søndag 14. april 2013

የፍትህ ጋዜጣ አሳታሚ እና የሰማያዊ ፓርቲ አመራር ከመንግስት ሸሽተው ተሰደዱ!


Araya na mastwal

የፍትህ ጋዜጣ አሳታሚ የሆነችው ማስተዋል የህትመት ስራ ድርጅት ስራ አስኪያጅ የነበረው ማስተዋል ብርሃኑ እና የሰማያዊ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር እና የፍትህ ጋዜጣ ድረ ገጽ አዘጋጅ የሆነው አርአያ ጌታቸው መንግስትን ሸሽተው ከሀገር ተሰደዱ!


 
ማስተዋል ብርሃኑ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የሚያዘጋጃት ፍትህ ጋዜጣ አሳታሚ የነበረ ሲሆን በተለይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት በኋላ ፍትህ፤ ”

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሞቱስ ለምን ሞቱ ትላለች…” ተብላ ከሰላሳ ሺህ ኮፒ በላይ እንድትቃጠል ቢደረግም መንግስታችን በቅጡ ስላልተደሰተ በአዘጋጁ ተመስገን እና በአሳታሚው ማስተዋል ብርሃኑ ላይ ክስ መመስረቱ ይታወቃል፡፡ (የማይታወቅ ከሆነ አሁን ይታወቅ)

እነ ማስተዋል ብርሃኑ በተከሰሱበት በዚህ ክስ በ50 ሺህ ብር ዋስትና ተለቀው ለሚያዝያ 17 2005 የተቀጠሩ ሲሆን በክሱ ጥፋተኛ ከተባሉ እስከ አስራ ሰባት አመት እስር ይጠብቃቸዋል፡፡ ማስተዋል ሸሽቶ ከመውጣቱ በፊት የመንግሰት ደህነነት ሰዎች በተደጋጋሚ እየተከታተሉ የእጅ ስልኩን በመንጠቅ ከማን ጋ እንደተደዋወለ እና ምን አይነት መልዕክት (ሜሴጅ) እንደተለዋወጠ በግድ ያዩበት እንደነበር ነግሮኛል፡፡

በነገራችን ላይ የፍትህ አሳታሚ እና ፍትህ ጋዜጣ በቀጠሮ ከተያዘው ክስ በተጨማሪ ወደ አርባ የሚጠጉ በይደር የተያዙ ክሶችም አሉበት፡፡

በተጨማሪም ከስድስት አመታት በፊት የተቃውሞውን ጎራ የተቀላቀለው ወጣት አርአያ ጌታቸው በበኩሉ በተለይ የፍትህ ጋዜጣ ድረ ገጽን ማሰናዳት ከጀመረ ወዲህ የበረታ ክትትል እና ማስፈራሪያ ከመንግሰት የስጋ ዘመዶች እንደደረሰበት ይናገራል፡፡

ከዚህ በፊት አንድ የፌደራል ፖሊስ ኮማንደር በመኪና አፍኖ የማያውቀው ቦታ ከወሰደው በኋላ ለተመስገን ደሳለኝ ከውጪ ሀገር ያሉ አሸባሪ ዲያስፖራዎች የሚያደርጉለት የገንዘብ እርዳታ መኖሩን እና በመሃል ሆኖ ገንዘቡን የሚያቀባብለው ደግሞ እርሱ እንደሆነ ነግሮት፤ ይህንን ድርጊቱን የማያቆም ከሆነ በእህትህ እና በእናትህ ላይ ፈርደሃል ማለት ነው… የሚል ዛቻ አድርሶበታል፡፡

ከአመት በፊት ይህ ማስፈራሪ የደረሰው አርአያ፤ ለቤተሰቦቹ ደህንነት ሲል ቤት ተከራቶ መኖር ቢጀምርም፤ ከአመት በላይ የዘለቀው ይኸው ማስፈራሪያ አሁንም እጅግ ተባብሶ “ከፍትህ ጋዜጣ ጋር ያለህን ግንኙነት አቁም ብለንህ እስካሁን አላቆምክም ስለዚህ እንገድልሃለን!” በሚል ቃል በቃል ማስጠንቀቂያ ሲደርሰው “ገዳዮቹን” መሸሹን ይናገራል፡፡

 አርአያ የፍትህ ጋዜጣ ድረ ገጽ አዘጋጅ የነበረ ከመሆኑም በላይ ሰማያዊ ፓርቲን ከመሰረቱት ግንባር ቀደም ወጣቶች አንዱ ነው፡፡

በፍትህ ምክንያት የተሰደዱት ማስተዋል ብርሃኑ እና አርአያ ጌታቸው አሁንም የደህንነታችን ነገር ስጋት ላይ ነው፤ ብለው ያሉበትን ቦታ እንዳልናገር አደራ ብለውኛል፡፡

 የምናገረው ነገር ግን አለኝ፤ በአዲስ መስመር እንዲህ እላለሁ፤
እንደዚህ እያባረሩ እና እንደዚያ እያማረሩ ስንት አመት መዝለቅ ይቻላል፡፡

 እውነት እውነት እላችኋለው ከጥቂት እርምጃ በኋላ እግራችሁ እግራችሁን ጠልፎ ይጥላችኋል!

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar