mandag 28. januar 2013

የከምሴ ነዋሪዎች የሀይማኖት መሪያችንን አናስወስድም በማለት ተቃውሞአቸውን ገለጡ


በኢሉባቦር ዞን ከመቱ ከተማ 15 ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ከምሴ ቀበሌ ፖሊሶች ሼህ ሳሊህ አብዱልቃድር የተባሉትን የእስልምና ሀይማኖት መሪ ለመውሰድ በሄዱበት ወቅት ህዝቡ ግለሰቡን አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ችግር መፈጠሩ ታውቋል።

ሼህ ሳሊህ አብዱልቃድር ከዚህ ቀደም በሽብርተኝነት ተከሰው 8 ወራት ከታሰሩ በሁዋላ መረጃ አልተገኘባቸውም በሚል በነጻ ተለቀው ነበር። ባለፈው ሳምንት ፖሊሶች እንደገና ወደ አካባቢው በመሄድ የእርሳቸውን ጓደኛ ያሰሩ ሲሆን፣ ዛሬ ደግሞ ሼኩን ለማሰር ወደ ቀበሌው ሲሄዱ ህዝቡ በነቂስ በመውጣትና ተክቢራ በማለት በመቃወሙ በህዝቡና በፖሊስ መካከል ፍጥጫ ተከስቶ ነበር። የህዝቡን ስሜት የተረዱት ፖሊሶች በቀጥታ ወደ ግጭት ከማምራት ይልቅ ከህዝቡ ተወካዮች ጋር ለመነጋጋር መምረጣቸ ው ታውቋል።

በሽማግሌዎችና በፖሊስ መካከል ያለው ውይይት ይህን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ እንደቀጠለ ነው።

በሌላ ዜና ደግሞ ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ መጡበት አካባቢ የተመለሱ ከ700 የማያንሱ የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ፣ ጥያቄያቸው ካልተመለሰ ትምህርት ለመጀመር እንደሚቸገሩ እየገለጹ ነው።

 ኢሳት የነጋገራቸው ተማሪዎች እንደሚሉት በዩኒቨርስቲው በሙስሊም ተማሪዎች ላይ የሚደርሰው ጭቆና የሚጀምረው ” ወደ ግቢ ለመግባት በሚደረገው ፍተሻ ነው”
በዛሬው እለት ወደ አዲስ አበባ የተመለሱ ተማሪዎች ከወላጆቻቸው ጋር በመሆን በትምህርት ሚኒስቴር በመገኘት ጥያቄያቸውን ለማቅረብ እቅድ ተይዞ እንደነበር ለማወቅ ተችሎአል።

 ይሁን እንጅ በተማሪዎች እና በመንግስት መካከል ስለነበረው ውይይት ለማወቅ የተደረገው ሙከራ አልተሳካም። የዩኒቨርስቲው አስተዳደር ሙስሊም ሴቶች ኒቃብ እንዳይለብሱ፣ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በጋራ በግቢው ውስጥ ስግደት ወይም ማንኛውም ሀይማኖታዊ ስነስርአት እንዳያካሂዱ ያወጣው መመሪያ እንደማይለወጥ አስታውቋል።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar