lørdag 19. januar 2013

የከተራ በአል ዛሬ በኦርቶዶክስ አማኞች ዘንድ እየተከበረ ነው


ኢሳት ዜና:-በመላ አገሪቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አማኞች እየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀበትን ቀን ለማሰብ የከተራ በአልን በድምቀት እያከበሩ ነው።

በአዲስ አበባ የሚገኙ በርካታ ታቦታት ከእየ አብያተክርስቲያናቱ ተነስተው በምእመናን ፣ ቀሳውስት እና ዘማሪያን ታጅበው ባህረጥምቀቱ ወደ ሚገኝበት ጃን ሜዳ አቅንተዋል።

በአሉ በድምቀት ከሚከበርባቸው ከተሞች መካከል አንዱ በሆነው ጎንደርም እንዲሁ ታቦታቱ ዛሬ ወደ ማደሪያቸው አቅንተዋል።
ለ3ኛ ጊዜ ጥምቀትን ተከትሎ የሚካሄደው የኢትዮጵያን በጎንደር የባህል ፌስቲቫል ቀዝቀዝ ባለሁኔታ መከበሩን ዘጋቢያችን ከስፍራው ገልጿል፡፡ በሲምፖዚየሙ ላይ አቶ በረከት ስምኦን ፤የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሩ አቶ አሚን አብዱልቃድር፣ የስነምግባርና ጸረሙስና ኮሚሽነሩ አቶ ዓሊ ሱሌይማን እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት መገኘታቸው ታውቋል።


በበዓሉ ላይ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የውጪ አገር ዜጎች(ቱሪስቶች) ተገኝተዋል፡፡ ትላንት ከሰዓት በሃላም የባህል ፌስቲቫሉ በጎንደር አደባባይ የተከናወነ ሲሆን የተገኘው የከተማው ሕዝብ ከአምናና ካቻምና ጋር ሲነጻጸር ቁጥሩና ድምቀቱ ያነሰ እንደነበር የዓይን እማኞች ገልጸዋል፡፡ለምን እንደቀዘቀዘ ግን ምክንያቱ በውል አልታወቀም፡፡ በአደባባይ ለተገኘው ሕዝብ የተለያዩ የባህል ቡድኖችና ት/ቤቶች የተውጣጡ ሰዎች ጭፈራዎቻቸውንና ሽለላዎችን አቅርበዋል፡፡ታዋቂው ድምጻዊ ፋሲል ደሞዝ ለሕዝቡ የተለያዩ ዘፈኞችን በማቅረብ ማዝናናቱ ታውቋል።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar