ኣንዲት የጉዲፈቻ ልጃቸውን ኣሰቃይተው ለሞት ያበቁ ባልና ሚስት አሜሪካውያን ከ28 እስከ37 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተፈረደባቸው።
የ13 ዓመትዋ ሐና ዊሊያምስ ህይወቷን ያጣችዉ በጎርጎሪዮሳዊዉ የዘመን ቀመር ግንቦት 12 ቀን 2011ሲሆን ከትናንንት በስተያ ማክሰኞ ዕለት ያስቻለው የሲኣትል ፍርድ ቤት አንደኛ ተከሳሽ ሚስት ወ/ሮ ካሪ ዊሊያምስ 37 ዓመት እና ባል ላሪ ዊሊያምስ ደግሞ 28 ዓመት እንዲታሰሩ ፈርዶባቸዋል።
ካሪ እና ላሪ ዊሊያምስ ኣንድ ሌላ እትዮጵያዊ የጉዲፈቻ ልጅን ጨምሮ ስድስት አብራካቸዉ የተገኙ ልጆችም ኣሏቸው።
በ ዩኤስ አሜሪካ ከሴኣትል በስተ ሰሜን 60 ማይልስ ወይንም 100 ኪ ሜ ላይ በምትገኘው መለስተኛ ከተማ ሲድሮ ዊሊ ነዋሪ የሆኑት ካሪ ዊሊያምስ እና ባለቤትዋ ላሪ ዊሊያምስ የራሳቸው 6 የአብራክ ልጆች እያላቸው ከእነዚህ በተጨማሪ ያኔ ሐና ዓለሙ ትባል የነበረችውን ሙዋች ሐና ዊሊያምስን እና የጉድፈቻ ወንድምዋን ዒማኑዔል ዊሊያምስን ከኢትዮጵያ በጉድፈቻ ያመጡኣቸው እ ኣ ኣ በ2008 ዓ,ም ሲሆን ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ የትምህርት ክፍል ኣስተባባሪ ወ/ሮ መታሰቢያ ሙሉጌታ እንደሚሉት ህጻናቱ ከጉዲፈቻ ቤተሰቦቻቸው ጋር በሰላም የኖሩት የመጀመሪያውን ዓመት ብቻ ነው።
ሀና ዊሊያምስ ሞታ የተገኘችው በ3ኛ ዓመትዋ መሆኑ ነው ኣሁንም እንደ እ አ ኣ ግንቦት 12 ቀን 2012ዓ ም ሲሆን ኣሙዋሙዋትዋም ወ/ሮ መታሰቢያ እንደሚሉት የምግብ እጥረትን ጨምሮ ተደብድባ መሆኑን ኃኪሞች መስክረዋል።
በመካከሉ ጉዳዩ እንደ መቀዛቀዝ ማለቱ ባይቀርም የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላት ባለመታከት ባደረጉት ክትትል የችሎቱ ሂደት እንደገና ተፋጥኖ ባለፈው ማክሰኖ በዋለው ችሎት ኣንደኛ ተከሳሽ ወ/ሮ ካሪ ዊሊያምስ በ37 ዓመት ጽኑ እስራት እንድትቀጣ ተፈርዶባታል። 37 ዓመት በአሜሪካ የመጨረሻው ረጅሙ ቅጣት ሲሆን ዳኛ ሱዛን ኮክ እንደሚሉት እንዲያውም ወንጀለኛዋ እድሜዋ ከፈቀደ ከዚያም በላይ በወህኒ ቤት ልትቆይ ትችላለች።
2ኛው ተከሳሽ እና የቦይንግ ኣውሮፕላን ፋብሪካ ሰራተኛ የሆነው ባል ላሪ ዊሊያምስ ደግሞ የ28 ዓመት ጽኑ እስራት ተፈርዶበታል። የሁለቱም ክስ ከሀና ዊሊያምስ ግድያ በተጨማሪም የወንድሙዋ ዒማኑዔል ዊሊያምስ በደል እና ድብደባንም ያካትታል።
ሁለቱ ወንጀለኛ ጥንዶች ከችሎት በቀጥታ ወደ ወህኒ ከተላኩ በኃላ ዒማኑዔል ዊሊያምስን ጨምሮ ስድስቱ የአብራክ ልጆችም ወዲያውኑ ለጉድፈቻ ተቋም መሰጠታቸውም ታውቀዋል።