fredag 28. november 2014

ሰበር ዜና – ከ40 በላይ የአንድነት አባላትና አመራሮች በቃሊቲ እስር ቤት ታገቱ

የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስራት አብርሃን ጨምሮ ከአርባ በላይ የሚሆኑ የፓርቲው አባላት ቃሊቲ እስር ቤት ውስጥ ታገቱ፡፡
አንድነት ፓርቲ የሚሊዮኖች ድምፅ ለህሊና እስረኞች በሚል መሪ ቃል ከህዳር 14 ጀምሮ እያካሄደያለው የማህበራዊ ሚዲያ ንቅናቄ አካል የሆነውን የህሊና እስረኞችን የመጎብኘት መርሀ-ግብር ለመሳተፍ ወደ ቃሊቲ እስር ቤት ያቀኑት የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስራት አብርሃ እና የፓርቲው የአዲስ አበባ ሰብሳቢ አቶነገሰ ተፋረደኝን ጨምሮ 40 የአንድነት ፓርቲ አባላት ለግዜው ምክንያቱ ባልታወቀ ሰበብ በእስር ቤቱ ግዜያዊ ማቆያ እንዲገቡ መደረጋቸውን የፍኖተ ነፃነት ምንጮች ከስፍራው ዘግበዋል፡፡
አንድነት የሚሊዮኖች ድምፅ ለህሊና እስረኞች በሚል መሪቃል በዚህ ሳምንት እያካሄደ ያለው ንቅናቄ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን ትኩረት ማግኘቱ ገዢውን ቡድን ማስቆጣቱ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
a1a2a3

onsdag 26. november 2014

ሰማያዊ ፓርቲን ያቀፈው የ9 ፓርቲዎች ትብብር በመንግስት አፈና ትግሉን እንደማያቆም አስታወቀ

ትብብሩ ባወጣው መግለጫ ህዳር 21 ለሚደረገው ስብሰባ ለመስተዳድሩ የሰለማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል ደብዳቤ ቢላክለትም ለመቀበል ፈቃደኛ ካለመሆኑም በተጨማሪ፣ ስብሰባውን የሚያስተባብሩት የመኢዴፓ ሊቀመንበርና የትብብሩ ገንዘብ ያዥ የሆኑት አቶ ኑሪ ሙደሲር ላይ የድብደባ ወንጀል እንደተፈጸመባቸው ገልጿል።‹‹ነጻነታችን በእጃችን›› ነው የሚለው ትብብሩ፣  በኢህገመንግሥታዊና ኢዲሞክራሲያዊ እርምጃዎች ወደኋላ እቅዱን በህጋዊ መንገድ ለማስቀጠል እስከ ህይወት መስዋትነት ለመክፈል ያለውን ቁርጠኝነት ገልጿል።
ገዢው ፓርቲ ከአፈና ድርጊቱ እንዲገታና ለቀረበው  ህጋዊ የዕውቅና ጥያቄ በአስቸኳይ መልስ እንዲሰጥ፣  የትግሉ አላማ የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በመሆኑ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለቀጣዩ ሠላማዊ ትግል የሚቀርበውን ጥሪ በንቃት እንዲከታተሉና ከፓርቲዎች ጎን እንዲቆሙ፣ በትብብሩን ያልተቀላቀሉ ፓርቲዎች እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር እና የትብብሩ መሪ ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት የትኛውንም ዋጋ ከፍለን ነጻነታችንን ማስመለስ ከሁሉም በላይ ዋጋ የምንሰጠው ነው ብለዋል። እቅዳቸው መስዋትነት ሊያስከፍል እንደሚችል የገለጹት ኢ/ር ይልቃል፣ አስፈላጊውን መስዋትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። ኢህአዴግ ለመግደልና ለማሰር ቆራጥ የሆነውን ያክል፣ እኛም ለመሞት ቆርጠናል ብለዋል
በሌላ በኩል ደግሞ በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የተከሰሱት አራቱ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች እና ስድስት ተከሳሾች  የክስ መቃወሚያ እንዲያቀርቡ ለታህሳስ 9 ቀን 2007 ዓ.ም ከፍተኛው ፍርድ ቤት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ የሺዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታ እና ዳንኤል ሺበሽ በሚገኙበት የክስ መዝገብ የተከሰሱት አስሩም ተከሳሾች  ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡ ሲሆን፣  የተከሳሽ ጠበቆች በጠየቁት መሰረት የተከሳሾቹን የክስ መቃወሚያ ለመቀበል ፍርድ ቤቱ ለታህሳስ 9/2007 ዓ.ም ቀጠሮ መስጠቱን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል። ተከሳሾች በሽብርተኝነት ወንጀል መከሰሳቸው የሚታወቅ ነው። አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ክሱ ፖለቲካዊ ነው በማለት ውድቅ ያደርጉታል።

torsdag 20. november 2014

የማንዴላን ጽዋ የተጎነጨው ሃብታሙ አያሌው (በዳዊት ሰለሞን

በ1972 የበጋ ወራት ኔልሰን ማንዴላ ከ27 ዓመት የእስር ፍርዱ 18ቱን ዓመት ወደሚያሳልፍበት ሮቢን ደሴት መጣ፡፡ጠባብ በሆነች ክፍሉ ወለሉ መኝታው፣ መጸዳጃው ደግሞ ቅርጫት ነበረች፡፡ ከባድ ስራ እንዲሰራም ይገደድ ነበር፡፡በዓመት ውስጥ ለ30 ደቂቃ እንዲጎበኘው የሚፈቀድለት ለአንድ ሰው ብቻ ነበር፡፡ በየስድስት ወራቱ አንድ ደብዳቤ እንዲቀበልና እንዲጽፍ ይፈቀድለት ነበር፡፡››

ሐብታሙ አያሌው ደቡብ አፍሪካ ያስተናገደችውን የዓለም ዋንጫ ለመመልከት ወደ አገሪቱ ባቀናበት አጋጣሚ ከልቡ የሚያደንቃቸው ኔልሰን ማንዴላ ለ18 ዓመታት የታሰሩባትን ታሪካዊዋን ክፍል በመጎብኘት የመታሰቢያ ፎቶ ግራፍ ተነስቶ ነበር፡፡

 የጸረ አፓርታይድ ትግል እንዲቀጣጠልና ጥቆሮች በገዛ አገራቸው ባይተዋር የሚሆኑበት የነጮች አገዛዝ እንዲያከትም ኢትዮጵያ ድረስ መጥቶ ወታደራዊ ስልጠና የወሰደው ማንዴላ በሮቢን አይስላንድ ከዓለም ተነጥሎ እንዲቀር ብዙ መከራ ተቀብሏል፡፡

 ወጣቱ ሐብታሙ በአእምሮው ይህንን እያሰላሰለ የነጻነት መንገድ ውጣ ውረድ እየታየው ገጽታውን ለካሜራ ባለሞያ የሰጠ ይመስለኛል፡፡ሐብታሙ በዚያን ወቅት የበሰለ እንጀራ ሌሎች ጋግረው እርሱ እንዲበላ ብቻ የሚጠበቅ ሰው ነበር፡፡

 ልክ ሙሴ በፈርኦን ቤት አድጎ የፈርኦን ልጅ መባልን በመጠየፍ የተራ ሰው ህይወት መምራት እንደጀመረ ሐብታሙም ሮቢንን የጎበኘው ‹‹ኢህአዴግ የጋገረውን እንጀራ ከመብላት ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኝ የዘመናችን ሮቢን (ማዕከላዊ) መታሰርን እየመረጠ ነበር፡፡

 ሐብታሙ ከደቡብ አፍሪካ መልስ ‹‹አንድነታችን ከልዮነታችን በላይ ነው›› በሚል መሪ ቃል ‹‹አንድነት›› የሚል ቃልና ስም አምርሮ ከሚጠየፈው ኢህአዴግ ጋር ትግል ጀመረ፡፡

 ሮቢንን የጎበኘው ሐብታሙ የማንዴላ መንፈስ ተጠናውቶት የኢትዮጵያ ፖለቲካ መፍትሄ ፍቅር፣መቻቻልና ብሄራዊ እርቅ ማድረግ መሆኑን መስበክ ቀጠለ፡፡

 ይህ ለኢህአዴግ ተንበርካኪነት፣የኒኦ ሊበራሊዝም አቀንቃኝነትና የነፍጠኞች አካሄድ ነው፡፡ ሐብታሙም ጥርስ ውስጥ ገባ፡፡ ‹‹ኢህአዴግ ከታሪክ ይማር›› የሚለው ውትወታው ጆሮ አለማግኘቱ ይታወቅ ዘንድም በአንድ ማለዳ ብሶት የወለዳቸው ነፍጥ አንጋቾች ሐብታሙን መሬት ላይ አስተኝተው እየጎተቱት ማዕከላዊ (ሮቢን) አስገቡት፡፡

 ሐብታሙ በኢትዮጵያው ሮቢን ቅዝቃዜው አጥንት ሰብሮ በሚገባ ክፍል ውስጥ ታስሯል፣ መኝታው ወለሉ ናት፤ ለወራት ቤተሰቦቹን እንዳያገኝ ጠበቃውም እንዳይጎበኙት ተደርጓል፣ ድብደባ ተፈጽሞበታል፣ ህክምና እንዳያገኝ ተደርጓል፣ ያልፈጸመውን ነገር እንደፈጸመ በማድረግ ቃሉን እንዲሰጥ ተገድዷል፣ክፍሉ በጨለማ የተዋጠች ከመሆኗም በላይ ከሌሎች እስረኞች ጋር እንዳይገናኝ ተወስኖበታል፡፡
ሐብታሙ ሮቢንን ሲጎበኝ
ሐብታሙ ሮቢንን ሲጎበኝ

የማንዴላ መንገድ በኢትዮጵያ ተመሳሳዩን ጽዋ እንደሚያስጎነጨው ተገንዝቧል፡፡ እናም ጽዋዋን ለመጠጣት የማንዴላ መንፈስ እንዲረዳው ጸሎት አድርጓል፡፡
But Robben Island became the crucible which transformed him. Through his intelligence, charm and dignified defiance, Mandela eventually bent even the most brutal prison officials to his will, assumed leadership over his jailed comrades and became the master of his own prison. He emerged from it the mature leader who would fight and win the great political battles that would create a new democratic South Africa.
በሮቢን ደሴት የብረት ግግር የተቆለፈበት ማንዴላ በዚያ የሚገኙ አረመኔ የእስር ቤት ሃላፊዎችን ልብ በማሸነፍ በሳል መሪ ሆኖ እንደወጣ ሁሉ ሮቢንን የጎበኘውና በኢትዮጵያው ሮቢን (ማዕከላዊ) የሚገኘው ሐብታሙም በዚሁ መንፈስና ጥንካሬ እንደሚወጣ እምነታችን ጽኑ ነው፡፡

 

“ሃና ናት” ተብሎ የተሳሳተ ፎቶ በመሰራጨት ላይ ነው

በቅርቡ ታፍና ከተወሰደች በኋላ; አስገድዶ መደፈር የደረሰባት እና ህይወቷ ያለፈው ወጣት ሃና ጉዳይ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው:: ከዚሁ ጋር ተያይዞ ታዲያ የሷ ያልሆነ ፎቶ በፌስቡክ እና በአንዳንድ ድረ ገጾች ላይ እየወጣ ነው:: ይህንን የተሳሳተ ፎቶ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚያሰራጩ ሰዎች አሉ:: ይህ ጉዳይ በአቸኳይ መስተካከል ያለበት ይመስለናል::
hanaአሁን ሆን ተብሎ ወይም በስህተት እየተሰራጨ ያለው ፎቶ ከአመታት በፊት አሜሪካ; በጉዲፈቻ መጥታ በአሳዳጊዎቿ ቸልተኝነት ህይወቷ ያለፈው ሃና ዊልያም ናት:: ትክክለኛውን ፎቶ በዚህ ድረ ገጽ ላይ ያገኙታል::

onsdag 19. november 2014

እንግሊዝ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን በተመለከተ ደብዳቤ መጻፏን ወያኔ አረጋገጠ



የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን በተመለከተ ለወያኔዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ደብዳቤ መጻፋቸውንና ወያኔም አቋሙን ግልጽ ማድረጓን የወያኔዉ ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሚኒስትሩ አቶ ሬድዋን ሁሴን ተናገረ። ሬድዋን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባለፈዉ ማክሰኞ በሰጠዉ ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ዴቪድ ካሜሩን ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደብዳቤ መጻፋቸውን የተለያዩ የውጭ ሚዲያዎች መዘገባቸውን ሰምቻለሁ ካለ በኋለ “ለምን ጻፉ ማለት አይቻልም፤ ጥያቄዉ መሆን ያለበት ምን መለሳችሁ ነው፤” በማለት የተለመደ የማጭበርበሪያ ቃላት ደርድሯል።

የተለያዩ የእንግሊዝ ሚዲያዎች ኢትዮጵያ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ላይ ቀደም ሲል የተፈረደውን የሞት ቅጣት እንዳትተገብር እንዲሁም ኢትዮጵያ ለሚገኘው የእንግሊዝ ኤምባሲ አቶ አንዳርጋቸውን የመጐብኘት ቋሚ ፈቃድ እንዲሰጥ በደብዳቤያቸው መጠየቃቸውንም ሬድዋን ሁሴን ተናግሯል።

ለዴቪድ ካሜሮን ደብዳቤ መልስ መሰጠቱን ያረጋገጠዉ ሬድዋን፣ “በተጨባጭ የተፈረደበትን ግለሰብ ነው የያዝነው፤ እንዲህ ብታደርጉት ባታደርጉት ብሎ ማንሳት ይቻላል። ምክንያቱም እነሱም የሚመለከታቸው በመሆኑ። በዚህ ምክንያት ግን የእኛ መልስ በራሳችን ሕግ መሠረት ዓለም አቀፍ ሕጉም በሚለው መሠረት የምናደርገውን እናደርጋለን፤” ብሏል። ኢትዮጵያ የምትተገብረው የራሷን ሕግ መሆኑን የገለጹት አቶ ሬድዋን፣ “ከነጭም ከጥቁርም የሚመጣን ደብዳቤ ተንተርሰን ምንም አንተገብርም፤” ብሏል። ከዚህ በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ደብዳቤ ጽፈው፣ በኢትዮጵያ በኩልም መልስ ተስጥቷል ያለዉ ሬድዋን ሁሴን በደብዳቤው የቀረቡ ጥያቄዎች ቅሬታ እንዳላስነሱ ሁሉ መልሱም ቅሬታ አያስነሳም የሚል ተስፋ በኢትዮጵያ በኩል መኖሩን ተናግረዋል።

“እነሱ ዜጋዬ ነው ብለዋል፤ የእነሱ ዜጋ እንደ ቼ ጉቬራ ነፃ አውጣ ተብሎ ኢትዮጵያ ውስጥ አልተላከም። የእነሱ ዜጋ ከነበረ የእንግሊዝን ዴሞክራሲ ይበልጥ ለመጨመር መታገል ይችል ነበር። ነገር ግን በኢትዮጵያ በቅጥር ነብሰ ገዳይነት ካልተሰማራ በስተቀር ሌላ ሚና አልነበረውም፤” ብለዋል።

ሽመልስ ከማልና ፈትያ የሱፍ በፕሬስ ድርጅት እየተወዛገቡ ነው

‹‹ችግሮች በአስቸኳይ ካልተፈቱ ለበላይ አካል እናሳውቃለን›› ፈትያ የሱፍ
‹‹ችግሮቹ ውጫዊ ናቸው›› አቶ ሽመልስ ከማል
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር







የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል እና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባህልና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፈትያ የሱፍ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዙሪያ እየተወዛገቡ እንደሚገኙ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

አቶ ሽመልስ ከማል የፕሬስ ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ ሲሆኑ፣ ላለፉት አራት አመታት ድርጅቱ በተለያዩ ችግሮች ተዘፍቆ እያለ በቦርድ ሰብሳቢነታቸው ችግሮቹን መፍታት የነበረባቸው ቢሆንም ተደጋጋሚ ማሳሰቢያዎችን ችላ በማለት ድርጅቱ ከእነ ችግሮቹ እንዲዘልቅ አድርገዋል በማለት የባህልና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፈትያ የሱፍ ተናግረዋል፡፡

 ሰሞኑን የ2007 የበጀት እቅድን ለመገምገም በተገናኙበት ወቅት የፕሬስ ድርጅት ቦርድ እና አስተዳደር በበርካታ ችግሮች ዙሪያ ወቀሳ እንደደረሰበትና ችግሮቹ እንዲፈቱም ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠ በራሱ ድርጅት እየታተመ የሚወጣው ኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ በቅዳሜ እትሙ አስነብቧል፡፡

በድርጅቱ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የአስተዳደር ብልሹነት መኖሩን የተናገሩት ፈትያ የሱፍ፣ ‹‹በራሱ ድርጅት በችግር የተተበተበ ጋዜጠኛ እንደምን የሌሎችን ድርጅቶችና ግለሰቦች የአሰራር ችግሮች ሊያጋልጥ ይችላል?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ አክለውም በተደጋጋሚ ችግሮቹ ለድርጅቱ አስተዳደር በሰራተኞች ሲቀርቡለት የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ እያለ ማለፉን የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ አውስተዋል፡፡


ፈትያ የሱፍ እንደሚሉት የፕሬስ ድርጅት ቦርድ እና አስተዳደር ችግሮቹን በአስቸኳይ የማይፈታ ከሆነ ወደሚመለከተው ከፍተኛ አካል ለማስተላለፍ ከውሳኔ ላይ መደረሱን አስረድተዋል፡፡

የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ሽመልስ ከማል በበኩላቸው የድርጅቱ ችግሮች ውጫዊ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ድርጅቱ የበጀት ችግሮች እንዳለበት ያወሱት አቶ ሽመልስ፣ በተጨማሪ ግን በድርጅቱ ላይ መጥፎ እይታ ያላቸው እና መጠቀሚያ ለማድረግ የሚፈልጉ አካላት በሰራተኞች ስም አላማቸውን ለማስፈጸም የሚሯሯጡ ወገኖች አሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

‹‹የግል እና የመንግስት ሚዲያ ይለያያሉ፤ በአመለካከት፣ በአሰራርና በጥራት ልዩነት አላቸው›› በማለትም ሰራተኞቹ ፕሬስ ድርጅት እንደ ግል ሚዲያ ሊሰራ እንደማይችል ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰብስቤ ከበደ እና አቶ ሽመልስ ከማል ከፍተኛ የሆነ የጥቅም ትስስሮሽ እንዳላቸው የሚገልጹት የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች፣ በዚህ ትስስራቸው የተነሳም የአቶ ሽመልስ ከማል ባለቤት ያለምንም ውድድር በድርጅቱ በጋዜጠኝነት ተቀጥራ ምንም ስራ ሳትሰራ ደመወዝ ትወስድ እንደነበር፣ በኋላ ግን ‹ስራውን አልቻልኩትም› በሚል ከድርጅቱ እንደወረጣች ይናገራሉ፡፡

አቶ ሰብስቤ ከበደ በሰራተኞች ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸው እና በተለያዩ ስብሰባዎች በይፋ ‹አልቻልክም ድርጅቱን ልቀቅ› ተብለው በሰራተኞች እንደተነገራቸው ምንጮች ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ግን ከአቶ ሽመልስ ከማል ጋር ባለቸው የጥቅም ትስስር በስልጣናቸው እስካሁን እንደሚገኙ፣ ይህም ድርጅቱን እና ሰራተኞችን እየጎዳ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

mandag 17. november 2014

የአሜሪካ ድምጽ ፒተር ሃይንላይንን ከሃላፊነቱ አነሳ


Peter goes(አዲስ ቮይስ) የአሜሪካን ድምጽ ዳይሬክተር ዴቪድ አንሶር የአፍሪካ ቀንድ የበላይ ሃላፊ የነበረው ፒተር ሃይንላይን ከሃላፊነቱ መነሳቱን አሳወቁ። ዳይሬክተሩ ባለፈው አርብ የክፍሉን ሰራተኞች በድንገት ሰብስብስበው እንዳስታወቁት ሃይንላይን ከሃላፊነቱ ተነስቶ በምትኩ የርሳቸው ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ዊሊያም ማርሽ በግዚያዊነት መሾማቸውን ገልጸዋል።
በቅርቡ በአሱዛ ፓስፊክ ዩኒቨርሲቲ ለአቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ተሰጥቶ የነበረ ክብር መሰረዙ ጋር በተያየዘ ከሄኖክ ሰማእግዜር ጋር በመተባበር የተዛባ ዘጋባ አቅርቧል የሚል ክስ ቀርቦበት የነበረው ፒተር ሃይንላይን የአስተዳደር በደል አቤቱታም በተጨማሪ በስሩ ያስተዳድራቸው ከነበሩ ሰራተኞች ቀርቦበት እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
የአሜሪካ ድምጽ የበላይ ሃላፊዎች በሃይንላይን ላይ የቀረቡትን አቤቱታዎች መመርመራቸውንና ከፍተኛ የአሰራር ጉድለቶች እንደነበር ማረጋገጣቸው ታውቋል። በጋዜጠኛና አክቲቪስት አበበ ገላው አቤቱታ የቀረበበትን ዘገባ በተመለከተ የአሜሪካን ድምጽ የበላይ አስተዳደር (Board of Broadcasting Governors) ጉዳዩን በጥልቀት መርምሮ ዘገባው ያለተሟላና ከአሜሪካ ድምጽ ደረጃ በታች የወረደ ነበር ሲል መግለጹ ይታወሳል።
ይሁንና የአሜሪካን ድምጽ የአማርኛ ክፍል ግዜውን በጠበቀ መልኩ አግባብ ያለው እርምትና ማስተካከየ ሳያደርግ መቅረቱና ስህትቱን ከማረም ይልቅ መሸፋፈን በመምረጡ ተጨማሪ አቤቱታ ለቪኦኤ የበላይ ሃላፊዎች ቀርቦ እንደነበር አበበ ገላው ገልጿል።
አበበ በተለይ ፒተር ሃይንላይን እንደ ባለስልጣን ሃላፊነት በተሞላበት መልኩ ማስተካከያ ከማድረግ ይልቅ አደናጋሪና የተዛቡ ዘገባዎችን በተደጋጋሚ እንዲቀርቡ ማድረጉ ለእርምጃው መወሰድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው የውስጥ አዋቂዎችን በመጥቀስ አስረድቷል።
አዲሱ የአፍሪካ ቀንድ ሃላፊ ሆነው የተሾሙት ማርሽ ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ሃላፊነት ለሶስት አመታት ማገልገላቸው የታወቀ ሲሆን በሰራተኞች የተከበሩና ለሙያቸው ትልቅ ከበሬታ ያላቸው መሆኑን ለማወቅ ተችላሏል። ፒተር ሃይንላይን ከሃልፊነት ቦታው ወርዶ ያልምንም አስተዳደራዊ ሃላፊንት ወደ አፍሪካ ክፍል መዛወሩ ለመረዳት ተችሏል።