torsdag 4. april 2013

በአማራ ተወላጆች ላይ የደረሰውን መፈናቀል ኢትዮጵያውያን ማውገዛቸውን ቀጥለዋል



ከ5 እስከ 10 ሺ የሚደርሱ የአማራ ተወላጆች ከቤንሻንጉል ጉሙዝ አካባቢ ተፈናቅለው ወደ መጡበት የትውልድ ቀያቸው እንዲመለሱ መደረጉ ኢትዮጵያውያንን ከጫፍ እስከ ጫፍ ማነጋገሩን ቀጥሏል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን በመወከል በሩዋንዳ በተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል የፍርድ ሂደት በአቃቢ ህግነት የተሳተፉት ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝና በጉራፈርዳ ወረዳ የተፈጸመው አማርኛ ተናጋሪዎችን የማፈናቀል ድርጊት በዘር ማጥራት ወንጀል በማንኛውም ጊዜ ሊያስጠይቅ እንደሚችል የተለያዩ አለማቀፍ ድንጋጌዎችን በመጥቀስ ለኢሳት መግለጻቸው ይታወሳል። አንድን ዜጋ በአገሩ በክልሉ ታጥሮ እንዲኖር ማስገደድ የዘር ማጥራት ወንጀል መሆኑን የገለጡት ዶ/ር ያእቆብ፣ ኢትዮጵያውያን መረጃዎችን በማሰባሰብ ተባብረው ጉዳዩን ወደ አለማቀፍ ፍርድ ቤት መውሰድ እንደሚኖርባቸው ገልጸው ነበር።

ኢሳት የነጋገራቸው የተለያዩ የሲቪክ ተቋማት እና የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች እንዲሁም ታዋቂ ጋዜጠኞች ድርጊቱን በመኮንን ኢትዮጵያውያን በቃ ሊሉት እንደሚገባ እየመከሩ ነው።

በአገር ውስጥ በመንቀሳቀስ ላይ ካሉት የሲቪክ ተቋማት መካከል የባለራእይ ወጣቶች ማህበር ሊቀመንበር የሆነው ወጣት ሀብታሙ አያሌው ፣ የብሄር ፖለቲካ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያን ሊበታትናት እንደሚችል ገልጾ፣ በኢትዮጵያዊነት መልክ ና ቅርጽ የተፈጠረውን ዜጋ መልሶ በመጎተት ወደ ጎሳ ቋጥኝ ማስገባት በልዩነት ላይ የተመሰረተ አስተዳደር ማራመድ መሆኑን ተናግሯል። ወጣት ሀብታሙ የብሄር ፖለቲካ አገሪቱን ይበታትናታል እየተባለ በምሁራን ሲሰጥ የነበረው የነበረው አስተያየት አሁን ፊት ለፊት እየመጣ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊነሳ ይገባዋል ብሎአል::

ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ እውቁ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ሲሆን ፣ ተመስገን አማርኛ ተናጋሪዎች ከተለያዩ ክልሎች እንዲወጡ መደረጋቸውን በማስታወስ፣ ” ካራቱሬን የመሳሰሉ ድርጅቶ በኢትዮጵያ ገብተው ሀብትና ንብረት እንዲያፈሩ ሲፈቀድላቸው የኢትዮጵያ ዜጎች ግን ይህን መብት ሊያገኙ አልቻሉም ብሎአል። እየመጣ ያለው አደጋ በአማርኛ ተናጋሪዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ዜጋ ላይ የሚደርስ መሆኑን የገለጸው ጋዜጠኛ ተመስገን፣ ተፈናቃዮች ሰዎች በመሆናቸው ብቻ ፣ “ነግ ለእኔ” ተብሎ ድርጊቱ ሊወገዝ ይገባል ሲል በአጽንኦት ተናግሯል።

ከጉራ ፈርዳ የተፈናቀሉ አማርኛ ተናጋሪዎች ከ1 ሺ ገጸች በላይ ያለው ማስረጃ ለአቶ መለስ ዜናዊ አቅርበው እንደነበር ያስታወሰው ጋዜጠኛ ተመስገን፣ አቶ መለስ ዜናዊ መልስ ሳይሰጧቸው በመሞታቸውን እሳቸውን የተኳቸው ባለስልጣናትም በእጅ አዙር ተመሳሳይ ፖሊሲ እየተገበሩ መሆኑን ገልጿል። ለሁሉም ድርጊት ህወሀት ተጠያቂ ነው የሚለው ጋዜጠኛ ተመስገን፣ የአማራውን ህዝብ እወክላለሁ የሚለው ብአዴንም ከተጠያቂነት እንደማያመልጥ ተናግሯል።

ቀደም ብሎ የተፈጠሩትም ሆነ አሁን እየተፈጠሩ ያሉት ህገወጥ ድርጊቶች በአፋጣኝ እልባት ካልተሰጣቸው አገሪቱ ወደ እርስ በርስ ግጭት መግባቱዋ አይቀርም በማለት ጋዜጠኛ ተመስገን ተናግሯል።

ጋዜጠኛ ዘሪሁን ተስፋየ በፌስ ቡክ ባሰፈረው ጽሁፍ ደግሞ ” ዛሬም ወያኔዎች ቀድሞ ሲያቀነቅኑለት የነበረውን ስሜት እያንጸባረቁ ነው። ትንሽነት አደገኛ ነው፤ በሽታው አጥንትን ሰርስሮ ይገባል። ይህንን ማከም ደግሞ የሁሉም ሕዝብ ድርሻ ቢኾንም፣ “ወያኔ ከሌለ እከሌ የሚባል ቡድን ያጠቃኛል” የሚል ስሜት ይዞ የሚያቀነቅነው እና ለወያኔ ርኩስ ፕሮጀክት ዋነኛ ተዋናይ የኾነው ሕዝብ ከፍተኛውን ሚና መጫወት ይኖርበታል። “እኔ ልሁን ደህና” በሚል ስሜት ዛሬ ነገሩን አቅልሎ ማየት ነገ የሚያስከፍለውን ዋጋ ያከብደዋል። ” ብሎአል።

ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽም በፌስ ቡክ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ ” የዛሬ አፈናቃዮች በብሔረሰብ ካባ ለመደበቅ ቢሞክሩም ሕግ ፊት የሚቀርቡበት ቀን እንደሚመጣ አምናለሁ። ተፈናቃዮዩቹ በሙሉ የአማራ ብሔር ተወላጆች ቢሆኑም አፈናቃዩ ወገን ግን የየትኛውም ብሔር ወኪል እንዳልሆነ እናስታውስ፤ አደራ። ግፈኞቹ፣ መዝባሪዎቹ፣ ወሮበሎቹ፣ ሆድ አደሮቹና ዘረኞቹ አፈናቃዮች ብሔራቸው “ነውር” ነው። ” ብሎአል።
 
ጋዜጠኛ ማስረሻ ማሞ በፌስ ቡክ በለቀቀው ጽሁፍ ” በቤንሻንጉል ጉምዝ የሚኖሩ ዜጎችም ኾኑ በአማራ ክልል የሚኖሩ ዜጎች ከኢትዮጵያ ምድር የፈለቁ ናቸው። ማንም በኢትዮጵያ ምድር ያለ ዜጋ ደግሞ በየትኛውም ስፍራ እየተንቀሳቀሰ ሥራ የመፈለግ እና ለተሻለ ሕይወት የተሻለ አማራጭ የመውሰድ መብቱ የሚገሰስ አይደለም።

 በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ የወረዳ አስተዳዳሪ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ግለሰቦችን “በሕገ ወጥ መንገድ ስለገቡ ወደመጡበት መመለስ” የሚችልበት ምንም ሕጋዊ መሠረት የለም። የአባራሪነት እና የተባራሪነት ፖለቲካው የመነጨው ከጭፍን ፖለቲካዊ አመለካከት በመኾኑ ይህ ውሳኔ በኢትዮጵያ ምድር ኢትዮጵያዊን ሕገወጥ እንዲባል አድርጎታል። እንግዲህ አንዳንዶች እንደሚሉት “አማራ” መኾን ዕዳ ነውን? ቤንሻንጉል መኾን በረከት ነውን? ትግሬ መኾን መታደል ነውን? የአንድ ብሔር ተወላጅ መኾን ከሰው ልጅ ሰብአዊ ፍጥረትነት ይልቃልን? የብሔር ፖለቲካ መርዝ ማለቂያ ወደሌለው አስቸጋሪ ፈተና ውስጥ የሚከተን ይህ ዓይነቱ አመለካከት በዜጎች መካከል እጅግ እየዳበረ በመጣ ቁጥር ነው። ይህ አይነቱ አስተሳሰብ ስር እየሰደደ እንዲመጣ ደግሞ መንግሥት ዋናውን ሚና ከተጫወተ አገር ተበላሸ ይባላል። ” በማለት ገልጿል።

ጃዋር ሙሀመድም እንዲሁ ” አሳዛኙ ነገር ገዢዎች በስልጣን ላይ የመቆያ ጊዜያቸውን ለማራዘም ቤተመንግስት ቁጭ ብለው የትኛውንም አይነት የማታለያ ዘዴ ሲጠቀሙ፣ ከአንድ ዶላር በታች በሆነ ገቢ ኑሮአቸውን የሚገፉ ጎስቋሎች ፣ ንጹህ አርሶ አደሮች ግን ወደ ጎን መገፋታቸው ነው። ዜጎች ኑሮ ውድነቱ የተነሳ ለመኖር በሚታትሩበት ወቅት ፣ ዜጎችን ከቤታቸው ማፈናቀል ፣ አገደኛ የሆነ ትምህርት ጥሎ የሚያልፍ፣ ጭቃኔ የተሞላበት ወንጀል በመሆኑ ፣ ሁላችንም የትኛውንም አይነት የፖለቲካ አስተሳሰብ ይኑረን ልናወግዘው ይገባል።” ብሎአል።

ከፖለቲካ ድርጅቶች ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ ” ዜጎች በፈለጉት የሀገሪቱ ምድሮች ያለምንምና ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመኖርና ንብረት የማፍራት የዜግነት መብታቸው ሆኖ እያለ፣ በተቀነባበረና በተሰላ ሁኔታ ዜጎችን ለዓመታት ሲኖሩበት ከነበሩበት ቀያቸው የሚናገሩት ቋንቋ ብቻ እንደመመዘኛ አድርጎ እንዲፈናቀሉ ማድረግ ከህግ ውጭ የሚደረግ ብቻ ሳይሆን በዘር ማጥፋት የሚያስጠይቅም ነው ” ብሎአል።

ውድ ተመልካቾቻችን በዚህ ጉዳይ ላይ የተለያዩ ኢትዮጵያውያንን በማናገር የተቀናበረውን ዝግጅት በትኩረት ፕሮግራም በሚቀጥሉት ቀናት የምናቀርብ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar