tirsdag 21. januar 2014

ከሱዳን ጋር የሚደረገው የድንበር ውዝግብ የሞራልና የሶሻል ጥያቄ እንጅ የህግ ድጋፍ የለውም ሲሉ አንድ የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን ተናገሩ

ባለስልጣኑ ይህን የተናገሩት የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትና የደህንነት ሰራተኞች በተገኙበት በተደረገው ግምገማና ውይይት ላይ ነው።
በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለውን ድንበር የማካለል እንቅስቃሴ ከ1965 ዓም ጀምሮ በጊዜው የውጭ ጉዳይ ሚ/ር በነበሩት ዶ/ር ምናሴ ሃይሌና በሱዳኑ አቻቸው ጃፋር ኤሊ ሜሪ መካከል የተጀመረ እና እስካሁኑም የዘለቀ መሆኑን ባለስልጣኑ አውስተዋል።
ሱዳኖች “ኢትዮጵያውያን የጉዊን መስመር እየተባለ የሚጠራውን ቦታ አልፈዋል” በሚል  ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ተመሰርቶ ኮሚቴ መቋቋሙን ያወሱት ባለስልጣኑ፣ “ይሁን እንጅ ኮሚቴው ምንም አይነት የድንበር ማካለል ሳያደርግ እስከዛሬ ቆይቷል ።”
“አሁን በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል የሚደረገውን ውይይት የምትገዛው ደብዳቤ ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የተለዋወጡት ደብዳቤ መሆኑን  ባለስልጣኑ ጠቅሰው ፣ ኮሚቴው በጊዜው ችግሩን በሰላም ለመፍታት የመፍትሄ ሃሳቦችን አቅርቦ እንደነበርም አክለዋል።
“ሱዳኖች ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያን መሬት ለመውሰድ አቅም አልነበራቸውም ” የሚሉት ባለስልጣኑ ፣ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1995/96 የግብጹን መሪ አዲስ አበባ ላይ ለመግደል የተደረገውን ሙከራ ተከትሎ የኢትዮጵያ ጦር አካባቢውን ከተቆጣጠረው በሁዋላ የ ትግራይና የአማራ ክልሎች ለኢንቨስተሮች በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የሱዳን  መሬት  መስጠታቸውን ገልጸዋል። ሱዳኖች ቀደም ሲል ጀምሮ ግዛታችንን መልሱ የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ ቢቆዩም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጥያቄያቸው እየገፋ ምጣቱን አብራርተዋል። 1965 ዓም ጀምሮ መሬት የሚባል ለሱዳን አለመሰጠቱትነ አጠንክረው የተናገሩት ባለስልጣኑ፣ በቅርቡ ግን የኢትዮጵያ መንግስት ልኡካን ሱዳንን በጎበኙበት ወቅት ሱዳኖች ያቋቋሙት ኮሚቴ አዲስ ሃሳብ ይዞ መቅረቡን ገልጸዋል።  አዲሱም ሀሳብ ” መሬቱን እንደያዛችሁት ቆዩ፣ የዜጎቻችሁን መብቶች እናስጠብቃለን፣ ነገር ግን ቢያንስ በንደፈ ሃሳብ ደረጃ መሬቱ የእኛ መሆኑን የሚያሳየውን ካርታ ተቀብላችሁ አረጋግጡልን ” የሚል መሆኑን ባለስልጣኑ አስረድተዋል
“በረኻት የሚባል የትግራይ ከተማ ላይ ሆናችሁ ሞባይላችሁን ብታወጡ የሚያሳያችሁ ሱዳንን ነው፣ እንዲሁም አርማጭሆ ላይ ሆናችሁ ሞባይሎቻችሁን ብታዩ ያላችሁበት ኢትዮጵያ የሚባለው ቦታ ሱዳን ነው ” የሚሉት ባለስልጣኑ፣ “የፈለገውን ፖለቲከኛ መሸወድ ይቻላል፣ ሳይንሱን ግን መሸወድ አይቻልም” በማለት ገልጸዋል
የአርማጭሆ መሬት ለሱዳን ተሰጠ እየተባለ የሚወራው ውሸት ነው ያሉት ባለስልጣኑ ፣  “አንዳንድ ጊዜ የሱዳን ፖሊስ ድፍረቱ ሲኖረው እየገባ ግጭት ይፈጥራል፣ የኛ ሚሊሺያዎችም የሚሰንፉ አይደሉም ፣ እንዲያውም የእኛ ሚሊሺያዎች የሱዳንን ወታደሮች እንደ ወታደር አይቆጥሩዋቸውም” በማለት በሱዳንና በኢትዮጵያ ድንበር ፖሊሶች መካከል ያለውን ልዩነት ተናግረዋል።
“አይናችን የሚያየውን ሁሉ እንይዛለን ማለት አይደለም” ያሉት ባለስጣኑ፣ በእርግጥ እንያዝ ካልን ካርቱምንም መያዝ እንችላለን ሲሉ የሱዳንን የመከላከያ ብቃት አጣጥለዋል።
አቶ መለስ በነበሩበት ጊዜ በሱዳኖች በኩል ለቀረበው ሃሳብ መልስ እንዲሰጥ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኮሚቴ በሀሳቦች ልዩነት የተነሳ እስካሁን መልስ መስጠት አለመቻሉንም ባለስልጣኑ ገልጸዋል።  አንዳንዱ የኮሚቴ አባል “ከአሁን በሁዋላ ሰዎቻችን ተነሱ ቢባሉስ እንዴት እሽ ብለው ይነሳሉ” የሚል ሀሳብ ያቀርባል ብለዋል።
“ጥያቄችን የሞራል እና የሶሻል እንጅ  የህግ ድጋፍ የለውም” የሚሉት ባለስልጣኑ፣ እርሳቸው አንዱ የኮሚቴው አባል ቢሆኑም መልስ ለመስጠት እንኳን እንደተቸገሩ ተናግረዋል።
“በ1965 በሞፈር ዘመት መሬት የያዙ አርሶአደሮች ከአርባ አመት በሁዋላ የያዛችሁት መሬት አገራችሁ አይደለም ሲባሉ ቢቃወሙ የሚገርም አይሆንም” የሚሉት ከፍተኛው ባለስልጣኑ፣ “የህግ ክርክሮች ቢነሱ የማንኮራባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም ቅሉ እስካሁን ግን የድንበር ማካለል ስራ አልተጀመረም  ።
ሱዳን ትሪቢዩን የተባለው ጋዜጣ በፈረንጆች አቆጣጠር በ2007 ሰፊ መሬት ከኢትዮጵያ  ለሱዳን መሰጠቱን የአካባቢውን አስተዳዳሪ ጠቅሶ መዘገቡ ይታወሳል።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar