በእነ ሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው እየታየ ያሉት ጦማርያን እና ወዳጅ ጋዜጠኞች ላይ የተመሰረተው ክስ ተሻሽሎ ቀርቧል የተባለው የክስ ዝርዝር ዛሬ በልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ተሰምቷል፡፡ ዛሬ ህዳር 24/2007 ጠዋት በዋለው ችሎት፣ በጦማርያኑ እና ጋዜጠኞች ላይ ተሻሽሎ የቀረበው የክስ ዝርዝር በንባብ የተሰማ ሲሆን በክስ ወረቀቱ ላይ ከተመለከቱት ነጥቦች መካከል ግልጽ ያልሆኑ ነጥቦችን አካትቶ እንዲሰጥ ለአቃቤ ህግ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል፡፡ ስለሆነም ሙሉ የክስ ወረቀቱ አርብ ለጠበቆቹ እንደሚደርስ ይጠበቃል፡፡
በጠቦቆቹ በኩል ክሱ ቀደም ብሎ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት መሻሻሉን ለማረጋገጥ ያለፈው የፍርድ ቤቱ ብይን ግልባጭ እስካሁን እንዳልደረሳቸው በመግለጽ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲደርሳቸው ጠይቀዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የብይኑ ግልባጭ ሳይደርሰን ተሻሻለ የተባለው ክስ መሰማት የለበትም ብለው የነበር ቢሆንም፣ ክሱን አይታችሁ መቃወሚያ ካላችሁ አስተያየት እንድትሰጡበት እድል እንሰጣለን ያለው ፍርድ ቤቱ ክሱ እንዲሰማ አድርጓል፡፡ ፍርድ ቤቱ ጠበቆቹ ያላቸውን አስተያየት ይዘው እንዲቀርቡ ለታህሳስ 7 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ታውቋል፡፡
ነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar