søndag 3. mars 2013

ጉምሩክና ግብር ከፋዮች እየተወዛገቡ ነው



የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ በተከማቸ የአክስዮን ድርሻ ላይ 10 በመቶ ክፍያ እንዲፈጸም ያወጣው መመሪያ አሁንም ከከፍተኛ ግብር ከፋዮቹ ጋር እያወዛገበው ይገኛል፡፡

በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/1994 መሰረት አክስዮን ማኀበራት ወይም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኀበር ካከፋፈሉት የአክስዮን የትርፍ ድርሻ 10 በመቶ እንዲከፍሉ የሚያስገድድ ቢሆንም ላለፉት ዓመታት በህግ አስፈጻሚው ችግር አዋጁ ተግባራዊ ሳይሆን ቆይቷል፡፡

የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን አዋጁ ከወጣ ከ10 ዓመታት በኋላ በያዝነው ዓመት መጀመሪያ የአፈጻጸም መመሪያ በማውጣት ወደኋላ ሄዶ ውዝፍ ዕዳ ከነቅጣቱ እና ወለዱ ለመሰብሰብ መነሳቱ ከፍተኛ ግብር ከፋዮችን አስቆጥቷል፡፡

ከፍተኛ ግብር ከፋዮቹ ባለስልጣኑ በራሱ ችግር መሰብሰብ ያልቻለውን ግብር ከ10 ዓመታት በኋላ ወደኋላ ሄዶ ለመጠየቅ የህግም የሞራልም ድጋፍ የለውም በሚል ተቃውሞአቸውን በተደጋጋሚ ቢያሰሙም ጨርሶ መግባባት አልቻሉም፡፡

ነጋዴዎቹ ግብር አለመከፈሉ ጥፋት እንኳን ተደርጎ ቢወሰድ በይርጋ ይታገዳል የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡

 በተጨማሪም ባለሰልጣኑ በራሱ ድክመት ያልሰበሰበውን ግብር ድንገት ተነስቶ እኛን ባለዕዳ ከማድረግ
ባለፈ ቅጣትና ወለድ ከፋይ ለማድረግ መነሳቱ አሳዛኝ ነው ብለውታል፡፡

በነጋዴዎች ተቃውሞ ጫና የበዛበት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ካለፉት ሳምንታት ጀምሮ ግብሩን ወደኋላ ሄዶ መጠየቁ እንደተጠበቀ ሆኖ ከግብር አለመከፈሉ ጋር ተያይዞ የጠየቀውን ቅጣትና ወለድ ለማንሳት ተገዶአል፡፡

በተጨማሪም የተጠየቀውን ፍሬግብር ክፍያ በረዥም ጊዜ እንዲከፈል መወሰኑን ለነጋዴዎቹ ይፋ አድርጓል፡፡

ይህም ሆኖ አሁንም በርካታ ግብር ከፋዮች አስቀድመን ባከፋፈልነው የአክስዮን ድርሻ እና መልሰን ለኢንቨስትመንት ያዋልነውን ገንዘብ አሁን ወደኋላ ተመልሰን ከየት አምጥተን ግብር እንከፍላለን በሚል በተቃውሞአቸው ቀጥለዋል፡፡

ባለስልጣኑ በየኣመቱ ከሚሰበስበው ግብር የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ድርሻ እስከ 80 በመቶ ይደርሳል፡፡

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar