የመብት፣ የዲሞክራሲ ፣ የሕግ የበለይነት፣ የነጻነትና የፍትህ ጥያቄ የጥቂት «ፖለቲከኞች» ወይም የፖለቲክ ፓርቲ መሪዎች ብቻ ጥያቄ አይደለም። የሚሊዮኖችም እንጂ።
መብታችንን አስረግጠን፣ ልእልናችንን አስደፍረን፣ በአገራችን እንደ ባሪያ የምንኖር ጥቂቶች አይደለንም። «የምትናገሩትን እኛ ነን የምንነግራችሁ። የሚጠቅማችሁን እኛ ነን የምናውቅላችሁ።በዚህ ሂዱ ስንላችሁ ትሄዳላችሁ፣ በዚህ ዉጡ ስንላችሁ ትወጣለች..» እያሉን፣ የግፍ ቀንበር በላያችን ላይ ጭነው፣ እኛ የኑሮ ዉድነት እያቃጠለን፣ እነርሱ ሚሊየነሮች ሲሆኑ ፣ እኛ ከመንደራችን ተፈናቅለን እነሱ በመንደራችን ቢዝነሳቸውን ሲገነቡ አይተን ዝም ብለን፣ በፍርሃት ካባ ተተብትበን ፣ ለአመታት ታስረን የተቀመጥን ጥቂቶች አይደለንም።
በ2006 ዓ.ም ግን፣ ምናልባትም የኢትዮጵያን ትንሳዔ መቃረብ የሚያመላክቱ አንዳንድ ክስተቶችን ለማየት ችለናል። ከነዚህም አንዱ የካቲት 16 ቀን 2006 ዓ.ም የሆነው ነው።
በባህር ዳር ከተማ ነው። አንድነት እና መኢአድ በጋራ በጠሩት ሰልፍ ፣ በከተማዋ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ ሕዝባዊ ማእበል ታየ። ከ250 ሺህ ነዋሪ ህዝብ አንድ ሶስተኛው፣ ወደ 80 ሺህ የሚጠጋው፣ ድምጹን ለማሰማት ወጣ። የፍህርትን ቀንበር ሰብሮ፣ «እምቢ ለአምባገነንነት፣ እምቢ ለጭቆና ፣ እምቢ ለዘረኝነት» እያለ ጮኸ።
ከሰልፈኞቹ መካከል፣ ከኋላ ወይንም ከዳር ሳይሆን ከፊት፣ በጀርባዋ ሕጻን ያዘለች አንዲት ሴት ትታያለች። ድምጿን ለማሰማት የማትፈራ ! ከአሁን ለአሁን ምን እባላለሁ ብላ ያልተሸማቀቀች ! «ሰው ያለነጻነቱ ምንድን ነው ?» እንደተባለው ለነጻነቷ የቆመች !! የዚች ሴት ፎቶ፣ በአለም ዙሪያ ሁሉ ተሰራጨ። ዳርና ጥግ ይዘን የተቀመጥን ብዙዎች ራሳችንን እንድንጠይቅ አደረገን። ሕሊናችንን ቆረቆረን። የአገር ጉዳይ የጥቂቶች ሳይሆን የእያንዳንዱ ኢትዮጵያ ጉዳይ እንደሆነ ይች ሴት አስተማረችን።
በአገራችን ታሪክ ሴቶች ትልቅ ሚና ሲጫወቱ በታሪክ አንብበናል። በዘመናችንም ተመልክተናል። እቴጌ ጣይቱ ፣ ጦር ሜዳ ድረስ በአዝማችነት በመዝመት ጀግንነት ምን ማለት እንደሆነ ያሳዩ የኢትዮጵያ እናት ናቸው። የዘመኑ ጣይቱዎችም ፣ እነ ርዮት አለሙ፣ ኤዶም ካሳዬ ፣ ማህሌት ፋንታሁን ለነጻነትና ለዲሞክራሲ ዋጋ እየከፈሉ ነው። የባህር ዳሯም ሴት፣ በራሷ መንገድ የጣይቱን ወኔ አሳይታናለች።
በአገራችን የሴቶች ተሳትፎ ምን ያህል ቁልፍ እንደሆነ ለማሳየት፣ ለለዉጥ የሚደረገዉም ትግል የጥቂቶች ሳይሆን የእያንዳንዱ ዜጋ መሆኑን ለማጉላት፣ እንዲሁም ዜጎች በእቴጌ ጣይቱ መንፈስ፣ እንደ ባህር ዳሯ ሴት፣ ለነጻነታቸውና ለመብታቸው ደፍረው መቆም እንዲጀምሩ ለማበረታታ፣ የልጅ እናት የሆነችዋን የባህር ዳሯን ሴት፣ የአመቱ ሰው አድርገን ስንመርጥ በታላቅ አክብሮት ነው።
2007 የለዉጥ አመት ይሁንልን !
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar