torsdag 31. januar 2013

ፍርድ ቤት ዛሬ ጠዋት በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ክስ ላይ ብይኑ አልደረሰልኝም በማለት ሌላ ቀጠሮ ሰጥቷል


የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት 16ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ጠዋት በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ክስ ላይ ብይን ለመስጠት የተሰየመ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ብይኑ አልደረሰልኝም በማለት ቀጠሮ ሰጥቷል።

የችሎቱ ዳኛ ፣ ጋዜጠኛ ተመስገን እና አሳታሚው ማስተዋል የህትመት ስራ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ የነበረው አቶ ማስተዋል ብርሀኑ መኖራቸውን ካረጋገጡ በሁዋላ ብይኑን ለመስጠት ለየካቲት አንድ ቀጠሮ ሰጥተዋል።

የጋዜጠኛ ተመስገን ጠበቆች በችሎቱ ላይ አልተገኙም። በችሎቱ ዲፕሎማቶችን ጨምሮ የጋዜጠኛው ቤተሰቦች፣ አድናቂዎችና ስራ ባልደረቦች ተገኝተዋል።

በቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ አንዲት ተማሪ ራሱዋን መጸዳጃ ውስጥ በመግባት አጠፋች



ገነቴ ጌታቸው የተባለችው ተማሪ መጸዳጃ ቤት ውስጥ ራሱዋን በመወርወር ያጠፋቸው ባለፈው ሳምንት ነው።

 በትምህርቷ ከፍተኛ ውጤት የነበራት ተማሪ ገነቴ ራሱን ለማጥፋት ለምን እንደወሰነች በትክክል ለማወቅ ባይቻልም ተማሪዎች እንደሚሉት ከሶስት ሳምንት በፊት የግቢው ተማሪዎች የውሀ፣ የመጸዳጃ እና ሌሎች አገልግሎቶች አልተሟሉልንም በሚል ተቃውሞ ከማስነሳታቸው ጋር ሊያያዝ ይችላል።

 ተማሪዎቹ ቤተሰቦቻቸውን በማስቸገር በሚላክላቸው ገንዘብ የፕላስቲክ ውሀ ሲገዙ መቆየታቸውን ያወሱት የሟቿ ባልደረቦች፣ ይሁን እንጅ ተማሪዋ የመጣችበት ቤተሰብ ይህን ለሟሟላት ባለመቻሉ ተማሪዋ በችግር ውስጥ ትገኝ ነበር ብለዋል።

 አሟሟቷንም ከገንዘብ ችግር ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ጠቁመዋል።

ትምህርታቸውን አቁመው የነበሩ ተማሪዎች ወደ ግቢያቸው ተመልሰው መደበኛ ትምህርት የጀመሩ ቢሆንም፣ የፌደራል ፖሊስ አባላት ግን አሁንም በዩኒቨርስቲው አካባቢ በብዛት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ለማወቅ ተችሎአል::


የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ አስተዳዳሪዎችን ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።

አብዛኞቹ የተፈናቀሉ የጉራፈርዳ ነዋሪዎች የደረሰቡት እንደማይታወቅ መኢአድ ገለጠ



በጭቆናና በአፈና ስልጣንን ለማራዘም የሚካሄደው ዘመቻ ቀጥሏል” በሚል ርእስ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ፣ በጉራፈርዳ ወረዳ የሚፈናቀለው አርሶአደር ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑንና የተወሰኑትም በሚዛን ተፈሪ፣ በጅማ፣ በአንቦ እና በአዲስ አበባ ያለመጠለያ ለልመና መዳረጋቸውን ገልጿል።

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አርሶአደሮች መሬታቸውን ተነጥቀው የአካባቢው ታጣቂዎች በጨረታ ስም እየተቀራመቱት መሆኑን የገለጠው መግለጫው፣ ወ/ሮ ስንዴ ስጦታው የተባሉ የስምንት ልጆች እናት በጥይት ተደብድበው በመሞታቸው ልጆቻቸው ያለአሳዳጊ መቅረታቸውን አብራርቷል።

ጥር 21 ከሌሊቱ 8 ሰአት ከወረዳው መስተዳደር የተላኩ አራት ወታደሮች ወደ አቶ ኢበሉ ማሞ ጊቢ በመግባት ሁለት በሬዎችና ሶስት በጎችን መውሰዳቸውን የጠቀሰው ድርጅቱ መግለጫ፣ 32 ሰዎችም እንዲሁ በእስር ቤት ያለምንም ፍርድ እየተሰቃዩ መሆኑን ገልጿል።

መኢአድ ” በጉራፈርዳ ህዝብ ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ እየተካሄደ ያለው ወከባ እስራትና እና ግድያ በአገራችን ታይቶ የማይታወቅ ሰብአዊ ረገጣና የአንድን ቋንቋ ተናጋሪ ህዝብን የማጥፋት ዘመቻ አካል ነው ” በማለት ገልጾ፣ ነዋሪዎቹ ከአካባቢው መልቀቅ እንዳለባቸው አለበለዚያ ግን ሁሉንም እንደሚገድሏቸው የወረዳው አስተዳዳሪዎች እና የፖሊስ ሀላፊዎች መግለጻቸውንም ይፋ አድርጓል።

በአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ላይ የተካሄደውን የሌሎች አገራት የዘር ማጥፋት ወደ አገራችን መግባቱን፣ በጉራ ፈርዳ የተፈጸመው ድርጊት እንደሚያመላክት የገለጸው መኢአድ፣ ድርጊቱን ኢትዮጵያውያን ተረባርበው እንዲያስቆሙት ጥሪ አቅርቧል።

በደቡብ ኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየተባባሱ መምጣታቸው ይነገራል።

የአቶ ጁነዲን ያለመከሰሰ መብት ያለመነሳት ጉዳይ ማነጋገሩን ቀጥሏል



ከሁለት ሳምንት በፊት ያለመከሰሰ መብታቸውን ለማንሳት በአጀንዳ መልክ ለፓርላማ ቀርቦ የነበረውና ባልታወቀ
ምክንያት ፓርላማው እንዳይወያይበት በተደረገው የቀድሞ የኦህዴድ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር
አቶ ጁነዲን ሳዶ ጉዳይ _ሕግ አስፈጻሚው አካል አሁንም ዝምታን መምረጡ አነጋጋሪነቱ ቀጥሎአል፡፡

ፓርላማው ከሁለት ሳምንት በፊት ባቀረበው አጀንዳ የአንድ የም/ቤት አባል ያለመከሰሰ መብት ስለማንሳት በሚል
ለውይይት አጀንዳ መያዙን ካስታወቀ በኃላ በድንገት ስብሰባው ከተጀመረ በሁዋላ ለሌላ ጊዜ መተላለፉ በአፈጉባዔው
በኩል ተገልጾአል፡፡

የፓርላማው ምንጮች እንደገለጹት አጀንዳው በፓርላማው ከኦሮሚያ ደራ ወረዳ ተመራጭ የሆኑትን አቶ ጁነዲን ሳዶን
የሚመለከት ነበር፡፡

ሆኖም ባልታወቀ ምክንያት አጀንዳው እንዲያድር ከተደረገ በሃላ ላለፉት አስራአምስት ቀናት
በላይ ዝምታ መመረጡ የብዙዎችን ትኩረት መሳቡ ታውቋል፡፡

አቶ ጁነዲን ሳዶ ባለቤታቸው ወ/ሮ ሐቢባ መሐመድ አዲስአበባ ከሚገኘው ሳዑዲ ኤምባሲ ገንዘብና የተለያዩ
መጽሐፍትን ተረክበው ሲወጡ እጅ ከፍንጅ ከተያዙበት ከሐምሌ 9 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ ከመንግስታዊ
ኃላፊነታቸውን በተጨማሪ በመስከረም ወር መጨረሻ የዓመቱ መደበኛ ሥራውን የጀመረው ፓርላማ ተገኝተው አያውቁም፡፡

ከባለቤታቸው ጥፋት ጋር ተያይዞ ከኦህዴድ አመራርነት ተገምግመው እንዲነሱ የተደረጉት አቶ ጁነዲን በጠ/ሚ
ኃይለማርያም አዲሱ ካቢኔም ተወግደው በአቶ ሙክታር ከድር መተካታቸው የሚታወስ ነው፡፡

ባለቤታቸው በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ክሳቸውን እየተከታተሉ ቢሆንም ከሳዑዲ ኤምባሲ ጋር ከነበራቸው ግንኙነት ጋር
በተያያዘ የምዋች እናታቸውን ኑዛዜ ለማስፈጸም የገንዘብ ዕርዳታ የጠየቁት ራሳቸው መሆናቸውን በመግለጽ ባለቤታቸው
በጉዳዩ እጃቸው እንደሌለበት በይፋ ቢናገሩም እስካሁን የተጠየቁበት ሁኔታ አለመኖሩ የህግ ሥርዓቱን ፍትሐዊነት
ጥያቄ ውስጥ ጥሎታል፡፡

ፓርላማው ያለመከሰሰ መብታቸውን ለማንሳት ያደረገው ሙከራም የከሸፈበት ምክንያትም ለብዙዎች እንቆቅልሽ እንደሆነ ነው፡፡

በተያያዘም ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም ባለቤታቸውን አቶ መለስ ዜናዊን በድንገተኛ በሞት ያጡት ወ/ሮ አዜብ
መስፍን ከሐዘናቸው ካገገሙም በሃላ በፓርላማ ውስጥ ተገኝተው እንደማያውቁ ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡

ፓርላማው በ3ኛ ዓመት የስራ ዘመኑን በመስረም ወር መጨረሻ ጀምሮ እስካሁን መደበኛ ስብሰባዎችን እያስተጎጎለም
ቢሆን 15 መደበኛ ስብሰባዎችን ያካሄደ ቢሆንም የፓርላማው አባል የሆኑት ወ/ሮ አዜብ በአንዱም ስብሰባ ላይ
አልታዩም፡፡

እንደ ምንጮቻችን ገለፃ አቶ መለስ ዜናዊ በሕወት በነበሩበት ጊዜ በቁም የተነሱትን ፎቶግራፍ ሁሉም አባላት
ሊያዩት በሚችሉበት ሁኔታ ፊት ለፊት የተሰቀለ ሲሆን ይህ ፎቶ በትልቁ ፊት ለፊት መሰቀሉ በብዙዎቹ የፖርላማ አባለት ዘንድ አሁንም ፖርላማውን እየመሩ ያሉት እርሳቸው እንደሆኑ የሚያሳስብ መንፈስ ፈጥሮባቸዋል::

በጉርዳፈርዳ በአማራ ተወላጆች ላይ የሚደርሰው የሰብአዊ መብት ረጋጣ ቀጥሏል

               
 
 በደቡብ ኢትዮጵያ ቤንች ማጂ ዞን በጉርዳፈርዳ ወረዳ በአማራ ተወላጆች ላይ የሚደርሰው የሰብአዊ መብት ረገጣ መቀጠሉ ተገለጸ።

በወረዳው ባለፈው ታህሳስ አንዲት የ8 ልጆች እናት በጥይት ሲገደሉ፣ ሁለት ህጻናት በመስተዳድሩ መኪና ተገጭተው መሞታቸውን የመኢአድ ም/ሊ/መንበር አቶ ወንድማገኝ ደነቀ ለኢሳት ገልጸዋል።

ታህሳስ 28/ 2005 ከምሽቱ 4 ሰአት ሲሆን 5 መሳሪያ የታጠቁ ወተዳሮች የ8 ልጆች እናት የሆኑትን ወ/ሮ አይቼሽ ስጦታውን በመኖሪያ ቤታቸው እንደገደሉዋቸው ነው ም/ ሊቀመንበሩ የተናገሩት።

ጥር 15 ቀን 2005 ዓ/ም ደግሞ የ4 እና የ7 አመት ህጻናት በመስተዳድሩ መኪና ተገጭተው ህይወታቸው ማለፉን ከአቶ ወንድማገኝ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሎአል።

ሌሎች 23 የአማራ ተወላጆች በወህኒ ቤት በመሰቃየት ላይ መሆናቸውንም_ የመኢአድ ተቀዳሚ የፐም/ል ፕሬዚዳንቱ አክለዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የመንግስት ባለስልጣናትን ለማናገር ብንሞክርም አልተሳካልንም

የሙስሊም መሪዎች የችሎት ውሎ አስቂኝ ነው ተባለ


ምንጮች እንደገለጡት በዝግ ችሎት በሚካሄደው የሙስሊም መሪዎች የፍርድ ቤት ውሎ 190 ምስክሮች እንደሚቀርቡ አቃቢ ህግ ቢያስታውቅም እስካሁን የቀረቡት ምስክሮች 11 ናቸው። ምስክሮችን የመስማት ሂደቱ በ10 ቀናት ውስጥ ይጠናቀቃል ቢባልም፣ በአሁኑ አካሄድ አቃቢ ህግ የምስክሮችን ቁጥር ካልቀነሰ በስተቀር በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥም ላይጠናቀቅ ይችላል።

የውስጥ ምንጮች እንደገለጡት አቃቢ ህግ ምስክሮችን ሲያቀርብ የአባታቸውን ስም ብቻ በመጠቀም ነው።

 ጠበቃው አቶ ተማም አባቡልጋ ምስክሮቹ የመኖሪያ አድራሻቸው ፣ ስራቸውና ማንነታቸው እንዲገለጥ ለዳኞቹ ቢያመለክቱም፣ ዳኞቹ “የምስክሮችን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ምስክሮቹ አድራሻቸውንም ሆነ ስራቸውን እንዲገልጡ አይገደዱም” የሚል ምክንያት በመስጠት ጥያቄውን አልተቀበሉትም።

አቶ ተማም ” በህገመንግስቱ አንቀጽ 20 መሰረት አንድ ጉዳይ በዝግ ችሎት ሊታይ የሚገባው አገር ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥል ሲሆን ብቻ ነው በማለት ” ቢከራከሩም ዳኞቹ ” የምስክሮች ድህንነትም የአገር ደህንነት ነው” በማለት ጥያቄውን ውድቅ ማድረጋቸውን ምንጫችን ገልጸዋል።

ጠበቃ ተማም ” በ1997 ዓም በቅንጅት መሪዎችና ጋዜጠኞች የፍርድ ቤት ሂደት ላይ እንደተደረገው የተከሳሾች ቤተሰቦች እና ዘመዶች ባይቀርቡ እንኳን ቢያንስ የውጭ እና የአገር ውስጥ ጋዜጠኞች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና የውጭ ዲፕሎማቶች እንዲገኙ ችሎቱ ፈቃድ ይስጥ በማለት ቢጠይቁም” ዳኞቹ ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ክርክሩ ያለታዛቢ እንዲቀጥል ሆኗል።

ምስክሮቹ ተከሳሾች በአደባባይ የተናገሩትን ከመድገም ውጭ እስካሁን አንድም አዲስ ነገር አለመናገራቸው ታውቋል። ምስክሮቹ የተመሰከረባቸውን ተከሳሾች ጠቁሙ ሲባሉ ሌሎችን ሰዎች እንደሚጠቁሙ፣ እስረኞችም በምስክሮች ድርጊትና በፍርድ ቤቱ ሂደቱ ድራማ እየተዝናኑ መሆኑ ታውቋል።

አጠቃላይ የፍርድ ሂደቱ የተበላሸ ኧንደሆነ የተረዳው መንግስት፧ ከውርደት ለመዳን በሚል የፍርድ ሂደቱን በዝግ ችሎት እንዲካሄድ ማድረጉን አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ ህግ ባለሙያ ተናግረዋል።

mandag 28. januar 2013

በአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ 13 ሚሊዮን ብር በማውጣት ፎርጅድ ቀለሞችን የገዙ ሰዎች ተያዙ


ከዩኒቨርስቲው ምንጮች ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በዩኒቨርስቲው ፋይናንስና ሂውማን ሪሶርስ ክፍል ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች 13 ሚሊዮን ብር ዋጋ የሚያወጣ ፎርጅድ ( የተጭበረበረ)የፕሪንተር ቀለምና የኮምፒተር እቃዎችን ገዝተዋል ተብለው በፌደራል ፖሊሶች ቁጥጥር ስር ውለዋል።
'
 የተያዙት ግለሰቦች ከዚህ ቀደም በከፍተኛ የሀላፊነት ቦታዎች ላይ የነበሩና ላለፉት 20 አመታት በተለያዩ መንገዶች ለአካባቢው ህዝብ የሚላከውን ገንዘብ በመዝረፍ የሚታወቁ ናቸው።

አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ ሰው እንደተናገሩት ገቢው በቀን አንድ ዶላር በሆነባት አገር ፣ ይህን ያክል የገንዘብ ዝርፊያ መካሄዱ አስገራሚ ነው ብለዋል።

 ግለሰቦቹ የኢህአዴግ ባለስልጣናት በመሆናቸው ህዝቡን ለማስደሰት ተብለው ታሰሩ እንጅ በቅርቡ ሊለቀቁ ይችላሉ በማለት ግለሰቡ አክለው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ሙስና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው።

የኦሮሞ ተወላጆች የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ጠየቁ

በኦሮሞ ጥናት ማኅበር፣ በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ የኦሮሞ ማኅበረሰብ ድርጅት፣ የኦሮሞ ወጣቶች ራስ አገዝ ማኅበር፣ የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ሊግና የኦሮሞ ድጋፍ ቡድን የተዘጋጀው ደማቅ የተቃውሞ ሰልፍ አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ኦልባና ሊሌሳን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
የአሜሪካ ድምጽ እንደዘገበው ከአቶ በቀለ ገርባ እና ከአቶ ኦልባና ሌሊሣ በተጨማሪ በስም የተጠቀሱት ወልቤካ ለሚ፣ አደም ቡሣ፣ ሃዋ ዋቆ፣ ሞሐመድ መሉ፣ ደረጀ ከተማ፣ አዲሱ ምክሬ እና ገልገሎ ጉፋ በእሥር ላይ እንደሚገኙ የሠልፉ አስተባባሪዎች ተናግረዋል፡፡x

የኦሮሞ ተወላጆች ሠልፍ በዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት
የኢትዮጵያ መንግሥት አቶ በቀለ ገርባን፣ አቶ ኦልባና ሌሊሣን፣ እንዲሁም ሌሎቹንም ሰባት የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ በፖለቲካ ምክንያት ተይዘው የረዥም ዓመታት እሥራት የተፈረደባቸውን ሰዎች ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ መንግሥት የኢትዮጵያን ሕገመንግሥት እንዲያከብር፣ ከፍርድ ውጭ የሆኑ ግድያዎችንና ንፁሃን ሰዎችን ያለክስ ለተራዘመ ጊዜ ማሠሩን እንዲያቆም የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት ጫና እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ የምጣኔ ኃብት ድጋፍ ከመስጠቷ በፊት የፖለቲካ እሥረኞች ሁሉ እንዲፈቱ አስገዳጅ ጫና እንድታደርግ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የኦሮሞን ሕዝብና የሌሎቹንም ሰብዓዊ መብቶች፣ ሃሣብን የመግለፅና የመደራጀት ነፃነቶችን እንዲያከብር አሜሪካ እንድትጠይቅ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት መሠረታዊ የሆኑ የዜጎችን መብቶች የሚጥሱ አዳዲስ ሕግጋትን ሁሉ፣ በተለይ ፀረ-ሽብር የሚባለውን ሕጉን፣ የፕሬስ ሕጉን፣ የረድዔት ድርጅቶች በሃገሪቱ ውስጥ እንደልባቸው እንዳይንቀሣቀሱ የሚገድበውን የሲቪል ማኅበራት ማቋቋሚያ ሕጉን፣ እንዲሁም ስካይፕንና ሌሎችም የሚድያ አገልግሎት ዘዴዎችን መጠቀምን ሕገወጥ የሚያደርገውን በቅርብ ያወጣውን ሕጉን እንዲሠርዝ እንዲሁም መንግሥት የሃይማኖት ነፃነትን እንዲያከብር እና በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ውስጥም ጣልቃ መግባት እንዲያቆም የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት እንዲጠይቅ የሚሉ ጥያቄዎች መቅረባቸውን ሬዲዮው ዘግቧል።x

የኦሮሞ ተወላጆች ሠልፍ በዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት
ድርጅቶቹ ለኢሳት በላኩት መግለጫ ላይ እንዳመለከቱት ደግሞ የአሜሪካ መንግስት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ ላኢ ትርጉም ያለው ጫና ማሳደር ካልቻለ የኢትዮጵያ መንግስት በኦሮሞ እና በሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት ይቀጥላል።

የኦሮሞ ተወላጅ ለስቴት ዲፓርትመንት በቀጥታ ለፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በግልባጭ በላኩት ደብዳቤ ላይ አናሳው የትግራይ ነጻ አውጭ ድርጅት ( ህወሀት) 40 በመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያን ህዝብ በሚወከለው የኦሮሞ ህዝብ ላይ ጥቃት እየፈጸመ ነው ብለዋል።

ደብዳቤው የሬቻን በአል ለማክበር በቢሸፍቱ የተገኙ 200 የኦሮሞ ተወላጆች ላለፉት አራት ወራት መታሰራቸውንና አሁንም አለመፈታታቸውን ጠቅሰዋል። እንዲሁም በየጊዜው ላለፈው አንድ አመት በየሳምንቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን እንደሚታሰሩ፣ በቅርቡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በተነሳው የዘር ግጭት 99 ተማሪዎች አብዛኛኦቹ የአሮሞ ተወላኮች መታሰራቸውን አውስተዋል። እንዲሁም የህወሀት አገዛዝ ባለፉት 21 አመታት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ በአብዛኛው የአሮሞ ተወላጆችን ሲያስር፣ ሲያሰቃይና ሲገድል መቆየቱን ገልጸዋል።

በቃሊቲ እስር ቤት ከታሰሩ እስረኞች ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት የኦሮሞ ተወላጆች መሆናቸውን ከእስር ቤት ፖለቲከኞች መናገራቸው ይታወቃል።

የከምሴ ነዋሪዎች የሀይማኖት መሪያችንን አናስወስድም በማለት ተቃውሞአቸውን ገለጡ


በኢሉባቦር ዞን ከመቱ ከተማ 15 ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ከምሴ ቀበሌ ፖሊሶች ሼህ ሳሊህ አብዱልቃድር የተባሉትን የእስልምና ሀይማኖት መሪ ለመውሰድ በሄዱበት ወቅት ህዝቡ ግለሰቡን አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ችግር መፈጠሩ ታውቋል።

ሼህ ሳሊህ አብዱልቃድር ከዚህ ቀደም በሽብርተኝነት ተከሰው 8 ወራት ከታሰሩ በሁዋላ መረጃ አልተገኘባቸውም በሚል በነጻ ተለቀው ነበር። ባለፈው ሳምንት ፖሊሶች እንደገና ወደ አካባቢው በመሄድ የእርሳቸውን ጓደኛ ያሰሩ ሲሆን፣ ዛሬ ደግሞ ሼኩን ለማሰር ወደ ቀበሌው ሲሄዱ ህዝቡ በነቂስ በመውጣትና ተክቢራ በማለት በመቃወሙ በህዝቡና በፖሊስ መካከል ፍጥጫ ተከስቶ ነበር። የህዝቡን ስሜት የተረዱት ፖሊሶች በቀጥታ ወደ ግጭት ከማምራት ይልቅ ከህዝቡ ተወካዮች ጋር ለመነጋጋር መምረጣቸ ው ታውቋል።

በሽማግሌዎችና በፖሊስ መካከል ያለው ውይይት ይህን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ እንደቀጠለ ነው።

በሌላ ዜና ደግሞ ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ መጡበት አካባቢ የተመለሱ ከ700 የማያንሱ የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ፣ ጥያቄያቸው ካልተመለሰ ትምህርት ለመጀመር እንደሚቸገሩ እየገለጹ ነው።

 ኢሳት የነጋገራቸው ተማሪዎች እንደሚሉት በዩኒቨርስቲው በሙስሊም ተማሪዎች ላይ የሚደርሰው ጭቆና የሚጀምረው ” ወደ ግቢ ለመግባት በሚደረገው ፍተሻ ነው”
በዛሬው እለት ወደ አዲስ አበባ የተመለሱ ተማሪዎች ከወላጆቻቸው ጋር በመሆን በትምህርት ሚኒስቴር በመገኘት ጥያቄያቸውን ለማቅረብ እቅድ ተይዞ እንደነበር ለማወቅ ተችሎአል።

 ይሁን እንጅ በተማሪዎች እና በመንግስት መካከል ስለነበረው ውይይት ለማወቅ የተደረገው ሙከራ አልተሳካም። የዩኒቨርስቲው አስተዳደር ሙስሊም ሴቶች ኒቃብ እንዳይለብሱ፣ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በጋራ በግቢው ውስጥ ስግደት ወይም ማንኛውም ሀይማኖታዊ ስነስርአት እንዳያካሂዱ ያወጣው መመሪያ እንደማይለወጥ አስታውቋል።

የአርቲስቷ ባል ኢትዮጵያ ውስጥ ታሰረ



        ተቀማጭነቱ ለንደን የሆነው የኢትዮጵያ ዳንኪራ የዳንስ ግሩፕ አባል የሆነችው አርቲስት እስከዳር ታምሩ እና ባለቤቷ  አበበ ወንድምአገኝ በደህንነት ሃይሎች የዛሬ ሳምንት ቦሌ አካባቢ ታሰሩ።

እንደ ደብረ ብርሀን ብሎግ ዘገባ ፤ጥንዶቹ የሁለት አመት ልጃቸውን ይዘው ከሎንዶን ወደ አዲስ አበባ የሔዱት በአል ለማክበር ነበር።

እዚያ እንደደረሱ ከታሰሩ በሁዋላ አርቲስት እስከዳር ስትለቀቅ ባለቤቷ አበበ አሁንም እስር ቤት ይገኛል።

አቶ አበበ ፍርድ ቤት ቀርቦም የሃያ ቀን ቀጠሮ የተጠየቀበት ሲሆን፤ቤተሰቦቹ አዲስ አበባ ለሚገኘው ለእንግሊዝ ኤምባሲ ስለጉዳዩ አሳውቀዋል።

<<ምክንያቱ ፖለቲካዊ ነው የሚል>> ጥርጣሬ ቢኖርም፤እስካሁን የታሰረበት ምክንያት ምን እንደሆነ በግልጽ የታወቀ ነገር የለም።


ካሁን በፊት በተመሣሳይ ኮሜዲያን መስከረም በቀለ ከብዙ ኣመታት ቆይታ በሁዋላ የ አገሩንና የቤተሰቦቹን ናፍቆት ለመወጣት ወደዚያው ባቀናበት ጊዜ ገና ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እንደደረሰ በሴኩሪቲዎች ተይዞ መታሰሩ ይታወሳል።


ጭንቀትና ስጋት ውስጥ የገባው መንግስት ወደ ቤተሰብ ለመጠየቅም ሆነ ለተለያየ ጉዳይ ወደ አገራቸው የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን እዛ እንደደረሱ ለቀበሌ ሪፖርት ማድረግ አለባቸው የሚል ህግ ድረስ ማውጣት መድረሱን ያስታወሱ አስተያዬት ሰጭዎች፤ የአርቲስቷ ባል መታሰር የሚያመለክተውም የመንግስት ጭንቀት፣ጥርጣሬና ስጋት እየጨመረ መምጣቱን ነው ብለዋል።

lørdag 26. januar 2013

ገቢዎች እና የከፍተኛ ግብር ከፋይ ኩባንያ ባለአክስዮኖች እንደተፋጠጡ ነው




የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በንግድ ማኀበራት ባልተከፋፈለ ትርፍ ላይ የ10 በመቶ የጣለው የግብር ውሳኔ
ከፍተኛ ግብር ከፋዮችን ኩባንያዎችና ባለአክስዮኖችን አስቆጥቷል፡፡

ባለስልጣኑ በተሻሻለው የገቢ አዋጅ ቁጥር 286/94 በአንቀጽ 4 ላይ የአክስዮን ማኀበራትና ኀላፊነቱ የተወሰነ
የግል ማኀበር ካከፋፈሉት የአክስዮን ድርሻ ትርፍ ገቢ የሚያገኝ ማንኛውም ሰው ባገኘው ገቢ ላይ የ10 በመቶ
ግብር እንደሚከፍል ይደነግጋል፡፡
ባለስልጣኑ ከዚህ በተጨማሪ ባልተከፋፈለ የአክስዮን ድርሻ ላይ ግብር እንዲከፈል

ወስኖ ከ1ሺ461 ያህል ኩባንያዎች 816 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ በማቀድ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡
ባለስልጣኑ
ለግብር ከፋዮቹ በላከው የግብር ውሳኔ መሰረት ወደኃላ ሄዶ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ በሂሳብ ሚዛናቸው ላይ
ለባለአክዮኖች ሳያከፋፍሉ የቆዩትን በዓይነትም ሆነ በጥሬ ገንዘብ ያለን ሐብት ላይ ታክስና ግብር እንዲከፍሉ
ወስኗል፡፡

በዚሁ የባለስልጣኑ እርምጃ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ የአንድ የግል ባንክ የሕግ ባለሙያ እርምጃው አክስዮን
ማኀበራት ሥራቸውን ለማስፋፋት የሚያደርጉት ጥረት ላይ አሉታዊ ውጤት ከመጣሉም በላይ ተደራራቢ ታክስን
የሚያስከትል በመሆኑ ተቀባይነት ያለው አካሄድ አይደለም ብለዋል፡፡

አያይዘውም በርካታ አክስዮን ማኀበራት በአነስተኛ ካፒታል ተቋቁመው በየዓመቱ ከሚያስመዘግቡት ትርፍ ባለአክስዮኖችን እያስፈቀዱ ገንዘቡን ከመከፋፈል ይልቅ ለኩባንያው ማጠናከሪያ እንዲውል በማድረግ የተሻለ ኢንቨስትመንት እንዲካሄድ የሚያደርጉበት ሁኔታ እንደነበረጠቅሰዋል፡፡

 በዚህ መንገድ ኩባንያዎች ሲጠናከሩ አዳዲስ ሥራዎችን በመክፈትና ያሉትን በማስፋፋት ተጨማሪ የሥራ
ዕድሎች እንዲፈጠሩ አስተዋጽዖ ከማድረጋቸው በተጨማሪም አዲስ በፈጠሩት እሴት አማካኝነት ለአገር ልማት ሊውል
የሚችል ታክስና ግብር የሚያስገቡበት ሁኔታ እንዳለ አስታውሰዋል፡፡


እሳቸው የሚሰሩበትን ባንክን በምሳሌነት በማንሳት ባለአክዮኖቹ ትርፍ ላለመከፋፈል በመወሰናቸው ባንኩ ለብድር አገልግሎት የተሻለ የፋይናንስ አቅም በማግኘቱ ትርፋማነቱ መጨመሩን ተናግረዋል፡፡

የአሁኑ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ታክስና ግብር ለማስገባት ብቻ
ያለመው አካሄድ ለአገር የማይጠቅምና የከፍተኛ ኩባንያዎች ባለአክዮኖች ሐብታቸውን ወደተጨማሪ ኢንቨስትመንት
እንዳያውሉ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው ብለዋል፡፡

ከጥር ወር 2005 ጀምሮ ተፈጻሚ እንደሚሆን በባለስልጣኑ የተወሰነው ይህው ለግብር ከፋዮች ተላከው ማስታወቂያ
በአመዛኑ ከፍተኛ የሚባሉ ግብር ከፋዮችን ማለትም ባንኮችን፣የመጠጥና የለስላሳ ኢንዱስትሪዎችን፣ሌሎች በአክስዮን
የተመሰረቱ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን የሚመለከት ነው፡፡እነዚህ በቁጥር አነስተኛ የሆኑ ግን በገቢ ረገድ
ከባለስልጣኑ ዓመታዊ ጠቅላላ የግብርና ታክስ ገቢ እስከ 80 በመቶ ገደማ የሚሸፍኑ ናቸው፡፡

በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ተቃውሞአቸውን ሲገልጹ ዋሉ



    

torsdag 24. januar 2013

ፓሊሶች በአራት ኪሎ የሚገኙ ቤቶችን በእሳት አቃጠሉ



ለረጅም አመታት በአራት ኪሎ አካባቢ የኖሩ ሰዎች ቦታው ለሼራተን ሆቴል ማስፋፊያ ይፈለጋል በሚል ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ ሲነገራቸው እንደቆየ የተናገሩት አይን እማኞች፣ ነዋሪዎቹ በበኩላቸው መንግስት ተተኪ ቤት እስካልሰጣቸው ድረስ አካባቢውን ለቀው እንደማይሄዱ ሲከራከሩ ቆይተዋል። ዛሬ ጧት ወደ አካባቢው ያቀኑት ፖሊሶች ነዋሪዎቹ እቃዎቻቸውን ሳያወጡ በቤታቸው ላይ እሳት በመልቀቅ ቤታቸውን አቃጥለውባቸዋል።

 ነዋሪዎቹ በጩሀት ወደ ፓርላማ በመሄድ አቤት ቢሉም ሶስት ሰዎችን በመወከል ችግራቸውን እንዲያቀረቡ ተነግሮአቸዋል። ፖሊሶች ወደ አካባቢው በመድረስ ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩ ነዋሪዎችን አባረዋቸዋል።

አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ የአይን ምስክር ለኢሳት እንደገለጡት፣ ተማሪዎች ደብተራቸውን እንኳን ሳያወጡ ቤታቸው እንደተቃጠለባቸው፣ ብዙዎችም በከፋ ችግር ላይ መውደቃቸውን ገልጸዋል።

በኢትጵያ ውስጥ በልማት ስም እየተበራከተ የመጣውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አለማቀፍ ሰብአዊ መብት ተማጓች ድርጅቶች ችላ እንዳሉት ተመልክቷል። በአላማጣ ላለፉት አንድ ወራት የከተማው ህዝብ በልዩ ፖሊሶች ሲዋከብ እንደነበርመዘገባችን ይታወሳል።

 በአዲስ አበባ ላፍቶ ክፍለከተማ ቤታቸው የፈረሰባቸው በርካታ ነዋሪዎች አሁንም በከፍተኛ ችግር ላይ መሆናቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሙስሊሙ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ አንድ ሥራ-አስኪያጁን ማባረሩ ታወቀ



                 
ከአየር መንገድ የውስጥ ምንጮች የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሼባ ማይልስ እየተባለ የሚጠራውን ክፍል በስራ አስኪያጅነት ሲመሩ የነበሩትን አቶ አብዱል ጀባር ሀሚድን ከስራ ያባረረው የአየር መንገዱ ሙስሊም ሰራተኞች ከሌሎች ወገኖች ጎን ተቀላቅለው ተቃውአቸውን እንዲገልጹ አደራጅቷል በሚል ምክንያት መሆኑ ታውቋል።
 ስራ አስኪያጁ በአሁኑ ጊዜ በእስር ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።

በተያየዘ ዜናም በሱፐርቫይዘርነት ደረጃ ስትሰራ የነበረችው ትእግስት ደምሴ ከስራ በተቀነሰ ሰራተኛ ላይ የሀሰት ምስክርነት እንድትሰጥ ተጠይቃ ፈቃደኛ ባለመሆና መሆኑ ታውቋል።

ኢሳት የኢህአዴግ አባል ለመሆን ፈቃደኛ ያልሆኑ 50 የአየር መንገዱ ሰራተኞች መባረራቸውንና በኢህአዴግ የወጣት ፎረም አባላት መተካታቸውን ገልጸ ነበር። ከስራ የተቀነሱት የ36 ሰራተኛች ሙሉ ስም ዝርዝር እና አሁን ያሉበት ደረጃ የደረሰን ሲሆን፣ ሙሉውን ዝርዝር በኢሳት ዌብሳይት ላይ ታትሞ መውጣቱን ለመግልጽ እንወዳለን።

በጉዳዩ ዙሪያ የአየር መንገዱን አመራሮች ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

onsdag 23. januar 2013

በአላማጣ የአንድ አካባቢ ነዋሪዎች ቀኑን ሙሉ በልዩ ሀይሎች ታግተው ዋሉ


          ጋርቬ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚኖሩ የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች ዛሬ ጧት ወደ ስራ ለመሄድ ሲነሱ አካባቢያቸው  በሙሉ በፌደራል ልዩ ሀይል ፖሊሶች ተከቦ አግኝተውታል። ማንም ከቤት እንዳይወጣ በማገድ የመንግስት ባለስልጣናት በስም ጽፈው የያዙዋቸውን ከ300 በላይ ቤቶች ሲያስፈርሱ ውለዋል።

በእያንዳንዱ ቤት በር ላይ ሁለት ሁለት ልዩ ፖሊሶች ቆመው የእያንዳንዱን ሰው ቤት እንቅስቃሴ በሚከታተሉበት ሁኔታ የተለያዩ ሰዎችን አግኝቶ ለማነጋገር ባይቻልም አንድ ከቤት እንዳይወጡ የታገዱ ሰው እንደገለጡት ለመጸዳዳት እና ልጆቻቸውን ለማጫወት እንኳን ከቤት ሳይወጡ ታግደው መዋላቸውን ገልጸዋል።

ቤት አፍራሽ ግብረሀይሎች ቀኑን ሙሉ ሲያፈርሱ ውለው አካበቢውን ከ11 ሰአት በሁዋላ ለቀው የሄዱ ሲሆን ፣ ንብረቶቻቸው ሜዳ ላይ የወደቁባቸው ሰዎች ራሳቸውን ስተው ሲወድቁ ዘግይቶ ያነጋገርነው አንድ የአይን እማኝ ገልጿል
ባለፈው ጥር ወር መግቢያ ላይ ተቃውሞውን መርተዋል ተብለው የታሰሩት ሰዎች ከእስር ቤት ሳይወጡ ቤታቸው እንዲፈርስ ተደርጓል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከማንነት ጋር በተያያዘ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ የሚነሳው ጥያቄ እየጨመረ መሆኑ ታውቋል። የትግራይ ክልል መንግስት ከዚህ ቀደም የነበሩ የተለያዩ በኦሮምኛና በአማርኛ የተጻፉ ወካይ ስሞችን በመለወጥ የአካባቢውን ታሪክና ባህል ለማጥፋት እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል። “የራያ ህዝብ ባህልና ታሪክ ” በሚል ርእስ በክብሮም አሰፋ የተጻፈው መጽሀፍ እንዳይሰራጭ መታገዱ በአካባቢው ያለውን ውጥረት እንደሚያሳይ ነዋሪው ገልጸዋል።

አላማጣ ኢህአዴግ ስልጣን ከመያዙ በፊት የወሎ ክፍለሀገር ግዛት እንደነበር ይታወሳል። በዚህ ጉዳይ ላይ የተለያዩ የአካባቢውን ሰዎች ለማነጋገር ጥረቶችን እያደረግን ነው እንደተሳካልን እናቀርባለን።

የአላማጣ ከተማ አስተዳዳር ጽህፈት ቤትን ለማነጋገር ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪዎችን ብናደርግም ሊሳካልን አልቻለም።

የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ሙስሊም ተማሪዎች ግቢአቸውን ለቀው ወጡ

    


             በባህርዳር ዩኒቨርስቲ ስር በሚገኙት በፔዳ ፣ ፖሊ፣ ይባብና ዘንዘልማ ካምፓሶች ይማሩ የነበሩ ከ95 በመቶ ሙስሊም ተማሪዎች ግቢአቸውን ለቀው መውጣታቸውን የተወሰኑትም ወደ መጡበት አካባቢ መመለሳቸውን ተማሪዎች ገለጹ።

 ተማሪዎቹ ግቢአቸውን በመልቀቅ ትምህርታቸውን ለማቋረጥ የወሰኑት ከሶስት ሳምንት በፊት የግቢው አስተዳዳሪዎች በዩኒቨርስቲው ውስጥ የሚደረግ ጸሎት እንዲቆም፣ ሴቶች ጂሃብም ኒቃምብ እንዳይለብሱ መከልከላቸውን ተከትሎ ነው።

አንዳንድ ተማሪዎች ከትናንት ጀምረው ትምህርት በማቋረጥ ተቃውሞአቸውን ሲገልጹ የነበረ ቢሆንም፣ የዩኒቨርስቲው አስተዳዳሪዎች “ትእዛዙ ከበላይ አካል የመጣ ነው ምንም ማድረግ አንችልም” የሚል ምላሽ መስጠታቸው ተማሪዎች ግቢያቸውን ለቀው እንዲወጡ አድርጓቸዋል። አንድ ተማሪ እንደገለጸው የተወሰኑ ተማሪዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለሳቸውን ፣ ሌሎችም ትኬት በመቁረጥ ላይ ናቸው።

tirsdag 22. januar 2013

መንግሥት የበጀት ጉድለቱን ለመሸፈን ከአገር ውስጥ ባንኮች ሊበደር ነው





        የአገሪቱን ኢኮኖሚና የዜጎችን ኑሮ እየተፈታተነ የሚገኘውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር ከ እንግዲህ ከአገር ውስጥ አንበደርም
        ሲል የነበረው የ ኢትዮጵያ መንግስት ዘንድሮ ያጋጠመውን የበጀት ጉድለት መሸፈን ባለመቻሉ ከ አገር ውስጥ ባንኮች ሊበደር
          እንደሆነ ሪፖርተር ዘገበ።

ለኑሮ ውድነቱ ጣራ መንካት አንዱና ዋነኛው ምክንያት መንግስት ከ አገር ውስጥ መበደሩና ይህንንም ብድር ለማሟላት ብር እንዲታተም ማድረጉ ነው በማለት የቀረበባቸውን ትችት ከብዙ ማንገራገር በሁዋላ የተቀበሉት ሟቹ ጠ/ሚ/ር አቶ መለስ ዜናዊ፤ “ከ እንግዲህ ግን መንግስት ፈጽሞ ከ አገር ውስጥ ባንኮች አይበደርም” ማለታቸው ይታወሳል።

ይሁንና የዘንድሮን 26.8 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት ለመሸፈን መንግስት ከአገር ውስጥ እንደሚበደር አስታውቋል።

መንግስት ብድሩን ለማግኘት ሲል እንዲታተም የሚያደርገው ብር እንደማይኖር ቢናገርም፤ባንኮች የማበደር አቅሟቸው እጅግ የተዳከመ በመሆኑ ገንዘብ ወደ ማተሙ ማምራቱ አይቀሬ እንደሆነ እየተነገረ ነው።

ጋዜጣው የጠቀሳቸው የ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ፦”የአገሪቱ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ በመቀዛቀዙ እና ከአገር ውስጥ ምንጮች ብድር ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ፣ መንግሥት ብር ማተም ውስጥ ሊገባ ይችላል ሲሉ “ ያስጠነቅቃሉ፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የ2005 ዓ.ም. የፌደራል መንግሥት በጀት 137 ቢሊዮን ብር መሆኑ ይታወሳል፡፡

 ይህንን በጀት ለመሸፈን ከታክስና የተለያዩ ገቢዎች 111 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን፣ ቀሪው 26 ቢሊዮን ብር ግን በበጀት ጉድለትነት ተይዞ በተለያዩ አማራጮች ለመሸፈን መታቀዱን ያስረዳል፡፡

ከእነዚህም መካከል 7.9 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን ከውጭ አገሮች ከሚገኝ የፕሮጀክት ብድር፣ 5 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን በዓለም ባንክ በኩል ለመሠረታዊ አገልግሎቶች ከለላ ከሚገኝ ብድር፣ እንዲሁም 169 ሚሊዮን የሚሆነውን ብር በእዳ ስረዛ ከሚገኝ ለመሸፈን መታቀዱን ይተነትናል፡፡

በመሆኑም ከላይ የተዘረዘሩት አማራጮች ከአጠቃላይ የበጀት ጉድለቱ 13 ቢሊዮን ብር ያህሉን የሚሸፍኑ ሲሆን፣ ቀሪውን 13 ቢሊዮን ብር ግን ከአገር ውስጥ ብድር ለመሸፈን መታቀዱን ያብራራል፡፡

መንግሥት ከአገር ውስጥ ምን ያህል ሊበደር እንደሚችል የተጠየቁት የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትር አቶ ሐጂ ኢብሳ ፣ “አሁን ላይ ሆነን መንግሥት ምን ያህል ሊበደር ይችላል የሚለውን መገመት አዳጋች ነው” ብለዋል፡፡

ነገር ግን ከብሔራዊ ባንክ የመበደር ዕቅድ በጭራሽ አለመኖሩን፣ ብድሩን በኢኮኖሚው ውስጥ በመንቀሳቀስ ላይ ከሚገኝ ገንዘብ ለመሸፈን መታቀዱንና እየተረጋጋ የመጣውን የዋጋ ንረት በማይጎዳ ሁኔታ እንደሚፈጸም አስረድተዋል፡፡

በኢኮኖሚ ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ከሚገኝ ገንዘብ ማለት ከሌሎች የመንግሥት አበዳሪ ባንኮች እንደ ንግድ ባንክና ልማት ባንክ እንደሆነ ጋዜጣው ያነጋገራቸው ከፍተኛ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡

 ነገር ግን እነዚህ ከፍተኛ የማክሮ ኢኮኖሚ ተንታኞች የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከመቀዛቀዝ ባለፈ ችግር ውስጥ ስላለ የባንኮች የማበደር አቅም የሳሳ መሆኑን ያሳያል ይላሉ፡፡

 ስለዚህ መንግሥት ብር የማተም ግዳጅ ውስጥ ሊገባ ይችላል ሲሉ ፍርኃታቸውን ይገልጻሉ፡፡

ሙስሊም ኢትዮጵያውያን በደቡብ አፍሪካ ተቃውሞአቸውን አሰሙ



           በኢትዮጵያ እና በዛምቢያ መካከል የተካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ ተከትሎ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን የተለያዩ መፈክሮችን 
          በመያዝ  መንግስት በሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይ የሚወስደውን እርምጃ ተቃውመዋል።

ሙስሊሞቹ መሪዎቻችን ይፈቱ፣ በእምነታችን አንደራደርም፣ የሀይማኖት ነጻነት ይከበር፣ የሚሉ መፈክሮችን በእንግሊዝኛ በመጻፍ ለአለም የቴሌቪዥን ተመልካቾች አሳይተዋል።

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ብሄራዊ ቡድኑን በከፍተኛ ስሜት ከመደገፍ አልፈው በእረፍት ሰአቶቻቸው ተቃውሞአቸውን ሲገልጹ ተስተውሎአል።

mandag 21. januar 2013

በኤርትራ የወታደሮች አመፅ ቆመ





            ያመፁ የኤርትራ ወታደሮች የማስታወቂያ ሚኒስቴሩን ለአንድ ቀን ከተቆጣጠሩ በኋላ ለቅቀው መውጣታቸው ተዘግቧል፡፡


           ወደ አንድ መቶ እንደሚሆኑ የተነገረው ወታደሮች ወደ ደቡብ የጦር ሠፈራቸው የተመለሱት ከፕሬዚዳንት   ኢሣያስ  አፈወርቂጋር ከተነጋገሩ በኋላ እንደሆነ ተሰምቷል፡፡


ዛሬ አብዛኛውን ቀን ዝግ ሆኖ የዋለው የሃገሪቱ ቴሌቪዥን ጠፍቶ የዋለበትን ምክንያት ሣይናገር ምሽት ላይ መደበኛ ፕሮግራሙን ቀጥሏል፡፡

የቴሌቪዥን ጣቢያው ድንገት ከመቋረጡ በፊት አንባቢው ሕገመንግሥቱ እንዲከበር እና የፖለቲካ እሥረኞች እንዲፈቱ የሚጠይቅ መግለጫ ያነብብ እንደነበረ ታውቋል፡፡


ስድስት ሚሊየን ሕዝብ ባላት ኤርትራ ከአምስት ሺህ እስከ አሥር ሺህ የፖለቲካ እሥረኞች ወህኒ ቤት ውስጥ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ቢሮ ገልጿል፡፡


እሥረኞቹ ዛሬ (ሰኞ) ረፋዱ ላይ በብረት ለበስ መኪና መምጣታቸውንና ቅሬታዎቻችን ናቸው የሚሏቸውን ጉዳዮች ዝርዝር ይዘው እንደነበረ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ብዙ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሠራተኞች አመልክተዋል፡፡

የወታደሮቹ ጥያቄ ምን እንደነበረ እና አመፁ በምን እንደተፈታ ለጊዜው የተገኘ ዝርዝር መረጃ የለም፡፡

አሥመራ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ዜጎቹ አሥመራ ከተማ ውስጥ ከሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች እንዲቆጠቡ ማሳሰቢያ አውጥቷል፡፡

የኤምባሲው መግለጫ የሚናገረው በአንዳንድ የዋና ከተማይቱ አካባቢዎች ወታደሮች በብዛት እየታዩ መምጣታቸውን ዲፕሎማቶች መናገራቸውን ነው፡፡


በሥልጣን ላይ ያሉት ፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከተገነጠለችበት ጊዜ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ መንበሩን እንደተቆናጠጡ መሆናቸው ይታወቃል፡፡


ኤርትራ ለውጭው ዓለም በአመዛኙ ዝግ የሆነችና በጠንካራ እፍኞች ተጨብጣ የሆነች ሃገር እንደሆነች ይነገራል፡፡

ዛሬ ስለተፈጠረው አጋጣሚ የመንግሥቱን አስተያየት ለመጠየቅ ስልክ በተደጋጋሚ ቢደወልም ባለሥልጣናቱ ስልኮቹን ሳያነሱ ቀርተዋል፡፡



ኤርትራ ሶማሊያ ውስጥ የሚንቀሣቀሱ አማፂያንን ታስታጥቀለች፤ ትረዳለች በሚል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዛሬ ሦስት ዓመት አካባቢ - እአአ በ2009 ዓ.ም ማዕቀብ እንደጣለባት ይታወሣል፡፡

የኢትዮጵያ ብረታ ብረት እንጂኔሪንግ ኮርፓሬሺን 70 በመቶው የአመራር ቦታ በህወሀት አባለት የተያዘ ነው ተባለ

ኢሳት ዜና:-ግንቦት7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ለኢሳት በላከው ሁለተኛ ጥናቱ ላይ እንዳመለከተው በ11 መምሪያዎች የተዋቀረው በስሩ አስራ ሦስት ግዙፍ እንዱስትሪዎቸን የሚያስተዳደርው የኢትዮጵያ ብረታ ብረት እንጂኔሪንግ ኮርፓሬሺን አስራ አንድ ትላልቅ መምሪያዎችና አስራ ሦስት ግዙፍ እንዱሰትሪዎች በዋና ሀላፊነት፤ በዳይሬክተርነትና በምክትል ዳይረክትርነት የሚመሩ በ29 የከፍተኛ አመራር አባላት ነው።

ከእነዚህ 29 ከፍተኛ አመራር አባላት ዉስጥ 69 በመቶዉ ወይም ሃያዉ የህወሀት አባላት የሆኑ ወታደራዊ መኮንኖች ናቸዉ።በዚህ ከፍተኛ የአመራር ቦታ ላይ የኦሮሞና የአማራ ተወላጆች ያላቸዉ ቦታ 31 በመቶ ወይም ከእያንዳንዳቸዉ በቅደም ተከተል ሦስትና ስድስት ሰዎች ብቻ ሲሆን ከተቀሩት አምስት ክልሎች በዚህ ከፍተኛ የአመራር ቦታ ላይ የተመደበ አንድም ሰዉ የለም ፣ እንደጥናቱ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ጠንካራ እንዱስትሪ ለመገንባት በሚደረገዉ ጥረት ዉስጥ ከፍተኛዉን ሚና ይጫወታል የሚባለዉ የብረታ ብረት እንጂኔሪንግ ኮርፓሬሺን በሲቪልና ወታራዊ መምሪያዎች ተከፋፍሎ የተዳራጀ ሲሆን በስሩ አስራ ሦስት ግዙፍ እንዱስትሪዎች እንደሚገኙ የጠቀሰው ግንቦት7፣ ከአስራ ሦስቱ እንዱስትሪዎች ዘጠኙን የሚያስተዳድሩት የህወሀት አባላት ናቸዉ። በኮርፖሬሺኑ ዉስጥ ከፍተኛ ስልጣን ከተሰጣቸዉ የህወሀት አባላት መካከል ብረጋዴር ጄኔራል ክንፈ ዳኘዉ የብረታ ብረት እንጂኔሪንግ ኮርፖሬሺን ዋና ዳይሬክተር ፤ ኮ/ል ተከስተ ኃ/ማሪያም በምክትል ዋና ዳይረክተር ማዕረግ የኮርፖሬት ፕሮዳክሺን ግንባታ ሀላፊ ፤ ኮ/ል ፀጋሉ ኪሮስ በምክትል ዋና ዳይሬክተር ማዕረግ የኮርፖሬት ወታደራዊ ምርቶች ሀላፊ ፤ ኮ/ል ሙሉ ወ/ሰንበት በምክትል ዋና ዳይረክተር ማዕረግ የኮርፖሬት ፕሮጀክቶች አስተደዳደር ሀላፊ፤ሻምበል ካህሳይ ክሽን የምርመራና ልማት ዳይረክተርና ሻምበል ገ/ስላሴ ገ/ጊዮርጊስ የአቅም ግንባታና ስልጠና ማዕከል ዳይሬክተር ይገኙበታል።

ከትግራይ ዉጭ ከሌሎቹ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔሰቦች በብረታ ብረት እንጂኔሪንግ ኮርፓሬሺን እንዱስትሪዎች ዉስጥ ከፍተኛ የሀላፊነት ደረጃ ባለዉ የአመራር ቦታ ላይ የመቀመጥ ዕድል ያገኙ ኢትዮጵያዉያን ቁጥር አራት ብቻ ናቸው። ኬሚካልና ሴንተቲክ እንዱስትሪ ሃለፊ መ/አ ሰለሞን ዘውዴ፣ አዳማ ጋርመንት እንዱስትሪ ሃለፊ ኮ/ል ፍሰሀ ግደይ፣ ሜታልስ እንዱስትሪ ሃለፊ ሻለቃ መኮንን በላይ፣ ፓወር እንዱስትሪ ሃለፊ፣ ሻምበል አሰፋ የሀንስ፣ ሆሚቹ ኢሚዩኔሽን ኢንጂነሪንግ ሃለፊ ኮ/ል ሀድጉ በላይ፣ ህብረት ማሽን ቱል ኢንጂነሪንግ ሃለፊ፣ ሻምበል ተሰማ ግደይ፣ ቢሾፍቱ አቶሞቲቭ ሎኮሞቲቭ ሀላፊ፣ ኮ/ል ገብረመድህን ገ ስላሴ ፣ የደጀን አቪየሽን እንዱስትሪ ሀላፊ ሳለቃ ኢሉ ጸጋየ እንዲሁም የጋፋት አርማመንት እንዱስትሪ ሀላፊ ሻለቃ ግሩም ገብረመድህን የህወሀት አባላት ትጋረይ ተወላጆች መሆናቸው በጥናቱ ተመልክቷል። የኢትዮ ፕላስቲክ እንዱስትሪ ሃለፊ አቶ ጋሻው እምሩ፣ እርሻ መሳሪያዎች እንዱስትሪ ሃለፊ ኮሎኔል ደሴ ዘለቀ እና የሀይቴክ እንዱሰትሪ ሀላፊ ኮ/ል ጸጋየ አንሙት የአማራ ተወላጆች ሲሆኑ፣ ከኦሮሞ ደግሞ የፋብሪኬንና ስትራክቸራል እንዱስተሪ ሀላፊው ኮ/ል ብቂላ ብቻ ተጠቅሰዋል።

ይህ ጥናት የተጠናዉ ከ2004 እስከ 2005 ዓም ባለዉ የአንድ አመት ግዜ ዉስጥ መሆኑን ተጠቅሷል። ግንቦት7 በቅርቡ በኢትዮቴልኮም ውስጥ ያለውን የብሄር ተዋጽኦ ይፋ ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግስት ሰዎቹ የሚሾሙት በዘራቸው ሳይሆን በችሎታቸው ነው በማለት ይከራከራል። መንግስት 7ኛውን የብሄር ብሄራሰቦች ቀን 200 ሚሊዮን ብር በማውጣት በባህርዳር ማክበሩ ይታወሳል።

lørdag 19. januar 2013

የከተራ በአል ዛሬ በኦርቶዶክስ አማኞች ዘንድ እየተከበረ ነው


ኢሳት ዜና:-በመላ አገሪቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አማኞች እየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀበትን ቀን ለማሰብ የከተራ በአልን በድምቀት እያከበሩ ነው።

በአዲስ አበባ የሚገኙ በርካታ ታቦታት ከእየ አብያተክርስቲያናቱ ተነስተው በምእመናን ፣ ቀሳውስት እና ዘማሪያን ታጅበው ባህረጥምቀቱ ወደ ሚገኝበት ጃን ሜዳ አቅንተዋል።

በአሉ በድምቀት ከሚከበርባቸው ከተሞች መካከል አንዱ በሆነው ጎንደርም እንዲሁ ታቦታቱ ዛሬ ወደ ማደሪያቸው አቅንተዋል።
ለ3ኛ ጊዜ ጥምቀትን ተከትሎ የሚካሄደው የኢትዮጵያን በጎንደር የባህል ፌስቲቫል ቀዝቀዝ ባለሁኔታ መከበሩን ዘጋቢያችን ከስፍራው ገልጿል፡፡ በሲምፖዚየሙ ላይ አቶ በረከት ስምኦን ፤የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሩ አቶ አሚን አብዱልቃድር፣ የስነምግባርና ጸረሙስና ኮሚሽነሩ አቶ ዓሊ ሱሌይማን እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት መገኘታቸው ታውቋል።


በበዓሉ ላይ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የውጪ አገር ዜጎች(ቱሪስቶች) ተገኝተዋል፡፡ ትላንት ከሰዓት በሃላም የባህል ፌስቲቫሉ በጎንደር አደባባይ የተከናወነ ሲሆን የተገኘው የከተማው ሕዝብ ከአምናና ካቻምና ጋር ሲነጻጸር ቁጥሩና ድምቀቱ ያነሰ እንደነበር የዓይን እማኞች ገልጸዋል፡፡ለምን እንደቀዘቀዘ ግን ምክንያቱ በውል አልታወቀም፡፡ በአደባባይ ለተገኘው ሕዝብ የተለያዩ የባህል ቡድኖችና ት/ቤቶች የተውጣጡ ሰዎች ጭፈራዎቻቸውንና ሽለላዎችን አቅርበዋል፡፡ታዋቂው ድምጻዊ ፋሲል ደሞዝ ለሕዝቡ የተለያዩ ዘፈኞችን በማቅረብ ማዝናናቱ ታውቋል።

onsdag 16. januar 2013

ቅዱስ ሲኖዶስ ያካሄደው ስብሰባ ውጥረት የተሞላበትና የመንግስት ግልጽ ጫና የታየበት መሆኑን የቤተክህነት ምንጮች ገልፁ

Miniatyrbildeኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሀዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በአዲስ አበባ በትናንትናው እለት ያካሄደው ስብሰባ ውጥረት የተሞላበትና የመንግስት ግልጽ ጫና የታየበት መሆኑን የቤተክህነት ምንጮች ገልጸዋል::
 
መንግስትም አቡነ መርቆሪዎስ መንበራቸው ላይ ተመልሰው ማየት እንደማይፈልግ በአቶ አባይ ጸሀዬ በኩል ግልጽ አቆሙን ያንጸባረቀ በመሆኑ የዕርቁ ጉዳይ ፍጻሜ ላይ መድረሱን ለማወቅ ተችሎል::
 
በውጭ የሚገኙ አባቶች በዛሬው እለት በሎስ አንጀለስ በጀመሩት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ ለመገኘት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ በትላንትናው እለት ከካናዳ ሎስአንጀለስ ገብተዋል::