torsdag 13. november 2014
ታሪክ እንደስኳርና ጨው በኪሎ
የአጼ ቴዎድሮስ፤ የአጼ ሚኒሊክ፤ የአጼ ዮሐንስ ደብዳቤዎችን ጨምሮ ሁለት ሺህ ኪሎ የሚመዝኑ ታሪካዊ ፋይዳቸው ከፍተኛ የሆኑ መጽሃፍትና ጋዜጦች ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መጽሃፍት በኪሎ 20 ብር ተቸበቸቡ።
በሃገር ውስጥ እንዲኖሩ የማድረግ ፍላጎት ያላቸው–በተቻለ ለኢትጵያዊያን ብቻ መጽሃፍ የሚሸጡ ነጋዴዎች በሽያጩ እንዳይሳተፉ ሲታገዱ፤ ከውጭ ሃገር ገዢዎች ጋር ግንኙነት ያላቸውና ጥቅሙን የሚያውቁ አትራፊዎች ግን በሚስጥር ተጋብዘው በርካሹ ገዙት።
የዮብ ሉዶልፍ፤ ጀምስ ብሩስ፤ ሮሲኒ፤ ሂስትሪ ኦፍ አቢሲኒያ፤ የፋሽስት ወረራ ጊዜ በወራሪው ሃይል ይታተሙ የነበሩ ጋዜጦች እንዳሉ፤ የቄሳር መንግሥትና የሮማ ብርሃን የተባሉት ጋዜጦች እና ሌሎችም የማይገኙና አሁን ቢገኙ ደግሞ ዋጋቸው በእጅጉ የናረ የሆኑ ውድ የሃገር ሃብት ጊዜ ያለፈባቸው፤ ጥቅም የሌላቸው፤ ያረጁ፤ ቦታ ያጣበቡ፤ በሚሉና በሌሎችም ሰበብ እንደ ስኳር መጥቅለያ ተራ ወረቀት በኪሎ ተቸበቸቡ።
ሚስጥራዊ ግን ንግዳዊ መሳይ የኢትዮጵያ ታሪክ ለተተኪው ትውልድ ሊተላለፍ የሚቻልበትን መንገድና ማስረጃ ሁሉ ድምጥማጡን ማጥፋት ቀደም ብሎ የታቀደ መሆኑ ሲሰማ ነበር። አሁንማ ሚስጥርነቱም ሳያስፈልግ፤ ምን ይሉናልም ገደል ገብቶ፤ “ላይጠቅሙ ቦታ ይዘው አዳዲስ መጻሕፍት ቦታ አጡ” (አዳዲስ የሚባሉትም ከ1983 ወዲህ በገዢዎቻችን አባላትና ስለጀግንነታቸው፤ ኢትዮጵያ ትላንት የተፈጠረች ሃገር የሚሉ አይነቶቹ ናቸው) በሚል አጉል ሰበብ እየተመረጡና የኢትዮጵያን ምንነት፤ ማንነት፤ ቀደምት ኢትዮጵያዊያን የፈጸሙት መልካም ምግባርና የኢትዮጵያዊነታቸው መገለጫ የሰፈረበት በውጭ ሰዎች የተጻፉት ዘመን ያስቆጠሩት የታሪክ መዛግብት በኪሎ ከስኳርና ጨው ባነሰ ዋጋ መሸጡ ያሳዝናል።
እነዚህ ጥንታዊ፣ ጥናታዊ፣ አብዛኛው በአይን ምስክር ላይ ተመስርተውና ምርምር ተካሂዶባቸው ጉልበት ጊዜ መዋዕለ ንዋይ ፈሶባቸው በምሁራን የተጻፉ፤ ሃገራችንን ጎብኝተው፤ ከማሕበረሰቡ ጋር ተግባብተውና ባሕልና ልምዱን ቀስመው፤ ልምዱን ተላምደው ለታሪክና ለትውልድም እንዲተላለፍ በማለት በዚያ መጓጓዣ እንደአሁኑ አልጋ ባልጋ ባልሆነበት ዘመን፤ ሽያጭ ያዋጣል አያዋጣም የሚለው ጥያቄ ባልታወቀበትና፤ ተጉዘው ያዩትንና የተረዱትን ላላዩትና እድሉ ላልገጠማቸው ሁሉ እንዲሆን ብለው ጽፈው ለሕትመት ያበቋቸው የሃገራችን ታሪካዊ ሰነዶች በኛው በዜጎቻችንን እንዲጠፉና እንዳይነበቡ ከቤተመዘክራችን ወጥተው አንዱን በ16ኛው ክፍል ዘመን የተጻፈውን መጽሐፍ ከአንድ ኪሎ ሽንኩርት ባነሰ ዋጋ በኛ ዘመን መሸጡ ያሳፍራል፤ ያናድዳል፤ ያሰቆጫል።
ሻጩ ብሔራዊ ቤተመዘክር የሀገራችን የታሪክና ሌሎችም መጻሕፍት፤ በኢትዮጵያዊያንም ሆነ በውጭ ደራሲያንና የታሪክ ተመራማሪዎች ያሳተሟቸው በነጻ የተገኙ፤ ዋጋ ተከፍሎባቸው የተሰባሰቡት፤ ተቀምጠው ለሕዝብ ንባብ የሚበቁበት፤ ለምርምር የሚውሉበት፤ ለማስረጃነት የሚጠቀሱበት ባለአደራ ተቋም እንዲሆን ነበር የተቋቋመው። አሁን ባህሪውን ለውጦ አደራ በላነቱን በግላጭ “ባለቤት ያላት በግ ላቷን ውጭ ታሳድራለች” እንዲሉ፤ በዚያ ቤተመዘክርም የተሰየሙት ሃላፊዎች ማን አለብን ባዮችና ማን ነክቷችሀ ተብየዎች በመሆናቸው የጥንቷን ኢትዮጵያ ታሪክ የሚያስተምረንን መጸሐፍ ሁሉ “ድምጥማጡን አጥፉ፤የዚች ሃገር ታሪክ “ሀ” ተብሎ የሚመዘገበው እኛ መግዛት ከጀመርንበት አንስቶ፤ የሚጻፈው ታሪክ ሁሉ እኛን መሰረት ያደረገ መሆን ስላለበት ከዚያ ውጭ ያለው ሁሉ ወደ ቤተመዘክር ጨርሶ እንዳይደርስ” በሚል መመርያ የተሰጠበት በመመስል መልኩ የታሪክ ቅርስ ሽያጩ ተካሄደ።
ሽያጩን የፈቀዱት የወመዘክር ሃላፊ መጪው ምርጫ ሰዉን ሁሉ ጠራርጎ በቀን አበል ሥልጠና ሲያስገባ እሳቸውም ሥልጠና ላይ በመሆናቸው፤ ቀደም ተብሎ ሲወራ የነበረው ሽያጭ በመዘግየቱ ኢትዮጵያዊነት የሚሰማቸውና መጽሃፍቱ በምንም መልኩ ከሃገር መውጣት የለበትም፤ መሸጡም አግባብ አይደለም የሚሉ ነጋዴዎች ሽያጩን አስቀድመው ሰምተው ለመሳተፍ ቢጠይቁም እንዳይሳተፉ ተደረጉ።
የሃላፊው ሥልጠና ላይ መግባት ሽያጩን ሲያዘገየውም ሽያጩ ተሰርዟል ተብሎ ቢታሰብም፤ ባለሥልጣኑ ወዲያው ሰልጥነው የወጡ የዕለቱ ዕለት ቅድሚያ ሰጥተው “ይሸጥ” ብለው በፊርማቸው አዘዙ። ከጠዋቱ በሁለት ሰአት ከ45 ደቂቃ ላይ ከመፈረማቸው በቅጽበት የተዘጋጁት መጫኛዎች ተከታትለው ወደ ወመዘክር ግቢ ገብተው፤ ከፍለው፤ ቅርሳችንን ጭነው ጭልጥ አሉ። ነገሩ አስቀድሞ በእቅድ ተደራጅቶ ያለቀ ሆኖ ነው እንጂ እንዴት ተብሎ እንዲህ ተፋጠነ ይባላል?!
በቃ ንብረትነቱ የገዢዎቹ ሆነና ወዲያው ወሬውን የሰሙ ከገዙት ላይ ለውጭ ሰዎች ከማለፉ በፊት ብለው ተሯሩጠው እጥፍ ከፍለው ለመግዛት ቢሞክሩ ዋጋው የትየለሌ ሆነና በመግዛት ፈንታ ቅስማቸው ተሰብሮ በሃዘን ወደየመጡበት ተመለሱ።
በጣም የሚያሳዝነው በረከት የጻፈው “የሁለት… ወግ” በሃሰትና በትርኪ ምርኪ የተሞላው የክብር ቦታ ተሰጥቶት መጪው ትውልድ የውሸት ታሪክ እንዲማርበት ሲደረግ በታሪክ ላይ ተመስርተው ለመዘገቡትና የኢትዮጵያን ምንነት ማንነት፤እምቢኝ አንገዛም ለጠላት አንንበረከክም፤ ሃገራችንን አሳልፈን ከመስጠት ለሃገራችን ሉአላዊነት፤ ለዳር ድንበሯ መከበር እራሳችንን እናሳልፋለን ስላሉት ቆራጦች የተጻፈው የማንነት ማረጋገጫ የማይረባ ያረጀ ተብሎ በኪሎ መሸጡ የደረስንበትን የታሪክ ዝቅጠት ያሳያል።
መጻሕፍቶቹ ቦታ አጣበቡ ከተባለ ለምን ቤተመጻሕፍታቸው ባዶውን ለሆነውና የመጽሐፍ ያለህ ብለው ለሚጮሁት የየክልሉ መንግሥታዊና የግል ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች በችሮታ አይሆንም ከተባለም ለነጋዴ በተሸጠበት ዋጋ አልተሰጠም?
እነዚህ የሃገርን ታሪክ፤ የሕዝብን ማንነት የሚዘክሩ የታሪክ ቅርሶች እንዲሸጡና ከኢትዮጵያዊያን እንዲርቁ መደረጉ ተተኪው ትውልድ ስለሃገሩ እንዳያውቅና ማንነቱን ጨርሶ እንዲዘነጋ ሆን ተብሎ የሚደረግ ደባ ነው።
“ጥቅም የላቸውም፤ አርጅተዋል፤ቦታ አጣበቡ፤ ከደራሲያን ማሕበርና ከዩኒቨርሲቲ ምሑራን አይተው እንዲሸጡ የወሰኑት ነው፤ ኮሚቴ ተቋቁሞ ረጂም ጥናትና ምርምር አድረጎበት የወሰነው ነው” ተብሎ ለሽያጭ፤ ያውም በኪሎቱ 20 ብር ከተቸበቸቡት የታሪክ ምስክሮቻችን በጥቂቱ እነሆ:
1 A NEW HISTORY OF ETHIOPIA JOB LUDOLF 1682
2 HISTORE DE ETHIOPIA GREEN LOPO 1728
3 JOURNAL OF A VISIT TO SOME PARTS OF ETHIOPIA GEORGE WADDING ESA 1822
4 LIFE IN ABYSSINIA MANSFIELD PARKYNS 1856
5 HISTRE EN ABYSSINIA D’ABADDI 1867
6 NARRATIVE OF THE BIRITISH MISSINO TO THEODROS KING OF ABYSINIA HARMUZD RASSAM 1869
7 CARDINAL MASSAIA 35 ANNI DI MISSIONE IN ALTA ETHIOPIA 1885
8 LE NEGUS MENELIK J.G VANDER HEXNI 1899
9 FIRST FOOT STEPS IN EAST AFRICA –EXPLORATION OF HARRAR CAPT, SIR RICHARD T BURTON 1925
10 VAT CHRONIQUE GEBRESELASI 1930
ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ በያለበት ይህን ድርጊት ሊያወግዘውና የብሔራዊ ቤተመዘክር ወመጻሕፍትን ሃላፊ የመጽሃፉን ሽያጭ የፈቀዱትን ባለፊርማ ለሕግ ማቅረብ ቀዳሚ ተግባሩ ሊያደርገው ይገባል።
ከዘመነ ትዝብቱ
Abonner på:
Legg inn kommentarer (Atom)
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar