በዋሺንግተን ዲሲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ለተወሰኑ ጊዜያት በተቃዋሚዎች ቁጥጥር ስር ውሎ ነበር። በዚህ ወቅት ሰለሞን የተባለ የኢምባሲው ባልደረባ በሰልፈኞች ላይ ተኩስ ፈጽሟል። ግለሰቡ ‘የኢምባሲው ጠባቂ ነው’ ከሚል ዜና ውጪ በርግጥ የግቢው ሴኩሪቲ ለመሆኑ ተጣርቶ የታወቀ ነገር የለም። ምናልባት ይህ ግለሰብ የግቢው ዘብ መሆኑን ብንቀበል እንኳን፤ ተኩሱን የከፈተው “ራስን ለመከላከል ወይስ ሰውን ለመግደል?” የሚለውን ጉዳይ በቅርብ ተከታትሎ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ነው። እስካሁን በደረሰን መረጃ መሰረት ተኩሱን በሰልፈኞች ላይ ከፍቶ የነበረው ግለሰብ ለጊዜው በፖሊስ ታስሮ መፈታቱን እዚህ ላይ ጠቅሰን እናልፋለን።
በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ተቃውሟቸውን የሚያሰሙት ኢትዮጵያውያን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ድምጻቸውን እያሰሙ ነበር። አሁንም እንደገና ወደ ተኩሱ ጉዳይ እንመለስ። በቪዲዮው ላይ በግለጽ እንደሚታየው ሁለት ግዜ በሰልፈኞቹ ላይ ተተኩሷል። ሶስተኝውን የተኩስ ሙከራ ግን ልብ ብለው ይመልከቱ። ሰላማዊ ሰልፈኛው ላይ በቅርብ ርቀት ለመተኮስ ሲሞክር፤ ጥይቱ ከሽፎበታል። ይህ ጥይት ባይከሽፍ ኖሮ በርግጥም የሰው ህይወት ሊጠፋ እንደሚችል መገመት ይቻላል። ግለሰቡ ወደ ውስጥ የገባውም ሽጉጡ መተኮስ ስላቆመ እንጂ፤ በተለይም የመጨረሻዋ ጥይት ስለከሸፈችበት ነው የሚመስለው። በመጨረሻ በዋሺንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ግርማ ብሩ ወደ ውጭ በመውጣት የተኮሰው ግለሰብ ወደ ውስጥ እንዲገባ ሲያደርጉት ታይቷል።
በዚህ ተኩስ ምክንያት የጠፋ ህይወት ባይኖርም፤ የአንዲት ሴት መኪና የፊት መስታወት ተሰባብሯል። በዚህ ምክንያት ተኩሱን የፈጸመው ግለሰብ የሚጠየቅበት ጥፋት ይጨምራል። አሁንም ቢሆን በዋሺንግተን ዲሲ የሚገኙ አክቲቪስቶች ጉዳዩን ችላ ማለት አይገባቸውም። ኢምባሲው ክስ ሊመሰርት ይችላል የሚለውን ታሳቢ በማድረግ፤ ሳይቀደሙ መቅደም ብልህነት ነው። በመሆኑም በመጀመሪያ ደረጃ ተኩሱን የፈጸመውን ግለሰብ ማንነት አጣርቶ ማወቅ ይጠበቅባቸዋል። በኢምባሲው እና በግለሰቡ ላይ ክስ መመስረትም ሌላኛው አማራጭ ነው። በክሱ ወቅት በርግጥ ተኩስ የከፈተው ግለሰብ የስራ ቅጥር እና ድርሻው ወይም የወር ደሞዝተኛነቱ ሽጉጥ ታጥቆ ኢምባሲውን መጠበቅ መሆን እና አለመሆኑን አጣርቶ ማወቅ ያስፈልጋል። ከሁለቱ ተኩሶች በተጨማሪ የከሸፈችው ሶስተኛ ጥይት፤ ከቅርብ ርቀት ላይ ስለተተኮሰ የሰው ህይወት ሊቀጥፍ ይችል እንደነበር ታሳቢ ማድረግ አስፈላጊ ነው።
ከላይ የገለጽነው ጉዳይ እንዳለ ሆኖ፤ ሰላማዊ ሰልፈኞቹ ወደ ኢምባሲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ገብተው ባለኮከቡን ባንዲራ አውርደው የኢትዮጵያን ባንዲራ መስቀላቸው የሚያኮራ ነው። ከምንም በላይ ግን ሃይል ሳይጠቀሙ በጨዋነት ሃሳብ እና ብሶታቸውን ማሰማታቸው ይበልጥ ደስ ያሰኛል። እንዲህ በሰላማዊ መንገድ በወጡ ሰልፈኞች ላይ በእብሪት ተኩስ መክፈት ግን በርግጥም ትክክል አይመስልም። በርግጥ ሰልፈኞቹ ‘ህገ ወጥ ናቸው’ ከተባለ ወይም ወደ ኢምባሲው ቅጥር ግቢ መግባታቸው ‘ትክክል አልነበረም’ ቢባል እንኳን፤ ጉዳዩን ለከተማው ፖሊስ ማሳወቅ እንጂ ተኩስ መክፈቱ ‘የመግደል ሙከራ ማድረግ’ በሚል የወንጀል አንቀጽ ስር ነው የሚወድቀው።
ወደፊት ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያያዥ ዜናዎች ካሉ፤ ይዘንላችሁ የምንቀርብ መሆኑን በማሳወቅ የዛሬውን አጭር ትንታኔ እዚህ ላይ እናበቃለን።
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar