fredag 19. april 2013
ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ የተመለሱ የአማራ ተፈናቃዮች በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ታወቀ
ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሀይል ተፈናቅለው በፍኖተሰላም እና ቻግኒ ከተሞች ሰፍረው የነበሩ ከ8 ሺ ያላነሱ የአማራ ተወላጆች ኢትዮጵያውያን ባሳደሩት ጫና ወደ መጡበት አካባቢ እንዲመለሱ ቢደረግም፣ በአካባቢው ያጋጠማቸው ያልጠበቁትና በህይወት የመቆየታቸውን ነገር አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን ያነጋገርናቸው ሰዎች ገልጸዋል።
መሬት ያላቸው ተወላጆች ተመላሽ ተፈናቃዮችን ስራ ለመቅጠር ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሰርተው ለማደር ተቸግረዋል። የዞን እና የወረዳ ባለስልጣናት የአካባቢው ሰዎች ተፈናቃዮችን ስራ እንዳይቀጥሩዋቸው ቅስቀሳ በማድረጋቸው ሰዎቹ ለመቀጠር አለመቻላቸውን ያነጋገርናቸው ተፈናቃዮች ይገልጻሉ።
የተፈናቃዮችን ችግር ያባባሰው ደግሞ መንግስት የሰጣቸው የምግብ ዱቄት የጤና ችግር ማስከተሉ ነው። ብዙዎቹ ተፈናቃዮች በተቅማጥ በሽታ እየተሰቃዩ መሆኑን ይናገራሉ።
በአካባቢው ያለው መለስተኛ የጤና ተቋም በአማካኝ ከአራት ሰአት የእግር ጉዞ በሁዋላ የሚገኝ ሲሆን፣ በእግር ተጉዞ ህክምና ለማግኘት እንኳ የገንዘብ ችግር አጋጥሟቸዋል። አርሶአደሮች እንደሚሉት ለበሽታ የዳረጋቸው ጊዜው ያለፈበት የተበላሸ ዱቄት ስለተሰጣቸው ነው።
የተለያዩ ተፈናቃይ አርሶአደሮችን አነጋግረን ለመረዳት እንደቻልነው ተፈናቃዮቹ ባለቡት ቦታ ስራ ለመጀመር ካልቻሉ ወደ መጡበት ቦታ ለመመለስ ፍላጎት አላቸው። አርሶደአሮቹ ንብረታቸው በሙሉ በዝርፊያ ያጡ በመሆኑ እንደ መጀመሪያው ጊዜ የትራንስፖርት ከፍለው ወደ መጡበት ቦታ መመለስ አይችሉም።
በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ህጻናት የትምህርት እድል አጥተው ጊዜያቸውን በከንቱ እያሳለፉ መሆኑንም ለማወቅ ተችሎአል።
በጉዳዩ ዙሪያ የፌደራል መንግስቱ ባለስልጣናትን አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
የኢትዮጵያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ምክትል ሚኒስትር የሆኑት አቶ ብርሀነ ገብረክርስቶስ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ የተፈናቀሉት የአማራ ተወላጆች ህገ ወጥ የመሬት ወራሪዎች በመሆናቸው መፈናቀላቸውንለጀርመን ድምጽ መግለጻቸው ይታወሳል።
የራዲዮ ጋዜጠኛዋ ” የክልሉ መንግስት እኮ ተሳስተን ነው ያፈናቀልናቸው በማለት መግለጫ ሰጥተዋል የሚል ጥያቄ ሲቀርብላቸው ” ተፈናቃዮቹ መመለሳቸውን አላውቅም” በማለት የሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግስት አለ እንዴ? የሚል ጥያቄ በማስነሳት እያወያየ ይገኛል።
Abonner på:
Legg inn kommentarer (Atom)
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar