onsdag 26. november 2014

ሰማያዊ ፓርቲን ያቀፈው የ9 ፓርቲዎች ትብብር በመንግስት አፈና ትግሉን እንደማያቆም አስታወቀ

ትብብሩ ባወጣው መግለጫ ህዳር 21 ለሚደረገው ስብሰባ ለመስተዳድሩ የሰለማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል ደብዳቤ ቢላክለትም ለመቀበል ፈቃደኛ ካለመሆኑም በተጨማሪ፣ ስብሰባውን የሚያስተባብሩት የመኢዴፓ ሊቀመንበርና የትብብሩ ገንዘብ ያዥ የሆኑት አቶ ኑሪ ሙደሲር ላይ የድብደባ ወንጀል እንደተፈጸመባቸው ገልጿል።‹‹ነጻነታችን በእጃችን›› ነው የሚለው ትብብሩ፣  በኢህገመንግሥታዊና ኢዲሞክራሲያዊ እርምጃዎች ወደኋላ እቅዱን በህጋዊ መንገድ ለማስቀጠል እስከ ህይወት መስዋትነት ለመክፈል ያለውን ቁርጠኝነት ገልጿል።
ገዢው ፓርቲ ከአፈና ድርጊቱ እንዲገታና ለቀረበው  ህጋዊ የዕውቅና ጥያቄ በአስቸኳይ መልስ እንዲሰጥ፣  የትግሉ አላማ የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በመሆኑ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለቀጣዩ ሠላማዊ ትግል የሚቀርበውን ጥሪ በንቃት እንዲከታተሉና ከፓርቲዎች ጎን እንዲቆሙ፣ በትብብሩን ያልተቀላቀሉ ፓርቲዎች እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር እና የትብብሩ መሪ ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት የትኛውንም ዋጋ ከፍለን ነጻነታችንን ማስመለስ ከሁሉም በላይ ዋጋ የምንሰጠው ነው ብለዋል። እቅዳቸው መስዋትነት ሊያስከፍል እንደሚችል የገለጹት ኢ/ር ይልቃል፣ አስፈላጊውን መስዋትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። ኢህአዴግ ለመግደልና ለማሰር ቆራጥ የሆነውን ያክል፣ እኛም ለመሞት ቆርጠናል ብለዋል
በሌላ በኩል ደግሞ በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የተከሰሱት አራቱ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች እና ስድስት ተከሳሾች  የክስ መቃወሚያ እንዲያቀርቡ ለታህሳስ 9 ቀን 2007 ዓ.ም ከፍተኛው ፍርድ ቤት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ የሺዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታ እና ዳንኤል ሺበሽ በሚገኙበት የክስ መዝገብ የተከሰሱት አስሩም ተከሳሾች  ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡ ሲሆን፣  የተከሳሽ ጠበቆች በጠየቁት መሰረት የተከሳሾቹን የክስ መቃወሚያ ለመቀበል ፍርድ ቤቱ ለታህሳስ 9/2007 ዓ.ም ቀጠሮ መስጠቱን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል። ተከሳሾች በሽብርተኝነት ወንጀል መከሰሳቸው የሚታወቅ ነው። አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ክሱ ፖለቲካዊ ነው በማለት ውድቅ ያደርጉታል።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar