ኢህአዴግ በሚመራው በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደ ውይይት ሲቪል ሰርቪስ መስሪያ ቤት ለተገልጋዩ ህብረተሰብ, ለህዝብ ተቋማት እና የመንግስት ቢሮዎች የአሰራር ስርዓቱ ውጤታማና ቀልጣፋ እንዲሆኑ ከማገዝ ይልቅ በፖለቲካ አሰተሳሰብ እና የፓርቲ ስራዎችን በመስራት የተጠመደ በመሆኑ በርካታ የሲቪል ሰርቪስ ስራዎች ሳይሰሩ እንደሚቀሩ ተመልክቷል.
ተገልጋዮች በአግልግሎት እጦት እየተማረሩ እና እየተሰቃዩ መሆናቸውን እየገለጹ መሆኑን በተደጋጋሚ ከገለጹ በሁዋላ ነው, የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም እና የሴክተር መስሪያ ቤቶች ለምርጫ 2007 ያላቸው ዝግጁነት በሚል ርዕስ ውይይት የተደረገው.
ተወያዮቹ, የሲቪል ሰርቪስ አደራጃጀት አብዛኛውን የመንግስት ሰራተኞች የኢህአዴግ ቲፎዞ እንዴት ማድረግ ይቻላል? በሚለው ጉዳይ ላይ በስፋት መክረዋል.
በመንግስት ሰራተኛው ዘንድ ከፍተኛ የምክክር መድረክ በመፍጠር እና በአሁኑ ስዓት በከፍተኛ ሁኔታ ጥያቄ እየሆነ የመጣውን የኑሮ ውድነት ጥያቄ ለመመለስ ደሞዝ መጨመር እንደሚያስፈልግ በውይይቱ የተነሳ ሲሆን, ይህን ከምርጫ 2007 ጋር በማያያዝ ተግባራዊ ማድረግ ኢህአዴግን አሸናፊ ያደርገዋል ተብሎአል.
ትግራይ; አማራ; ደቡብ እና ኦሮምያ ሲቪል ሰርቪስ ቢሮዎች በተሰጣቸው መመሪያ መሰረት ደሞዝ ማሻሻያ ሰርተው ያጠናቀቁ ሲሆን, ኢህአዴግን የምርጫ ስትራቴጂ ተከትሎ ተግባራዊ ለማድረግ መመሪያ እየጠበቁ እንደሆነ በበሮዎች ተወካዩች በኩል ገልፀዋል.
የአንድ ለአምስት ስትራቴጅ በመንግስት ሰራተኛው ዘንድ ተቀባይነት ማጣቱ ለሲቪል ሰርቪሱ ፈተና እንደሆነበት የተገለጸ ሲሆን; በቀጣይ ለፖለቲካው እንቅፋት ሊፈጥር እንደሚችል ታስቦ; በአንድ ለ አምስት ተሳትፎ ያላደረገ እና በሚሰጡት ዙሪያ ውይይት የማያደርግ ስው የዲሲፒሊን እና የደሞዝ ቅጣት እንዲወሰድበት የሚል ሃሳብ ተነስቷል.
የደሞዝ ክፍያ ጭማሪ ነጋዴው በማያውቀው መልኩ ካልተከናወነ እሳት ላይ ቤንዚን እንዳይፈጥር እና በዋጋ ንረት ሃገሪቱ እንዳትመታ እና የታለመው የምርጫ ስኬታማነት አደጋ ውስጥ እንዳይገባ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ተብሎአል.
ኢህአዴግ የሚመራው የሚቀጥለው ውይይት "የኢህአዴግ ጽ / ቤት በትምህርት, በንግድ እና ትራንስፖርት ዘርፍ የሴክተር መስሪያ ቤቶች ለምርጫ 2007 ያላቸው ዝግጁነት" በሚል እንደሚካሄድ ከኢህአዴግ ምንጮች ያገኘነው መረጃ ያስረዳል.
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar