mandag 23. juni 2014

የአንድነት የአዋሳ ሰልፍ “በእስር ተጀምሮ በእስር ተጠናቀቀ”

የሚሊዮኖች ድምጽ ለመሬት ባለቤትነት በሚል አንድነት ፓርቲ በአዋሳ ሊያካሂደው የነበረው ሰልፍ ፣ የሰልፉ አስተባባሪዎችና የፓርቲው የአመራር አባላት በመታሰራቸው ምክንያት ሳይካሄድ ቀረ።
ሰልፉ ከመካሄዱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በፓርቲው ቅስቀሳ የተደናገጡት የሚመስሉት የአዋሳ ባለስልጣኖችና ፖሊስ አባላት 37 የሚሆኑ በቅስቀሳ ላይ የተሰማሩ አመራሮችንና ደጋፊዎችን ይዘው በተለያዩ እስር ቤቶች አስረዋቸዋል።
በማግስቱ እስረኞችን ለመጠየቅና ስንቅ ለማቀበል ከሄዱት መካከልም አንዳንዶች መታሰራቸውን በስፍራው የሚገኘው የአንድነት ፓርቲ የአዲስ አበባ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ያሬድ አማረ ለኢሳት ገልጸዋል።
ከአዲስ አበባ የሄዱና የአዋሳ የፓርቲው አመራሮች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡና ክስ ሳይመሰረትባቸው በመታሰራቸው የረሀብ አድማ ያደረጉ ሲሆን፣ ዛሬ ሰኞ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ እየተጠበቀ መሆኑን አቶ ያሬድ አክለው ተናግረዋል።
መድረክ በአዋሳ በከፍተኛ ወከባ ውስጥ ሆኖ የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጉ ይታወቃል። አንድነት ፓርቲ በተለያዩ ክልሎች እየዞረ በርካታ ህዝብ የሚሳተፍበት ሰላማዊ ሰልፎችን እያደረገ ነው። በአዋሳው ሰላማዊ ሰልፍ በኦሮሞ ወጣቶች ላይ የተወሰደው እርምጃ፣ የኑሮ ውድነት፣ ከማንነት ጋር በተያያዙ የሚታዩት የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እና የመሳሰሉት ጉዳዮች ይነሳሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር።
አንድነት በአዋሳ ለሚያካሂደው የተቃውሞ ሰልፍ ለክልሉ መንግስት የእውቅና ደብዳቤ ያስገባው ከአንድ ወር በፊት ነበር። የከተማው ምክር ቤት እስካለፈው አርብ ድረስ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት እየተነጋገርነበት ነው በማለት ሲያጓትተው ቆይቷል።
አንድነት ፓርቲ  በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ “በተለየ ሁኔታ በደቡብ ክልል እየታየ ያለው መንግስታዊ አፈናና ጸረ ህግ አቋም እንዲገታ ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን” ብሎአል።
“የስርዓቱ መንግስታዊ አፈናና ፀረ-ሕዝብ አቋም በመላ ኢትዮጵያ የተዘረጋ ቢሆንም ፓርቲያችን በእንቅስቃሴዎቹ ውስጥ እንደታዘበው በደቡብ ክልል በተለየ ሁኔታ ተጠናክሮ ቀጥሏል” ያለው አንድነት፣  “በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ ሹማምንቶች ባደረባቸው የገዥነት መንፈስ ሰላማዊ እንቅስቃሴዎችን በማፈንና ብሎም ያለምንም ማስረጃና ምክንያት ሰላማዊ ታጋዮችን ወደ እስር ቤት በመክተት ተግባራዊ እያደረጉት ” ነው ብሎአል።
በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ወደእስር ቤት መወሰዳቸውን፣ ቁጫ ላይ ተጠርቶ የነበረው ሰላማዊ ሰልፍም እንዲሁ በጉልበት፣ በእስርና አፈና እንዳይካሄድ መደረጉን የገለጸው አንድነት፤ የክልሉ ዋና ከተማ በሆነችው አዋሳ የተጠራው ሰልፍ በህገወጥ እስር መጠናቀቁን ገልጿል፡፡
“በክልሉ ለመዝጋት እየተሞከረ ያለውን የህዝብ ጥያቄ ከህዝብ ጋር በመሆን መፍትሔ እንዲያገኝ እናደርጋለን” የሚለው አንድነት ጉዳዩን ወደ ህግ እንደሚወስደውም ገልጿል።
ያለምንም ወንጀል የታሰሩ አባሎቻችንና አመራሮቹ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳ እንዲፈቱ የጠየቀው ፓርቲው ፣ በደቡብ ክልል እየታየ ያለውን መንግስታዊ አፈናና ፀረ-ሕዝብ አቋም እንደሚታገለው አስታውቋል።ዘግይቶ በደረሰን ዜና ደግሞ በቅስቀሳ ላይ የነበሩት አመራሮች የዋስትና መብታቸውን ተከልክለው ወደ እስር ቤት እንዲመለሱ ተደርጓል።
መስተዳድሩ ከጻፈው ደብዳቤ ለመረዳት እንደሚቻለው ሰዎቹ የታሰሩት በህገወጥ መንገድ ሲቀሰቅሱ ተገኝተዋል በሚል ነው።                                 

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar