lørdag 14. juni 2014

ያለ ክስ ለ 50 ቀኖች በእስር የሚገኙት ጦማሪዎች እና ጋዜጠኞች ክስ እንዲቀርብባቸው ዳኛው ፖሊስን አዘዙ

bloggers1


ዛሬ ቅዳሜ ሰኔ 7፣ 2006 ዓ.ም በቀጠሯቸው መሠረት አራዳ በሚገኘው ፍርድ ቤት የቀረቡት ሦስት ጋዜጠኞች አስማማው ኃ/ጊዮርጊስ፣ ተስፋለም ወልደየስ ኤዶም ካሳዬ እና ሦስት ጦማሪያን ዘላለም ክብረት፣ አጥናፍ ብርሃኔ፣ ናትናኤል ፈለቀ እንደተጠበቀው በፖሊስ ተጨማሪ የ28 ቀናት ቀጠሮ የተጠየቀባቸው ሲሆንፍርድ ቤቱም ለሐምሌ 5 ፣ 2006 ዓ.ም እንዲቀርቡ የተጠየቀውን የጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል፡፡

አራዳ ምድብ ችሎት ከወትሮው በርከት ያሉ የተጠርጣሪ ቤተሰብና ወዳጆች በፍርድ ቤቱ ግቢ ተገኝተዋል፡፡ ግንቦት 9፣ 2006 በነበረው ችሎት ከእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ሦስት ቤተሰብ ወደ ችሎት እንዲገባ ተደርጎ የነበረ ሲሆን በዛሬው ችሎት ላይ ግን ማንም ድርሽ እንዲል አልተፈቀደለትም፡፡ የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ አቶ አመሃ መኮንን ጉዳዩ በዝግ ችሎት እንዲታይ አለመወሰኑን ገልጸው የችሎት አዳራሾቹ እጅግ ጠባብ መሆን እና የፖሊስ ፈቃደኛ ሆኖ አለመገኘት ምክንያት እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡


ፖሊስ በድጋሚ ቀጠሮ በሚጠይቅበት ወቅት በደፈናው ‘በርካታ ሥራዎችን ሰርተናል፤ የሚቀሩን ነገሮች አሉ…’ ቢልም ዳኛዋ ግን ተሰርተዋል የተባሉት ነገሮች እና አላጠናቀቅናቸውም የሚሏቸውን ነገሮች በዝርዝር እንዲያቀርቡ ጠበቅ ያለ ማሳሰቢያ ስለሰጡ ፖሊስ ምላሽ ለመስጠት መገደዱን የተናገሩት አቶ አመሃ፤ ‘ምስክሮች ይቀሩናል፣ ተባባሪዎች ወደ ክልል ስለሸሹ እነሱን የሚያመጣ የፖሊስ ኃይል ልከናል፣ ሰነድ ማስተርጎሙም አላለቀልንም…’ የሚሉትን በየቀጠሮው የሚያቀርቧቸውን ምክንያቶች አሁንም እንዳቀረቡ ተናግረዋል፡፡


ጠበቆች በፖሊስ ምላሽ ላይ አስተያየት እንዳላቸው ተጠይቀው “ልጆቹ ከታሰሩ 50ኛ ቀናቸው ነው፡፡ የፈለገውን ያህል የተወሳሰበ ወንጀል ቢሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ ማውጣት ይቻል ነበር፡፡ ነገሮች የሚያሳዩት ግን ፖሊስ እነዚህ ሰዎች ማስረጃ ሳይሰበስብ የያዛቸው መሆኑን ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሀገሪቱን ሕግ የጣሰ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ የተጨማሪ ቀጠሮ ጥያቄውን እንዳይቀበለው ጠይቀናል ያሉት አቶ አመሃ በሁለተኛ ደረጃ የሰነድ ማስተርጎም በፖሊስና በተርጓሚው መሃከል የሚካሄድ ነው ተጠርጣሪዎቹን በእስር ለማቆየት የሚያበቃ አይደለም፤ የቴክኒክ ምርመራ የሚባለውም ቢሆን እዚያው ፌደራል ፖሊስ የሚካሄድ በመሆኑ ልጆቹ በዋስ እንዲለቀቁ፤ ይኽ ካልሆነ ግን ፖሊስ ቀጠሮ የጠየቀበት ሕጋዊ ምክንያት አለው እንኳን ከተባለ የመጨረሻ ቀጠሮ እንዲሆን ፍርድ ቤቱን መጠየቃቸውን ገልጸዋል፡፡


ፍርድ ቤቱ በሚቻል መንገድ ፖሊስን ጫን ብሎ መጠየቁን የሚናገሩት አቶ አመሃ መኮንን ፖሊስ በየጊዜው የሚቀርባቸው አራት ምክንያቶች ‘ተባባሪ አልያዝንም፣ ምስክሮች አልተቀበልንም፣ የሰነዶች ትርጉም አልመጣልንም እና ከባንክ ለሽበርተኝነት ተግባር እንዲሆን ስለመጣላቸው ገንዘብ የሚገልጽ ሰነድ አልመጣልንም ’የሚሉት ምክንያቶች ከዚህ በኋላ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ሆነው መቅረብ እንደማይችሉ ዳኛዋ በመዝገብ ላይ ማስፈራቸውንም ገልጸዋል፡፡


ፖሊስ ሌላ ቀጠሮ ለማራዘም የሚያስችል ምክንያት ካለው ማቅረብ የሚችል ሲሆን ከዚህ ቀደም ያቀርባቸው የነበሩት ምክንያቶች ከዚህ በኋላ ተቀባይነት አይኖራቸውም ቢባልም ፍርድ ቤቱ የሐምሌ 5ቱ ቀጠሮ የመጨረሻው ነው ብሎ እንዳልደመደመ አቶ አመሃ አስረድተዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ፍርድ ቤት ፈቅዶ እያለ ፖሊስ ጠያቂ እንዳያገኘን ከልክሎናል ብለው ቅሬታቸውን ያሰሙ ሲሆን ፖሊስ በሰጠው ምላሽ ጠያቂ እንዳልተከለከለ ገልጾ ከቢሮ የአስተዳደር ችግሮች አንጻር ሁሌ ላይሳካ ይችላል ሲል መልሷል፡፡


 ጋዜጠኛ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ ለረዥም ጊዜ የሚያሰቃየው የጀርባ ህመም እያስቸገረው በመሆኑ ወንበር እንዲገባለት ጠይቆ ይህ እንዳልተፈጸመለት ተናግሯል፡፡ በእለቱ የአስማማውን ጉዳይ የያዙት መርማሪ በመገኘታቸው ‘አስማማው ቢጠይቀኝ አደርጋለሁ’ ሲሉ መልሰዋል፡፡ ይኽ የጤና ጉዳይ በመሆኑ ለድርድር የማይቀርብ በመሆኑ የሚጠይቁት ነገር አቅም በፈቀደ መጠን እንዲሟላ ዳኛዋ ማዘዛቸውንም ጠበቃ አመሃ ተናግረዋል፡፡

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar