onsdag 20. november 2013

በሳውድ አረቢያ በኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰውን ጥቃት የሚቃወሙ ሰልፎች እንደቀጠሉ ነው

በሳውድ አረቢያ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የላቸውም በሚል የሳውዲ ፖሊሶች እና ወጣቶች በኢትዮጵያውያን ሴቶች፣ ህጻናትና ወንዶች ላይ የፈጸሙትን የሰብአዊ መብት ጥሰት በመቃወም በተለያዩ የውጭ አገራት የሚካሄዱት የተቃውሞ ሰልፎች እንደቀጠሉ ሲሆን ፣ በዛሬው እለት በስዊዘርላንድ በርን በተካሄደው ተቃውሞ ኢትዮጵያውያኑ ስሜታቸውን ለመቆጣጠር ተስኖአቸው ታይተዋል።
ኢትዮጵያውያኑ የሳውዲን መንግስትና የኢትዮጵያን መንግስት የሚያወግዙ መፈክሮችን እያሰሙ ወደ ሳውዲ ኢምባሲ ያቀኑ ሲሆን፣ ፖሊስ ከዘጋጀላቸው የመቃወሚያ ክልል በማለፍ በሳውዲ ኢምባሲ አቅራቢያ የተቃውሞ ድምጻቸውን አሰምተዋል
ከፍተኛ የጸጥታ ሰራተኞች በተመደቡበት የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ የተሳካ እንደነበር ወጣት አክቲቪስት ጴጥሮስ አሸናፊ  እንዲሁም ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን ድረስ 8 ሺ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን ማምጣቱን ገልጿል። የተጠቀሰውን አሀዝ ለማረጋገጥ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴውድሮስ አድሀኖም ብንደውልም፣ ስብሰባ ላይ መሆናቸውንና ፣ አብዛኛው መረጃ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ማግኘት እንደምንችል ገልጸውልናል።
ምንም እንኳ አሁንም ከ20 ሺ ያላነሱ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ለመመለስ እየተጠባበቁ ቢሆንም፣ የሳውዲው ንጉስ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን የውጭ አገር ዜጎች የማስወጣቱ ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሰጡት አዲስ ትእዛዝ በሌሎች የአገሪቱ ከተሞች በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ ሌላ አደጋ ይዞ ይመጣል ተብሎ ተሰግቷል።
ከውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባገኘነው መረጃ መሰረት በሳውዲ አረቢያ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ከ180 ሺ ያላነሱ ኢትዮጵያውያን ይገኛሉ።
የሳውዲ መንግስት ተገቢውን ይቅርታ እንዲጠይቅ፣ በዜጎች ላይ ላደረሰው በደል ካሳ እንዲከፍል እንዲሁም ወንጀለኞችን ለፍርድ እንዲያቀርብ የሚጠይቁ ሰላማዊ ሰልፎች በተከታታይ እንደሚደረጉ ለኢሳት የሚደርሱ መረጃዎች ያሳያሉ።
በዚህም መሰረት  ኖቬምበር 21  በጀርመን በርሊን ከተማ ሳውድ አረቢያ ኢምባሲ ፊት ለፊት ከጠዋቱ 9 ሰአት ጀምሮ የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚደረግ አዘጋጆች አስታውቀዋል።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar