tirsdag 5. november 2013

በአማራ ክልል ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች እና አመራሮች መካከል መተማመን እንደሌለ ጋዜጠኞች ተናገሩ


በአማራ ክልል ጋዜጠኞች እና በፖለቲካ ታማኝነት ተሹመው በሚያገለግሉ መሪዎች መካከል መተማመን የለም ሲሉ ጋዜጠኞች ለኢሳት ተናግረዋል፡፡ በጋዜጠኞች እና በአመራሩ መካከል ለተፈጠረው ልዩነት በርካታ ምክንያቶች ቀርበዋል። ጋዜጠኞቹ ለክልሉ ቴሌቪዥን ስርጭት ልዩ ምልክት ወይም ሎጎ ሁኖ እንዲያገለግል የተመረጠው የሰማእታት ሃውልት አርማ የአማራን ህዝብ የሚወክል አይደለም በማለት ተቃውሞ እያሰሙ ነው፡፡
በአመራሮች በኩል በሚታየው ከባድ የሙስና ወንጀል ደግሞ የግዥ  ክፍል ሃላፊ የሆኑት አቶ አሰፋ አቤልነህ ፤ ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ሰይድ እሸቴ እና ምክታላቸው አቶ መዝሙር ሐዋዝ ባ 2 ፎቅ ቤት በህንፃው አስገንቢ በሆነው ድርጅት እየተገነባላቸው መሆኑ በቅርቡ በተካሄደው የካቢኔ ግምገማ ይፋ ሆኗል ሲሉ ጋዜጠኞች ይናገራሉ።
ሰራኛው እና አመራሩን ሆድ እና ጀርባ ያደረገው ሌላው ምክንያት ጋዜጠኞች 1 ሺ 800 ብር ወርሀዊ ክፍያ ሲያገኙ ምክትል ስራ አስኪያጁ የ 10 ሺ ብር ወርሀዊ ደሞዝ ተከፋይ መሆኑ  ነው ፡፡
በቅርቡ ዋና ስራ አሰኪያጁ የሚዲያውን ነፃነት ለመቆጣጠር 42 የሹመት ቦታዎችን ይፋ ያደርጉ ሲሆን የራሳቸው እና ለፖለቲካው ተማኝ ናቸው ብለው የአሰቡዋቸውን ከፅሃፊ ጅምሮ በከፍተኛ የሚዲያ ቡድን መሪነት ቦታ ሹመዋቸዋል፡፡
ጋዜጠኞች በተደጋጋሚ ለክልሉ ቅሬታ ሰሚ ያስገቧቸው ደብዳቤዎች እንደሚያሳዩት በአመራሩ መመራረቸውን እና የመልካም አሰተዳደር ጥያቄ በማንሳት ላይ መሆናቸውን የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡
“በልተን ማደር አልቻልንም” የሚሉት ጋዜጠኞች ከብአዴን በቀጥታ ያለምንም የስራ ዘርፍ ሚዲያውን እንዲወክሉ በስራ-አስኪያጅ ላይ ሌላ ስራ አስኪያጅ ተሹመው የተቀመጡት አቶ ስዩም አድማሱ በጋዜጠኞች ላይ እየወሰዱት ያለው እርምጃ አሰነዋሪ እና አሰፀያፊ እየሆነ መጥቱዋል ሲል ያክላሉ፡፡
አንዳንድ ጋዜጠኞች ከአርበኞች ግንባር ጋር ግንኙነት አላችሁ ተብለው በጎጥ እየተለዩ እንደሚገለሉ እና እርምጃ እንደሚወሰድባቸውም ታውቁዋል፡፡
ሚዲያዎች ልማታዊ ጋዜጠኝነትን አንግበው የኢህአዴግን አስተሳሰብ እንዲያራምዱ የሚገደዱ ሲሆን በዘር እና በፖለቲካ አስተሳሰብ ላይ በተመረኮዘ መልኩ ሹመት ይሰጣል፡፡
የሕዝብን ጥቅምና ዕምነት አመዛዝነን ለመስራ ስንፈልግ በፍፁም አይፈቀድልንም የሚሉት ጋዜጠኞች የፓርቲ ጥቅም ከማስጠበቅ ውጭ ሌላ አሰተሳሰብ ማራመድ ፈጽሞ መከልከሉን ተናግረዋል፡፡
ከኢቲቪ ብቻ አስራ ሶስት ዘጋቢዎች ከስራቸው ታግደው የተባረሩ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ኤደን ገብረህይዎት ፤ ሰብለ ወረስ ፤ ክብካብ አስፋው ፤ካሰሁን ምትኩ እና ላምሮት ስዩም ይጠቀሳሉ፡፡ ከፋና ብሮድካስት ኮርፖሬት 29 ሰዎች ተገደው እረፍት እንዲወጡ ወይም ከስራ እንዲሰናበቱ ተደርጓል፡፡ ከአዲስ ዘመን እና ከኢትዩጵያን ሄራልድ 6 ዘጋቢዎች ከተቃዋሚዎች ጋር አብራችሁዋል ፤ ድርጅቱ የሰጣችሁን ተልኮ አልተወጣችሁም በሚል ከስራቸው ተሰናብተዋል፡፡
በታጋይ ታደሰ ሚዛን እና ወታደር አሸብር ከሰላም ሙሉጌታ እና ነብዩ ወንደወሰን የሚመራው የኢቲቪ ዘገባ ወደ ውጭ ሃገር ለዘገባ መሄድ ፈጽሞ  ውጭ መሄድ የተከለከለ መሆኑን  በመቃወማቸው ማሰጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ገልፀዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአማራ ክልል ብዙሃን መገናኛ ድርጅት በአምስተርዳም ኢሳት የሚጠቀምበትን የዜና መለያ መግቢያ እና የኤርትራ ቴሌቪዥን  የዜና ዘገባ መለያ ሙዚቃ/አይዲ/ በመውሰድ ጥቅም ላይ እያዋለው መሆኑ ታውቋል።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar