የአቦከር መሰናዶ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የታሰሩት የሁለተኛ ደረጃ ፈተና ካጠናቀቁ በሁዋላ ከግቢያቸው በመውጣት መፈክሮችን እያሰሙ ወደ ማሃል ከተማ በመጓዝ ላይ እያሉ ነው። ተማሪዎቹ “በሀረር ክልል የሚታየው አድሎ ይቁም፣ ፍትሃዊ አስተዳደር ይኑር፣ መንግስት በህዝብ ላይ የሚያደርሰው በደል ይቁም” የሚሉና ሌሎችንም መፈክሮች እያሰሙ ተቃውሞአቸውን ሲገልጹ አርፍደዋል።
የክልሉና የፌደራል ፖሊስ በጋራ ተቃውሞውን የተቆጣጠሩት ሲሆን፣ ተቃውሞውን አስነስተዋል ያሉዋቸውን ከ25 በላይ ተማሪዎች እየደበደቡ ወደ እስር ቤት ወስደዋቸዋል። የፖሊስን ዱላ ለመሸሽ በሚል በሃረር መካነ-ስላሴ ካቴደራል ቤተክርስቲያን የገቡትን ተማሪዎች አስወጥተው መውሰዳቸውን በተለይ ያሬድ የሚባል ተማሪ በድብደባው ክፉኛ እንደተጎዳ ወኪላችን ገልጿል።
የሀረሪ ክልል ባለስልጣናት የሚፈጽሙት አስተዳደራዊ በደል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ነዋሪዎች ይናገራሉ። የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች በሚኖሩባት ሃረር ፍትሃዊ የሆነ ውክልና እንደሌለና የመስተዳደሩ ባለስልጣናት ሁሉንም ብሄሮች እኩል እንደማያስተናግዱ የከተማዋ ነዋሪዎች በምሬት ይገልጻሉ።
ከ20 በላይ ነጋዴዎች ብጥብጥ በማስነሳትና የመንግስት ንብረት እንዲወድም በማስደረግ ወንጀል ተከሰው ዋስትና ተከልክለው በእስር ቤት እንደሚገኙ ይታወቃል።
በክልሉ የሚታየውን ችግር በተመለከተ ባለስልጣናቱን ለማነጋገር ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም አልተሳካልንም።
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar