጣምያን ባሕር ማዶ ለትምህርት ወይ ለሥራ በስደት ሲኖሩ፤ ቃሉ ይለያይ እንጂ የዝማሬያቸው ቃና የቅኔያቸው መንፈስ፤ ‹‹ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ
   አገርም እንደሰው ይናፍቃል ወይ›› የሚል ነው

søndag 31. mars 2019

አዲስ አበባ የጽንፈኝነት ሒሳብ ማወራረጃ መሆን የለባትም!

31 March 2019

የአዲስ አበባ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ጥያቄ የማንሳትም ሆነ የመፍትሔ ሐሳብ የማቅረብ መብት አለው፡፡ በአዲስ አበባ ጉዳይ የሚደረግ ንግግርም ሆነ ውይይት፣ ክርክርም ሆነ ድርድር ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መሆን ይኖርበታል፡፡ ስለመላዋ ኢትዮጵያም ሆነ ስለአዲስ አበባ የሚነሱ ጥያቄዎችም ሕጋዊ፣ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ይዘት እንዲኖራቸው ሲደረግ የጽንፍ ግብግቦች ይወገዳሉ፡፡ ከዴሞክራሲ የጨዋታ ሕግ ያፈነገጡና የአንድ ወገን የበላይነትን ለመጫን የሚደረጉ መውረግረጎች የማያስፈልጉትን ያህል፣ በስሜታዊነት እየተነዱ ለፍጥጫ የሚዳርጉ ደመነፍሳዊ እንቅስቃሴዎችም ለማንም አይጠቅሙም፡፡ የአዲስ አበባም ሆነ የመላ አገሪቱ ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው በጉልበት ሳይሆን፣ በጨዋነትና በሠለጠነ መንገድ ብቻ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ‹አዲስ አበባ የማን ናት?› የሚለው አሰልቺ ጥያቄ ከኢትዮጵያውያን አዕምሮ ውስጥ መውጣት አለበት፡፡ ይህ የስግብግብነት መገለጫ የሆነ ጥያቄ ለአርቆ አሳቢዎቹና አስተዋዮቹ ኢትዮጵያውያን አይመጥናቸውም፡፡ አዲስ አበባ ከመላ ኢትዮጵያውያን አልፋ ልክ እንደ ኒውዮርክ፣ ጄኔቫና ብራሰልስ የዓለም ከተማ መሆኗ መታወቅ አለበት፡፡ የኋላቀሩ የጽንፈኝነት ሒሳብ ማወራረጃ መሆን የለባትም፡፡
ኢትዮጵያውያን በአዲስ አበባም ሆነ በመላ አገሪቱ የሚያሳስቧቸው በርካታ ችግሮች አሉባቸው፡፡ ከሰብዓዊና ከዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች ጀምሮ፣ እስከ መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ድረስ ከመጠን ያለፉ ችግሮች አሉ፡፡ ከድህነት ወለል በታች በሆነ ኑሮ በርካታ ሚሊዮኖች ይማቅቃሉ፡፡ የባሰባቸው ደግሞ በአደገኛ የጉዞ መስመሮች አገር ለቀው ይሰደዳሉ፡፡ እንደ ሰደድ እሳት በሚፋጅ የኑሮ ውድነት የሚጠበሱ ዜጎች ቁጥር አታካች ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ በተቃርኖ የተሞላው ፖለቲካ የአቅጣጫ መጠቆሚያ እንደሌላት መርከብ በከንቱ ይባዝናል፡፡ ኃላፊነት የጎደላቸው ግለሰቦችና ስብስቦች በእያንዳንዱ ጉዳይ ቅራኔ ሲፈበርኩ ውለው ያድራሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ቅደም ተከተልና ዋና ሥራችንን መለየት ካልቻልን፣ በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች የምንፈጥራቸው ችግሮች ተያይዘን እንድንጠፋ ያደርጉናል፡፡ በኢትዮጵያ የዛሬ ዓመት የተጀመረውን ለውጥ እያደናቀፉ ያሉት ፋይዳ ቢስ ተቃውሞዎችና ጥርጣሬዎች ናቸው፡፡ አንድ ላይ መቆም ሲቻል በተቃርኖ መለያየት መዘዙ የከፋ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ጉዳይ ሲነሳ ‹‹ልዩ ጥቅም›› የሚባለውን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ በመጥቀስ፣ ሁሉንም ነገር ለማጋበስ ማሰብ ዕብደት ነው፡፡ አዲስ አበባ በውስጧ አቅፋ የያዘቻቸው ነዋሪዎቿ (ከመላ አገሪቱ የተሰባሰቡ መሆናቸው ታሳቢ ሆኖ)፣ በዙሪያዋ ያሉ አርሶ አደሮች፣ ብዙ ነገሮችን የሚመጋገቡ ዙሪያዋን ያሉ ከተሞች፣ ወደፊት አዲስ አበባ መጥተው ለመኖር የሚያስቡ ዜጎች፣ ወዘተ. እንዳሉ መረሳት የለበትም፡፡ ስለዚህ የሁሉንም ወገኖች ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረገ ሕጋዊ፣ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ አሠራር እንዲሰፍን የሁሉም ድርሻ መሆን አለበት፡፡ ከዚህ ውጪ መተሳሰብን፣ ሰጥቶ መቀበልንና ሰብዓዊነትን እየገፉ በጉልበት እንሞካከር ማለትም ሆነ ቅራኔ መዝራት ለማንም የማይጠቅም ኋላቀርነት ነው፡፡ በየትም ዓለም እንደሚታወቀው ከተማ ይሰፋል፣ ያድጋል፣ ይዘምናል፡፡ ከገጠርና ገጠር ቀመስ ከሆኑ ከተሞች የሚመጡ ሰዎችን ይቀበላል፡፡ የግብርና ምርቶችን ከአካባቢው አርሶ አደሮች ሲወስድ፣ ለአርሶ አደሮች የኢንዱስትሪ ምርቶችን ያቀርባል፡፡ ሁለቱ በበርካታ ጉዳዮች እየተገናኙ ጥቅሞቻቸውን በፍትሐዊነት ያስከብራሉ፡፡ በዚህ ሒደት ደግሞ አንዱ ሌላውን እንዳይበድል ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡ በዚህ መንፈስ ተከባብሮና ተባብሮ መሥራት ሲቻል መቃረን ፋይዳ ቢስ ይሆናል፡፡
በአሁኑ ጊዜ እጅግ በጣም አሳሳቢ የሆነው ጉዳይ ለውጡን የሚመራው ቡድን ላይ ጥርጣሬና ተቃውሞ ማየሉ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ለውጡ ተደናቅፎ ወደ ኋላ መመለስ ከተጀመረ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማሰብ ይገባል፡፡ አሁን ዋነኛው ጉዳይ ዴሞክራሲ የሚፈልጋቸውን መሠረታዊ ነገሮች ማመቻቸትና ማበልፀግ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ንጣፍ የሆኑት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማክበር፣ የዴሞክራሲ መደላድሎችን ማመቻቸት፣ በሚለያዩ ጉዳዮች ላይ በጨዋነትና በሥርዓት መነጋገር፣ በሐሰተኛ መረጃዎች ላይ በመንጠልጠል ለፀብ አለመፍጠንና ንቃተ ህሊናን ማጎልበት ልዩ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህንን የዴሞክራሲ ጅምር በጥያቄዎችና በጫጫታዎች ጋጋታ እንዲቀጭ ዕድል ከመስጠት ይልቅ፣ ችግሮች ሲያጋጥሙ መፍትሔ ለመስጠት መትጋት ይሻላል፡፡ ከዚህ በፊት ያጋጠሙ መልካም ዕድሎች በተደጋጋሚ እንዴት እንዳመለጡ ይታወቃል፡፡ አሁንም ሌላ ዕድል ይኖራል በማለት ይኼንን ዕድል ማበላሸት የማይወጡት ችግር ውስጥ ይከታል፡፡ አዲስ አበባን የሁላችንም ናት ብሎ የበለጠ ማሳደግና ማስዋብ በታሪክ ያስከብራል፡፡
የአዲስ አበባ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ መገንዘብ ያለባቸው፣ ከጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍና ኪሳራ በመለስ ያለው የጋራ ጥቅም እንደሚበልጥ ነው፡፡ በተለይ የፌዴራል መንግሥት፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከወገንተኝነት የነፃ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ይህ ኃላፊነት ከወገንተኝነት ነፃ እንዲሆን የሚጠየቀው እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል የመሰለውን ካርድ እየመዘዘ ሲመጣ፣ የማይወጡበት ቅርቃር ውስጥ ስለሚከት ነው፡፡ በግል፣ በመንግሥት ወይም በፓርቲ የተለያዩ አቋሞችን እያንፀባረቁ ማደናገር አይገባም፡፡ ሕዝብም ይህንን ግልጽነት ይጠይቃል፡፡ በሌላ በኩል የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ የፖለቲካ አቀንቃኞች ኃላፊነት ሊሰማቸው ይገባል፡፡ ሕዝብን ለጋራ ዕድገት ከማሠለፍ ይልቅ ለማቃረን ነገር መቆስቆስ ውጤቱ ተያይዞ መጥፋት ነው፡፡ አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆኗን በመገንዘብ ለጋራ ጥቅም በአንድነት መሥራት እየተቻለ፣ መሰሪ ድርጊት ውስጥ መገኘት የታሪክና የትውልድ ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ ለነፃነት፣ ለፍትሕና ለእኩልነት ታግለናል እየተባለ አምባገነንነትን መልሶ የሚያቋቁም ድርጊት ውስጥ መገኘት ያሳፍራል፡፡ ከዚህ ዓይነቱ አሳፋሪና ከንቱ ድርጊት ውስጥ በፍጥነት መውጣት የግድ ይላል፡፡ አዲስ አበባን የጽንፈኝነት ሒሳብ ማወራረጃ ማድረግ ተገቢ አይደለምና!

lørdag 30. mars 2019

Lema Megerssa: ለማ መገርሳ 👉ስለ ከተማ ዲሞግራፊ 👉 ስለ ተቀነባበረ የስም ማጥፋት ዘመቻ 👉ስለ ኢትዮጵያዊነት 👉ስለ ኦሮሞና አማራ ህዝብ

የኦሮሚያ ክልል ዋና አስተዳዳሪ ለማ መገርሳ  
👉ስለ ከተማ ዲሞግራፊ
👉 ስለ ተቀነባበረ የስም ማጥፋት ዘመቻ
👉ስለ ኢትዮጵያዊነት 
👉ስለ ኦሮሞ እና የአማራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት  

👉ስለ ስለ ኦዲፒ-አዴፓ ግንኙነት

onsdag 13. mars 2019

አርበኞች ግንቦት 7 በሀገሪቱ እየታዩ ያሉ አጠቃላይ ጉዳዮችን በተመለከተ ያወጣው አስቸኳይ መግለጫ

አርበኞች ግንቦት 7 በሀገሪቱ እየታዩ ያሉ አጠቃላይ ጉዳዮችን በተመለከተ ያወጣው አስቸኳይ መግለጫ
ለዘላቂው የሚበጀንን ለዘብተኛውን መንገድ ትተን ዋልታ ለረገጡ አጥፊ ጽንፈኞች አገራችንን እንዳናስረክብ እንጠንቀቅ !

Image may contain: text

Image may contain: text

Image may contain: text

Image may contain: text
Image may contain: text

søndag 10. mars 2019

ዛሬ ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ላይ ነች ሲባል ሁሉም ጥያቄ በአንድ ይመለሳል ማለት አለመሆኑን ለመገንዘብ የሚያቅተን ከሆነ ነገን የተሻለ ነገር ማግኘት አንችልም፡፡

ሰላም ለሁሉም ፍላጎታችን መሳካት መሠረት ነው፡፡ ያለ ሰላም ዕቅዶቻችንንም አገራዊ ራዕያችንንም ከግብ ለማድረስ አንችልም፡፡ ሰላም ማጣት የሚያስከፍለው ዋጋ እንደዘበት አይታይም፡፡ ሕይወትና ንብረትን በማሳጣት ብቻ አይወሰንም፡፡ ሰላም ያጣ ሕዝብና አገር ማንነቱንና ክብሩን ያጣል፡፡ የውርደት ማቅ የለበሰ፣ ለተመጽዋችነትና ለእንግልት የተዳረገ እንደሚሆን የእኛው የኋላ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ 
ለሰላም ሳንካ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በመነጋገርና በመደማመጥ መፍትሔ ማግኘት ሲቻል በበሬ ወለደ ወፈ ሰማይ ወሬዎች ሳቢያ ኢትዮጵያ እየተፈተነች ነው፡፡ እንኳንና ለግጭት ለጭቅጭቅ በማያበቁ አጀንዳዎች አንዱ ሌላው ላይ ጦር እንዲያነሳ የሚደረግበት ነውረኛ ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደምናየው የግጭቶች ምንጭ ተብለው የሚጠቀሱ ጉዳዮች አንገታችንን ያስደፋሉ፡፡ እንደ ሕዝብ፣ እንደ አገር እንዲህ ያለውን ክፋትና ነውር ከየት ተማርነው የሚያሰኙ ጸያፍ ድርጊቶች በጓዳችን እያየን ነው፡፡ ነገን የማያስመኙ፣ ተስፋን የሚያሳጡ ክፋቶች የዕለት ዜና እወጃ ሆነዋል፡፡ 
ነገሩን ጠለቅ ብለን ስናየው አንዱ በሌላው ወገኑ ላይ እንዲነሳበት ጥቂት ክፉ ጠንሳሾች የሚያራግቡት ወሬ ለዚህች አገር አደጋ እየሆነ ነው፡፡ ‹‹ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው›› የሚለው የአበው አባባል እኛው ላይ የተተረተ እስኪመስል ድረስ በወሬ የሚነዳው፣ ማን አለ፣ ለምን አለ፣ እንዴት ተባለ፣ በምን ተፈልጎ ተባለ ወዘተ. የሚሉ መሠረታዊ ጥያቄዎችን በማነሳትና በመመርመር ምላሽ ከማግኘት ይልቅ ነሲበኞች ዋጋ ከፍለው ሌላውንም እያስከፈሉ ነው፡፡ 
መልካም አጋጣሚዎችን በአግባቡ ከመጠቀም ይልቅ እኔ ብቻ ከሚል እሳቤ ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› እንዳለችው እንስሳ በየቦታው በተቧድኖ የሚደረጉ ግርግሮች ሰላምን በማወክ ለውድቅት እያንደረዱን ነው፡፡ ጨዋነትን በመቃረን የራስ ፍላጎትን ለመጫንና ለማስተግበር ማሴር እየተበራከተ ነው፡፡ አንዱ ሌላውን ችሎና ተጋግዞ፣ ያለችውን ተቃምሶ ይኖር የነበረውን የኅብረተሰብ ክፍል፣ ያለፍላጎቱ በመጎትጎትና በማስገደድ ጭምር የሚፈጸም ጥቃት እየባሰበት ሲመጣ እያየንም እየሰማንም ነው፡፡ አንዳንዴም በጋራ መኖር ጥቅማችንን ይነካናል የሚሉና አሻግሮ ነገን የመመልከት አቅም ያነሳቸው ጥቂት ግለሰቦች በማንነት ስም የሚለኩሱት የጥፋት ክብሪት መልሶ ራሳቸውን እንደሚፈጃቸው አያውቁም፡፡ ወይም ደግሞ አውቀውም አጥፍቼ ልጥፋ ያሉ ይመስላሉ፡፡ 
በታሪኳ የተፈናቀሉትን የምታስጠልለው፣ የተሰደዱትን የምታስጠጋው ኢትዮጵያ የዓለም ቁንጮ ተፈናቃዎች ምንጭ ሆና መገኘቷ እንደ ሕዝብ ለእኛ ከውርደት በላይ የሕልውናችን ማክተም ምልክት እየቀረበ የመምጣቱ ፍንጭ እንዳይሆን ማሰብ ይኖርብናል፡፡ 
በግጭት ያተረፉ ይኖራሉ፡፡ የግጭት ነጋዴዎች ግን ለልጆቻችን ነገን ለሚያስናፍቁን እንቦቅቅላዎቻችን፣ ለወጣቶችና ጎምሶቻችን፣ ለቅርሶቻችንና ለመከበሪያ ማንነታችን ቦታ የሌላቸው በሰው ቁስል እንጨት የሚሰዱ፣ በሰው ሲቃ የሚንደላቀቁ የደም ከበርቴዎች እንደሆኑ ብንገነዘብ የሚያጣላን ችግር ምንኛ ኢምንት እንደሆነ በተረዳን ነበር፡፡ 
ተወደደም ተጠላ በለውጥ መንገድ ላይ በኩራት ለማራመድ የኢትዮጵያችን ሰላሟ መጠበቁ ግድ ነው፡፡ ጥያቄ አለኝ፣ ችግር ደርሶብኛል ተጎድቻለሁ የሚለው አካል ሁሉ ለሚያነሳው ጉዳይ ምላሽ መስጠት የሚጠበቅበት አካል ኃላፊነቱን በሐቅና በአግባቡ በመመለስ ከግርግርና ካለመተማመን የፀዳ ማኅበረሰብ በመፍጠር ችግሮችን የመፍታት አቅም ማዳበር አለበት፡፡ ለዚህ መተባበርና መነሳት የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት ነው፡፡ 
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንዳየነው የአገር ሽማግሌዎች የሃይማኖት አባቶች አባገዳዎች ያበረከቱዋቸው አስተዋጽኦ እንደ ምሳሌ የሚወሰድና ሽማግሌ አያሳጣን ብለን እስከማወደስ የደረስንባቸውን የመረጋጋት ሥራ ተሠርተዋል፡፡
ነገር ግን ካለው ችግር አንፃር አሁንም በየባህሉና በየሃይማኖቱ አንቱ የተባሉ ሽማግሌዎች ተግባር የተገኘው መረጋጋት በአግባቡ መጠቀም ካልቻልንና በሰበብ አስባቡ ለግጭትና ለልዩነት በር የሚከፍቱ አጀንዳዎችን ይዞ በመምጣት አንፃራዊን ሰላም መልሶ የሚበርዝ ከሆነ የሽምግልና ትርጉሙ አልገባንም ማለት ነው፡፡ ደግሞም  እዚህም እዚያ ለሚከሰቱ ግጭቶች ሁሉ ሽማግሌዎችን እያፈላለጉ መዝለቅ አይቻልም፡፡ ዜጎች ራሳቸውን መግራት፣ እንዴት ተባብሮ መኖር እንደሚገባን በማሰብ ካልተራመድን አገርን በጋራ ለማራመድ ይቸግራል፡፡  
ስለሰላም የሚያስተምር አባት እንዴት እናጣለን፡፡ የሰላምን አስፈላጊነት ለመረዳት ከእልቂታችን መማር አይጠበቅብንም፡፡ እንደሞኝ ከራሳችን ሳይሆን ከሌሎች ለመማር የሚያበቁ በርካታ እልቂቶችን በዚያችን አይተናል፡፡ እያየንም ነው፡፡ ስለዚም የሰላም አስተማሪዎች ሊበራከቱልን ይገባል፡፡ በልጆቻችን ዘንድ ስለፍቅርና አንድነት፣ መልካምነትና መተሳሰብን በማስረጽ የነገ ሕይወታቸው እንዲያበራ በማድረግ በኩል ወላጆች፣ ጎረቤትና ሰፈር አድባሩ አለሁ ይመለከተኛል ሊል ይገባዋል፡፡
ሰላም የሁሉ ነገር መሠረት ነው የሚባለው አውቀንም ሆነ ሳናውቅ በፈጠርነው ግጭት በሚፈሰው ደም በመውደድ የግልና የአገር ሀብት እንዳይባክን ማድረጉ ብቻ አይደለም፡፡ ሰላም ከሌለ ነግዶ ማትረፍ የለም፡፡ እያንዳንዷ ግጭት ኢኮኖሚው ላይ የሚማረረው ተፅዕኖ ሁሉንም ይጎዳል፡፡ ጉዳቱን ለማካካስ ደግሞ የበለጠ ያደክማል፡፡ ጠባሳውንም መሻር ለየቅል ይችላል፡፡
ስለዚህ በሰበብ በአስባቡ እየተነሱ ሰላምን የሚያናጉ ተግባሮችን መፈጸም የማይሽር ጠባሳ ከህሊና የማይወጣ ፀፀትም ያስከትላል፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ላይ ነች ሲባል ሁሉም ጥያቄ በአንድ ይመለሳል ማለት አለመሆኑን ለመገንዘብ የሚያቅተን ከሆነ ነገር የተሻለ ነገር ማግኘት አንችልም፡፡ ሁሉም ተነስቶ አዋቂና ፈራጅ ላለመሆን የሚሻ ከሆነም ለውጥ መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡
በለውጡ የተገኘውን መልካም ጅምር ለማስቀጠል ከተፈለገ ሰላም ወሳኝ እንደመሆኑ ሁሉ ዕድሉን በአግባቡ መጠቀም እንዳይችል እንቅፋት መሆን ነገን ማበላሸት ነው፡፡ 
ነገሮችን ረጋ ብሎ ማመዛዘን የሚኖርብን ጊዜ ላይ ነን፡፡ በየፌስቡኩ የሚዥጎደጎደውን ክፉ ክፉ ነገር እየለቀሙ እሱንም እያራገቡ ነገር ማቀጣጠሉ የሚመረጥ ከሆነ ይህችን አገር እያበጀናት አይደለም፡፡ ዛሬ ለውጡን የሚመሩ አካላት የእስካሁን ጉዞ ብዙ ተስፋ እየሰጠ የመሆኑን ያህል ይኼንን ተስፋ ለማጉበጥ የሚደረጉ ጥረቶች የተሻለ ነገር እንደሚያመጡ እየታወቀ ጥቂቶች የሚያራምዱት አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ቆም ተብሎ ሊታሰብባቸው ይገባል፡፡ ሰላም እያሳጡ ሰላም ማምጣት እንዳልተቻለ አድርጎ ማንፀባረቅም በጎ አይደለም፡፡ 
በተለይ አግባብም ይሁን አግባብ ስለመሆኑ የማይታመንባቸው ጥያቄዎችን የሚያቀርቡ አካላት ፈራጅም ሆነው መታየታቸው ነገር ብዙ የሚያነጋግር ቢሆንም ሁሉም እንደ ዜጋ ባለበት ኃላፊነት አቋሙን ያንፀባርቅ እንጂ እኔ ብቻ አይሆንም፡፡
በአጠቃላይ የዚህች አገር የሰላም መጓደል ዕድሜ በተራዘመ ቁጥር ለሥርዓት አልበኝነትም በር እየከፈተ ስለሚሄድ ብዙ ነገር ሊያሳየን ይችላል፡፡ ስለዚህ አሁንም የሕግ ማስከበር ሥራ በብርቱ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ዛሬ ዝም ብለን የለቀቅነው ነገር ለሕግ ተገዥ የሆነ ኅብረተሰብ በእኩልነት የሚያምን ትውልድ ሊኖረን ይገባል፡፡
10 March 2019

mandag 11. februar 2019

የሶርያ ኃይሎች በአማፅያን ቡድን የተያዙ ቦታዎችን ማስመለሳቸውን ገለፁ


የካቲት 11, 2019
ፎቶ ፋያል
ፎቶ ፋያል
በዩናይትድ ስቴትስ የሚደገፉት የሶርያ ዲሞክራስያዊ ኃይሎች እስላማዊ መንግሥት ነኝ በሚለው ፅንፈኛ የአማፅያን ቡድን ተይዘው የነበሩ 41 ቦታዎችን አስመልሰናል አሉ።
በዩናይትድ ስቴትስ የሚደገፉት የሶርያ ዲሞክራስያዊ ኃይሎች እስላማዊ መንግሥት ነኝ በሚለው ፅንፈኛ የአማፅያን ቡድን ተይዘው የነበሩ 41 ቦታዎችን አስመልሰናል አሉ። እስላማዊ መንግሥት ነኝ የሚለው ቡድን ከሚቆጣጠረው የመጨረሻ ምሽግ ለማባረር እየተዋጉ መሆናቸው ታውቋል።
"ሙስጣፋ ባሊ" የተባለው የሶርያ ዲሞክራስያዊ ኃይሎች ቃል-አቀባይ ባግሁዝ በተባለው መንደር የነበረውን የጽንፈኛው ቡድን ምሽግን አፍርሰናል ሲል በትዊተር አስታውቋል። ይሁንና ከባድ ውጎያ መቀጠሉን ሳይገልፁ አላለፈም።

ቀራፂ በቀለ መኮንን ስለ አፄ ኃይለ ሥላሴ ሐውልት ይናገራል



Image copyrightFANA TVሠዓሊና ቀራፂ በቀለ መኮንን
Image captionሠዓሊና ቀራፂ በቀለ መኮንን
ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረት ጉልህ ሚና ከነበራቸው መሪዎች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሱት የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ የመታስቢያ ሐውልት በአፍሪካ ሕብረት ቅጥር ጊቢ ውስጥ የካቲት 03/2011 ዓ.ም ተመርቋል። 
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የአፍሪካ ሕብረት አዲስ አበባ ውስጥ በሚያካሂደው 32ኛ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የመጡ የሃገራት መሪዎች እና የተጋበዙ እንግዶች ተገኝተዋል። የእርሳቸው ሐውልት መቆሙንም ተከትሎ በርካቶች ሲነጋገሩበት ነበር።
ሐውልቱን ከቀረፁት ቀራፂያን መካከል በግምባር ቀደምትነት የሚጠቀሱትን ሰዓሊና ቀራፂ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር በቀለ መኮንንን አነጋግረናል። 
ቢቢሲ፡ የቆመው ሐውልት ጃንሆይን አይመስልም የሚሉ አስተያየቶች ሲሰሙ ነበር። ለዚህ ያለህ ምላሽ ምንድን ነው?
በቀለ፡ አንድ ሥራ ተሰርቶ ሲጠናቀቅ ብዙ ዓይነት ሃሳብ እንደሚመጣ ይጠበቃል። ሃሳቦቹ ትክክል ናቸው ማለት ግን አይቻልም፤ እኔም ሰምቻቸዋለሁ። ስለዚህ ይህንን አስተያየት የሰጡት በሙሉ ንጉሡንም ሐውልቱንም አይተዋቸው አያውቁም። 
ይህንን ሃሳብ ይዘው ሲጨቃጨቁ የነበሩት አንድ ተማሪ በስርቆሽ ያነሳውን የሐውልቱን ፎቶ ይዘው ነው፤ ዛሬ ላይ ሳይ ቀረብ ብለው ሐውልቱን የጎበኙ ሰዎች 'አፉ በሉን! 'እያሉ ሲለጥፉ አይቻለሁ። (ሳቅ) ፎቶ ሲነሳ ጥንቃቄና ሙያ ይጠይቃል እንግዲህ ንጉሡ አልፈዋል (ሳቅ) የቢቢሲው ጋዜጠኛ ያነሳውን ፎቶግራፍ ገፃችሁ ላይ አይተው በእርሱ መዳኘት ይችላሉ። የንጉሡ ቤተሰቦችም በእያንዳንዱ ሒደት ይጎበኙት ነበር፤ አሁን ባለውም ደስተኞች ናቸው።
ቢቢሲ፡ ሐውልቱን ለመስራት እንደ ሞዴል የተጠቀማችሁት ፎቶ ግን የትኛውን ነው?
በቀለ ፡ ከ300 ፎቶግራፎች በላይ ከተለያዩ ቦታዎች ተሰብስበው ስናጠና ነው ቆየነው፤ ቅርፅ ለመስራት አንድ ፎቶ ብቻ መጠቀም አይቻልም፤ በእርግጥ እርሳቸውን መግለፅ ይኖርበታል። አንድ እንግሊዛዊ ቀራፂ ንጉሡ በሕይወት እያሉ እንግሊዝ በቆዩበት ጊዜ አጠገባቸው ሆኖ እያየ ሁለት ሦስት መልክ ያለው ሐውልት ሰርቷል። የጥበብ ሥራ በመሆኑ ቅርፁን ስታይው ጃንሆይን አይመስሉም። 
በመሆኑም በአፍሪካ ኅብረት ምስረታ ጊዜ የነበሩ ፎቶግራፎች ብዙ ናቸው። ወደ 100 የሚሆኑ በአፍሪካ ህብረት ምስረታ ወቅት የነበሩ ፎቶዎችን ሰብስበናል። እንግዳ ሲቀበሉና ስብሰባ ሲያደርጉ የሚለብሷቸው ልብሶችና የሚገልጿቸው አካላዊ ገለፃዎች ላይ ተመስርቶ ተሰራ እንጂ የአንድ ፎቶግራፍ ውጤት ብቻ አይደለም።
ቢቢሲ ፡ የተጠቀምከው ጥበባዊ ግነት አለ?
በቀለ፡ በትክክል! እጃቸውና ደረታቸው ላይ፤ ደረታቸው አካባቢ ገነን ለማድረግ ሞክረናል። የጠቢቡ ነፃነት የሚባል ነገር አለ አይደል? በማይበላሽና ከስርዓት በማይወጣ መንገድ ገነን ለማድረግ ሞክረናል። ሌላው ሰውነታቸው መለስ ይላል። በእርግጥ በአካልም እንደዚህ ነበሩ፤ እጃቸውንም ሲፅፉ እንደሚታየው፤ እኛም ዳቦ ስንቀበል እንዳየነው ሎጋ ቀጠን ቀጠን ያሉ ጣቶችን በማድረግ የምንችለውን ሁሉ አድርገናል። 
ቢቢሲ፡ ሐውልቱ ከምንድን ነው የተሰራው?
በቀለ፡ የተሰራው ከነሃስ ነው። 
ቢቢሲ፡ በቀላሉ በዝናብና በፀሀይ እንዳይበላሽ የተለየ ጥበብ ተጠቅማችኋል ?
በቀለ፡ ነሃስ የሚመረጠው ለዚህ ነው፤ ዓለም ላይ ለልዩ ጉዳዮች ካልሆነ በስተቀር የህዝብ ሐውልቶች ብዙ ጊዜ የሚሰሩት በነሃስ ነው። በነሐስ እንዲሰሩ የሚፈለገው በውስጣቸው ያለው አብዛኛውን የሚይዘው መዳብ ነው፤ መዳብ ደግሞ ኦክስጅን ስለሚይዝ አሮጌ ሲሆኑ የሻገተ አረንጓዴ ይሆናሉ።
እናም ኦክስጅን እንዲስብ አድርገን ነው የሰራነው ይህም አካበባቢውን እንዲመስልና በጊዜ ሂደት መልኩ እንዲለወጥ ይፈለጋል...ያ እንዲሆን አድርገን ነው የምንሰራው። ጠንካራ ብረትም ስለሆነ አይሰበርም አይሸማቀቅም፤ ነገር ግን ኦክስጅን ይወስዳል... ልክ መዳብ ያላቸው ሳንቲሞች ሲቆዩ እንደሚፈጥሩት ቀለም ዓይነት፤
ቢቢሲ፡ ቀመቱና ክብደቱ ምን ያህል ነው?
በቀለ ፡ ከነመቆሚያው ወደ ሦስት ሜትር ነው። ይህም የእርሳቸውን ቁመት ሁለት እጥፍ ይሆናል ማለት ነው። ክብደቱ ደግሞ ከ650 እስከ 680 ኪሎግራም ይመዝናል። በትክክል ይታወቃል ነገር ግን ሲበየድ የተጨመሩ የብየዳ ብረቶች ኪሎ ስለሚጨምር ነው የ30 ኪሎ ግራም እንደ ግምት የተቀመጠው።
ቢቢሲ፡ የት ነው የተሰራው?
በቀለ፡ የሸክላ ሞዴሉ አዲስ አበባ የኒቨርሲቲ ሲሆን ቀሪው ሥራ የተከናወነው እንግሊዝ ኤምባሲ አካባቢ በተከራየነው ቤት ነው። ቁርጥራጮቹን ይዘን የመጨረሻውን ሞዴል የሰራነው በእኔ ስቱዲዮ ውስጥ ነው።
በአፍሪካ ኅብረት የቆመው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ
Image captionበአፍሪካ ኅብረት የቆመው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ
ቢቢሲ፡ ሐውልቱ ተቀርፆ ለመጠናቀቅ ምን ያህል ጊዜ ፈጀ?
በቀለ፡ እንደሌሎች አገራት ለጥበብ ሥራዎች የሚሆኑ ግብዓቶች የማግኘት እድሉ ባለመኖሩ ረዘም ያለ ጊዜ ፈጅቶብናል ... ስድስት ወር አካባቢ ነው የፈጀው።
ቢቢሲ ፡ ሥ ራው ወደ እናንተ የመጣው እንዴት ነበር ?
በቀለ፡ እኔ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው የማስተምረው፤ እኔን ቢያነጋግሩኝም በዩኒቨርሲቲው ያሉ ባለሙያዎችን በቡድን ነው ስንሰራ ቆየነው። ፕሮፌሰር ዘይኑ፣ ተመራቂ ተማሪ የሆነው አቶ ሔኖክ አዘነና ሌሎች በነሃስ ጥበብ ላይ ሙያ ያላቸው ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል።
ቢቢሲ፡ ምን ያህል ገንዘብ ወጣበት?
በቀለ፡ ብዙ ነው የፈጀው... እ... እስካሁን አልደመርኩትም ብዙ ገንዘብ ነው የወጣበት። ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ተፈላጊውን ውጤት ለማምጣት የሰው ጉልበትም በጣም የበላ ነው።
ቢቢሲ፡ እንደው ገንዘቡን ከእዚህ እስከዚህ ብሎ ማስቀመጥ ይቻላል?
በቀለ፡ ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ ነው፤ ለሂደቱ የሚያስፈልጉ ኬሚካሎች አሉ አገር ውስጥ የሌሉ... ቁሳቁሶች አሉ .. በጣም ብዙ ነገሮች አሉ ...
ቢቢሲ፡ እንደው በትክክል ባይሆንም ስንት አወጣ ማለት እንችላለን?
በቀለ፡ ከ1.5 ሚሊየን ብር በላይ ነው ለማቴሪያል ብቻ የወጣው።
ቢቢሲ፡ ምን ያህል ነው የተከፈላችሁ?
በቀለ ፡ ታክስ ይኖራል... ገና ነው ...ሰርተን ያስረከብነውም ሰሞኑን ስለሆነ ቀስ ብለን የምናየው ነው የሚሆነው ...ብዙ ገንዘብ አይኖረውም ትንሽ ስለሆነ፤ የሥራውን ጥበባዊም ሆነ የሰው ኃይል ዋጋውን እንደማይመልስ ግን አረጋግጣለሁ።
ቢቢሲ፡ የገጠማችሁ ተግዳሮት ምንድን ነው?
በቀለ፡ ብዙ ነገር የተሳካ ነበር ማለት ይቻላል፤ የግብዓት ጉዳይ ግን እጥረት ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ጠፋ ማለት ይቀላል። ከእርሳስ አቅም እራሱ አላሰራ እስኪል ድረስ ... ልክ የጋፋት የቴዎድሮስ ሰዎች አፈር አቅልጠው ብረት ሥሩ እንደተባሉት ዓይነት ነገር ነው። ብቻ በጥንታዊው መንገድም ቢሆን ብዙ የሰው ኃይል በመጠቀም ወደሚፈለገው ነገር መጥተናል። 
ቢቢሲ ፡ የሐውልቱን ወ ጪ የሸፈነው ማነው?
በቀለ ፡ ኢትዮጵያን ወክሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው። 
ቢቢሲ፡ ሌላ ተባባሪ አካል የለም?
በቀለ፡ እኛ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ነው የምንገናኘው
ቢቢሲ፡ ከዚህ በፊት በሌሎች አገራት ከተሰሩት የቀዳማዊ ኃይለ ሥ ላሴ ሐውልቶች ይህን ለየት የሚያደርገው ምንድን ነው?
በቀለ፡ በዚህ መጠን ሙሉ ነሃስ ተሰርቶ አያውቅም። የትም አገር፤ የትም ቦታ! የእርሳቸውን መጠን ሁለት እጥፍ ተሰርቶ አያውቅም እሱ ነው ለየት የሚለው።
ቢቢሲ፡ ሐውልቱ መቆሙን ተከትሎ የተቃውሞና የድጋፍ ሀሳቦች እየተንሸራሸሩ ነው፤ ይህንን እንዴት ትመለከተዋለህ?
በቀለ ፡ ኖርማል ነው... ጤና ነው ብዬ ነው የማስበው። ሰው አንድ ዓይነት አይደለም። አንድ ዓይነት አለመሆኑም ጥሩ ነው፤ አንዳንዴ የኛ የሚከፋው እ... ነገራችንን ሁሉ የክፋት የክፋት መንገዱን ሁሉ እየነቀስን እየነቀስን.. እዚች አገር አንድም ጥሩ፣ እንድም ደግ፣ አንድም አዋቂ፣ አንድም ፃድቅ እንዳይኖር እስከማድረስ ድረስ እንሄድና ፅንፋዊ ሆነን ራሳችን ማጥፋታችን ነው እንጂ የሚከፋው... እየሱስም ተቃዋሚ ነበረው አይደል ? ተቃዋሚ መኖሩ አይደለም ክፋቱ እኔ ከሌለሁበት ሁሉንም ነገር ይጥፋ የሚል ነገር አለብን፤ እሱ ነው ክፉ ነገር እንጂ የተወሰኑ ሰዎች ቢቃወሙ ጤነኛ ነገር ነው ብየ አስባለሁ።
በተለይም እርሳቸው ከሄዱ በኋላም ብዙ የሰራናቸው ያጠፋናቸው ነገሮች አሉ። እነርሱን የምንቆጥር ከሆነ እንዳልኖርን ነው የሚቆጠረው፤ ቢያንስም ቢበዛ ደግ ደጉን ስናነሳ ነው እንደ እድሜ የምንቆጥረው ጊዜውን... 
ቢቢሲ፡ ሐውልቱ በመቀረፁ እንደ ግለሰብ ምን ተሰማህ?
በቀለ ፡ ልጅም ሆኜ ቢሆን አስታውሳቸዋለሁ ከእጃቸው ዳቦና ብር ተቀብያለሁ፤ ብዙ ጊዜ አይቻቸዋለሁ። ታሪካቸውንም እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ አውቃለሁ፤ ትልቅና ኢትዮጵያን ያኮሩ ሰው አንደሆኑ፣ በተለይ ከእርሳቸው በኋላ ኢትዮጵያ ምን እንደሆነች እንደኛ ኖሮ ለሚያውቅ ሰው ቢመለከት ከእርሳቸው ምን እንደታጣ ማመዛዘን ስለሚችል ይህን ሁሉ ስታስቢ እንዴት ደስ ላይል ይችላል? 
ቢቢሲ፡ ስለ እርሳቸው ምን ትውስታ አለህ?
በቀለ፡ እንግዲህ ተወልጄ ያደኩት ደብረዘይት ነው፤ አሁንም ከደብረዘይት አልተነጠልኩም፤ ጃንሆይ ደብረ ዘይት በየሳምንቱ ይመጡ ነበር። ለመዝናኛ ይመርጧታል።
ያኔ ከዘጠኝ ዓመት አንበልጥም ያን ጊዜ ሕፃናት ተሰልፈን ስንጠብቃቸው እንግዳ ያዙም አልያዙም ይቆማሉ፤ ቆመው ብርና ዳቦ ይሰጡናል። አርብ አርብ ደብረዘይት ቅዳሜና እሁድን ለማሳለፍ እንዲሁም ለማስቀደስ ይመጣሉ፤ እንጠብቃቸዋለን።
የእጃቸው ስስነት ያ የሚነገርላቸው ግርማ ሞገስ በተለየ ዓይን ነበር የምንመለከታቸው። እቤት ደግሞ ገንዘቡን ስንሰጥ የብዙ ልጆች እናት ገንዘቡ በረከት እንዲኖረው ተብሎ ከእንጀራ ስር ይቀመጣል።
ይህ ሕብረተሰቡ ምን ያህል ለንጉሡ ታማኝ እንደነበረ የሚያሳይ ነው። ዓለምም እንደዚህ ነው የሚያያቸው፤ ምንም ይሁን ምን ብዙ ታሪክ ያላቸው ሰው ናቸው።