ሰዉ ልጆች በርሃብ እንዲሞቱ በድፍረት የፈረደዉ ብአዴን:- የጉራፋርዳ አማራ ተፈናቃይ ነገር
————-
የባርነት ሀሳብ ተሸካሚዉ ብአዴን ነጻነት እና እኩልነት የሚባሉ ነገሮች መኖራቸዉን ያዉቅ ይሆን?:- እዉን ገዱስ የሰዉ ቁመት አለዉ?
——-
ሸንቁጥ አየለ
=======
የግል ገጠመኜ እንደ መነሻ:-
————
-ገዱ ሰሞኑን ጎንደር ላይ ለተገኘዉ አቢይ “ጠቅላይ ሚኒስቴር ካሁን ብኋላ ለህዝቦች ነጻነት ፍትሃዊነት: እና እኩልነት እንዲሰሩ አሳስባለዉ” ብሎ የተናገረዉን ንግግር እደመጥሁ ገዱ ድራማ እየሰራ ነዉ እዉን ገዱ እና ብ አዴኖች የነጻነት ቁመት አላቸዉ የሚል ጥያቄ በህሊናዬ ቢነሳ የነዚህን ሰዎች ሁኔታ የሚዳሥሱ ማህደሮችን ማሰስ ጀመርኩ::
– ከጥቂት አመታት በፊት ወደ አስር የሚጠጉ ትልልቅ እና አለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በጋራ የሚተገብሩት እና ከሚሊዮን በላይ ሰዎችን በመላ ሀገሪቱ የሚረዳ አንድ የሰበአዊ ርዳታ ፕሮግራም ቅድመ ማስተንቀቂያን ዘርፍ አስተባብር ነበር::በተለይም ይሄ ፕሮግራም የራሱ የዳታቤዝ እና ፈጣን የመረጃ ልዉዉጥ ከመላ ሀገሪቱ እንዲኖረዉ ማድረግ ችለንም ነበር::ዳታቤዙንም አስተባብር ስለነበረ ከመላ ሀገሪቱ ካሉ ወረዳዎች የርሃብ: እና የልዩ ልዩ የአደጋ መረጃዎች በሰዓታት ዉስጥ ይደርሱን ነበር:: እርዳታዉ የሚገኘዉ ደግሞ ከአሜሪካ መንግስት ስለነበረ የአሜሪካ መንግስት ምንም ያህል ሚሊዮን ቁጥር ያለዉ ተረጅ ምግብ ይፈልጋል ብለን መረጃ አቀናብረን ካቀረብን ያለምንም ማወላወል በቂ ምግብ ያቀርብ ነበር::ፈረንጅ አለቆቻችን በጣም የሚገርም ባህሪያቸዉ መረጃ ካቀረብንላቸዉ በፍጥነት ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ከሚገኘዉ የአሜሪካ እርዳታ ጽፈት ቤት ጋር መረጃ በመለዋወጥ በቂ ምግብ ዝግጁ እንዲሆን ይሰሩ ነበር::
-በዚህ አጋጣሚ ዉስጥ የትግራይ እና የኦሮሚያ የወረዳ እና የክልል አመራሮች ለተራቡ ሰዎች የተሻለ የእርዳታ ምላሽ ለመስጠት ሲተጉ አስተዉል ነበር::በተለይም የትግራይ የወረዳ አስተዳዳሪዎች ክልል ላይ ያሉ ሀላፊዎች የተዛባ ዉሳኔ ወስነዉ በወረዳ ያለዉ ርሃብተኛ እህል የማይደርሰዉ ከሆነ አጥብቀዉ ሲከራከሩ ወደ ኋላ አይሉም ነበር::የኦሮሚያ የወረዳ አስተዳዳሪዎች ከሞላ ጎደል ቢያንስ የርሃብተኛ ቁጥር ላለመደበቅ ሙከራ ያደርጉ ነበር::
-በተለይም በአመታዊ የምግብ ዋስትና ጥናት ወቅት (የተባበሩት መንግስታት የሚሳተፍበት እና የሚመራዉም) የኦሮሚያ የወረዳ ባለስልጣናት የሚያሳዩት ትጋት መልካም ነበር::ኦሮሚያ ላይ በክልል ደረጃ የጦፈ ክርክር ሲደረግ እና የምግብ ዋስትና ጥናቱ እንዲጸድቅ ሙሉ ድጋፍ ለማድረግ የክልልሉ መንግስት ሲታገል አማራ ክልል ግን ትርክቱ ሌላ ነበር:: ሰዎች በርሃብ ማለቃቸዉን እንደ ጀብዱ የሚቆጥሩት የብ አዴን አመራሮች የተራበ ካለ ከብቱን እና የቤት ንብረቱን ሸጦ ይብላ ካልተሳካለትም ይሰደድ ሲሉ ይመልሱ ነበር::
የባርነት ሀሳብ ተሸካሚዉ ብአዴንን ማሳያ ነጥቦች
—————–
አመታዊ የምግብ ዋስትና ጥናት ሲደረግ የብአዴን ባለስልጣናት ከወረዳ እስከ ክልል አንድ አይነት ቋንቋ እና ክፋት ያራምዳሉ::ይሄዉም ለምሳሌ የተቋማት የጋራ የምግብ ዋስትና ጥናት 2ሚሊዮን ህዝብ በአማራ ክልል ርሃብተኛ አለ ብሎ ሪፖርት ቢያደርግ “የለም ይሄ ጥገኝነትን ለማስፋፋት ነዉ::በክልላችን ከ200 ሽህ በላይ ርሃብተኛ የለም::ካለም ቻይናም የሚያልቀዉ አልቆ ነዉ ወደ እድገት ጎዳና የገባዉ” በማለት ይከራከሩና ጥናቱን ዉድቅ ያደርጉታል::
– አሁንም የተቋማት የጋራ የምግብ ዋስትና ጥናት 1 ሚሊዮን ህዝብ በአማራ ክልል ርሃብተኛ አለ ብሎ ካቀረበም ” የለም በክልላችን ያለዉ ርሃብተኛ መቶ ሽህ ብቻ ነዉ” ሲሉ ጥናቱን ዉድቅ ያደርጉታል:: አንዳንድ እልህኛ እና እዉነተኛ ባለሞያዎች አሉ::በተለይም የተወሰነ ነጻነት ያላቸዉ እና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች ወይም መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የሚወከሉ ባለሞያዎች ወጥረዉ ይከራከራሉ::
-ከክልል ባለስልጣናት እስከ ዞን ባለስልጣናት ብሎም እስከ ወረዳ ባለስልጣናት አንድ የሚመልሱት መልስ “ከራበዉ ከብቱን ሸጦ ይብላ::ጥሪት ሀብቱን ሸጦ ይብላ::ካልቻለም ይሰደድ::ካስፈለገም ይሙት::ይሄ እናንተ የምታጠኑት ጥናት ግን ጥገኝነት እና ስንፍና የሚያስፋፋ የተረጅነት መንፈስ የሚያበረታታ ስለሆነ አንቀበለዉም” ብለዉ ቁጭ ይላሉ:: በመላዉ ሀገር ህዝብ ችግር ላይ ሲወድቅ መንግስት ህዝብን በመደጎም ህይወቱን እንደሚያተርፍ ግን ጠፍቷቸዉ አይደለም::ሌላዉ ቀርቶ አሜሪካ ዉስጥ ዜጎች ሲቸገሩ በመንግስታቸዉ ተደጉመዉ የገጠማቸዉን ክፉ ቀን እንደሚያልፉት ብአዴኖች ያዉቃሉ::ሆኖም የባርነት መንፈስ ዉስጥ ናቸዉ እና የሚያልቀዉ አልቆ..ሲሉ ሳይዘገንናቸዉ መልስ ይሰጣሉ::
– ይሄን አይነት መልስ በተለይም በጎንደር እና በወሎ ልዩ ልዩ ወረዳዎች ሰዎች በርሃብ እዬሞቱ የወረዳ ባለስልጣናት ደጋግመዉ ቢመልሱልን አንድ ጊዜ አሜሪካኖቹን ቢፈሩ ብለን የአሜሪካ እርዳታ ድርጅት ባለስልጣናትን ወደ ወረዳዎቹ እንዲሄዱ አግባብተን በዬወረዳዎች ጉብኝት እንዲያደርጉ ሆኖ ነበር::ባለስልጣናቱም ባዩት ነገር አዝነዉ የክልል እና የፌደራል ባለስልጣናትን ለማነጋጋረ ሞከሩ::የፌደራል ባለስልጣናት እኛ በክልል ዉሳኔ ዉስጥ አንገባም ብለዉ ቁጭ::በየወረዳዎቹ ግን ሰዎች እየሞቱ ነበር::
– ይሄ ሁሉ ሁኔታ እየተከናወነ ሳለ የቅድመ ማስጠንቀቂያ የዳታቤዝ ስልጠና በሚል አንድ ስልጠና አዘጋጅተን ነበር::የመረጃ: የዉሳኔ እና በርሃብ ላይ ያለን ህዝብ ህይወት የመታደግ ቁርኝት የሚያሳይ አንድ ድራማ በስልጠናዉ መካከል እዲካተት አድርጌ ነበር::ድራማዉን በደንብ አስቤበት ስላዘጋጀሁት ተዋንያን ሆነዉም የሚተዉኑት ሰዎችን ከስልጠናዉ ተሳታፊዎች መሃከል በጥንቃቄ መርጫቸዉ ነበር::በዚህ መሰረትም ዉሳኔ ሰጭ ሆኖ እንዲቀመጥ ግን ምንም ዉሳኔ መስጠት የማይችል ሆኖ እንዲተዉን ያደረግሁት የድራማዉ ተዋናይ ደግሞ አንድ የብአዴን ባለስልጣን የነበረ ሰዉ ነበር::ስም እዚህ አላነሳም::ግን ባለስልጣኑ የዋዛ ሹመት አይደለም የነበረዉ::
– እናም በትወናዉ ዉስጥ በጣም በሚገርም ሁኔታ የበላዮቹን እያሰበ እና በፍርሃት ተሸብቦ ህዝብ እየሞተ የተለያዬ ምክንያት እየሰጠ ምንም ነገር ሳይወስን ቁጭ ብሎ ሲንገታገት ይስተዋላል::በመጨረሻም የሚሞተዉ ሰዉ ሳይሆን የሚያሳስበዉ የእርሱ ስልጣን ሆኑ ከስልጣኑ እንዳይነሳ ሲጨነቅ እና ሲርበተበት ይታያል::ድራማዉን በሚገርም ሁኔታ ተዉኖት ነበር::በስልጠና ሂደት ዉስጥ “role play” ብለን የምንጠራዉ የዚህ አይነት ድራማ በስልጠና ህደት ዉስጥ ሁኔታዎችን ከብዙ ቃላት በላይ ቁልጭ አድርጎ እንደሚያሳይ የሚያዉቅ ያዉቀዋል::
-ድራማዉን ተዉነዉ ሲጨርሱ ለብቻችን ስንሆን ይሄን የብአዴን ባለስልጣን አንድ ጥያቄ ጠየቅሁት::”ድራማዉን እየሰራህ ምን ተሰማህ?” የሚል ጥያቄ:: :አቀርቅሮ ዝም አለ::አሁንም ደግሜ ጠዬቅሁት::አልመለሰልኝም::ለሶስተኛ ጊዜ ስጠይቀዉ በጣም አዝኖ ” ባርነት ነዉ የተሰማኝ” ብሎኝ ቁጭ:: ድንገት ሳላስበዉ ሰፊ ፈገታ እፊቴ ላይ ታዬ::እኔ ፈገግ ስል::እሱም ቀና ብሎ ሲያዬኝ ፊት ለፊት ተያዬን:: ለምን ፈገግ እንዳልኩ ልቤን ያነበበዉ ይመስል “ይገባኛል::ምን እንደሚያስቅህ ይገባኛል::” አለኝ::ይሄ የብአዴን ባለስልጣን የኔን አቋም በብዙ መንገድ ጠንቅቆ ያዉቃል ብቻ ሳይሆን ገና አንድ አረፍተ ነገር ስናገር ምን እያሰብኩ እንደሆነ የሚረዳ ይመስለኛል::
– እኔም ምንም እንኳን ዉስጤን እንዳነበበዉ ባዉቅም “አይገባህም::አይገባህም::አይገባህም::” ስለ ሶስት ጊዜ መለስኩለት::እርሱም በማዘን እና በጥልቅ ብስጭት ” የሆነ ትምክህት አለብህ::ስለሀገር እና ህዝብ አንተ ብቻ የምትቆረቆር ይመስልሃል::እኛ እዚህ ኢህኣዴግ ዉስጥ ያለን ሰዎች ህዝብ ቢያልቅ በርሃብ ከምድረ ገጽ ቢጠፋ የምንፈልግ ይመስልሃል::?” ሲል ተቆጣኝ::
– አሁንም ፈገግ ብዬ እያዬሁት ነበር::ፈገታዬ ደግሞ አዎና የሚል ነበር::እርሱም አንብቦታል መሰለኝ “ቆይ ግን ምን እንድናደርግ ነዉ የምትፈልገዉ::ከድርጅቱ አቅጣጣ ዉጭ ምን እናድርግ?” ሲል ጠዬቀኝ::አሁን ግን የመሸነፍ ስሜት የተሰማዉ ይመስላል::እኔም አጋጣሚዉ ተመቸኝ እና መልሴን ሰጠሁት::”ኢህአዴግ ምንም አቅጣጫ አልሰጣችሁም::ህዉሃቶች እና ኦህዴዶች ስለተራበ ህዝባቸዉ ወገባቸዉን ይዘዉ ሲከራከሩ እናንተ ግን የተራበ ህዝባችሁን ከፈለገዉ ከብቱን ሽጦ ይብላ አለዚያም ይሰደድ የምትሉ አይደላችሁም? እና እራሳችሁ ብአዴኖች የፈጠራችሁት ችግር ነዉ::ፌደራል ላይ ያሉትም ባለስልጣን ለአማራአ ክልል ብቻ የተለዬ ዉሳኔ አይሰጡም::ወይም ይሰጣሉ ብዬ አላስብም::” ስል አብራራሁለት::
– “እና…” ይሄ ባለስልጣን ተኮሳተር::ሲኮሳተር ፈገግ ብዬ “እናማ የድራማዉ ተዋናይ የተወነዉ ሚና ብአዴኖች ጋ ያለ መሰለኝ?” ስል አብራራሁለት:: በዚህ ቅጽበት እንደ እሳት ቱግ አለ::” ገባኝ::ለካ ይሄን የስልጠና ፕሮግራም ስታዘጋጅ ይሄን ድራማ የጻፍከዉ እኛን ለመስደብ ነዋ::” እየተመናጨቀ ጥሎኝ ሄደ::
– ጥቂት እንደሄደ ስሙን ጠራሁት::ዞር አለ:: “እንደዉነቱ ከሆነ የድራማዉ ዋናዉ ግብ የብአዴንን ባህሪ ማሳዬት ነዉ::ለምሳሌ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳታ ቤዝ ትግራይ እና ኦሮሚያ በእኛ አስተባባሪነት እንድሰራላቸዉ ፈቃደኛ ሲሆኑ የአማራ ክልል ግን የፌደራልን ፈቃድ ጠይቄ ነዉ ዳታቤዙን እንድትሰሩልን የምፈቅደዉ እያላችሁ ነዉ::ትግራይ ክልል እና ኦሮምያ ፌደራል እንጠይቃለን አላሉም::አማራ ክልል ይሄን አቋም ከዬት አመጣዉ?” ስል ጠዬቅሁት:: እርሱም ወደኔ እያስተዋለ “እና ?” ሲል ጠዬቀኝ::እኔም “ድራማዉ ዉስጥ ያለዉ ሚና ጉዳይ ነዋ” ስል መለስኩለት:: እናም እየተቆጣ ጥሎኝ ሄደ::
-የሚገርመዉ ከአንድ ወረዳ ወደ ክልል የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ ለመድረስ ከአንድ ወር እስከ ሶስት ወራትን ይፈጃል::መረጃዉም በመንገድ ላይ ሊጠፋ ይችላል::በዳታቤዙ ቅድመ ማስጠንቀቂያዉ ስርዓት ቢዘረጋለት ግን በሰዓታት ዉስጥ በያንዳንዱ የክልሉ ወረዳዎች የሚደርስ አደጋ ሁሉ ለባለስልጣናቱ ይደርሳል::ፈጣን ዉሳኔም ማሳለፍ ይችላሉ::እንዲህ አይነቱን አሰራር ለመዘርጋት ነዉ እንግዲህ የአማራ ክልል የብአዴን ባለስልጣናት የፌደራል መንግስትን ተይቀን የሚሉት::ለነገሩ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳታቤዝ እንዲሰራላቸዉ የፈቀዱትም የኦሮሚያ እና የትግራይ ክልልሎች አሰራሩ ሳይዘረጋላቸዉ በሀሳብ የቀረበት ብዙ ምክንያት ተከተለ::
የገዱ ቁመት ምን ያህል ነዉ:- ገዱ ከማን ነዉ ነጻነትን እና ፍትሃዊ አስተዳደርን የሚጠብቀዉ
————————-
ገዱ ሰሞኑን አቢይን ጎንደር ጋብዞት ሳለ የጀግና እና የነጻ ሰዉ የሚመስል ሀሳብ አንስቶ ባይ ነዉ ይሄ ሁሉ ትዝታ የመጣብኝ::ጠቅላይ ሚንስቴር አቢይን “… ለነጻነት እና ለፍትህ እንዲሰሩ አሳስባለሁ…” ብሎ ቁጭ:: እኔ ደግሞ እዉን ገዱ ነጻነት የሚያዉቅ ሰዉ ነዉ ስል እራሴን ጠዬቄ ይሄን ጽሁፍ ማዘጋጀት ጀመርኩ::
የሰዉ ልጆች በርሃብ እንዲሞቱ የፈረደዉ ብአዴን:- የጉራፋርዳ አማራ ተፈናቃይ ነገር
————————
– ከላይ ባልኩት ፕሮጀክት ዉስጥ ስሰራ ግማሽ ሚሊዮን አማሮች ከጉራፋርዳ ሲባረሩ ለፈረንጅ አለቆቼ አንድ ጥናት አቅርቤላቸዉ ነበር::” እነዚህ የተፈናቀሉ አማሮች የሚበሉት የለም::የእኛ ፕሮጀክት ሊርዳቸዉ ከቻለ እኔ ደግሞ የአማራ ክልል ባለስልጣናትን ሄጄ አነጋግራለሁ::” ስል ሀሳብ አቀረብኩላቸዉ:: ፈረንጆቹ አለቆቼ በፍጥነት “በቂ ምግብ ስላለን ሰዎቹን እንረዳለን” የሚል መልስ ሰጡኝ እና እኔም ጉዜዬን ወደ ባህርዳር አደረግሁ::
-ባህርዳርም እንደደረስሁ የአማራ ክልል ባለስልጣናትን ማነጋገር ጀመርኩ:: ካነሳሁባቸዉም ነጥብ ዉስጥ “የአማራ ክልል ከጉራፋርዳ ለተፈናቀሉት አማሮች በደብረብርሃን ወይም በባህርዳር አለዚያም በሆነ ቦታ መጠለያ ካዘጋጀ የኛ ፕሮጀችት በቂ የምግብ እርዳታ ያቀርባል” የሚል ሀሳብ አቀርበሁላቸዉ:: እነዚህ ባለስልጣኖችም ከላይ እስከታች የመለሱልኝ መልስ አስደንጋጭ ነበር::ይሄዉም ” እነዚህ ከጉራፋርዳ የተፈናቀሉ አማራዎች የሰዉ ሀገር ሄደዉ የወረሩ ናቸዉ::ስለዚህ የአማራ ክልል በእነዚህ ሰዎች ጉዳይ አያገባንም” ሲሉ መልስ ሰጡ::ይሄ አቋም የተወሰኑ ባለስልጣኖች መስሎኝ ብዙዎቹን በሰዉም በግልም አነጋገርኳቸዉ:: መልሳቸው ግን ያዉ ነበር::ይባስ ብለዉም በግል የነገሩኝን ነገር በአደባባይ በሚዲያ ወጥተዉ ተናገሩ:: የሰዉ ሀገር ሄደዉ የወረሩ : ዛፍ የጨፈጨፉ ናቸዉ የሚል እና የጸረ አማራዉን የሽፈራዉ ሽጉጤን ንግግር የሚያጸድቅ ዉሳኔን የአማራ ክልል ይዞ ብቅ አለ::እዉን ይሄ ተረት ተረት እንጅ እዉነት ይመስላል?
-እናም በዚህ የአማራ ክልል የሚባል ዉስጥ የመሸጉ የጸረ አማራ ሀይላት አቋም የተነሳ ከአባቶቹ ሀገር ከጉራ ፋርዳ የተባረረዉ እና በሜዳ የተበተነዉ ግማሽ ሚሊዮን አማራ አለ አንዳች እርዳት በርሃብ እና በድህነት ብሎም በበሽታ እየተቀጠቀጠ እና እየሞተ አሁን ድረስ የትም ተበትኖ ይገኛል::ህጻናቱ በጎዳና ምናልባትም በበሽታ አልቀዋል:: አዛዉንት በብርድ እና በበሽታ አሸልበዋል::ጎልማሶች ከትዳራቸዉ ተናጥለዉ ትዳራቸዉ ፈርሶ የትም ለማኝ ሆነዋል::ግን ይሄ ህዝብ ምን ወገን አለዉ? ይሄንንስ ማን ይናገርለታል?
– እንግዲህ ይሄን ሳስብ ነዉ ገዱ የሚባለዉ የወያኔ ባሪያ ለሌላዉ የወያኔ ባሪያ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቢይ የህዝብ ነጻነትን የተመለከተ ንግግር እያደረገ በህሊናዬ “የባርነት ሀሳብ ተሸካሚዉ ብአዴን ነጻነት እና እኩልነት የሚባሉ ነገሮች መኖራቸዉን ያዉቅ ይሆን?” የሚል ጥያቄ የተመላለሰብኝ::አማራ ነኝ ብለዉ ከአማራ አብራክ የወጡ እነ ገዱ አማራዉ በርሃብ : በዉርደት እና በስደት ሲጠፋ በምግብ እንኳን እራሱን እንዲመግብ እንርዳዉ የሚሉ የፈረንጅ ሰዎች ፈቃደኛ ሲሆኑ አባቶቹ በመሰረቱት ሀገሩ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚኖረዉን አማራ “የሰዉ ሀገር ሄዶ ስለወረረ ተፈናቅሎ በርሃብ ቢያልቅ አያገባንም” ሲሉ የተዘባበቱት የባርነት ሀሳብ ተሸካሚዎች እንጅ ምን ሊባሉ ይቻላሉ? እንጃ ደጋግሜ ሳስበዉ ለእነዚህ ሰዎች መግለጫ ቃል ያጥረኛል::
– በግል ህይወቴ ይቅር ባይ እንደሆንኩ አብሮኝ የኖረ ያዉቃል::በአማራ ህዝብ ላይ ወያኔ እና የወያኔ አገልጋይ እነ ብአዴን የሰሩትን ነገር ሳስብ ግን ነብዩ ሳሙኤል ህዝበ እስራኤል በጉዞ ላይ እያለ ባጠቁት ጠላቶች ላይ የፈጸመዉ ድርጊት ነዉ በህሊናዬ የሚመላለሰዉ:: መጽሀፈ ሳሙኤል ቀዳማይ 15 (32-33) :-
“ሳሙኤልም፦ የአማሌቅን ንጉሥ አጋግን አምጡልኝ አለ። አጋግም እየተንቀጠቀጠ ወደ እርሱ መጣ። አጋግም፦ በውኑ ሞት እንደዚህ መራራ ነውን? አለ። ሳሙኤልም፦ ሰይፍህ ሴቶችን ልጆች አልባ እንዳደረገቻቸው እንዲሁ እናትህ በሴቶች መካከል ልጅ አልባ ትሆናለች አለ፤ ሳሙኤልም አጋግን በእግዚአብሔር ፊት በጌልገላ ቈራረጠው።”
እግዚአብሄር ይሄን የዋህ ህዝብ እንዲህ በጠላጠላትነት የተበቀሉትን ጠላቶች የሚመታበት ዘመን እንዳለ እሙን ነዉ::የዚህን የዋህ ህዝብ ጠላቶች አንድም በነብይ ወይም በጦረኛ ከምድረገጽ እግዚአብሄር እንደሚመታ አምናለሁ::ቀኑ ይመጣል::ይሄን ግን ነገርን በጊዜዉ ዉብ አድርጎ ለሚያከናዉን አምላክ ልተወዉ እና ወደ ተነሳሁበት ዋና ጥያቄ ልግባ::
-ይሄ ጥያቄ በየቀኑ በህሊናዬ እየተመላለሰ የሚበጠብጠብጠኝ ቢሆንም አሁን የገዱን የህዝብ ነጻነት ይከበር ንግግር እየሰማሁ ግን በህሊናዬ ጮክ ብሎ ተሰማኝ::እናም የባርነት አስተሳሰብ ተሸካሚዎቹ ብ አዴኖች ባይመልሱልኝም ህዝብ እንዲያስታዉሰዉ ከቻለም አንዳንድ እርዳታ ማድረግ ቢችል ጥያቄዉን ወደ አደባባይ አወጣሁት::
ጥያቄዉ:- ከጉራ ፋርዳ የተፈናቀለዉ የአማራ ህዝብ ምን ዉስጥ ገባ? አሁን በምን አይነት መከራስ ዉስጥ ይገኛል?
—————————————-
ከጉራ ፋርዳ የተፈናቀለዉ ግማሽ ሚሊዮን የአማራ ህዝብ (ወንዱ ሴቱ: ህጻናቱ: አዛዉንቱ) የት ነዉ አሁን ያለዉ? በጎዳና? በሞት መቃብር? በድህነት ዉስጥ? አሁንም እየተንከራተተ::
ለምሆኑ አሁን እነዚህን ዜጎች ወይም ወደፊት መልሶ ሊያቋቁማቸዉ: ሊያሰፍራቸዉ የሚችል አካል ማን ነዉ? ሌላዉ ቀርቶ መብታቸዉ ምን እንደሆነ አሳዉቆ መብታቸዉን እንዲጠይቁ ሊያደራጃቸዉ የሚችል አካልስ ማን ነዉ? የባርነት ሀሳብ ተሸካሚዉ ብአዴን ነጻነት እና እኩልነት የሚባሉ ነገሮች መኖራቸዉን ያዉቅ ይሆን?:- እዉን ገዱስ የሰዉ ቁመት አለዉ? ገዱ የሚመራዉ የባርነት ሀሳብ ተሸካሚ እንዲህ አይነት የህዝብ ጥያቄ ያነሳል ተብሎ መቼም አይጠበቅም::
-በአማራ ህዝብ የተደራጁ ድርጅቶች (የፖለቲካም ቢሆኑ : የሲቪልም ቢሆኑ) የዚህ ህዝብን መልሶ መቋቋም ሊያነሱለት ይገባል ብዬ አስባለሁ::በቅርቡ ከሶማሌ ክልል ለተፈናቀለዉ በሚሊዮን የሚጠጋ የኦሮሞ ህዝብ በዶክተር መራራ የሚመራዉ መድረክ እና ኦህዴድ ደጋግመዉ የተፈናቃይ ወገኖቻችንን የመልሶ መቋቋም ጥያቄዉን ወደ ህዝብ እያቀረቡለት ነው::ይሄም ይበል የሚያስብል ነዉ::
-ሆኖም ከጉራ ፋርዳ የተፈናቀሉ አማራዎች ሁኔታን ተቃዋሚዎችም: ሚዲያዎች ዝምታን የመረጡት እነዚህ ዜጎች ምን ስለበደሉ ነዉ? ጥያቄዬ ማለቂያ ለዉም::ስለሆነም እዚህ ጋ ማቆም አለብኝ::የገዱን “ህዝቡ ካሁን ብኋላ የፍትህ የነጻነት እና የዲሞክራሲ መፍትሄዎችን እንዲያገኝ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቢይን አሳስባለሁ” ብሎ የተናገረዉን ንግግር ሰምቼ እንደገና ነገሩ እንደ አዲስ ኩልል ብሎ በህሊናዬ ተመላለሰ::ገዱ የተባለ እና ብአዴን የተባለ የባርነት ተሸካሚዎች ለመሆኑ እነዚህ ከጉራፋርዳ የተፈናቀሉ እና ከሌላ አካባቢ የተፈናቀሉ አማራዎች ምግብ እንኳን እንዲያገኙ ወደፊት ይፈቅዱላቸዉ ይሆን?ምግብ ለሰዉ ልጅ የማይፈቅድ ሰዉ ስለ ነጻነት ያወራል ቢባል ታላቅ ቀልድ ነዉ::ምግብ ማግኘት ከመሰረታዊ የሰዉ ልጆች የሰበአዊ መብት ዉስጥ ይመደባልና::
– ብአዴን ዉስጥ የተሰገሰጉ የባርነት ሀሳብ ተሸካሚ የህዉሃት ባንዳዎች ግን እዉነት ነጻነት ምን እንደሆነ ከቶስ ያዉቃል? ሰዉ የራሱ ወገን ምግብ እንኳን ተመግቦ እንዳያድር የሚጨክን ህሊና ካለዉ በዉኑ እነ ገዱ : እነ አያሌዉ ጎበዜ: እነ አዲሱ ለገሰ: እነ እንቶኔ እነ እንቶኔ የሚባሉ ብአዴን ዉስጥ ከሃያ አመታት በላይ የመሸጉ ሰዎች በእዉኑ ነጻነትን ያዉቁታል ተብሎ ይጠበቃል? ሀሰት ነዉ::ዉሸት ነዉ::ፈጽሞ ነጻነት አያዉቁም::እነዚህ የባርነት ሀሳብ ተሸካሚዎች እንጅ:: አሁንስ ከነዚህ ሰዎች ህሊና የነጻነት ሀሰብ ይፈልቃል?ሀሰት::ለመሆኑስ ገዱ ለሚመራዉ ህዝብ የአማራ ህዝብ ነጻነት ለማጎናጽፍ ካሰብ ከማን ነዉ ነጻነትን እና ፍትሃዊ አስተዳደርን የሚጠብቀዉ? ለመሆኑስ የገዱ ቁመት ምን ያህል ነዉ?ቢያንስ ለሚመራዉ ህዝብ ምግብ የማግኘት መሰረታዊ የሰበአዊ መብቱን የሚያከብር ሰዉ ነዉ?