ኢትዮጵያን ላለፉት 23 ዓመታት የገዛው ኢህአዴግ መጪውን ምርጫ ተከትሎ በአዲስ አበባና በዋና ዋና የአገሪቱ ከተሞች ረብሻዎች ሊነሱ እንደሚችሉ ፓርቲው ድምዳሜ ላኢ መድረሱን አስታውቋል።
የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት በኢትዮጵያ መንግስት አሸባሪ ተብለው የተፈረጁት በተለይ ግንቦት7 እና ኦነግ ምርጫውን ተከትሎ በምርጫ 97 የታየውን አይነት የህዝብ አመጽ ለማስነሳት እየሰሩ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሰው ኢህአዴግ፣ ከአሁኑ ጀምሮ በአንድ ለአምስት አደረጃጀትና የከተሞችን ነዋሪዎች ስለ አሸባሪዎች አላማ እና ግብ በማስረዳት ህዝቡ በአመጹ ተሳታፊ እንዳይሆን እንደሚያስተምር አስታውቋል።
አሸባሪ የተባሉ ድርጅቶች በመልካም አስተዳደር፣ በሙስና እና በኢኮኖሚ ዙሪያ የሚታዩ ክፍተቶችን ተጠቅመው ህዝቡ በመንግስት ላይ እንዲነሳ ሊያደርጉ ይችላሉ አለው ኢህአዴግ፣ ለዚህ አላማ እንዲረዳቸው ደግሞ ኢሳትንና ቪኦኤን የመሳሰሉ የመገናኛ ብዙሀንን በአገር ውስጥ ደግሞ አንዳንድ ጽንፈኛ አስተሳሰብ ያላቸውን መጽሄቶች ሊጠቀሙ ይችላሉ ብሎአል። በአገር ውስጥ በሰላማዊ ትግል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ፣ ለአመጽ ጥሪው ህጋዊ ሽፋን ለማሰጠት ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ ።
በተለይ የአዲስ አበባ ህዝብ የአሸባሪዎች ኢላማ እንዳይሆን ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ኢህአዴግ ገልጿል።
በሚቀጥለው አንድ አመት ውስጥ በአዲስ አበባ እና በክልል ዋና ዋና ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች እና የመንግስት ሰራተኞች በሽብረተኝነት ዙሪያ ተከታታይ ትምህርት የሚሰጣቸው ሲሆን፣ ግንባሩም ከእዚህ ስልጠና የአካባቢ የሰላም ጠባቂዎችን እንደሚመለምል ፣ በፖለቲካ አስተሳሰባቸው ገዢውን ፓርቲ አይደግፉም የሚባሉትን የመለየት ስራም እንደሚሰራ ታውቋል።
ኢህአዴግ ምርጫውን ተከትሎ ሊነሳ የሚችል ማንኛውም ተቃውሞ ሽብርተኝነት ነው ሲል ድምዳሜ ላይ ደርሷል። በምርጫ ሂደቱ ላይ ፍትሀዊ ያልሆኑ አሰራሮች እንዲሁም የድምጽ ማጭበርበሮች እንኳን ቢከሰት ተቃዋሚዎች የተቃውሞ ሰልፍ እንዲያደርጉ አይፈቀድላቸውም።
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar