onsdag 22. mai 2013

በገላሺ ከተማ የኢትዮጵያ ወታደሮች 10 ሰዎችን መግደላቸውን ኦብነግ አስታወቀ


የኦጋዴን ነጻ አውጭ ግንባር ( ኦብነግ) ለኢሳት በላከው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው ትናንት ግንቦት 13 ቀን 2005 ዓም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከልዩ ሚሊሺያ ጋር በመተባበር በወሰደው እርምጃ አቶ ማካሊ ሙስጠፋ ሀሰን፣ አቶ ሻፊ አው ካሊፍ፣ አቶ አብዱላሂ አብዲ፣ አቶ ሻኩል አብዲ፣ አቶ ፋራህ ሙሀመድ፣ አቶ አብዲሀይ ሼክ አህመድኑር እና አቶ አብድራሺ ሻፊቺች የተባሉትን ነዋሪዎች ገድለዋል።

የግድያው ምክንያት በጋላሺ የጦር ምድብ የሚገኙ 70 የልዩ ሚሊሺያ አባላት ከድተው እጃቸውን ለግንባሩ መስጠታቸውን ተከትሎ ፣ ነዋሪዎቹ የጠፉትን ወታደሮች አድራሻ እንዲያወጡ ከተጠየቁ በሁዋላ ነው። ወታደሮቹ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ 7 ሰዎችን እጆቻቸውን ካሰሩ በሁዋላ እንደረሹኑዋቸው፣ 3ቱን ደግሞ ከከተማዋ 3 ማይል ርቅት በሚገኝ ቦታ ላይ እንደገደሉዋቸው ግንባሩ አስታውቋል።

ግንባሩ እንዳለው በዚህ አመት ብቻ ከ300 ያላነሱ የአካባቢው ተወላጆች በመከላከያ ሰራዊት እና በልዩ ፖሊስ አባላት ተገድለዋል።

 ጉዳዩን በማስመልከት ቃለምልልስ ያደረግንላቸው የግንባሩ የውጭ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ሀሰን አብዱላሂ፣ የከዱት ወታደሮች ግንባሩን መቀላቀላቸው እውነት ቢሆንም፣ የተገደሉት ነዋሪዎች ግን ድርጅቱ አባላት አለመሆናቸውን ገልጸዋል።

የግንባሩ የውጭ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት አቶ ሀሰን አብዱላሂ በመከከላከያ ሰራዊት እና ልዩ ሚሊሺያ የሚፈጸመው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል
በጉዳዩ ዙሪያ የመንግስትን መልስ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar