fredag 1. mars 2013

የኩማ አስተዳደር ህዝቡን ማፈናቀሉን በዘመቻ መልክ ጀመረ


ከስልጣኑ ለመልቀቅ የሁለት ወራት ጊዜያት የቀሩት የኩማ አስተዳደር“ፈጣን ለውጥ አምጪ” በሚለው ፕሮግራሙ በተለያዩ አካባቢዎች በልማት ስም የአዲስአበባን ነዋሪ የማፈናቀል ስራውን በዘመቻ መልክ እያከናወነ መሆኑ ተጠቆመ፡፡

ከባቡር፣ከመንገድ እና በኢንቨስትመንት ስም በተለይ በቦሌ፣በቂርቆስ፣በልደታ፣በኮልፌ ቀራኒዮ፣በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተሞች ካለፉት ሁለት ሳምንት ወዲህ ዜጎችን ከሕግና ስርዓት ውጪ የማፈናቀሉን ሥራ ተፋፍሞ መቀጠሉን ከየአካባቢው ያገኘናቸው መረጃዎች እየጠቆሙ ነው፡፡

ከባቡር መስመር ዝርጋታ ጋር በተያያዘ በ22 አካባቢ በአምስት ቀናት ጊዜያት ውስጥ ንብረታቸውን እንዲያነሱ ዜጎች በመገደድ ላይ ናቸው፡፡ በአካባቢው የሚገኙ የግል ይዞታ ባለንብረቶች ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት ተገቢውን ካሳ በወቅቱ ያልተከፈላቸው ሲሆን የካሳው ጉዳይ በተመለከተ ውጪ ሆናችሁ ተከታተሉ የሚል ምላሽ በመስጠት ሜዳ ላይ እንዲወድቁ መደረጉ እንዳሳዘናቸው አንድ የችግሩ ሰለባ ለኢሳት ዘጋቢ ነግረውታል፡፡

በኡራኤል ቤተክርስቲያን አካባቢ የኮንስትራክሽን የፋብሪካ ውጤቶችን በማከፋፈልና በመቸርቸር የንግድ ስራ የተሰማሩና ወደአንድ ሺ የሚጠጋ ጊዜያዊና ቋሚ ሰራተኞች ያሏቸው ነጋዴዎችም በተመሳሳይ መልክ በአምስት ቀናት ጊዜ ውስጥ እንዲለቁ መገደዳቸውን ጠቅሰው በሕግና በስርዓቱ ቢሆን ቢያንስ የ90 ቀናት ማስጠንቀቂያ ሊሰጣቸው ይገባ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

የኡራኤል አካባቢ ከሊዝ ነጻ በምደባ ለአንድ የእምነት ተቋም ተሰጥቷል የተባለው በ1998 ዓ.ም እንደነበር ነጋዴዎቹ አስታውሰው በቦታው ላይ ያለን ነጋዴዎች በሕጉ መሰረት የማልማት ቅድሚያ እንዲሰጠን ጥያቄ ብናቀርብም ሰሚ ማግኘት አልቻልንም ብለዋል፡፡

በአካባቢው የሚገኙ የተወሰኑ የመንግስት ቤቶች መኖራቸውን እና የኪራይ ውል እስከ2006ዓ.ም የታደሰ እንዳላቸው ነጋዴዎቹ አስታውሰው ቀድሞ የኪራይ ውሉ ሳይቋረጥ ምንም ዓነት ማስጠንቀቂያ ሳይደርሳቸው በድንገት በአምስት ቀናት ልቀቁ መባላቸው አሳዛኝ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡

የኩማ አስተዳደር የሊዝ ቦርድ በሕግ ከተሰጠው ስልጣን ውጪ ከሶስት ጊዜ በላይ አንድን ጉዳይ ማየት እንደማይችል እየታወቀ ቦርዱ ግን ለስድስት ጊዜያት ያህል ጉዳዩን በማየት በሕገወጥ ውሳኔ እንድንፈናቀል ተደርጓል ብለዋል፡፡

ነጋዴዎቹ አያዘውም በስራቸው በርካታ ሰራተኞችን እንደሚያስተዳድሩ ከፍተኛ ግብርም ከፋዮች መሆናቸውን በማስታወስ ቦታው ለሃይማኖት ተቋም በነጻ ከሚሰጥ በሊዝ ክፍያ የማልማት የቅድሚያ መብታችን ይከበርልን በሚል ያነሳነው ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያጣ መደረጉ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡

ነጋዴዎቹ በዛሬው ዕለት ከህግና ከስርዓት ውጪ እየተወሰደ ያለው እርምጃ እንዲቆምላቸው ለፍርድ ቤት አመልክተው ፍ/ቤቱ ለፊታችን ሰኞ ወረዳው ምላሹን ይዞ እንዲቀርብ የታዘዘበትን ወረቀት ቢያስገቡም ሰዎቹ ከአድራጎታቸው ሊታቀቡ እንዳልቻሉ በመጥቀስ ከፍ/ቤት ውጪ ለማን አቤት እንላለን ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የኩማ አስተዳደር በሚያዝያ ወር 2005 ኢህአዴግ ብቻውን ከሚወዳደርበት ምርጫ በኋላ ፈርሶ በሌሎች የኢህአዴግ ሰዎች ይተካል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከዚህ ቀደም በተለያዩ በላፍቶና በቦሌ ክፍለከተሞች የተፈናቀሉ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መፍትሄ ሳያገኙ አሁንም በከፍተኛ ችግር ላይ ወድቀው ይገኛሉ።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar