በምርጫ 2002 የተስተዋሉ ጉድለቶች ሳይስተካከሉ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ መወጣቱን እና ወደ ምርጫ 2007 መገባቱን በመቃወም ሊያደርገው ባሰበው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ እስከ 100ሺ ሰዎች ሊሳተፉ እንደሚችሉ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ገለፀ።
የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥላሁን እንዳሻው እንደገለፁት በ2002 ዓ.ም የተካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ደረጃው የወረደ እና ዴሞክራሲያዊነቱን ያልጠበቀ በመሆኑ ህዝቡ በነፃነት ምርጫ መርጧል በማያስብል መልኩ መጠናቀቁን ተከትሎ በወቅቱ ፓርቲው በምርጫው ውስጥ ጉድለቶች መኖራቸውን በማንሳት ከገዢው ፓርቲ ጋር ለመደራደር ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ቢያቀርብም እስከ አሁን ድረስ አዎንታዊ ምላሽ ማግኘት አልቻለም። ይህን ጥያቄ ለምርጫ ቦርድም ገልፆ እንደነበረ የገለፁት አቶ ጥላሁን፤ ይልቁንም የነበሩት ግድፈቶች ምንም አይነት እርምት ሳይደረግባቸው የምርጫ ጊዜ ሰሌዳን በማውጣት ወደ ምርጫ 2007 መጓዝ መምረጡንም ገልፀዋል። በመሆኑም ገዢው ፓርቲ ለጥያቄው አዎንታዊ ምላሽ አለመስጠቱን በመቃወም የፊታችን ታህሳስ 5 ቀን 2007 ዓ.ም ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ አስቧል። ሰላማዊ ሰልፉ መነሻውን ግንፍሌ ወንዝ ድልድይ በማድረግ በቀበና ወንዝ ድልድይ እና በባልደራስ በኩል በማድረግ መድረሻውን ወረዳ 8 ኳስ ሜዳ አድርጎ ከጠዋቱ 3 ሰዓት እስከ 7 ሰዓት ይካሄዳል።
ሰላማዊ ሰልፉ የፓርቲው ብቻ ሳይሆን የህዝቡ በመሆኑ ህዝቡ በንቃት ከተሳተፈ ወደፊት የማይገፉበት እና ግቡንም የማይመታበት ሁኔታ እንደሌለ አቶ ጥላሁን ገልፀው፤ የሰልፉ መረጃ ለህዝቡ በአግባቡ ከደረሰ ከአዲስ አበባ እና አካባቢዋ የተውጣጣ በትንሹ ከ20 እስከ 30ሺህ የሚደርስ ህዝብ እንደሚሳተፍ ገልፀዋል። የቅስቀሳ ስራው በአግባቡ ከተሰራ ግን እስከ 100 ሺህ የሚደርስ ህዝብም ሊሳተፍ እንደሚችል አቶ ጥላሁን ጨምረው ገልጸዋል።
ፓርቲው ሰላማዊ ሰልፉን ለማካሄድ ጠይቆ የነበረው ቦታ መነሻውን የፓርቲው ጽ/ቤት በማድረግ በራስ መኮንን ድልድይ ፒያሳ ጀጎል አደባባይን ይዞ ቸርቸል ጎዳናን አልፎ መዳረሻውን ድላችን ሀውልት ለማድረግ የነበረ ሲሆን፤ ነገር ግን ፈቃድ ማግኘት ባለመቻሉ ሰልፉ መደረግ ስላለበት ሁለተኛውን አማራጭ ለመቀበል መገደዱን አቶ ጥላሁን ገልፀዋል። የፓርቲው መጀመሪያ ምርጫ በመሀከል ከተማ የሚያልፍ እና ከአራቱም የከተማዋ አቅጣጫ ሰዎች ሊሳተፉበት የሚችሉበት ቦታ መሆኑን የገለፁት አቶ ጥላሁን፣ አሁን በተፈቀደላቸው ቦታ በሚደረገው ሰልፍ ላይ ግን የተሳታፊው ቁጥር የተጠበቀውን ያህል ላይሆን እንደሚችል ገልጸዋል።
ሰላማዊ ሰልፍን በተመለከተ ሕገ መንግሥቱ ማስፈቀድ ሳይሆን ማሳወቅ ስለሚል ፓርቲው እውቅና እንዲሰጠው ጠይቆ የእውቅና ደብዳቤ በአጭር ጊዜ ውስጥ መውሰዱ የተገለፀ ሲሆን፤ በፈቃድ ደብዳቤው ፓርቲው ቅስቀሳ የሚያደርግባቸውን መንገዶች ያካተተ ፍቃድ እንደተሰጠው ገልጿል። ፓርቲው በማይክሮፎን፣ ወረቀት በመለጠፍ እና በራሪ ወረቀቶችን ጭምር በመበተን ቅስቀሳ የማድረግ ፈቃድም እንደተሰጠው አቶ ጥላሁን ጨምረው ገልፀዋል። ፓርቲው ከዚህ ቀደም ካጋጠሙት ነገሮች ትምህርት ወስዶ እንደሆን የተጠየቁት አቶ ጥላሁን፤ በሰላማዊ ሰልፍ ወቅት ችግር የሚገጥመው ከፓርቲው ሳይሆን ከገዢው ፓርቲ የማደናቀፍ ስራ የተነሳ መሆኑን ገልፀው፤ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ቅስቀሳው እየተካሄደ እንደሆነ እና ከመጪው አርብ ጀምሮም ወረቀቶቹ እንደሚለጠፉ፤ በራሪ ወረቀቶችም እንደሚበተኑ አሳውቀዋል።
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar