በዓሉን አስመልክቶም ከንጋቱ 12 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ 21 ጊዜ መድፍ ተተኩሶአል፡፡ የአቶ መለስ ሙት ዓመት ጉለሌ በሚገኘው የዕጽዋት ማዕከል የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣የጎረቤት አገር መሪዎች፣ዲፕሎማቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከብርዋል፡፡ በተለይ የመንግስት ሠራተኞች በግዳጅ በመስቀል አደባባይ የሻማ ማብራት ስነስርዓት እንዲያካሂዱ መታዘዛቸው ታውቋል፡፡
ይህን ተከትሎም በርካታ ሠራተኞች ዕለቱን እንደዕረፍት በመቁጠር በስራ ገበታቸው ላይ እንዳልተገኙ፣ የተገኙትም መደበኛ ስራቸውን ማከናወን ሳይችሉ እንደቀሩ የጠቆመው ዘጋቢያችን ኃላፊዎችም በዓሉን እያከበሩ በመሆኑ ስራ የሚከታተል ሀላፊ እንዳልነበርም አክሏል፡፡
በተለይ በአዲስአበባ ማዘጋጃ ቤት በሚገኙ የተለያዩ ቢሮዎች በመንግስት ወጪ ከፍተኛ መጠን ያለው ጧፍ ተገዝቶ ከቀኑ 9 ሰዓት ጀምሮ በመስቀል አደባባይ ሠራተኞቹ ተገኝተው የቀድሞ መሪያቸውን ሙት ዓመት እንዲያስታውሱ መመሪያ ተሰጥቶአቸዋል።
የመንግስት ሐብትና የስራ ሰዓት እየባከነ መሆኑ ገዥዎቻችን ልብ አላሉትም የሚለው አንድ አስተያየት ሰጪ በአሁኑ ወቅት በመለስ ስም የተለያዩ ንብረቶች እየተገዙ እግረመንገድም በየቢሮው ምዝበራው እየተጧጧፈ መሆኑ አሳዛኝ ነው ብሎአል።
የጎዳና ላይ ተዳዳሪዎች እና የተለያዩ ህጻናት ሳይቀር በመኪኖች እየተጫኑ ለመለስ ሙት አመት እንዲገኙ መደረጉን ዘጋቢያችን ከላከው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል።
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar