lørdag 4. januar 2014

ኢህአዴግ በመንግስት ወጪ ለመጪው ዓመት ምርጫ ሕዝብ የማደራጀትና የመቀስቀስ ስራ ጀመረ


ኢህአዴግ ከ2007 አገር አቀፍ ምርጫ ጋር በተያያዘ በተለይ በአዲስአበባ ከተማ ሕዝብ ቅሬታ የሚያቀርብባቸውን የመልካም አስተዳደር፣ የሙስናና የልማት ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ በጀት መድቦ እየተንቀሳቀሰ ነው።
የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር የ2006-2007 ዕቅድ አካል እንዲሆን በተደረገው ይህ ከመጪው ዓመት ምርጫ ጋር በቀጥታ የተያያዘው ዘመቻን በብቃት እንዲያስፈጽሙ ለክፍለከተማና ወረዳ አመራሮች ግልጽ መመሪያ ከመተላለፉም ባሻገር በአቅም ግንባታ ስልጠና መወጠራቸው ታውቋል፡፡
በዚሁ መሰረት በከተማ አስተዳደር ውስጥ መልካም አስተዳደርን ሊያሰፍንና ልማትን ሊያፋጥን የሚችል የልማት ሠራዊት በመገንባት ፣የወረዳዎችን ሁለንተናዊ አቅም ማሳደግ፣ቀልጣፋ፣ውጤታማ ፍትሐዊ አስተዳደር በማስፈን የህዝቡን እርካታ ማረጋገጥ ዓቢይ ዕቅድ ሆኖ እየተሰራበት ይገኛል፡፡ ይህንንም ለማሳካት በአዲስአበባ በየደረጃው የሚገኙ የ3 ሺ 500 አመራሮች አቅምና ክህሎት በማሻሻል
ዕቅዱን የማስፈጸም ብቃትና ቁርጠኝነትን ለማሳደግ ስልጠናዎች እየተሰጡ ነው።
በአስተዳደሩ በተለያዩ ቢሮዎች የሚገኙ የመንግስት ሠራተኞችንም አመለካከትና የክህሎት ችግሮችን በመቅረፍና ልማታዊ አስተሳሰብ እንዲያዳብሩ ማድረግም የዕቅዱ አካል ሲሆን በመንግስት መዋቅሩ ካሉት ሰራተኞች 75 በመቶ የሚሆኑትን የለውጥ ኃይል ለማድረግ፣ከዚህ ውስጥ 60 በመቶው በያዝነው በ2006 በጀት ዓመት ለመፈጸም ታቅዶ እየተሰራበት መሆኑ ታውቋል፡፡
ኢህአዴግ ከዚህ ቀደም የፈጠራቸው የተለያየ አደረጃጀቶች ማለትም የወረዳና የክፍለከተማ እንዲሁም የከተማ የሕዝብ አማካሪ ምክርቤቶች ፣የሴቶች፣የወጣቶች የመሳሰሉ አደረጃጀቶችን በመጠቀም በመጪው ምርጫ ወሳኝ ሚና እንዲጫወቱ “ልማትና መልካም አስተዳደርን ለማፋጠን” በሚል ሽፋን የአስተዳደሩ የበጀትና የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ታውቋል፡፡
በዚሁ መሠረት 38ሺህ የከተማ፣የክፍለከተማና የወረዳ ምክርቤት አባላትን፣ 50ሺህ የተለያዩ የሕዝብ አደረጃጀቶችንና ልዩ ልዩ ተለጣፊ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የሲቪክ ማህበራት አቅም በዚህ ዓመት እንዲያድግ እንደሚደረግ ታቅዶአል፡፡
ገዥው ፓርቲ ከምንም በላይ አነስተኛ ጥቃቅን ተቋማትን በብዛት በማደራጀትና ያሉትንም በብድር በማጠናከር ለምርጫ ድጋፍ ለማሰባሰብ ከወዲሁ እየሠራ ነው፡፡ በዕቅዱ መሰረት ዘንድሮ እና በቀጣይ ኣመት በድምሩ ለ475 ሺህ ስራአጥ ወጣቶች ስራ እፈጥራለሁ ብሎአል፡፡ አዲስ ስራ ፈላጊ ዜጎች ፍላጎታቸው እየታየ በ16 ሺህ 500 ኢንተርፕራይዞች እንዲደራጁ እንደሚደረግ፣ ከዚህ ውስጥ 8 ሺህ 750 በዚህ ኣመት እንደሚደራጁ ተመልክቶአል፡፡በተጨማሪም ለአዲስ ስራ ፈላጊዎችና ለነባር ኢንትርፕራይዞች ብር 1 ቢሊዮን 700 ሚሊዮን እንዲቆጥቡና 2 ቢሊዮን 7 ሚሊዮን ብር ብድር እንዲመቻችላቸው ተወስኖ እየተሰራበት መሆኑን ለማወቅ ተችሎአል፡፡
ኢህአዴግ ለቀጣዩ ዓመት አገር አቀፍ ምርጫ ከወዲሁ በልማትና በመልካም አስተዳደር ሽፋን ሕዝብ የማራጀትና የመቀስቀስ ስራዎችን ማከናወኛ የሚውለውን በጀት በአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር የሚሸፈን መሆኑም የአስተዳደሩ ምንጭ ጠቁሟል፡፡

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar