tirsdag 31. desember 2013

የውጭ ሃገር የስራ ስምሪት ኤጀንሲዎች መካከል ከ100 በላይ የሚሆኑት ሊከሰሱ ነው

የሳዑዲ መንግስት የመኖሪያና የስራ ፈቃድ የሌላቸውን ኢትዮጽያዊያን ማባረሩን ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ኤጀንሲዎች መካከል ከ100 በላይ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተሳትፈዋል የተባሉ ኤጀንሲዎች ላይ ክስ ለመመስረት መዘጋጀቱን ከአዲስ አበባ ከተማ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የተገኘ መረጃ ጠቆመ፡፡
በኢትዮጽያ በአጠቃላይ 470 የውጭ ሃገር የስራ ስምሪት ኤጀንሲዎች የሚገኙ ሲሆን 100 ያህሉ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ተሳትፈዋል በሚል ተጠርጥረዋል፡፡
ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ እጃቸው አለበት የተባሉት ኤጀንሲዎች ወደ ውጭ ሃገር ለስራ የሚልኳቸውን ዜጎች በህጉ መሰረት በነጻ ሊልኳቸው ሲገባ ክፍያ በመቀበል ፣ የስምሪት ፈቃድ ከተከለከለ በኋላ በድብቅ በመላክ እና ለስራ የላኳቸውን ዜጎች መረጃዎችን ሲጠየቁ ምላሽ ለመስጠት ያለመቻል ጥፋቶች ተገኝተውባቸዋል ተብሎአል፡፡
በግልም ሆነ በኤጀንሲዎች በኩል በቅጥር ወደየተለያዩ ሃገራት የሚደረገው ጉዞ በአሁኑ ወቅት መታገዱ የሚታወስ ሲሆን፥ ይህን ተከትሎም በህጋዊ መንገድም ጭምር ወደ የተለያዩ የአረብ ሃገራት ለስራ የሄዱ ዜጎች በቀጣሪዎቻቸው የሚደርስባቸውን እንግልት እና የአገልግሎት ክፍያ ክልከላ ለላኩዋቸው ኤጀንሲዎች ቢያሳውቁም ምላሽ ማጣታቸውን በተደጋጋሚ በማንሳት ቅሬታ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።
የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ብቻም ሳሆን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በቅርቡ ከሳዑዲ ተመላሾችን በማስመልከት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጣታቸውን ህገወጥ ወደአሉዋቸው ኤጀንሲዎች መቀሰራቸው መንግስት በተለያዩ የኣረብ አገራት ኢትዮጽዊን እየረደሰባቸው ያለውን ሰቆቃ ወደአንድ ወገን በመውሰድ ራሱን ከተጠያቂነት ለማንጻት መፈለጉን የሚያሳይ ነው በሚል ከወዲሁ ትችቶች እየቀረቡበት ነው፡፡
በፌዴራል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ብቻ ከ2001 እስከ 2005 ዓ.ም ድረስ በህጋዊ መንገድ ወደዓረብ አገራት 459 ሺህ 810 ኢትዮጵያዊያን መጉዋዛቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።
በሌላ ዜና ደግሞ በሪያድ ሳውድ አረቢያ የሚገኙና የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ስራ ለመቀጠር ባለመቻላችን ለከፍተኛ ችግር ተዳርገናል ይላሉ። የሳውዲ መንግስት ለኩባንያ ባለቤቶች በሚያስተላልፈው ትእዛዝ ኢትዮጵያውያኑ ካለፉት 3 ወራት ጀምሮ ስራ ለመቀጠር አለመቻላቸውንና ቤተሰቦቻቸውም የምግብ፣ የቤት ኪራይና ሌሎች ወጭዎችን ለመሸፈን እንደተሳናቸው ገልጸዋል። በሳውድ አረቢያ ለመኖር ህጋዊ የስራ ፈቃድ የላችሁም በሚል ከ150 ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው መመለሳቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በአገሪቱ የቀሩት ዜጎች ” የኢትዮጵያ መንግስት” አንድ መፍትሄ ይፈልግልን ሲሉ ተማጽነዋል።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar