ኤልያስ ገብሩ
ሰኔ 01 ቀን 2006 ዓ.ም በሽብርተኝነት ወንጀል ከተጠረጠሩ በኋላ፤ በእነዘላለም ወርቅአገኘሁ የክስ መዝገብ፣ ከአንድ ዓመት በላይ ጉዳያቸው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ሲታይ ቆይቶ ባለፈው ሳምንት ነሐሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም በነጻ እንዲሰናበቱ በችሎቱ ትዕዛዝ ከተሰጣቸው አምስት ግለሰቦች መካከል 2ኛ ተከሳሽ ሀብታሙ አያሌው እና 7ኛ ተከሳሽ አብርሃም ሠለሞን እስከአሁን ድረስ ከቂሊንጦ እስር ቤት መፈታት ባለመቻላቸው የተነሳ፣ በዛሬው ዕለት ማረሚያ ቤቱ ላይ ክስ መቅረቡ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት የቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው ከሆነ፣ ከላይ በተጠቀሰው ቀን፤ ፍርድ ቤቱ፣ በክሱ ከተራ ቁጥር 2-5 እና 7ኛ ተከሳሽ ክሱን መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ እንዲሰናበቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት የመፍቻ ትዕዛዙን በ15/12/2007 ዓ.ም ለማረሚያ ቤቱ ቢደርስም ተከሳሾቹ እስከአሁን ድረስ ከእስር ሊለቀቁ አለመቻላቸውን ይጠቅሳል፡፡ በመሆኑም ‹‹ፍርድ ቤቱ ይህንን ባደረጉ የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ላይ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ባለማክበራቸው ሕጋዊ እርምጃ ከመውሰድ ጋር ተከሳሾቹን እንዲለቅ ጥብቅ ትዕዛዝ እንዲሰጥልኝ በማክበር አመለክታለሁ›› ሲሉ ለ2ኛ ተከሳሽ ሀብታሙ አያሌው ባለቤቱ ወ/ሮ ቤተልሄም አዛናው እና ለ7ኛ ተከሳሽ አብርሃም ሠለሞን ወላጅ እናቱ ወ/ሮ መሠረት ገ/ጊዮርጊስ በዛሬው ዕለት ትዕዛዙን ለሰጠው ችሎት ክሳቸውን ማቅረባቸው ታውቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በነጻ ካሰናበታቸው ተከሳሾች መካከል አብርሃ ደስታ፣ የሺዋስ አሰፋና ዳንኤል ሺበሺ ችሎት በመድፈር ወንጀል ሁለት ጊዜ ያህል መቀጣታቸው የሚታወስ ሲሆን ባለፈው ሳምንት ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ ተከትሎ አቃቤ ሕግ በአምስቱም ተከሳሾች ላይ ይግባኝ ጠይቆ ከእስር እንዳይፈቱ ዕግድ አቅርቦ ነበር፡፡ እንዲሁም የተቀሩት አምስት ተከሳሾች እንዲከላከሉ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ መስጠቱ ይታወቃል፡፡
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar