onsdag 4. juni 2014

በሁለት ዙር የሰለጠኑ 235 የድረ ገፅ መረጃ ማዛባት የሚችሉ ፕሮፓጋንዲስቶች በስራ ላይ መሆናቸው ታወቀ፡፡

ኢህአዴግ በመላ ሐገሪቱ በኢንተርኔት ድረ ገፅ መንግስት እየደረሰበት ያለውን ትችት ለመቀነስና ፤ የተደበቁ መረጃዎች ተጋላጭነታቸውን ለመቆጣጠር በማሰብ የሰለጠኑ ወጣቶች ስራ መጀመራቸውን ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመልክቷል፡፡
ኢህአዴግ በአዳማ ናዝሬት በሁለት ዙር ያሰለጠናቸው 235 ብሎገሮች በፊስ ቡክና በተለያዩ የማህበራዊ የመገናኛ መንገዶች፣ተቃዋሚ የሚመስሉ ስያሜዎችን በማውጣት ህዝብ የማደናገር፤ መንግስትን በሚቃወሙ መረጃዎች ላይ ምላሽ የመስጠት ፤ መንግስትን የሚደግፉ መረጃዎች በየጊዜው በመረጃ መረቡ ለህዝብ እንዲደርስ የማድረግ ተልእኮ ተሰጥቷዋል።
ስልጠናውን የወሰዱት ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የኢህአዴግ ደጋፊዎች ሲሆኑ፣ ምርጫውን ያካሄዱት የመንግስት ኮሚኒኬሺን እና የኢህአዴግ ሊግ ናቸው፡፡ ሰልጣኞቹ ተጠሪነታቸው በክልሉ ላሉ የኢህአዴግ መሪ ፓርቲዎች ሲሆን፣ የመንግስት ከሚኒኬሺን መስሪያቤት በበኩሉ መረጃዎችን በበላይነት የማረም እና የማስተካከል ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡
በቅርቡ በተካሄደ የመጀመሪያው ዙር አፈፃፀም የአማራ ክልል መልካም ውጤት ማስመዝገቡን ፤ በፊስቡክ አመራርነት ለቤነሻንጉል ጉሙዝ ተሞክሮ ማካፈሉ መደነቁን የመንግስት ኮሚኒኬሺን ሚኒስትር ሬድዋን ሁሴን በባህር ዳር ላይ በተካሄደው የመንግስት ከሚኒኬሺን ባለሙያዎች ግምገማ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
የኢህአዴግ የስልጠና መምሪያ ሃላፊ አቶ አዲሱ ለገሰ ደግሞ  ከኢሳት ከሚወረወረው የጦር ፕሮፓጋንዳ መዳን የምንችለው በኢቲቪ ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ ሚዲያው ነው ሲሉ ለተመራቂዎች ተናግረዋል።
እስካሁን ባለው መረጃ ሰልጣኞቹ 2 ሺ 350 የፊስ ቡክ ፤ የቲውተር ፤ እና የብሎግ አካውንቶችን  ከፍተዋል።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar